Monday, March 10, 2014

የኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች በዶ/ር ደብረጽዮን ፍቃድ ካልሆነ ምንም ዓይነት ውሳኔ መስጠት እንደማይችሉ ተገለጸ


የደህንነት ሹሙ አቶ ጌታቸው አሰፋና ባለስልጣኖቻቸው በሙስና እና በዘረፋ ላይ ተሰማርተዋል
የፍርድ ቤቶች እና የተቃዋሚ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ ማኮላሸት ለአለቃ ጸጋዬ በርሄ ተሰቷቸዋል
የጦር ሰራዊቱን በተጠንቀቅ የሚከታተሉ ወታደራዊ ደህንነቶች ተደራጅተው በየእዙ ተበትነዋል


ምኒልክ ሳልሳዊ

በመከላከያ ሰራዊት የሕወሓት መኮንኖች ስር የሰደደው የሙስና እና የዘረፋ አድራጎት በደህንነት መስሪያ ቤት ውስጥም ከሹሙ ከአቶ ጌታቸው እና ከባለስልጣኖቻቸው ጀምሮ እስከ ገራፊዎች ድረስ መንሰራፋቱን ውስጥ አዋቂ ምንጮች ገልጸዋል:: እንደውስጥ አዋቂ ምንጮቹ መረጃ ከሆነ የደህንነት ባለስልጣኖቹ የተዘፈቁበት የሙስና ተግባር በተጨማሪ ዘረፋን እና ሴት መድፈርን እንዲሁም የቡድን ወንጀሎችን ያካተተ መሆኑ ተጠቁሟል::በተለያዩ ከተሞች የሚገኙ ባለሃብቶችን በማስፈራራት ከፍርድ ቤት ትእዛዝ ውጪ በማሰር እንዲሁም የሙስና ወንጀል ተገኝቶብሃል ይህን ያህል ገንዘብ አምጣ ካላመጣህ እንገድልሃለን እስከማለት በከመድረሳቸውም በተጨማሪ ይህንን ጉዳይ ለፖሊስ የጠቆመ ባለሃብት በማፈን ንብረቱ ባማገድ እና በተለያዩ ስልቶች የተጠየቀውን ገንዘብ እንዲሰጥ በማስገደድ ላይ መሆናቸውን ምንጮቹ ጠቁመዋል::

ከዚህ ቀደም በሙስና የተከሰሱ የስርኣቱ ባለስልጣናትን ተገን በማደርግ በአዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ ባለሃብቶችን በመከታተል እና ደህንነት ቢሮ ድረስ በመውሰድ በሙስና ከታሰረው ስም እየተጠቀሰ … ከሚባል ባለስልጣን ጋር ግንኙነት አለህ ማስረጃ ተገኝቶብሃል በማለት በፈጠራ ወንጀል ባለሃብቱን በመዝረፍ ስራ ላይ ተሰማርተው የነበረ እና እንዲሁም የአዲስ አበባን ቆነጃጅት ቢሯቸው ድረስ በግብረአበሮቻቸው አፋኝነት እና አስገዳጅነት በመውሰድ ካለፍላጎታቸው አስገድደው በመድፈር ላይ ናቸው ያሉት ምንጮቹ ተራ የደህንነት አባላት ለዚሁ ተልእኮ ተሰማርተው የሚሰሩት ምንም አይነት ወንጀል በቡድን ሲፈጽሙ የሚጠይቃቸው አለመኖሩን የሕዝቡን በደል የከፋ አድርጎታል::

ኢትዮጵያውያን በሕወሓቱ የደህንነት መዋቅር የሚመራ የሽብር ተግባራትን አጥብቆ ስለሚፈራ እና በየጊዜው በሕወሓት ደህንነቶች መሪነት የሚወሰዱ እርምጃዎች በሃገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ስጋትን በመፍጠራቸው በየእስር ቤቱ የሚካሄዱ ሕገወጥ ጸረ ፍትህ ተግባራት እና የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች የኢትዮጵያውያን የቀን ተቀን አጀንዳ ሆነው መምጣታቸው ገዢው ፓርቲ ሕዝቡን ምን ያህል እንዳሸበረ ይጠቁማል ሲሉ ምንጮሹ አክለው ገልጸዋል::

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሕወሓትን ሳይጨምር ብኣዴን ኦሕዴድ ደኢሕዴግ እና አጋል የክልል ጎሳ ፓርቲዎች ከአቶ ደብረጽዮን በሚወርድ ትእዛዝ ካልሆነ በስተቀር ምንም አይነት እርምጃ በፍቃዳቸው መፈጸም እንደማይችሉ ተነግሯቸዋል:: በቅርቡ የአቶ አለማየሁ አቶምሳን ሞት ተከትሎ አፈጻጸሙ በዶ/ር ደብረጽሆን መልካም ፍቃድ እንደሆነ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የተባለው የኦሕዴድ ሙክታር ከድር አቶ አለማየሁ ደክመው እያየ እና እያወቀ ሆስፒታል እንዲሄዱ አስቸኳይ ትብብር እንዲደረግ ወይዘሮ አስቴር ማሞ ስትጠይቀው ለዶ/ር ደብረጽሆን ነግረሽ አስፈቅጂ በማለት ሕወሓት በኦሕዴድ አናት ላይ ምን ያህል እየሸና እንዳለ እንዲሁም በሞራላቸው አመራሮቹ እንዳይራመዱ እያደረገ እንዳለ ፍንትው አድርጎ ያሳየ ነው:: ማንኛውም የኢሕኣዴግ አባል እና አጋር ድርጅት በድርጅቱ ሊቀመንበር ወይንም ምክትል አማካኝነት በቅድሚያ ለዶ/ር ደብረጺሆን ሪፖርት ማድረግ እና ሁኔታው ታይቶ ፈቃድ እና ውሳነ ካልተሰጠው በስተቀር መፈጸም እንደማይችል ትእዛ መተላለፉ ሲታወቅ በአዲስ አበባ እና በክልል ያለው የፍርድ ቤቶች እና የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ በአለቃ ጸጋይ በርኸ ስር ክትትል እየተደረገ እርምጃ የሚወሰድበት መሆኑ ሲታውቅ የጦር ሰራዊቱን በተመለከት በተዋረድ የሚያስተዳድሩ የወታደራዊ ደህንነት የሕወሓት መኮንኖች ተደራጅተው በየእዙ መመደባቸው ታውቋል:

የሴት ነገር ሰማያዊ በቢጫ (ከቹቹቤ)

