Friday, May 2, 2014

ኢቴቪ በራሺያ ፍቅር ዩክሬንን ጠምዷታል፤ መዘዙ ለአገራችን ነው



 የአገራችን የመንግስት ቴሌቪዢንና ሬድዮ፣ ለበርካታ ሳምንታት በራሺያና በዩክሬን “ድራማ” ዙሪያ ያለማቋረጥ የሚያሰራጩት ነገር፣ ለአገራችን ምን አይነት መዘዝ እንደሚያስከትል የተገነዘቡት አይመስልም። “ድራማው”፣ የሚያሳዝንና የሚያሳስብ እንጂ፣ የሚያስቦርቅና የሚያስፈነድቅ ድራማ አይደለም። በጠበኛ እብሪት የተለከፈው የራሺያ መንግስት  ዋና አቀናባሪነትና ስፖንሰርነት በሚመራው በዚሁ ድራማ፤ ዩክሬን በጎሳና በሃይማኖት ስትሰነጣጠቅ እየታየ ነው። እና፣ ይሄን እያዩ በደስታ ጮቤ መርገጥ ተገቢ ነው?
የውጭ ጠበኞች የሚያሴሩባትና የውስጥ ጣጣዎች የሚያስቸግሯት አገርኮ ዩክሬን ብቻ አይደለችም። ኢትዮጵያም፣ ከሩቅና ከቅርብ፣ በጎሳም ሆነ በሃይማኖት ሰበብ “እንበጥብጣት” የሚሉ (የራሺያ አይነት)የውጭ አገር ጠበኞች አሉባት። አንዳንድ የግብፅ ባለስልጣናት ኢትዮጵያን ለመበጥበጥ ሲዝቱ ሰምተናልኮ። ለብጥብጥ የሚሆን ሰበብ ደግሞ ሞልቷል። አገራችን፣ከጎሳና ከሃይማኖት ጋር የተቆራኙ ነባርና ኋላቀር የውስጥ ጣጣዎች የሉባትም እንዴ? እንደ ዩክሬን ለአደጋ የሚያጋልጡ የአገራችን ጣጣዎች ጥቂት አይደሉም። የራሺያ መንግስትና የኬጂቢ ኮለኔል የነበሩት ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ በዩክሬን ላይ የሚያካሂዱት ዘመቻ ድብቅ ሚስጥር አይደለም። የግብፅ መንግስት፣ የሶማሌ ክልል ተወላጆች እንዲገነጠሉ በማሴር፣ “የራሳቸውን እድል በራሳቸው ይወስኑ” እያለ ዘመቻ ቢያካሂድ እንደማለት ነው። ከኢትዮጵያ ጎን የሚሰለፍ አለኝታ ይኖራል? ምናልባት፣ ዩክሬንንም ከጥቃት የሚያድን አለኝታ መንግስት አይኖር ይሆናል። ግን፣ አነሰም በዛ ከጎንሽ ነን ብለው የሚከራከሩላት የአሜሪካና የአውሮፓ ወዳጅ መንግስታትን አላጣችም። ኢቴቪ ይህንንም ሲያወግዝ ነው የምንሰማው። በራሺያ ሴራ ዩክሬን ስትሰነጣጠቅ እያየን ብንቦርቅ፣ በራሳችን ላይ መዘዝ መጋበዝ እንደሆነ እነኢቴቪ እንዴት አልተረዱትም?
