Saturday, August 17, 2013

ሰላም ምንድነው? (ታደሰ ብሩ)

ታደሰ ብሩ
መንደርደሪያ
የወያኔ ሰዎች ጋር የፓለቲካ ሙግት መሰል ነገር ከገጠማቸው ውይይቱን ያለ ጥርጥር የሚረቱበት ወደሚመስላቸው ወደ “ሰላም” ጉዳይ ይስቡታል። ከዚያም አገራችን ለዘመናት ሰላም የራቃት የነበረ መሆኑን ያስቷውሷችሁና “እድሜ ለኢሕአዴግ ይኸው የሰላም አየር እየተነፈስን ነው” ይሏችኋል። ንግግራቸውን የመቀጠል እድል ካገኙ መረር ብለው “ነገር ግን ፀረ-ሰላም ኃይሎች አልተኙልንም። በሰሜን፣ በምሥራቅ፣ በአገር ውስጥ፣ በዲያስፓራ ….” እያሉ የፀረ-ሰላም ኃይሎች ረዥም ዝርዝር ያቀርቡላችኋል።
የእርስዎ ጭንቅላት “ድልድይ እያፈረሰ አዲስ አበባ የገባ ድርጅት ስለ ሰላም ለመስበክና ሌሎቹን በአሸባሪነት ለመክሰስ እንዴት ልብ አገኘ?” በሚል ጥያቄ ተጠምዶ ሊሆን ይችላል።
ወያኔ ወዳጅዎ ግን እርቆ ሄዷል “አንተም የፀረ-ሰላም ኃይሎች መጠቀሚያ ሆነሃል፤ ከዚህ ተግባርህ ብትታቀብ ይሻልሃል። ዓለም ዓቀፍ መስፈርት ያሟላ የማያፈናፍን የፀረ-ሽብር ሕግ አለን” …. እያለ ይቀጥላል። በሰላም ስም ሰላምዎን አድፍርሶት ይውላል።
በወያኔ ቴሌቪዥንና ራድዮ የሚተላለፉ ቃላት ብዛት ስታትስቲክስ ቢኖር ኖሮ “ሰላማችን” አንደኛ ይወጣ ነበር ይሆናል። ምናልባት አንደኝነት ካጣ ደግሞ “በልማታችን” ተበልጦ ሁለተኛ ይወጣ ነበር።
በሰላም ስም ማጭበርበር የተጀመረው ዛሬ አይደለም። አዶልፍ ሂትለር የቼክ ሪፑብሊክን ከመውረሩ በፊት አስገራሚ የሰላም ጥሪ አድርጎ ነበር፤ ሩሲያን ከመወረሩ በፊት ደግሞ የሰላም ውል ተፈራርሞ ነበር። በአንድ ወቅት የሶማሊያው ዚያድ ባሬ መቋድሾ ውስጥ ታላቅ የሰላም ሰልፍ መርቷል። ከዩጋንዳው ማርሻል ኢዲአሚን ዳዳ በርካታ ኒሻኖች አንዱ “የእንግሊዝ የሰላም ኒሻን” የሚባለው ነው። ሆኖም ግን ከላይ የተጠቀሱ ሰዎች የሚታወቁት በሰላምተኝነታቸው አይደለም። ልክ እንደእነሱ ሁሉ የኛዎቹም ወያኔዎች ለሰላም ከእኔ ወዲያ ላሳር ቢሉ አይግረመን።
ለመሆኑ “ሰላም” ምንድነው?
እኔ ይህን ይህንን ጥያቄ ለራሴ ካነሳሁ ከሀያ ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል። የዛሬ 23 ዓመታት ገደማ ከፃፍኩት የተማሪነት ጊዜዬ ረዥም ግጥም ውስጥ ሶስት አንጓዎችን ብቻ ልጋብዝዎት።
ሰላም
ሰላም !!!!!