ከቹቹቤ

Ethiopian women protested in Addis Ababa
በተለምዶ የሴት ነገር ስንል የማሳነስ የማቀጨጭ ነው። የሴት ነገር ግን ሁሌም ቢሆን ከዚህ በላይ እንደሆነ ሁላችንም እናውቃለን። የሴትን ነገር የሚያሳንሱ ቢኖሩ ጉልበት አምላኪዎች ብቻ ናቸው። አርግዛ አምጣና ወልዳ የምታሳድግን ሴት እንደ ቅርንጫፍ ከጎድን አጥንት ተሰራች የሚለው አሳናሽ አገላለጽም የሃይማኖት ድጋፍ ይዞ ስለተነሳ ሴቶች ራሳቸው ያነሱ ሆነው እስከሚሰማቸው ድረስ ተጽዕኖ አሳዳሪ መሆኑ እውነት ነው። ዘፍጥረት ወንዴና ሴቴ ሆነው የተፈጠሩትን ሌሎች ፍጡራን (እንስሳውን እጽዋቱን) ሁሉ እግዜር እንዴት እንደፈጠራቸው መናገሩን አላውቅም።  የኔዋ እናት ግን በምንም መልኩ ከኔው አባት አንሳ የጎድን ፍልቃቂው ልትሆን አይቻላትም። እንዴት ተደርጎ! እኔም በማህጸን ውስጥ ሞተር ሲገጠምልኝ፣ እግርና እጅ ሲሰራልኝ አፍንጫ ጆሮና አይኔ ዲዛይን ሲደረግ ስለቆየሁ እርሷ የኔ ፈጣሪ ናት ብዬ ነው እምዬ ስላት ደስ የምሰኘው። እርግጥ ነው የተወሰነ ጥሬ ሃብት ከአባቴ ወስዳለች። በዚያው አይን የኔ የምትሆነው ሴቲቱ ከጎድኔ አንዱ ተቀንሶ እንደተሰራች መቀበል ያዳግተኛል። በእንስሳቱ አለም የሴቶች ሚና እጅግ በጣም ጉልህ መሆኑን ለተመለከተ የሰው ፍጡር ሲሆኑ ሊያሳንስበት የሚችልበት ምንም ምክንያት የለውም። በተለይ በማህበራዊ እንስሳትም ሆነ ነብሳት ውስጥ ሴቲቱ አልፋና ኦሜጋ ናት። ቢሆንም…..ቢሆንም አውቄ በድፍረት ሳላውቅ በስህተት ላልኩት ንስሃ ልግባና ሰማያዊ በቢጫ እንዴት ደስ እንዳሰኘኝ ልናገር።
የቪድዮ ሽራፊ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች መወያያ መድረክ ድህረ ገጽ ላይ ተመለከትኩ። ቢጫ ቲሸርት የለበሱ ቆነጃጅትም አየሁ። ሁሉም ያምራሉ በስፖርት የዳበረ የሰውነት ቅርጽም አላቸው። ወበታቸውን እያደነቅሁ አሯሯጣቸውን ለመመልከት የማጫወቻውን ቁልፍ ስጫነው የበለጠ ማረኩኝ። ማማር ብቻ ቢሆን ምን ነበረበት። የጥንካሬያቸው፣ የጀግንነታቸው የድፍረታቸው መጠን የበለጠውን ማረከኝ። ወጣትነትን በነጭ ሽብር፣ በቀይ ሽብር ስመለከት ቆይቼ ሰማያዊን በቀደም ሳደንቅ ነበር። ቢጫን የሰጠሁት ተስፋ ቆርጠው ጠጅ ቤት ለቀሩት ነበር። አሁን ቢጫ ንቁና የሚያማምሩ ወጣት ሴቶች ነፃነት ነፃነት እያሉ ሲዘምሩበት ሰማሁ ተመለከትኩም። የወያኔን እስር ቤት ያጨናነቁትን እገሌ ከእገሌ ሳይመርጡ ከጋዜጠኛው፣ ከፖለቲከኛው፣ በሃይማኖት ምክንያት ከታጎሩት ሳይቀር ስም እየጠሩ ይፈቱ እያሉ አደባባዩን ሲሰነጥቁ ተመለከትኩ። አይ ሴት! አልኩ ሴት እኮ ይሁን ብላ ከገባች የማትናወጥ ሃይል ናት እያልኩ ኮራሁ። በወጣቶች ተስፋ ማድረግ ለካንስ ህይወት ያለመልማል፣ በዚያ ላይ በወጣት ሴቶች! የነገውን ትውልድ አምጠው በሚወልዱት እናቶች መኩራት በእርግጥም ተስፋን ያለመልማል አልኩ።
ወደ ቪድዮው አናት ላይ የተጻፈውን ሳነብ ደግሞ የሰማያዊ ፓርቲ አክቲቪስቶች መሆናቸውን አነበብኩ፤ ሰማያዊ ነገር ለምልክትም ወጣቶቹ ላይ አላየሁም ነበር። ነገሩ ሲገባኝ የበለጠ ደስ አለኝ። ሌላውን ማንበብ ስጀምር ግን መታሰራቸውን ተረድቼ አዘንኩ።  አሁን ጥያቄያቸው በሙሉ ቀላል ሆኖ ሳለ በዲሞክራሲ በታነጸች አገር ዘለዓለማዊ ክብርና ሞገስ ለታጋዮቻችን የሚል እንደ ሃይለማርያም ያለ መሪ ባለበት ሃገር እነዚህ ወጣቶች መታሰራቸው ምን ይባላል? አልኩ። ሰውየው ለወያኔና ለተቀጥላዎቻቸው ሳይሆን ለታጋዮች በሙሉ ብለው አስረግጠው ከተናገሩ ወዲህ ያለው መዘባረቅ አይሆንምን? አሰኘኝ። ደግሞ ኑሮ ልክ አጣ አማረርን አሉ እንጂ በመንግስታችን ላይ ተማረርን አላሉም። ነፃነት የሚጠላ የትግሬ ነፃ አውጪ ነው አንዴ የሚገዛን? የሚል ቁጣን የሚያስነሳ ስህተት በመንግስት አካላት በመወሰዱ ሴቶቹ ሁሉ ተጋግዘው እንደ ላይቤርያ አምባገነኖችን ሊፈነግሉ ይችላሉና ማሰሩ ትግል ማክረሩን ላሳስባቸው ፈቀድኩ። ቢሰሙ ኖሮ ከሕዝብ ይስማሙ አልነበር አትድከም የሚል የኔው ሃሳብ አቋረጠኝና ምክሬን ተውኩት።
በዚህ ቪድዮ ላያ ያየሁት ትንሽ ቢሆንም የተሰማኝ ግን ትልቅ ስሜት ነበር። አዎ የሃገራችን ሴቶች ሊደመጡ ይገባል! ሊከበሩ ይገባል! ሊሳተፉ ይገባል! ለዚህም ሁኔታዎችን ማመቻቸትና መፍቀድ ይገባል! ስክነት ብልህነትና እውቀት እንጂ ሩጫ ግርግርና ጡንቻ ብቻውን አገር አይለውጥም! የሚል መፈክር እያሰማሁ ከሁዋላቸው የምከተልም መሰለኝ።
ለሴት እህቶቻችን፣ እናቶቻችን፣ ሚስቶቻችንና ጓደኞቻችን በሙሉ ክብር ይሁን!
ነገን አምጠው ለሚወልዱ ቁርጠኛ ወጣቶች ሁሉ ክብር ይሁን!
http://ecadforum.com/Amharic/archives/11349/