በእርግጥ የራሺያና የዩክሬን ጉዳይ፣ እዚሁ ለአገራችን የራሱ አንደምታና ትርጉም እንደሚኖረው እነ ኢቴቪ አያውቁም ማለቴ አይደለም። ትርጉም እንዳለው ስለሚያምኑማ ነው፤ ነገሩን እንደራሳቸው ጉዳይ የእለት ተእለት ዘመቻ ያደረጉት። በእርግጥ፣ “ዜና ወይም ዘገባ አሰራጨን እንጂ ዘመቻ አላካሄድንም” ሊሉ ይችላሉ። ግን፤ዜና ወይም ዘገባ ማሰራጨት ሌላ! በራሺያ ፍቅር የታወረ እስኪመስል ድረስ፤ በዩክሬንና በምዕራብ አገራት ላይ ጭፍን የጥላቻ ዘመቻ ማራገብ ደግሞ ሌላ! የኢቴቪ ዜናዎችና ዘገባዎች፣ በስሜት የጦዘ “ቲፎዞ” ከሚሰነዘረው ጭፍን አስተያየት አይለዩም። ጭፍን አስተያየት፣ በዜና ወይም በዘገባ ስም ሲቀርብ ምን ይባላል? “ፕሮፓጋንዳ” ይባላል። ሌላ መጠሪያ ስም የለውም። ለዚያውም ማንንም የማይጠቅምና ሁሉንም የሚጎዳ ቀሽም ፕሮፓጋንዳ!
ፕሮፓጋንዳ በተፈጥሮው፣ እውነተኛ መረጃዎችን በማጥፋትና በማግለል፣ በማጣመምና በማድበስበስ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዳይፈጠር ስለሚያግድ ጎጂ ነው። ከረዥም ጊዜ አንፃርም፣ የእውነትን ክብር በመሸርሸር፣ በሁሉም ተቀናቃኝ ቡድኖች ዘንድ ጭፍንነት እየተስፋፋና ስር እየሰደደ እንዲሄድ ያደርጋል። የኢቴቪ ፕሮፓጋንዳ ቀሽምነት ግን፣ ከዚህም ይብሳል። ብዙ ሰዎች ወደ ፕሮፓጋንዳ የሚሮጡት፣ ውሎ አድሮ እንደሚጎዳ ስለማያውቁ፤ ወይም ደግሞ ጎጂነቱ ባይጠፋቸውም ለማያዛልቅ የአጭር ጊዜ ጥቅም እጅ ስለሚሰጡ ነው። የኢቲቪ ፕሮፓጋንዳ ግን፤ቅንጣት ታህል የአጭር ጊዜ ጥቅም የለውም። ከንቱ ድካም ነው። “ከንቱ ድካም” ሲባል ግን፤ እርባና ቢስነቱን ለመግለፅ ያህል እንጂ፤ “ምንም ውጤት አያመጣም” ለማለት አይደለም። መጥፎ ውጤት ያስከትላላ – አገሪቱንና ነዋሪዎቿን ለአደጋ በሚያጋልጥ የተሳሳተ አስተሳሰብ የተቃኘ ፕሮፓጋንዳ ነዋ። “እርባና ቢስ ነው” የምለውም፤ ኢቴቪ ወደ ፕሮፓጋንዳ እንዲገባ የሚገፋፋ መነሻ ሰበብ የለም ማለቴ አይደለም።
ለግንዛቤ የሚያስቸግር ውስብስብ ጉዳይ አይደለም። በጭላንጭልም ቢሆን አይኑን በመክፈት ለአንድ አፍታ ከጭፍንነት ለመራቅ ፈቃደኛ የሆነ ሰው፣ በቀላሉ ሊገነዘበው ይችላል። የራሺያ መንግስት በዩክሬንና በሌሎች ጎረቤት አገራት ላይ የሚሸርበው ሴራና የሚያካሂደው ዘመቻ፤ የኤርትራ መንግስት በጎረቤቶቹ ላይ ከሚፈፅማቸው ጠበኛ ድርጊቶች ብዙም አይለይም። ይሄ አጥፊ ተመሳሳይነት ለኢቴቪ የማይታየው ለምን ይሆን? የፕሮፓጋንዳው መነሻ ሰበብስ ምንድነው? የሁለቱም ጥያቄዎች መልስ አንድ ነው -“የቀለም አብዮት”!