አንዱ ለፀሎተ ውዳሴው
ሌላው ለፍሬከርስኪ ጉባዬው
ደሞ ሌላው … ለነገር ማጣፈጫ
ለፈራጅ አዕምሮ ማቀጨጫ
ለአምባ-ገነን ሥልጣን መጨበጫ
ስንቱ ለከንቱ በከንቱ ያነሳሻል
አንስቶ …. ክቦ … ክቦ … ይጥልሻል
ከልጅነቴ ጀምሮ የምሰማት
ልጅ፣ ሽማግሌው የሚወዳት
የማትለወጥ ጣፋጭ ቃል
“ሰላም” የምትባል
ትርጉሟ ጠፍቶብኛል
እባካችሁ የገባችሁ አስረዱኝ
ሰላም ምንድን ናት ንገሩኝ።
በኢራን፣ በኢራቅ፣ በጋዛ ሠርጥ፣ ካምፑቺያ
ኒኳራጓ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ናምቢያ
በሰሜን ሕንድ ፣ በአፍጋኒስታን፣ በኢትዮጵያ
ያለሽ እናት፣ ያለህ ወገን
ያለህ ሕፃን
ሰላም ምን ማለት ነው ንገረኝ
ዋጋዋ ምን ያህል ነው አስረዳኝ
አንተም የአውሮፓው ሰው ንገረኝ
ስንት ነብስ፤ ስንት ሀብት፤ ስንት ጥይት ነው
ሰላምን ገዝቶ ለማቆየት ‘ሚከፈለው?
ሕዳር 1982
2. ሰላም ምን ማለት ነው?
ከላይ ቅንጫቢውን ብቻ ያቀረብኩት ረዥም መራር ግጥም ከፃፍኩ 23 ዓመታት ተቆጥረዋል። ከዚያ ወዲህ የፓለቲካ ሥርዓት ተቀይሯልጥያቄው ግን ከያኔው ይበልጥ ዛሬ አንገብጋቢ ሆኗል።
እውን ሰላም ምን ማለት ነው?
በጣም አጭርና ግልጽ የሆነ ትርጓሜ በመስጠት ልጀምር፤
ሰላም ማለት የሁከት (violence) አለመኖር ማለት ነው።
ይህ ትርጓሜ ትክክል ቢሆንም እዚህ ላይ መቆም ግን ነገር ማድበስበስ ነው።
የሚከተሉትን ሁለት ምሳሌዎችን ያጢኗቸው።
1. ማጅራት መቺዎች የበዙበት መንደር ውስጥ ሁከት እንጂ ሰላም የለም። ቶሎሳ ማጅራት መቺዎች የበዙበት መንደር ነዋሪ ነው፤ እናም በሰላም እጦት ኑሮውን በስጋትና በሰቀቀን እንዲያሳልፍ ተገዷል። ቶሎሳ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የመንደሩ ነዋሪዎች ሰላማቸው ተናግቷል።
2. “ረዥሞ” የተባለው ሰፈር አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች ረዣዥሞች ሲሆኑ አጭር ሰው አይወዱም። ሆኖም ግን ተፈጥሮ “ጠማባቸው” አጭር አድርጋ የፈጠረቻቸው ጥቂት ሰዎች ረዥሞ ሰፈር ውስጥ ይኖራሉ። እነዚህ ሰዎች በሚደርስባቸው መድልዖ፣ ማንጓጠጥና ማግለል ምክንያት ሰላማቸው ተናግቶ ኑሮዓቸውን በምሬት፣ በስጋትና በሰቀቀን እንዲያሳልፉ ተገደዋል። ጠንክር ይህንን የስጋትና የሰቀቀን ኑሮ በረዥሞ መንደር የሚገፋ ቁመተ አጭር ሰው ነው።
ቶሎሳና ጠንክር ሰላም የራቃቸው ሰዎች ናቸው። የሁለቱ የሰላም እጦት ምክንያት ግን ለየቅል ነው። የቶሎሳው ቀጥታና ግልጽ ጥቃት ሲሆን የጠንክር ግን ውስብስና መዋቅራዊ ነው። መፍትሔዎቻቸውም ለየቅል ናቸው። የቶሎሳን ችግር ዘበኛ ወይም ጠባቂ በመቅጠር መወጣት ይቻላል። የጠንክርን ችግር ለመፍታት ግን የሥርዓትና የአስተሳሰብ ለውጥ ይፈልጋል።