Sunday, March 9, 2014

ትግሉን በእስራት እና በግድያ ማስቆም አይቻልም

ነፃነት እንፈልጋለን ያሉ ሴት እህቶች በአደባባይ ተቃውሞ ካሰሙ በኋላ 6ቱ ወዲያው ታሰሩ (የተቃውሞውን ቪድዮ ይዘናል)



ሰማያዊ ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ እና የድርጅት ጉዳይ ሃላፊው ከሴቶቹ ጋር በቁጥጥር ስር ውለዋል
የሰማያዊ ፓርቲ ወጣት ቡድን እንደዘገበው ዛሬ በተካሄደው የሴቶች 5ሺሜትር ሩጫ ላይ የሰማያዊ ፓርቲ የሰቶች ጉዳይ ባመቻቸው እድል የፓርቲው ሴቶች የሮጡ ሲሆን በሩጫውም ላይ የተለያዩ መፈክሮች ማለትም ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ ትፈታ፤ አቡበከር ይፈታ፣ እስክንድር ይፈታ፣ አንዷአለም ይፈታ፣ ነፃነት እንፈልጋለን እና ሌሎች ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች አሰምተዋል::
ከመነሻው የጀመረው የተቋውሞ ድምጽ እስከ ማብቂያው የቀጠለ ሲሆን ሩጫቸውን ጨርሰው ሊገቡ ሲሉ በፖሊሶች ተቆርጠው በአሁኑ ሰዐት ታስረው ይገኛሉ። በሩጫው ወቅት ተቋውሞ ሲያሰሙ የሚያሳይ ቪድዮ እና ፎቶ እንደደረሰን ምንለቅ መሆኑን በትህትና እንገልጻለን::
የሰማያዊ ፓርቲ የሴቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሴት አባላት እና ከእናርሱ ጋር የነበሩ ሴቶች በዛሬው እለት በተካሄደው ሩጫ ላይ ተሳትፈው ሃሳባቸውን በመግለጽ ላይ አንዳሉ በሩጫው መጨረሻ ላይ በፖሊስ ታፍሰው ወዳልታወቀ ቦታ ተወስደዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአከባቢው የነበሩት የሰማያዊ ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ብርሃኑ እና የድርጅት ጉዳይ ሃላፊው አቶ ጌታነህ ሴቶቹ መታሰራቸው ምንም አግባብነት እና ህጋዊ መሰረት የለውም በማለታቸው ከሴቶቹ ጋር በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
የእስረኞች ስም ዝርዝር
1 ንግስት ወንድይፍራ(የህዝብ ግንኙነት ኮሚቴ)
2 ወይንሸት ሞላ (የምክርቤት አባል)
3 ወይኒ ንጉሴ(አባል)
4. እመቤት ግርማ(አባል)
5. ሜሮን አለማየሁ (አባል)
6. ምኞት መኮንን(አባል)
ለጊዜው የሴቶች ጉዳይ እና የህግ ጉዳይ ኮሚቴ የሆኑት ኢየሩስ ተስፋው እና ኤልሳ ወሰኔ ያሉበትን ልናውቅ አልቻልንም፡፡
ከነዚህ ሴቶች በተጨማሪም በቦታው የነበሩት የፓርቲው ህዝብ ግንኙነት አቶ ብርሀኑ ተ/ያሬድ ፤ የድርጅት ጉዳይ ሀላፊው አቶ ጌታነህ ባልቻ እና የህዝብ ግንኑነት ኮሚቴ አቶ አቤል ኤፍሬም ናቸው፡፡
እንዲሁም የሰማያዊ ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ አቤል ኤፍሬም በአካባቢው ስለነበሩ ብቻ በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ያሉበትን ለማጣራት የሰማያዊ ወጣት ክንፍ አባላት በእንቅስቃሴ ላይ መሆናችንን እያስታወቅን የደረስንበትን ይፋ የምናደርግ መሆኑን እናስታውቃለን፡
ትግሉን በእስራት እና በግድያ ማስቆም አይቻልም::