መንግስት፣ ኢህአዴግ ወይም የመንግስት ሚዲያ፣ ለበርካታ አመታት በ“ቀለም አብዮት” ላይ ብቻ ክፉኛ ስላፈጠጡ፤ ዛሬ ዛሬ ሁሉም ነገር “የቀለም አብዮት” እየሆነ ይታያቸዋል። ሊያሳስባቸው አይገባም ማለቴ አይደለም። የስልጣን ጉዳይ ነውና ቢያሳስባቸው አይገርምም። እንዲያውም፤ እነሱን ብቻ ሳይሆን፤ ማንንም ሰው ሊያሳስበው ይገባል። “የመጣው ይምጣ” ወደሚል ተስፋ ቢስነት ለዘቀጠ ሰው ወይም “ሳይደፈርስ አይጠራም” ከሚል አላዋቂነት ላልተላቀቀ ሰው ካልሆነ በቀር፤  ነባሩን አስተዳደር የሚያናጋ እንቅስቃሴ ሲፈጠር ማንኛውም ጤናማ ሰው በጥሞና ማሰብ ማሰላሰል ይኖርበታል። “ለውጥ” በቁንፅል ለጤናማ ሰው በቂ አይደለም። የተሻለ ነገር ለማምጣት የሚያስችል መሆን አለበት – “ለውጥ”። “የመጣው ይምጣ” ብሎ በጭፍን መደናበር ግን ጤንነት አይደለም። “የባሰ ቢመጣስ?” የሚል ጥያቄ አለና ነው። ጤናማና ብልህ ሰው፤ ነገሮች ጥርት ብለው እንዲወጡ ለማድረግ ከመነሻው አስበው፣ መላ አበጅተውና መድረሻቸውን አቅደው ይጣጣራሉ እንጂ፤ “መጀመሪያ ይደፍርስ፤ ያኔ የደፈረሰውን ለማጥራት እናስብበታለን” ብለው በጭፍን አይገቡበትም። “ከደፈረሰ በኋላ ባይጠራስ?” የሚል ጥያቄ አለና ነው።
በተጨባጭ ያለውን እውነታ ከመነሻው በአግባቡ መገንዘብ፤ ወደፊት የሚመኙትን የተሻለ ሕይወት በቅጡ ለይቶ መድረሻውን ማወቅ፤  ከመነሻ ወደ መድረሻ የሚጓዙበት ትክክለኛውን መንገድ መምረጥ ያስፈልጋል። ተጨባጩን እውነት፣ የለውጡን መንገድ እና የታለመውን ሕይወት፣ … ሦስቱንም አስተሳስሮ ማሰብ እንደሚያስፈልግ ከተገነዘብን፤በዘመናችን “የቀለም አብዮቶች” ተብለው የሚጠሩ “የለውጥ እንቅስቃሴዎችን” ሁሉ በጅምላ እየፈረጁ በደፈናው መደገፍም ሆነ መቃወም፤ ከአላዋቂነት ወይም ከጭፍንነት የዘለለ ትርጉም እንደማይኖረው ይገባናል። ለምን? “የቀለም አብዮቶች” ሁሉ እኩል አይደሉም። የብዙ ሰዎችን (የሕዝብን) ትኩረት በመማረክ የሚጀመሩ የለውጥ እንቅስቃሴ ከመሆናቸው በስተቀር፤ ብዙም ተመሳሳይነት የላቸውም። በተነሱበት እውነት፣ በመረጡት መንገድና ባለሙት የሕይወት ግብ ይለያያሉ።
ለምሳሌ የመጀመሪያው የቀለም አብዮት ነው ተብሎ በኢህአዴግ መፅሔት የተጠቀሰው፤ “velvet revolution”ን ተመልከቱ። በ1982 ዓ.