ሰዎች በማጅራት መቺዎች በሚዘረፉበት ከተማ ውስጥ ሰላም የሌለ መሆኑን ማሳመን ቀላል ነው። ሰዎች በመንግሥት በሚዘረፉበት ከተማ ውስጥ ሰላም የሌለ መሆኑ ማሳመን ግን የዚያን ያህል ቀላል ላይሆን ይችላል። የመንግሥት ዘረፋ እንደ ግለሰብ ዘረፋ ቀጥተኛና ግልጽ አይደለም። መንግሥት ሲዘርፍ ማጅራት መቺዎችን ማሠማራት ላያስፈልገው ይችላል። መንግሥት ኢፍትሃዊ ታክስ በመጫን ዘረፋውን ሕጋዊ ሊያደርገው ይችላል። የመንግሥት ዘረፋ በግልጽ ላይታይ ይችላል፤ ቀስ እያለ እየተብላላ ቆይቶ ሲፈነዳ ግን ውጤቱ አንድ ወይም ሁለት ማጅራት መቺዎችን ለፍርድ ከማቅረብ ጋር የሚመሳሰል አይደለም።
ከላይ ከቀረቡት ምሳሌዎች ሁለት ዓይነት ሰላሞች መኖራቸውን መገንዘብ እንችላለን። እነዚህ ሁለት ዓይነት ሰላሞች አሉታዊ ሰላም እና አዎንታዊ ሰላም ተብለው ይጠራሉ።
1. አሉታዊ ሰላም (Negative Peace) – አሉታዊ ሰላም በግለሰብ ወይም በቤተሰብ ላይ ግልጽ ሁከት (Direct Violence) ያለመኖር ውጤት ነው።
በሰዎች ሕይወት ወይም ንብረት ላይ ቀጥተኛ ጥቃት ሲፈፀም ግልጽ ሁከት ተፈፀመ ይባላል። ለምሳሌ፣ ጦርነት በሰውም በንብረትም ላይ ቀጥተኛ ጥቃት የሚያደርስ በመሆኑ ግልጽ ሁከት ነው። ዝርፊያና ቅሚያም ግልጽ ሁከቶች ናቸው። ግልጽ ሁከት ከሌለ ዘራፊዎች፣ ኪስ አውላቂዎች፣ ወመኔዎች፣ ልጃገረዶችን የሚደፍሩ ምግባረ ብልሹዎች የሉም ማለት ነውና ሰዎች በሰላም ወጥተው በሰላም ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ።
በግልጽ ሁከት መወገድ ሳቢያ የሚገኘው ሰላም “አሉታዊ ሰላም” ይባላል። አሉታዊ ሰላም ሲኖር “ሁሉ አማን” የሆነ ሊመስል ይችላል ሆኖም ሁከቱን እንጂ የሁከቱን ሥረ ምክንያት ስለማያስቀረው ወደፊት ሁከት የመነሳት እድሉ ከፍተኛ ነው።
2. አዎንታዊ ሰላም (Positive Peace) – አዎንታዊ ሰላም የመዋቅራዊ ሁከት[1] (structural vilolence) ያለመኖር ውጤት ነው።
መዋቅራዊ ሁከት በአድሎዓዊ ሥርዓት ሳቢያ የሚደረግ ተቋማዊ ጥቃትን ይመለከታል። ዘረኛ ፓሊሲ ለምሳሌ አንዱ ዘር ሌሎቹን እንዲያጠቃ መንገድ የሚያመቻች በመሆኑ ተቋማዊ ሁከትን ይፈጥራል። ወንዶች በሴቶች ላይ የበላይነት እንዲኖራቸው ሥርዓቱ የሚፈቅድ ከሆነ ውጤቱ በሴቶች ላይ የሚደርስ ተቋማዊ ጥቃት ነው። በተዛባ የሀብት ክፍፍል ሳቢያ የሚመጣ ድህነት የመዋቅራዊ ሁከት ውጤት ነው። የፍትህ መዛባት፣ ግዙፍ ሙስናዎች (Grand Corruption)፣ በሥልጣን መባለጎች የመዋቅራዊ ሁከት ውጤቶች ናቸው። ማይምነትም ቢሆን በአብዛኛው የመዋቅራዊ ሁከት ውጤት ነው።
በመዋቅራዊ ሁከት መወገድ ምክንያት የሚገኝ ሰላም “አዎንታዊ ሰላም” ይባላል። በሌላ አነጋገር አዎንታዊ ሰላም የሚሰፍነው ማኅበራዊ ፍትህ ሲሰፍን ነው። አዎንታዊ ሰላም ሲኖር ሰዎች ችግሮቻቸውን በድርድር ይፈታሉ። አዎንታዊ ሰላም በማኅበራዊ ቡድኖች መካከል ቀና የሆነ መስተጋብር መኖሩ አመልካች ነው።
3. አሉታዊ ሰላም እና አምባ-ገነን አገዛዞች