“ለስድስት ወር ያልጋ ቁራኛ የዳረገኝ የግድያ ሙከራ” የኢየሩሳሌም አርአያ እውነተኛ ታሪክ

የሞት “ድግስ”
መስከረም 4 ቀን 1996ዓ.ም ለኢትኦጵ ጋዜጠኛ የስልክ ጥሪ ይደርሰዋል። “ በነገው እለት ከቀኑ 6ሰአት መስቀል አደባባይ በሚገኘው የትግራይ ልማት ዋና ቢሮ 4ኛፎቅ እንድትገኝ” የሚል ማስጠንቀቂያ አዘል ጥሪ ነበር የደረሰው። ከዛ በፊት ለስድስት ወር የአየር መንገድ የደህንነት ሃላፊ ሃይሌ ጋዜጠኛውን ሲያስጨንቀው፣ የተለያዩ የማግባቢያ ወይም መደለያ ሃሳቦችን ሲያቀርብለት ቆይቷል። መስከረም 2 ቀን ደግሞ በቀበሌ 06/07 መ/ር ቢሮ እንዲገኝ የሚገልፅ መጥሪያ ቢደርሰውም በአጋጣሚ ጋዜጠኛው ስላልተመቸው አልሄደም። በማግስቱ የቀበሌውን ሊ/መ አቶ ቢሻው አበጋዝን ያገኘውና « ትላንት ፈልጋችሁኝ ነበር፤ ለምን ነበር?» ሲል ይጠይቀዋል፤ ቢሻውም « እኛ አይደለንም የፈለግንህ፤ ከደህንነት ቢሮ የመጡ ሰዎች ናቸው የፈለጉህ፤ ባለመምጣትህ ተናደው ነው የሄዱት፤ ለምን እንደፈለጉህ አልነገሩንም፤» በማለት መለሰ። …ከዛ በኋላ ነው – የመስከረም 4 ጥሪ የደረሰው፤ በማግስቱ በተባለው ቢሮ ተገኘ። ከ30 ደቂቃ ቆይታ በኋላ የማህበሩ ዳይሬክተር « ከሚፈልጉህ የበላይ አካላት ጋር አገናኝሃለሁ» በማለት ለጋዜጠኛው ተናግሮ በሚያሽከረክራት ኒሳን መኪና ተያይዘው ቦሌ በሚገኘው የደህንነት ቢሮ አመሩ።..ከአንድ ግዙፍና አስፈሪ ገፅታ ካለው ሰው ጋር ጋዜጠኛውን አገኛኝቶት ወጥቶ ሄደ። ..« እሺ ኢየሩሳሌም አርአያ..» አለ ንቀት በተሞላበት ሁኔታ፤ አስከተለና፥ « ወ/ስላሴ እባላለሁ፤ ….ከእኛ ባልደረባ ጋር ስትገኛኝ ነበር፤ መንግስት ብዙ አማራጮችን አቅርቦልህ..አንተ ግን አሻፈረኝ ብለሃል። ለመሆኑ የምታወጣቸው መረጃዎች ተፅፈው ነው የሚሰጡህ?…ለምንድነው መረጃ የሚሰጡህን የሕወሐት ሰዎች የማትነግረን?..የምናስራቸው፣ የምንጠይቃቸው መስሎህ ነው?…» ሲል ሹሙ ሲናገር፣ ጋዜጠኛው ግን የቀረቡትን መደራደሪያዎች እንደማይቀበል ተናገረ። ለሁለት ሰአት ተኩል ከደህንነት ሃላፊው ጋር ውዝግብ የተቀላቀለበት ቃላት ተለዋወጡ። በተለይ የደህንነት ሹሙ « ..የትግራይ ተወላጅ ያውም ቤተሰብህ አድዋ ሆነው..እንዴት ፀረ-ሕወሐት ትሆናለህ?..ከጠላቶቻችን አንዱ ከሆነው ኢትኦጵ ጋዜጣ ጋር እንዴት ትሰራለህ?..» እያለ ከመናገሩ በተጨማሪ « እንዳንተ የተለማመጥነውና የታገስነው የለም። ብንገድልህስ?..» ሲል በንቀት ሲጠይቅ፣ ጋዜጠኛውም « ምንም ጥያቄና መልስ አያስፈልገውም፤ አሁኑኑ ሽጉጥህን መዘህ ልታደርገው ትችላለህ። እኔ ብእር እንጂ የያዝኩት – ከጀርባዬ ያሰለፍኩት ሰራዊትና መሳሪያ የለም። ..ደግሞም ለስልጣን ያበቋችሁን 36ሺህ ታጋዮች ላይ ምን እንደፈፀማችሁ ስለማውቅ..» አላስጨረሰውም፤ ..« እሱ አይመለከትህም፤ ከማን ጋር ምን እያወራህ እንዳለህ እወቅ!?..ከዚህ በኋላ እንድታስብበት የ15 ቀን ጊዜ ብቻ ሰጥተንሃል። በነዚህ ቀናት አቋምህን አስተካክለህ፣ የተባልከውን ካልፈፀምክ ግን…እንገድልሃለን!! ማንም አያድንህም!! ጨርሻለሁ።» በማለት አምባረቀበትና አሰናበተው። ..ከአስራ አምስት ቀን በኋላ ረቡዕ መስከረም 20 ቀን 1996ዓ.ም ከምሽቱ 3፡30 ሰአት ገደማ በመኖሪያ ቤቱ አቅራቢያ ወ/ስላሴ ያሰማራቸው ሰባት የፌደራል ፖሊስ አባላት “አቦ ድልድይ” አቅራቢያ ጋዜጠኛውን ጠብቀው በያዙት ዱላ የቻሉትን ያክል ቀጥቅጠውና ከፍተኛ ጉዳት አድርሰው ወደ ድልድዩ ወረወሩት። ሶስት ጥርሱ ተሰበረ፣ ጭንቅላቱ 5 ቦታ ተፈነካከተ፤ ሁለቱ እጆቹ፣ ግራ እግሩ፣ ወገቡ፣..አጠቃላይ አካሉ ተጎዳ። …እነ ወ/ስላሴ ከድርጊቱ በኋላ ለጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና 5 ጊዜ ስልክ ደውለው « የኢየሩሳሌምን ሬሳ ሂድና ከምኒሊክ ሆስፒታል ውሰድ..» ሲሉ ተሳለቁ።…ከጨካኞች፣ ገዳዮችና አምባገነኖች ..የሚጠብቅ ፈጣሪ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባትን የጋዜጠኛውን ነፍስ በኪነ-ጥበቡ ታደጋት። እነሆ ከአስር አመት በኋላ የቀድሞ የደህንነት ሹም ወ/ስላሴ ወ/ሚካኤል እስር ቤት ሲወረወር፥ በእርሱ “ሞት የተደገሰላት” የጋዜጠኛው ነፍስ በህይወት ቆይታ ለማየት በቃች። ሁሉም የዘራውን ሊያጭድ ግድ ነው!! …ይህ ታሪክ የእኔ ነው።
(በምስሉ የሚታየው ለስድስት ወር ያልጋ ቁራኛ የዳረገኝ የግድያ ሙከራ ከተፈፀመብኝ በኋላ፣ )

Friday, March 7, 2014

International womens day

International womens day March 8, was established on february 18, 1909 in USA. However, it was officially declared on Augest 1910 in Coupenhagen, Denmark. The aim was to chariesh , honor women and enable them to encourage participating in economical, social and political aspects, so that their human right will be respected dispite gender difference.

When we come to ethiopia, March 8 was celebrated for the past 37 years. Despite, the actual meaning and message of the slogan that is raised each year, it is not seen being practised in the society. The event is celebrated country wide for that day but we see the contrary of the message through out the year. As a result, Ethiopia is one of the top countries known for women human right abuse. Despite the constitution that clearly states the right of every women, we see under age girls subjected to human trafficking, forced for prostitution and it is seen done mostly by government officials.


In addition, a lot of uneducated young girls will be forced to leave their country one way or another, to make their livings in arab countries. Most young girls will go through legal agreement which is signed by agents run by government officials . However, these young girls will be subjected to a lot of human right abuse in these countries and Ethiopian government will not protect them according to the signed aggrements. We can see the November, 2013 saudi arabia masacre.


Currently in Ethiopia, it is very difficult for educated young girls to be successful in their feild. This is because young girls on education like in universities and coledges might be subjected to harrasmenment by their lecturers. Furthermore, after they graducate its very difficult for them to find jobs because they will face the same problem. However, the administration in schools, coledges , university and government officess is

not accountable and transparent. As a result many young girls will loss hope.

We ethiopian women hope one day we could fully practice our rights and freedom in our country . To acheve this we must all work together so that this day will be soon.




 Hanna Semere

http://www.ethiolion.com/Pdf/03072014women_day_presentation.pdf

Thursday, March 6, 2014

“ነገረ ኢትዮጵያ” የሰማያዊ ፓርቲ ጋዜጣ ወቅታዊ ጉዳዮችን ይዛ ወጥታለች


  • ውህደት ወይስ ትብብር?
  • ስለ ሀገርና ወገን የሚታገሉትን ማዋከቡ ይቁም! (ርዕሰ አንቀጽ)
  • “አገርን ከመቁረስ በላይ ምንም ነገር ሊመጣብን አይችልም”
  • “መንግስት›› አሳልፎ የሰጠው ሉዓላዊነት”
                               [ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ]
Semayawi Party newspaper "Negere Ethiopia" Issue 2
 http://ecadforum.com/Amharic/archives/11323/