ም ቼኮዝላቫኪያ ተብላ ትጠራ በነበረችው አገር የተካሄደ የለውጥ እንቅስቃሴ ነው። ያኔ የነበረው እውነታ ምን ነበር? አፈና በሰፈነበት የኮሙኒስት ስርዓት ውስጥ፤ በነፃነት ማሰብና ሃሳብን መግለፅ፣ ማንበብና ሃሳቦችን መቀበል ወንጀል ነበር። የሰዎች ስራ፣ ምርት፣ ንብረትና ኑሮ በሙሉ በመንግስት ቁጥጥር ስር ነው። ከኮሙኒስት ፓርቲው ውጭ ሌላ አማራጭ የፖለቲካ ሃሳብ መሰንዘርም ሆነ ፓርቲ ማቋቋም ወንጀል ነው። የመምረጥም ሆነ የመመረጥ መብት የለም። በአጠቃላይ፤ በስለላ የታመቀ፣ በአፈና የደነዘዘ፤ በመንግስት ቁጥጥር የተራቆተና የደኸየ ኢኮኖሚ፤ በራሽን የታጠረና መላወሻ ያጣ ኑሮ፤ … በአጠቃላይ እያንዳንዱ ሰው ፓርቲንና መንግስትን በባርነት የሚያገለግል አቅም አልባ፣ ምስኪንና ክብረቢስ ፍጥረት ተደርጎ የሚቆጠርበት የውርደት ሕይወት ነበር። በአጭሩ በደርግ ዘመን በኢትዮጵያ ውስጥ ከነበረው ሕይወት ብዙም አይለይም። የነፃነትን ጭላንጭ የሚዘጋ፣ የብልፅግናን እድል የሚሰብር፣ የእኔነትን ክብር የሚያኮላሽ የኮሙኒዝም ስርዓት።
ደግነቱ፤ ሰው ብርቱ ነው። ከፍርሃትና ከአፈና የመላቀቅና የነፃነትን አየር የመተንፈስ ሰውኛ ፍላጎት ጠፍቶ አይጠፋም። መላወሻ ከሌለው የመንግስት ጭሰኝነትና ከንብረት አልባነት ተገላግሎ ንብረት የማፍራትና ብልፅግናን የመቋደስ ምኞት ተዳፍኖ አይቀርም። የካድሬና የቀበሌ ሊቀመንበር ሎሌ፤ የሚሊሻና የታጣቂ መጫወቻ ከመሆን ተገላግሎ፣ አንገትን ቀና አድርጎ ሕይወትንና ሰላምን የማጣጣም ህልም ብን ብሎ አይሰወርም።
በኮሙኒስት ስርዓት ውስጥ የነበረው እውነታ፤ በአፈናና በፍርሃት፣ በዝርፊያና በድህነት፣ በሸክምና በውርደት የተሞላ ኑሮ ነው። ወደፊት የተመኙት ሕይወትና ያለሙት መድረሻስ ምን ነበር? የነፃነት አየርን መተንፈስ፣ የብልፅግና እድልን መቋደስና የሕይወትን ጣዕም ማጣጣም ነው። በእርግጥም፤ ከአብዮቱ በኋላ፤ የግል ሚዲያና የፖለቲካ ምርጫ ተጀመረ። የግል ንብረትና የቢዝነስ ስራ ተፈቀደ። አንገትን ቀና አድርጎ የመራመድ የእፎይታና የሰላም መንፈስም ተገኘ። በእርግጥ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ነፃነት እንዲሁም ሰው የመሆን ክብር በተሟላ ሁኔታ ሰፍኗል ማለት አይደለም። ግን ከድሮው በእጅጉ በእጅጉ ይሻላል። በከፊልም ቢሆን፤ ወዳለሙትና ወደተመኙት መድረሻ የሚያሸጋግር መልካም ለውጥ እውን ሆነ ማለት ነው። እንዴት?  በምን አይነት የለውጥ እንቅስቃሴ? አደባባዮችንና ጎዳናዎችን በሚያጥለቀልቁ የተቃውሞ ሰልፎች ነው፣ የቀድሞው አምባገነን የኮሙኒስት ስርዓት ፈርሶ ለውጥ የመጣው።