በአንድ አገር ውስጥ አዎንታዊ ሰላም አለ ማለት በዜጎች መካከል መዋቅራዊ መድልዎ አይደረግም ማለት ነው። አዎንታዊ ሰላም የሰፈነበት አገር ሕዝብ ከራሱ ጋር የታረቀ ነው። በዚህ አገር ውስጥ ለዘላቂ ሰላም አስተማማኝ መሠረት ተጥሏል ብለን አፋችንን ሞልተን መናገር እንችላለን። ይህ ማለት ግን አንድ ሰካራም ሌላውን የሚፈነክትበት አጋጣሚ የለም ማለት አይደለም። ፈጽሞ ግጭቶች አይነሱም ማለትም አይደለም። እንዲያውም በየጊዜው ሰልፎችና ተቃዉሞዎች በአደባባይ የሚሰሙበት ግርግር የበዛበት አገር ሊሆን ይችላል። ሆኖም ግን አለመግባባቶች ቢነሱ መፍትሔ የሚያገኙበት አሠራር አለ። አዎንታዊ ሰላም ችግሮች ሲፈጠሩ መፍትሔ እየፈለገላቸው ራሱን ጠብቆ የሚያቆይ ሰላም ነው። የአዎንታዊ ሰላም መኖር ለዘላቂ ሰላም ዋስትና ነው።
በአንፃሩ አዎንታዊ ሰላም ሳይኖር አሉታዊ ሰላም ሊኖር ይችላል። ማኅበራዊ ችግሮች ሳይነኩ ግልጽ ሁከቶችን ብቻ በማስወገድ ወይን በማፈን አሉታዊ ሰላምን ማስፈን ይቻላል።
አምባገነን መንግሥታት የአሉታዊ ሰላም አፍቃሪዎች ናቸው። የመንደር ሌቦችን፣ ማጅራት መቺዎችን፣ ወመኔዎችን እያደኑ አይቀጡ ጥቃት ይቀጣሉ። በዚህም ዓይነቱ ሥራቸው “የሰላም አባት” የተባሉ አምባገነኖች ብዙ ናቸው። ታድያ ግን ተቃዋሚዎቻቸውንም ከሌቦችና ዘራፊዎች ጋር ደብልቀው ይቀጣሉ። በውጤቱም ብዙዎች አምባገነን መንግሥታት የሚኩራሩበትን “ሰላም” ያሰፍናሉ። ይህ ዓይነቱ አሉታዊ ሰላም “አደገኛ ሰላም” ብለን መጥራት እንችላለን።
ታሪክን ገረፍ እናድርግ። በጆሴፍ ስታሊን “ቆራጥ አመራር” ሳቢያ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ እስከ ሚካኤል ጎርባቾች አመራር ድረስ ለአርባ ዓመታት ያህል የዘለቀ አደገኛ አሉታዊ ሰላም በመላው የሶቭየት ኅብረት ግዛት ውስጥ ሰፍኖ ነበር። ምሥራቅ ጀርመንን 1949 እስከ 1990 እአአ ለ 41 ዓመታት ሉዓላዊት አገር አድርጎ ያቆያት ሕዝብን በክርን በመደቆስ በተገኘ አሉታዊ ሰላም ነው። አልባኒያም ከ30 ዓመታት በላይ በጡንቻ “የሰላም ደሴት” ሆና ኖራለች። ሊቢያ በኮሎኔል ሞአመር ጋዳፊ ብርቱ “ሕዝባዊ ክንድ” እና በአረንጓዴው መጽሐፍ አረንጓዴ መመሪያ ለ30 ዓመታት ኮሽታ የማይሰማባት ሁለመናዋ አረንጓዴ የሆነች አገር ሆና ነበር። ሙባረክ እስራኤልን የመሰለ የጎረቤት ባላንጣ እያለበት እንኳም ግብጽን ለ30 ዓመታት “በሰላም” ገዝቷል። አውሮፓ ውስጥ አሉታዊ ሰላም ለተራዘመ ጊዜ ከቆየባቸው አገሮች ግንባር ቀደሟ ዩጎዝላቢያ ናት። እአአ 1929 እስከ 1991 ለ68 ዓመታት ጉልበት ያፈረጠው አሉታዊ ሰላም ዩጎዝላቪያን ሰብስቦ አቆያት።
ከላይ ከተዘረዘሩት ምሳሌዎች በቀላሉ መረዳት እንደሚቻለው አደገኛ የሆነው አሉታዊ ሰላም ለተወሰነ ጊዜ መልካም ቢመስልም ከረዥም ጊዜ ውጤቶቹ አንዱ ውድመት መሆኑ ነው። ሶብየት ኅብረት ተበታትና ከካርታ ጠፋች። ምሥራቅ ጀርመን በምዕራብ ጀርመን ተውጣ ከካርታ ጠፋች። ዮጎዝላቢያ እጅግ አሳዛኝ በሆነ መንገድ ተበታትና ከካርታ ጠፋች። አልባኒና አዲስ አገር እንደና ተዋቀረች። ሊቢያ አረንጓዴ ሰንደቅ ዓላማዋን ጥላ ከአርባ ዓመታት በፊት ወደነበረው ማንነቷ ለመመለስ እየጣረች ነው። ግብጽ ገና ራሷን ፈልጋ ማግኘት አልቻለችም። አብዛኛውም ጊዜ አሉታዊ ሰላሞች ሲደፈርሱ የቆሙበትን ሥርዓት ይዘው ነው የሚጠፉት።