ጃፓን + ኢህአዴግ – ቻይና = መንበርከክ

ኢህአዴግ በሁለተኛው መንታ መንገድ ላይ

ethio japan


ከቻይና ጋር የጀመሩት መወዳጀት ሥር ሰድዶ በሁለት እግሩ ከመቆሙ በፊት አቶ መለስ በሞት ከተለዩ በኋላ የኢህአዴግና የቻይና ግንኙነት በርካታ መንታ መንገዶች እየገጠሙት መጥተዋል፡፡ ከምዕራቡ ዓለም ከፍተኛ ገንዘብ በበጀት ድጎማም ሆነ በዕርዳታ የሚሠጠው ኢህአዴግ ምዕራባውያን ከቻይና ጋር ካላቸው ፍጥጫ አንጻር እየገባበት ያለው አጣብቂኝ በየጊዜው እየጨመረ መጥቷል፡፡ “ምርጫው በምርጫ” እየተወሳሰበበት የመጣው ኢህአዴግ በአንድ በኩል የአሜሪካንን ፍላጎትና ጥያቄ መፈጸምና ማስፈጸም፤ በሌላ በኩል ደግሞ አፈናውን ለማጠናከርና የግዛት ዘመኑን ለማርዘም ከቻይና የሚያገኘው በቅድመ ሁኔታ ያልታሰረ “ጥቅም” በሁለት ጽንፍ ወጥረውታል፡፡ አሁን ደግሞ ሌላ “ወጣሪ” ብቅ ብሎ በመንታው መንገድ ላይ ሌላ መንታ ፈጥሮበታል – ጃፓን!
ቻይና በተለይ በአፍሪካ እያደረገች ያለችው የንግድ እንቅስቃሴና ኢንቨስትመንት የምዕራባውያንን ዓይን ከሳበ ቆይቶዋል፡፡ በተለያዩ ሰበቦችም የቻይናን እንቅስቃሴ ለመሰለል ምዕራባውያን በግልጽ መረጃ ከመሰብሰብ እስከ ወታደራዊ ተቋማት መገንባት ከዚያም አልፎ በቻይና “ፍቅር” ተለክፈው እንቅፋት የሆኑባቸውን እስከ “ማስወገድ” ዓላማቸውን ሲያሳኩ ቆይተዋል፤ አሁንም እያደረጉት ይገኛሉ፡፡
በጂኦግራፊዊ አቀማመጥ ምስራቃዊ ከመሆን በስተቀር የምዕራቡ ዓለም አካል የሆነችው ጃፓን፤ የቻይናን ሁኔታ በቅርብ ስትከታተል ቆይታለች፡፡ በተለይ ሁለቱ አገራት ካላቸው ታሪካዊ ጥላቻ አኳያ ጃፓን ቻይናን በማሳደዱ ተግባር ከምዕራቡ ዓለም ጋር ሆና እስከ አፍሪካ ዘልቃለች፡፡abe and abe
በቅርቡ የጃፓኑ ጠ/ሚ/ር ሺንዞ አቤ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሦስት የአፍሪካ አገራት ያደረጉት ጉብኝት “የሁለቱ አገራት የቆየ ግንኙነት …” ብሎ ኢቲቪ እንደዘገበው የቀለለና ጥሩ የፎቶ ዕድል ፈጥሮ ያለፈ ብቻ አይደለም፡፡ ቀልደኛው የጃፓን መሪ አቤ “ትምህርት ቤት ሳለሁ ልጆች ሁሉ አበበ እያሉ ይቀልዱብኝ” ነበር እንዳሉትና የሻምበል አበበ ቢቂላን ፎቶ ተሸልመው የሄዱበት የመዝናኛ ጉብኝትም አልነበረም፡፡ ጠ/ሚ/ር አቤ አህጉር አቋርጠው የመጡት ለሌላ ጉዳይ ነው – ቻይና!!! ተያይዞም ከምዕራባውያን ጋር የተገመደ ወታደራዊ የበላይነት በአፍሪካ!
ጃፓን “ተለውጣለች”
ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ “ሰላማዊነት” መመሪያዋ አድርጋ ለዘመናት የቆየችው ጃፓን ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በውጭ ፖሊሲዋ ላይ ለውጦችን አካሂዳለች፡፡ ጦርነቱ ከተጠናቀቀ በኋላ የሕገመንግሥቷ አንቀጽ 9 እንደሚለው ጃፓን ሰላማዊ መንገድን የምትከተል፤ በሌሎች አገራት ጣልቃ የማትገባ ብቻ ሳትሆን ድርጊቱን “ለዘላለም የምታወግዝ”፤ ዓለምአቀፍ ግጭቶችን ለማስወገድ የጦርነት እርምጃ በጭራሽ የማትወስድ አገር መሆኗን ያስረዳል፡፡ ሲቀጥልም የጦርነት እርምጃው በምድር፣ በባህር እና በአየር የሚደረገውን ሁሉ የሚጠቀልል እንደሆነ በግልጽ ይናገራል፡፡ ከዚህም የተነሳ ነበር ሌሎች አገራት ጦራቸውን “የመከላከያ ሠራዊት” እያሉ ሲጠሩ ጃፓን ግን የአገሯን ጦር “የጃፓን ራስን የመከላከል ኃይል” በማለት የሰየመችው፡፡
መስከረም አንድ (ሴፕቴምበር 11) በአሜሪካ “የአሸባሪዎች ጥቃት” ከደረሰ ወዲህ የጃፓን ህገመንግሥትም እየላላ፤ በማሻሻያዎችም ለውጥ እየተደረገበት መጥቷል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “ዓለምአቀፋዊ ሰላምና ትብብርን” ለማጎልበት በሚል ጃፓን ጦሯን ከዓለምአቀፍ ኢምፔሪያሊስቶች ጋር ማሰለፍ ጀመራለች፡፡ አሜሪካ አፍጋኒስታንን በወረረች ጊዜ ጃፓን የድጋፍ ክንዷን ዘርግታለች፤ በቀጥታ ውጊያ በመሳተፍ ባይሆንም በተዛማጅ አገልግሎቶች፡፡
ቻይና ከአፍሪካ አምባገነኖች ጋር በጥቅም በመተሳሰር እየመሠረች ያለችው የጠበቀ ግንኙነት ዓይናቸውን “ያቀላው” ምዕራባውያን በቻይና ላይ የሚያደርጉትን ስለላ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መጥተዋል፡፡ ለዚህ ተግባር የጃፓን ተሳትፎ ከምንጊዜውም በላይ አስፈላጊ ሆኗል፡፡ ተሳትፎው ለምዕራባውያን በራሱ የሚሰጠው ጥቅም ቢኖርም ለጃፓን በተለይ ከታሪካዊ ጠላቷ ቻይና ጋር ለምታደርገው ሁለገብ ፉክክር የራሱን የቻለ እገዛ ያደርግላታል፡፡
ምዕራባውያን፤ ጃፓን እና ቻይና