እንግዲህ፤ የአገሬው ሰዎች ምን አይነት ሁኔታ ውስጥ እንደነበሩ ቃኝተናል – መነሻቸውን። የመጣውን ለውጥ ተመልክተናል – መድረሻቸውን። የተጓዙበትን አቅጣጫ አይተናል- መንገዳቸውን። ከዚህ ውስጥ ምን የሚያስወቅስ እንከን አገኛችሁበት? በተቃውሞ ሰልፍ ከአምባገነንነት መላቀቃቸውና ለውጥ ማምጣታቸው ያስወቅሳቸዋል? ደም ሳይፈስ በተቃውሞ ሰልፍ ብቻ መልካም ለውጥ መገኘቱ መታደል ነው። የሚያስሞግስ እንጂ የሚያስወቅስ አይደለም። ሌላው ቀርቶ፤ የመቶ ሺዎችን ህይወት የቀጠፈና የሚሊዮኖችን ኑሮ ያናጋ ጦርነት ተካሂዶ በኢትዮጵያ ለውጥ መምጣቱስ ያስወቅሳል እንዴ? ነውጠኛና አመፀኛ ብለን ኢህአዴግን ማውገዝ ተገቢ ነው? በጭራሽ። በእርግጥ፣ በጠባቡም ቢሆን ሃሳብን የመግለፅና በምርጫ የመሳተፍ እድል ባለበት አገር፤ “ለውጥ አመጣለሁ” ብሎ ወደ ጦርነት መግባት ተገቢ አይደለም። ሃሳብን የመግለፅና ምርጫ የማካሄድ እድል እየተዘጋ ካልሄደ በቀር፣ እንኳን በጦርነት ይቅርና በጎዳና ሰልፎች መንግስትን ለመለወጥ መነሳትም፤ ተገቢ የማይሆንበት ጊዜ አለ። በተለይ ደግሞ፣ ከነባሩ ስርዓት በእጅጉ የተሻለ መልካም ለውጥ እንደሚመጣ በእርግጠኝነት የማናውቅ ከሆነ፤ ነገር ማደፍረስ ጥቅም የለውም። በስሜት ደረጃ ጥሩ ጥሩ ነገሮችን ከመመኘት ባሻገር፤ የምንመኛቸውን ነገሮች እውን ለማድረግ ምን አይነት ስርዓት እንደሚያስፈልግ በትክክል ካላወቅንና መድረሻችንን በቅጡ መለየት ካቃተን፤ “የለውጥ እንቅስቃሴ” ሁሉ ከንቱ ይሆናል። የእነ ግብፅ እና የእነ ሊቢያ አብዮቶች፤ እንዲሁም በጆርጂያና በዩክሬን የተካሄዱ ፀረ ራሺያ አብዮቶች በዚህ ጎራ የሚመደቡ ናቸው። በነባር ችግሮች እየተማረሩ የተሻለ ነገር ከመመኘት በስተቀር፤ መድረሻቸውን በግልፅ ለይተው ባለማወቃቸው፤ብዙም ሳይራመዱ ለቀውስ ተዳርገዋል።
ግን ከእነዚህም የባሰ ሞልቷል። የተሻለ ነገር በመመኘት ሳይሆን ወደ ባሰ ክፉ ስርዓት ለመጓዝ የሚካሄዱ የለውጥ እንቅስቃሴዎች አሉ። የሶሪያ እና የሴንትራል አፍሪካ ቀውሶችን መጥቀስ ይቻላል። በራሺያ አቀናባሪነት ዩክሬን ውስጥ እየተካሄደ ያለው ፀረ ምዕራብ አገራት እንቅስቃሴም፣ ከዚሁ የጥፋት ጎራ የሚመደብ ነው።
ፀረ ራሺያ አቋም የያዙ ዩክሬናዊያን አደባባዮች ማጥለቅለቅ “ለውጥ” ለማምጣት ተቃውሞ ሰልፍ ሲያካሂዱ፤ መንግስት በወሰደው እርምጃ ከመቶ በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ከዚህ በኋላ ነው፤ ፕሬዚዳንቱ ከስልጣን ተባርረው መንግስት የተለወጠው። ኢቴቪ ይህንን ምን ይለዋል? መፈንቅለ መንግስት ብሎ ይጠራዋል። በምርጫ ስልጣን የያዘ መንግስት የፈረሰው፣ “የቀለም አብዮተኞች” ባካሄዱት መፈንቅለ መንግስት ነው በማለት ኢቴቪ በየእለቱ ሳያወግዝ አያልፍም። በመንግስት ስለተገደሉት ሰዎች አንዳችም የትችት አስተያየት አይሰነዝርም።