ወደ ራሳችን ጉዳይ እንመለስ። ወያኔ ነጋ ጠባ “ሰላማችን፤ ሰላማችን” የሚለው የትኛውን ዓይነት ሰላም ፈጥሮ ነው?
•ዘረኝነት የፓለቲካ ሥርዓቱ መታወቂያ ሆኖ እያለ፤
•ኢፍትሃዊ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል እና ሙስና የሥርዓቱ መለያ ሆነው እያለ፤
•ፍትህ ተዋርዳ ፍርድ ቤቶች ገዢዎች የሰጡት ቅጣት ማሳወቂያ በሆኑበት፤
•በዘርና በፓለቲካ ወገንተኝነት የተዋቀሩት የጦር ሠራዊት፣ የፓሊስና የስለላ ተቋማት ኢትዮጵያዊያንን ማጥቂያ ሆነው እያለ፤
•በፓለቲካ እምነታቸውና በሀይማኖቻቸው ምክንያት ታስረው ሰቆቃ እየተፈፀማቸው ያሉ ወገኖቻችን ብዛት በአስደጋጭ ፍጥነት እየጨመረ ባለበት ሁኔታ፤
•ሚሊዮኖች ድሀ ገበሬዎች ከይዞታቸው እየተፈናቀሉ በገዛ አገራቸው ስደተኛ የሆኑበት ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን እያየን፤
•ኢትዮጵያዊያን ገበሬዎች ቤተሰቦቻቸውን የሚመግቡት ቁራጭ መሬት አጥተው እያለ ሰፋፊ ለም መሬቶች ለውጭ ባለሀብቶች በገፍ እየተሸጠ ባለበት ሁኔታ፤
•የወያኔ ሹማምንት በሀብት ላይ ሀብት እየጨመሩ ከተሞችን በሕንፃዎች ሲያሽቆጠቆጡ ዛንጋባ እንኳን አጥተው በረንዳ ላይ የሚያድሩ ዜጎች ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ መሆኑን በገዛ ዓይኖቻችን እያየን፤
•ከፍተኛ ትምህርታቸው ያጠናቀቁ ወጣቶች ለሚጠብቃቸው የሥራ እድል ባይማሩ ኖሮ ይበልጥ ተመራጭ ይሆኑ የነበረ የመሆኑ አሳዛኝ ሐቅ እያየን፤
•ወጣቶች በተስፋ እጦት ከአገር ሲሰደዱ በባህር ሰጥመው አሊያም በበረሃ ንዳድ ተቃጥለው እያለቁ ባሉበት በአሁኑ ሰዓት፤
•አብዛኛው ሰው ቁርስ፣ ምሳና ራቱን ደርቦ “ቁምራ” እየበላ ስለ ተከታታይ ዓመታት 11.6 % ዓመታዊ የኢኮኖሚ እድገት መስማት ግዴታ የሆነበት የጉድ አገር ሆኖ እያለ፤
•የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪቃና የአረብ አገራት እስር ቤቶች በኢትዮጵያዊያን ወንዶችና ሴቶች ተሞልተው እያለ፤ እና
•ወያኔ የሚያደርሰው ግፍ ሞልቶ በፈሰሰበት በአሁኑ ወቅት “ሰላማችን፣ ሰላማችን” እያለ ሲነዘንዘን መስማት ልብን ያቆስላል።
ይኸ ሁሉ ኢፍትሃዊነት ባለበት ሊኖር የሚችለው ሰላም አሉታዊ ሰላም ያውም ተቃውሞን በጉልበት በመደፍጠጥ የሚገኘው አደገኛ አሉታዊ ሰላም ብቻ ነው። ለዚህም ነው ወያኔ ሕገወጥነትን ሕጋዊ የሚደርጉ አዋጆችን የሚያወጣው።
በጉልበት የሚመጣ አሉታዊ ሰላም ለአገራችን አይበጃትምና የወያኔን ሰላም መቃወም ተገቢ ነው። ከብዙ አገሮች ልምድ እንዳየነው አደገኛው አሉታዊ ሰላም ከመኖሩ አለመኖሩ ይሻላል። የወያኔ ሰላምም ለኢትዮጵያችን የሚበጅ አይደለም።
4. ሰላምተኛነት ሁሌ ትክክል ነውን?