ቻይና በተለይ በአፍሪካ የምታደርገውን መጠነሰፊ ኢንቨስትመንት በቅርብ ለመሰለልና ማንኛውንም እንቅስቃሴዋን ለመቆጣጠር አሜሪካ በፖሊሲ ደረጃ የወሰደችው እርምጃ በአፍሪካ ወታደራዊ የበላይነትን መጎናጸፍን ነው፡፡ (ጎልጉል: “በአልቃይዳ ሰበብ ቻይናን መቆጣጠር፤ የኦባማ አስተዳደር መጪው የአፍሪካ ዕቅድ” በሚል የዘገበው እዚህ ላይ ይገኛል:: “አሜሪካ በአፍሪካ ወታደራዊ የበላይነቷን ልታረጋግጥ ነው! ፕሮግራሙን ለማስፈጸም 35 አገሮች ተመርጠዋል” በሚል የተጻፈው ተጨማሪ ዘገባ እዚህ ላይ ይገኛል)
ይህንን ወታደራዊ የበላይነት ተግባራዊ ለማድረግ አሜሪካ በአፍሪካ እጅግ ዘመናዊ ወታደራዊ ተቋማትን እየመሰረተች ትገኛለች፡፡ በከፍተኛ መኮንኖቿም አማካኝነት የአፍሪካን ወታደሮች በማሰልጠን “የአህጉሩን ሰርዶ በአህጉሩ በሬ” እያስኮመኮመች ነው፡፡ የአፍሪኮም (AFRICOM) መቋቋም እንዲሁም በአፍሪካ የተካሄዱ የቅርብ ጊዜ ጦርነቶች ከዚህ ጋር ተያይዘው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ አቶ መለስ ኢትዮጵያን በማይመለከታት ጦርነት ከሶማሊያ ጋር ያናከሷት ይኸው ለምዕራቡ ዓለም ካላቸው ተላላኪነትና ጉዳይ አስፈጻሚነት የተነሳ እንደነበር ይታወሳል፡፡camp lemonnier
አሜሪካ በአፍሪካ ከምታካሂደው ወታደራዊ የበላይነት እንቅስቃሴ በተለይ “አሸባሪነትን ለመዋጋት” በሚል በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ የምትፈጽመው ተግባር ጎልቶ የሚታይ ነው፡፡ በድርጊቱም የዛሬ 10ዓመት አካባቢ በጅቡቲ የሚገኘውን ለሞኒር የጦር ሠፈር የራሷ አደረገች፡፡ ብዙም ሳትቆይ የጦር ሠፈሩን በማዘመን ቀድሞ ከነበረበት በአምስት እጥፍ አሳደገችው፡፡ ይህ የሆነው የጦር ሠፈሩን ከፈረንሳይ ከተረከበች ሦስት ዓመታት በኋላ ነበር፡፡ በዚህ የጦር ሠፈር አራቱም የአሜሪካ ወታደራዊ ክፍሎች – ምድር ጦር፣ አየር ኃይል፣ ባህር ኃይል እና ማሪን – የሚገኙ ሲሆን በአፍሪካ ቀንድ ዙሪያ የሚገኙት ጅቡቲ፣ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ኬኒያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ዑጋንዳ፣ ሲሸልስና የመን በጣምራ ጦሩ ዕይታ ውስጥ የተካተቱ ናቸው፡፡ ከእነዚህ አገራት በተለይ በኢትዮጵያ በብላቴና ሁርሶ በኬኒያ ደግሞ በማንዳ ቤይ የጅቡቲው ጦር ሠፈር ቅርንጫፍ የሆኑ የዕዝ ማዕከላት ይገኛሉ፡፡ ታህሳስ 27፤1999 የታተመው ኢትዮጵያን ሔራልድም ይህንኑ በማመን “የኢትዮጵያ መካላከያ ሠራዊት” በብላቴና ሁርሶ ውስጥ በአሜሪካውያኑ እንደሚሰለጥን ዘግቧል፡፡ ኢህአዴግ ሶማሊያን በወረረ ጊዜ ሠራዊቱ ከአሜሪካውያኑ የተቀበለውን ሥልጠና በተግባር የማዋል ብቃቱን ለማሳየት ወረራው የወታደራዊ ሳይንስ ቤተሙከራ ሆኖ አገልግሏል፡፡
ይህ በጅቡቲ የሚገኘው የጦር ሠፈር እየተስፋፋ በመጣበት ወቅት ኢስት አፍሪካን የተባለው የኬኒያ ጋዜጣ አሜሪካ የጦር ሠፈሩን በተረከበች ጊዜ ለአካባቢው አገራት የምትሸጠው መሣሪያ የዋጋ መጠን 1ሚሊዮን ዶላር ያህል የነበረው ከሦስት ዓመት በኋላ ከ25 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማደጉን ዘግቧል፡፡ ይህ አኻዝ የዛሬ 7ዓመት አካባቢ የተነገረ ሲሆን የቅርብ ጊዜውን መጠን በዚሁ ስሌት ለመገመት አያዳግትም፡፡
abe djibouti
ሺንዞ አቤ በጅቡቲ ከጃፓን ወታደሮች ጋር
ጃፓን በህገመንግሥቷ የጸናውን “ሰላማዊነት” በማሻሻያ ከቀለበሰች ወዲህ ወታደራዊ ተስፋፊነቷ እየጨመረ መጥቷል፡፡ በሶማሊያ የባህር ላይ ውንብድናና የመርከብ ዝርፊያ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ነው በሚል ኢኮኖሚያዋ በባህር ንግድ ላይ የተመሠረተው ጃፓን አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አለብኝ በማለት ቻይናን በእጅ አዙር ለመግጠም ወደ አፍሪካ ብቅ አለች፡፡ ቻይናን ከተለያየ አቅጣጫ የጠመዱት ምዕራባውያን ለጃፓን ውሳኔ ይሁንታ በመስጠት ግልጽ ድጋፍ አደረጉ፡፡ የሶማሊያን ችግር የመፍታት አማራጭ ከመውሰድ ይልቅ ሶማሊያን ፈርሳ በምትኩ የምዕራባውያን አሻንጉሊት የሆነ አዲስ አገር በአፍሪካ ቀንድ ባሉ ተላላኪ መሪዎች መፍጠር “ቀላሉ” አማራጭ ሆኖ በመወሰዱ ነበር ፑንትላድ የተመሠረተው፡፡ አሜሪካ በሶማሊያ ላይ ካላት የቆየ ቂም አንጻር በአሁኑ ጊዜ ፑንትላንድን ማንኛውንም “አሸባሪ” ብላ የምትፈርጀውን ለማጥቃት እንደፈለገች የምትፈነጭበት አገር አድጋታለች፡፡ ኢህአዴግም ለፑንትላንድ መሪዎች በልምድ ያካበተውን “ንቃት” የሚሰጥ ሲሆን በቅርቡ የፑንትላንዱ መሪ አዲስ አበባን መጎብኘታቸው ከዚህ ጋር አብሮ የሚጠቀስ ነው፡፡
አሜሪካውያኑ “አሸባሪነትን” ምክንያት በማድረግ የጦር ሠፈሮችንና ወታደራዊ ተቋማትን ያለ ከልካይ ሲገነቡ ጃፓንም ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ የተጠቀመችው “ምክንያት” በወቅቱ በቀይ ባህርና በሰላጤው መተላለፊያ የሰፈነው የመርከብ ጠለፋና የባህር ላይ ውንብድናን ነበር፡፡