በራሺያ የሚደገፉ ዩክሬናዊያን፣ በክሬሚያ እና በሌሎች ምስራቃዊ ክልሎች ምን አይነት “የለውጥ እንቅስቃሴ” እንደሚያካሂዱ ተመልከቱ። በተቃውሞ ሰልፍ አልያም በታጣቂ ቡድኖች አማካኝነት፣ አደባባዮችን ብቻ ሳይሆን የመንግስት መስሪያ ቤቶችን በሃይል ይቆጣጠራሉ። መንግስት መስሪያ ቤቶቹን ለማስለቀቅ ሲሞክር አምስት ሰዎች ተገድለዋል። ኢቴቪ ስለተገደሉት ሰዎች ሲናገር፤ 5 የነፃነት ታጋዮች ተገድለዋል በማለት ነው የገለፀው። ለማንኛውም “የነፃነት ታጋዮቹ” በሃይል የተቆጣጠሯቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች አልተለቀቁም። እናም በራሺያ የሚደገፉት “የቀለም አብዮተኞች” ፤ በምርጫ ስልጣን የያዙ የክልልና የከተማ አስተዳደሮችን ለማፍረስ ችለዋል። በእርግጥ ኢቴቪ እነዚህን፣ የቀለም አብዮተኞች አይላቸውም። የራስን እድል በራስ የመወሰን መብታቸውን ለማስከበር የሚጠይቁ የነፃነት ታጋዮች እያለ ነው የሚጠራቸው።
ክሬሚያ የተሰኘው የዩክሬን ክልል እንዲገነጠልና ወደ ራሺያ እንዲጠቃለል የተደረገውም፤ እነዚሁ በራሺያ የሚደገፉ “የቀለም አብዮተኞች” (በኢቴቪ አጠራር “የነፃነት ታጋዮች”) ባካሄዱት የተቃውሞ ዘመቻ አማካኝነት ነው – በምርጫ ስልጣን የያዘውን አስተዳደር በሃይል በመቆጣጠርና በማፍረስ።
በአንድ በኩል፤በምርጫ ስልጣን የያዙ ፕሬዚዳንት በተቃውሞ አመፅ ከስልጣን ሲባረሩ፤ “በቀለም አብዮተኞች የተፈፀመ ትልቅ ወንጀል ነው” ተባለ። እሺ። በሌላ በኩል፤ በምርጫ ስልጣን የያዙ የክልል ፕሬዚዳንቶችና የከተማ አስተዳዳሪዎች፤ በተቃውሞ አመፅ ሲባረሩስ? “በነፃነት ታጋዮች የተገኘ ትልቅ ድል ነው” ተባለ። ታዲያ እንዲህ አይነቱ ፕሮፓጋንዳ እዚያው እርስ በርሱ የሚጣፋ ከንቱ ድካም አይደለምን? ለአጭር ጊዜ የሚያገለግል ጥቅም እንኳ የለውም። ይልቅ ለረዥም ጊዜ የሚዘልቅ ጉዳት አለው። እንዴት በሉ። በራሺያ አቀናባሪነትና ድጋፍ፣ የክሬሚያ ክልል ከዩክሬን ተገንጥሎ ወደ ራሺያ መጠቃለሉ፤ በኢቴቪ ቤት “የነፃነት ትግል” ነው። ይህንን ሁኔታ ወደ አገራችን አምጥተን እንየው።  ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ “በቀለም አብዮት” መንግስት ተለወጠ እንበል። ከዚያስ? ከዚያማ ልክ የራሺያ መንግስት እንዳደረገው፤ የሶማሊያ መንግስትም የኢትዮጵያ አካል የሆነው የሶማሌ ክልል እንዲገነጠል ድጋፍ ይሰጣል። የክልሉ መስተዳድር ስልጣን የያዘው በምርጫ ቢሆንም፤ በሶማሊያ መንግስት ስፖንሰር አድራጊነትና በተቃውሞ ሰልፈኞች አማካኝነት እንዲፈርስ ይደረጋል እንበል። ከዚያም በሶማሊያ መንግስት ወታደራዊ አለኝታነት ተማምነው፤ የኢትዮጵያን ህገመንግስት በሚጥስ መንገድ የሶማሌ ክልል እንዲገነጠል በምርጫ አስወስነናል ይላሉ፤ ወደ ሶማሊያ እንዲጠቃለልም ያደርጋሉ። ምናባዊ ታሪክ ነው። ነገር ግን ከእውነተኛው ታሪክ ጋር ያን ያህል አይራራቅም። እስከዛሬ አልተሳካም እንጂ፤በርካታ የሶማሊያ ፖለቲከኞች ለረዥም አመታት ያቀነቀኑትን አቋም እንዲሁም በተደጋጋሚ ያካሂዱትን ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ሙከራ ስንመለከት፤ ምናባዊው ታሪክና እውነተኛው ታሪክ ተቀራራቢ መሆናቸውን ለመገንዘብ አይከብድም።
ለነገሩ ከላይ እንደጠቆምኩት፤ የኤርትራ መንግስት ጠበኛ ባሕሪዎችንም መመልከት ይቻላል። ለወጉ ያህል እንኳ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲንቀሳቀሱ የማይፈቅድ፣ ሌላው ቢቀር ለወጉ ያህል እንኳ ዜጎች በምርጫ እንዲሳተፉና ሶስት አራት ነፃ ጋዜጦች እንዲታተሙ እድል የማይሰጥ፣ ከጎረቤቶቹ ሁሉ የባሰ የለየለት አምባገነን መንግስት ነው። ነገር ግን፤ የተለያዩ ክልሎችን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል የሚፈልጉ ቡድኖችን እያሰባሰበ ይደግፋል፤ እያስታጠቀ ያሰማራል – የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት በሚል መፈክር እያሳበበ። እንዲህ አይነቱ ዘመቻ እንዴት እንደ ነፃነት ትግል ይቆጠራል?     
 አንድ የጥንት አባባል አለ – “ምን ያለበት ምን አያወራም” የሚል አይነት። አባባሉን ከዘመናዊ አኗኗር ጋር እንዲጣጣም ከፈለግን፤ “መስተዋት ውስጥ የተቀመጠ፣ ስለ ድንጋይ ውርወራ አያወራም” ልንለው እንችላለን። በመላው ዓለም ብዥታና ግርግር በበዛበት ዘመን ነው የምንኖረው። ከኋላቀርነትና ከግጭት ያልተላቀቀ አህጉር ውስጥ ነው ያለነው – ለዚያውም ለበርካታ አስርት አመታት ባልረገበ ጥላቻና ባልተቋረጠ ግጭት የሚታመሰው የአፍሪካ ቀንድ!  በዚያ ላይ፤ ከኋላቀር የጎሳና የሃይማኖት ጣጣዎች ጋር ስትዳክር ዘመናትን ያስቆጠረች ናት – አገራችን። እዚህ ውስጥ ሆነን፤ የድንጋይ ውርወራን እያዳነቅን ባናወራ ያሻላል።
Source-www.addisadmas.com

No comments:

Post a Comment