በዚህ ንዑስ አርዕስት ሥር ለማለት የፈለግሁትን ሁሉ ሁለት ትላልቅ ስም ያላቸው ሰዎች ስላሉልኝ ለእነሱ ቦታ እለቃለሁ።
ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ
ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ታህሳስ 4 ቀን 2002 ዓ. ም. (December 10, 2009) የኖቤል የሰላም ሽልማት ሲቀበሉ ያደረጉት ንግግር ሙሉው መሰማት (ወይም መነበብ) ያለበት ቢሆንም አንባቢዎቼን ላለማሰልቸት አለፍ አለፍ ብዬ ልጥቀስ[2]።
እውነቱን በመቀበል እንጀምር − ብጥብጥ ያለበት ቅራኔን በእኛ እድሜ ማስቀረት አንችልም። ለወደፊቱም ሕዝቦች − በግልም ሆነ በጋራ − ኃይልን መጠቀም አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ከሞራል አንፃርም ተገቢ የሚሆንበት ሁኔታ ይኖራል።
አንሳሳት! ክፋት በዓለም ላይ አለ። በሰላማዊ ትግል ሂትለርን መግታት አይቻልም ነበር። ድርድር የአልቃይዳን መሪዎች መሣሪያዎቻቸውን እንዲጥሉ አያደርግም። አንዳንዴ ጉልበት መጠቀም ያስፈልጋል ማለት ከሃቅ የራቀ ምፀት አይደለም፤ ይልቁንስ ታሪክን በቅጡ መረዳት፤ የሰውን ልጅ ድክመቶችን ማወቅ እና የምክንያታዊነት ውስንነትን መገንዘብ ነው።
ሲቪል ዜጎች በገዛ መንግሥታቸው የሚታረዱበት ሁኔታ፤ የእርስ በርስ ጦርነቶች ወይም አንድን የዓለም አካባቢ ሊያምሱ የሚችሉ ብጥብጦችና ሰቆቃዎችን ለመከላከል ኃይልን የመጠቀም አማራጭ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።
ሰላም ተመራጭ መሆኑ መታመኑ ብቻውን ሰላምን ለማስገኘት አይበቃም። ሰላም ኃላፊነት መቀበል ይጠይቃል። ሰላም መስዋዕትነትን ይጠይቃል።
ሰላም የሚታይ ብጥብጥ አለመኖር ማለት አይደለም። ፍትሃዊ ሰላም ዘላቂነት የሚኖረው በእያንዳንዱ ግለሰብ ተፈጥሮዓዊ መብቶችና ክብር ላይ የተገነባ ሲሆን ነው።
ዜጎች የመናገር፣ የማምለክ፣ መሪዎቻቸውን የመምረጥ ወይም ያለፍርሃት የመሰብሰብ ነፃነታቸው በተገፈፉ ጊዜ ዘላቂ ሰላም አይኖርም። …. እንደምናውቀው አውሮፓም ሰላም ያገኘችው ነፃ ስትሆን ነው።
ፕሬዚዳንት ኦባማ ኢትዮጵያዊ ሁነው ይህንን ንግግር አዲስ አበባ ውስጥ ተናግረውት ቢሆን ኖሮ ሕገወጥነትን ሕጋዊ ያደረጉ አንቀጾች ተጠቅሰውባቸው ንግግራቸው ለአሸባሪነታቸው የማያሻማ ማስረጃ ሆኖ እድሜ ልክ ያስፈርድባቸው ነበር። እሳቸው ግን ኦስሎ ውስጥ በበርካታ ካሜራዎች ፊት ለፊት የሰላም የኖቤል ሽልማት ለመቀበል ይህንን ተናገሩ።