በኤድን ሠላጤ በየዓመቱ 20ሺ የሚሆኑ የጭነት መርከቦች ያልፉበታል፡፡ ከዚህ ውስጥ 10በመቶው የጃፓን መርከቦች ሲሆኑ ኢኮኖሚያዋ በከፍተኛ ሁኔታ በውጭ ንግድ (ኤክስፖርት) ላይ ጥገኛ የሆነችው ጃፓን 90በመቶ የሚሆነው የውጭ ንግድ ሸቀጦቿ በዚሁ የባህር መንገድ ላይ ጥገኛ ነው፡፡ በመሆኑም የባህር ላይ ውንብድናው እየከፋ ሲመጣ ጃፓን ህልውናዋን ለማስከበር እርምጃ እንድትወስድ በከፈተላት በር ተጠቅማ ለሞኒየር ጦር ሠፈር የከተመውን የአሜሪካንን ኃይል “አስጠጉኝ” ማለት ጀመረች፡፡ በዚህ ብቻ አላበቃም፤ ጃፓን ከአገሯ ውጭ ለመጀመሪያ ጊዜ ወታደራዊ የጦር ሠፈር በጅቡቲ መሠረተች፡፡ ጥቂት ዓመታትን ያስቆጠረው ይህ ሠፈር ሲመሰረት ከ40ሚሊዮን ዶላር በላይ ፈጅቷል፡፡
pirates
በሶማሊያ የባህር ላይ ወንበዴዎች
በጅቡቲ ትልቁ ወታደራዊ የበላይነት ያላት ፈረንሣይ በዚህ ሁሉ ውስጥ “የዓለምአቀፋዊ ኢምፔሪያሊዝም” አካል እንደመሆኗ ወታደራዊ ተስፋፊነቱ የእርሷም ፖሊሲ ነው፡፡ ከቻይና ጋር “በፍቅር የሚወድቁ” የአፍሪካ አገራትን ለይታ በማጥቃት ቀድሞ የነበራትን የቅኝ ግዛት ተስፋፊነትና የበላይነትን በእጇ ለማስገባት የምትጥረው ፈረንሣይ፤ ቻይና በተበረገደ በር ገብታ የምትዝቀው የአፍሪካ ሃብት “ዓይን ከማቅላት” በላይ ሆኖባታል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት በኮትዲቯር አሁን ደግሞ በመካከለኛው የአፍሪካ ሪፑብሊክ ፈረንሳይ የተጠመደችበት ጦርነት በመገናኛ ብዙሃን ሲዘገብ ሌላ መስሎ ቢቀርብም ጉዳዩ ግን ቻይናን ነጥሎ ከመምታት ያለፈ እንዳልሆነ ወታደራዊ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ ከጦርነቶቹ ጋር አብሮ የሚነሳው የዘር፣ የሃይማኖት፣ ወዘተ ግጭትና የሕዝብ ዕልቂት እሣተጎመራው ሲፈነዳ እንደሚቃጠለው ሣር ዓይነት በእንግሊዝኛው አጠራር “collateral damage” የሚባለው ነው፡፡ ይህ የአፍሪካውያን ሰቆቃና ዕልቂት የሚፈልጉትን ዓላማ እስካስፈጸመ ድረስ ለምዕራባውያን ብዙም የሚገዳቸው እንዳልሆነ አደጋን በማያያዝ በራሳቸው ህዝብ ላይ የሚፈጽሟቸው “ወንጀሎች” ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ፈረንሣይና ጃፓን
japan and france
የጃፓንና ፈረንሣይ ውጭ ጉዳይና መከላከያ ሚኒስትሮች
ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሦስት የአፍሪካ አገራትን በጎበኙበት ሰሞን የውጭ ጉዳይና የመከላከያ ሚኒስትሮቻቸው ከፈረንሣይ ጋር መጠነሰፊ ስምምነት ለማድረግ ፓሪስ ነበሩ፡፡ በደሴቶች የይገባኛል ጥያቄ ከቻይና ጋር ፍጥጫ ውስጥ ያለችው ጃፓን የመከላከያ ኃይሏን በማጠናከር ላይ ትገኛለች፡፡ ለዚህም ዘመነኞቹ ፈረንሣይ ሰራሽ የጦር መሣሪያዎች፣ ሔሊኮፕተሮች፣ የባህር ውስጥ መርከቦች (ሰብማሪን) በእጅጉ ያስፈልጓታል፡፡ ፈረንሣይ ከቻይና ጋር በተያያዘ በአፍሪካ ላይ ለተጠመደችበት ተግባር የጃፓንን ድጋፍ ትፈልጋለች፡፡ ለዚህም ነው በቀድሞዎቹ የፈረንሣይ ቅኝ አገራት – ማሊና መካከለኛው አፍሪካ – ፈረንሣይ እያካሄደች ለምትገኘው ጦርነቶች ጃፓን ቀጥተኛ ድጋፍ እንደምትሰጥ በይፋ ያስታወቀችው፡፡ ይህ ከቃል ያለፈው ድጋፍ በተግባር ተተርጉሞ ለማሊው ጦርነት ጃፓን 735 ሚሊዮን ዩሮ ዕርዳታ ለፈረንሣይ ጦር ሰጥታለች፡፡ ለመካከለኛው አፍሪካ ጦርነትም ተመሳሳይ ድጋፍ እንድትሰጥ ይጠበቅባታል፡፡
ለእንደዚህ ዓይነቱ የ“እከክልኝ ልከክልህ” ወዳጅነት ጃፓንም ከቻይና ጋር ለምትቆራቆስባቸው ደሴቶች ጉዳይ የፈረንሣይን ግልጽ የፖለቲካ ድጋፍ አግኝታለች፡፡ ሁለቱ ሚኒስትሮች ፈረንሣይን ከጎበኙ በኋላ በወጣው የጋራ መግለጫ ፈረንሣይ በሳንካኩ/ዲያዖዩ ደሴቶች ጉዳይ የቻይናን ተስፋፊነት አውግዛለች፡፡ የጃፓኑ ውጭ ጉዳይ ሚ/ርም ከፈረንሣይ ጋር የፈረሙት አዲሱ ስምምነት ሁለቱ አገራት “በደኅንነትና መከላከያ ዙሪያ ለሚያደርጉት ትብብር አዲስ ፈር ቀዳጅ” እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የኢህአዴግ ጭንቀት
ኢህአዴግ በኢትዮጵያ የሚያካሂደውን ማንኛውንም ሕዝብን የሚጎዳ ተግባር በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍም ሆነ የተቃውሞ ድምጻቸውን የሚያሰሙትን ሁሉ “አሸባሪ” በማለት እስርቤት ሲያጉር፣ ሲያሰቃይ፣ ሲገድል፣ … መቆየቱ በግልጽ የፈጸማቸው ተግባራቱ ከበቂ በላይ ማስረጃ ናቸው፡፡ የጃፓኑ ጠ/ሚ/ር ኢትዮጵያን በጎበኙ ወቅት በአዲስ አበባ የሚገኙ ቻይናውያን የተቃውሞ ድምጻቸውን አሰምተዋል፡፡ በዚህም ብቻ አላበቁም፤ አዲስ አበባ በሚገኘው የጃፓን ኤምባሲ በመሄድ አምባጓሮ ፈጥረው እንደነበር በዓለምአቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ተዘግቧል፡፡ በኢትዮጵያ በኮንስትራክሽን ሥራ ላይ የሚገኙ ቻይናውያንን ፊርማ በማሰባሰብ ተቃውሟቸውን ለኤምባሲው አቅርበዋል፡፡ አሶሺየትድ ፕሬስ የዓይን እማኞችን ጠቅሶ እንደዘገበው ቻይናውያኑ “ሳንካኩ ደሴት የእኛ ናት” የሚል ትልቅ መፈክር ሰቅለውም ነበር፡፡ ይህንን ሁሉ ሲያደርጉ “በአሸባሪነት” የወነጀላቸው የለም፡፡