የሰላም የኖቤል ሽልማት ተሸላሚው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ “አንሳሳት! ክፋት በዓለም ላይ አለ። በሰላማዊ ትግል ሂትለርን መግታት አይቻልም ነበር” አሉ። ቀጥለውም “ሲቪል ዜጎች በገዛ መንግሥታቸው የሚታረዱበት ሁኔታ፤ የእርስ በርስ ጦርነቶች ወይም አንድን የዓለም አካባቢ ሊያምሱ የሚችሉ ብጥብጦችና ሰቆቃዎችን ለመከላከል ኃይልን የመጠቀም አማራጭ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል” አሉ።
ማርቲን ሉተርን ኪንግ
የማርቲን ሉተርን ኪንግን “ፍቅር፣ ሕግ እና ሕዝባዊ እምቢተኝነት[3]” ሙሉውን ማንበብ ይጠቅማል። ለአሁኑ ግን አንዲት ትንሽ ጥቅስ ብቻ ልውሰድ፡
ሰላም ማለት ፍትህ፣ ቀና ፍላጎትና ወንድማማችነትን የመሳሰሉ አዎንታዊ ነገሮች መገኘት ጭምር እንጂ ጭንቀት፣ ውዥንብር ወይም ጦርነት የመሳሰሉ አሉታዊ ነገሮች አለመኖር ማለት ብቻ አይደለም። ኢየሱስ “ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም” ሲል …… እኔ እንደሚመስለኝ ለማለት የፈለገው የሚከተለውን ነው። …. ውጥረትም ሆነ ቅራኔ የሌለበት የድሮዉን አሉታዊ ሰላም አይደለም ይዤላችሁ የመጣሁት። እኔ ይዤላችሁ የመጣሁት በብርሀንናና በጨለማ፣ በፍትህና ኢፍትሃዊነት መካከል ባለ ፍትጊያ የሚንቀለቀለውን አዎንታዊውን ሰላምን ነው።
….
5. ማጠቃለያ
የወያኔ ካድሬዎች፣ ራድዮና ቴሌቪዥናቸው ስለ ሰላም አውርተው አይጠግቡም። “ሰላማችንን አደጋ ላይ ሊጥሉብን ሞከሩ” በሚል ሰበብ በርካታ ወገኖቻችን በእስር ቤቶች እየማቀቁ ነው።
ሰላም አንድ አይነት ስታንዳርድ የወጣለት የፋብሪካ ሸቀጥ አይደለም። ጥሩ ሰላም አለ፤ መጥፎ ሰላምም አለ። እናም ወያኔዎች የሚዘፍኑለት የሚያቅራሩለት ሰላም ምን ዓይነት ሰላም እንደሆነ መርምረን ማወቅ የራሳችን ኃላፊነት ነው።
ሕዝብ በማፈንና በመርገጥ የሚመጣ ሰላም በረዥም ጊዜ አገርን የከፋ አደጋ ላይ ይጥላልና አንፈልገውም። አደገኛውን አሉታዊ ሰላምን መቃወም ሕዝብን፣ ነፃነቱንና አገሩን ከሚወድ ዜጋ ሁሉ የሚጠበቅ ተግባር ነው። በሰላም ስም ሲያታልሉን ልንታለልላቸው አይገባም።
ሰዎች በሰላም ውለው መግባታቸው ብቻውን የዘላቂ ሰላም ምልክት አይደለም። የዘላቂ ሰላም ዋስትና ማኅበራዊ ፍትህን ማስፈን ነው፤ ይህ ደግሞ ወያኔ ሥልጣን ላይ ሆኖ የሚሆን ነገር አይደለም።
አስተያየት መስጠት ከፈለጉ: tkersmo@gmail.com

No comments:

Post a Comment