በኢትዮጵያ የቻይናው አምባሳደርም የከረረ ተቃውሟቸውን በጠ/ሚ/ር አቤ ጉብኝት ላይ ሰንዝረዋል፡፡ ጃፓን የቻይናን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር እየሠራች መሆኗንና “ወታደራዊ የበላይነቷን” እንደገና እያንሰራራችው እንደሆነ ወንጅለዋል፡፡ ጠ/ሚ/ሩን “ችግር ፈጣሪ፣ አዋኪ” በማለት የከሰሱት አምባሳደር በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የጃፓን ሠራዊት በቻይናውያኑ ላይ ያደረሰውን አሰቃቂ ተግባር የሚያሳይ ፎቶ በማሳየት ምሬታቸውን ገልጸዋል፡፡ETHIOPIA-CHINA-JAPAN-DISPUTE  CDS1148
የፈለገውን ዓይነት በቴክኖሎጂ የረቀቀ የአፈና መሣሪያ ከቻይና ያላንዳች ቅድመ ሁኔታ እያገኘ ያለው ኢህአዴግ ከቻይና የሚያገኘውን ጥቅም ከምዕራባውያን ከሚቀበለው ዕርዳታና የበጀት ድጋፍ ጋር ለማስታረቅ መንገዱ እየጠበበበት እንደመጣ የሚጠቁሙ ክስተቶች አሉ፡፡ ሁኔታው በአምባገነንነት ከመቀጠሉ ኅልውናው ጋር የተሳሰረ መሆኑ ችግሩን ይበልጥ ያወሳስበዋል፡፡ የዓለም ባንክ የሚሰጠውን ዕርዳታ በተመለከተ ሊወስድ የተዘጋጀበት እርምጃ እንዳለ ሆኖ ለምዕራባውያን በመላላክና ጉዳይ በማስፈጸም “ብቃታቸውን ያስመሰከሩት” መሪውን ካጣ ወዲህ ኢህአዴግ ከቻይና በሚያገኘው ጥቅምና የታዘዘውን እየፈጸመ ከምዕራባውያን በሚያገኘው ዕርዳታ መካከል መንታ መንገድ ላይ ይገኛል፡፡
ምዕራባውያን ከጃፓን ጋር ወግነው የሚያደርጉት ተግባራት በቻይና ላይ ቀጥተኛና አሉታዊ ተጽዕኖ ያለው በመሆኑ ኢህአዴግ በግድ መልስ የሚሰጥበት ነው፡፡ ይህም ደግሞ በግንኙነት መሻከርም ሆነ መጎልበት ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ አለ፡፡ ለዚህም ይመስላል የጃፓኑ ጠ/ሚ/ር ኢትዮጵያን በጎበኙ ሰሞን የውጭ ጉዳይ ሚ/ር መ/ቤት በአፈቀላጤው አማካኝነት “የአያገባኝም ማስተባበያ” የሰጠው፡፡ ዲና ሙፍቲ ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “ይኼ የቻይና መንግሥት ጉዳይ ነው የሚሆነው፡፡ የእኛ ጉዳይ አይደለም … ከቻይና ጋር የጠበቀ ግንኙነት አለን፡፡ በዚህም ልክ ከጃፓንም ጋር የጠበቀ ግንኙነት አለን፡፡ ይህንን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንፈልጋለን፡፡ …  ከአገሮች ጋር ያለንን ግንኙነት በአንዱ ኪሳራ አናራምድም” ብለዋል፡፡ ይህ ጃፓን እንዳትቀየም የተሰጠ ማስተባበያ ቻይናም እንዳታኮርፍ በመለማመኛነት የቀረበ ጭምር ነው፡፡abe_africa
የውጭ ጉዳዩ በዚህ ዓይነት የተወጠረ ሁኔታ ላይ ያለው ኢህአዴግ በአገር ውስጥም የሕዝቡን ዕለታዊ ጥያቄዎች ለማሟላት አለመቻሉ ከፍተኛ ምሬት እያስነሳበት ይገኛል፡፡ በተለይ የከረረ ተቃውሞና ነቀፋ ከደጋፊዎቹና ጥቅመኛ ባለሟሎቹ እየቀረበ መምጣቱ የብዙዎችን ትኩረት እየሳበ ነው፡፡ መውደቁን ገምተው በድል አጥቢያ አርበኛነት የተናገሩት ይሁን ወይም የለውጥ ፍላጎታቸውን የገለጹበት ጊዜውን ጠብቆ የሚታወቅ ቢሆንም ቀድሞ ሲባል እንደነበረው በአሁኑ ጊዜ ኢህአዴግ “የመንግሥት ሌቦች” ያሉት ድርጅት ሳይሆን ኢህአዴግ ራሱ የዚያ “ባለማዕረግ” ሆኗል፡፡
በአንድ መልኩ በአገር ውስጥ ሊከሰት የሚችለውን ማኅበራዊ ነውጥ ለማክሸፍ፣ በሌላ በኩል በቻይና ድጋፍ የሕዝቡን ድምጽ በማፈንና መብት በመርገጥ በአምባገነንነት ለመቀጠል የሁልጊዜ ምኞቱ የሆነው ኢህአዴግ “ምርጫውን በምርጫ” የሚያሳክር “ምርጫ” ተደቅኖበታል፡፡ የደም ሥሩ የሆነውን የምዕራባውያን ድጎማ ላለማጣት ለአሜሪካና ለቻይና ታሪካዊ ጠላት ጃፓን መንበርከክ የማይፈልገው ቢሆንም የማይቀርና በመንታው መንገድ ላይ የተፈጠረ ሌላ መንታ ሆኖበታል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ለመጪው ምርጫ በሩን እንዲከፍት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ እየደረሰበት ያለው ጫና ከሕዝብ ብሶትና ዕሮሮ ጋር ተዳምሮ የኢህአዴግን “ፍንዳታ” አቀሬነትና ቅርብነት በካድሬዎቹና ደጋፊዎቹ ጭምር እንዲተነበይ አድርጎታል፡፡ (ከላይ የሚታየው ፎቶ ሺንዞ አቤና ሃይለማርያም ደሳለኝ ውይይት ከማድረጋቸው በፊት ሁለት ባለሥልጣናት የደረቀ አንበሳ ፊት ቆመው ሲመክሩ ነው – ፎቶው ከ Wall Street Journal የተገኘ)
http://www.goolgule.com/japan-eprdf-and-china/