Thursday, November 22, 2012

የሕዝብ ራእይ ለምን በአምባገነን ስም ይጠራል?

የኢትዮጵያ ሲቪክ ንቅናቄ
Ethiopian Civic Movement

አቶ ሃይለማርያም „የታላቁን መሪ ራእይ“ እንደሚተገብሩ ቃል ገብተዋል፤ ለውጥ እንደሚያደርጉ ግን አልገለፁም፡፡ ኢህአዴግ በአቶ መለስ ፍላጎት ብቻ ይመራ፣ የኢትዮጵያ ህዝብም በሰውየው ፍላጎት ይገዛ ነበር፡፡ ከዛ ፍላጎት ማፈንገጥ ለግምገማ ያጋልጥና በጠላትነት ያስፈርጅ ነበር፡፡ ያገዛዙ ጠባይ በድርጅቱ አባላትም አለመተማመንን አስርፆና አስፍኖ፣ አባላቱ በግልፅ ሃሳባቸውን እንዳይገልፁ አፍኖ ስለቆየ ኢህአዴግ ከአቶ መለስ ሞት በሁዋላም እስካሁን የሚመራው በሟቹ መንፈስ ነው፡፡አባላቱ ከአፋኙ ባህል ገና አልተላቀቁም፡፡ ስለዚህ የአቶ ሃይለማርያም ንግግር የተጀመረውን መቀጠል ከሚለው ሃሳብ አለመውጣቱ ለጊዜው አያስገርምም፡፡

አቶ ሃይለማርያም የኢህአዴግ ባለስልጣን ሆነው፣ በተለይም በመለስ ዜናዊ ተመርተው ለዚሁ ስልጣን የበቁ እንደመሆናቸው፣ ባጫር ጊዜ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋትና አንዳንድ የፖለቲካ ለውጦችን በማድረግ አገሪቱን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማሸጋገር ይችላሉ ብሎ መጠበቅ አይቻልም፡፡ በተለይም ቁልፍ የሆኑ ተቋሞች እንደ ዴህንነትና የጦር ሓይሉ በወንጀል የሚጠየቁና በሙስና የተጨማለቁ የህወሓት ሰዎች ቁጥጥር ውስጥ እስከሆኑ ድረስ ለውጥ ይመጣል ብሎ መጠበቅ አይቻልም፡፡

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አገርን በማስቀደም ላይ የታነፀ ፍላጎትና ራእይ ካላቸው ግን ታሪክን መስራት ባጭር ጊዜ ባይሆንም ይችላሉ፡፡ በጎርባቾቭ የለውጥ ፍላጎት እንደ ህወሓት/ኢህአዴግ ስታሊናዊ አሰራርና አደረጃጀት የነበረውና ብቻውን ከ70 ዓመት በላይ የገዛው የሶቬት ኮምዩኒስት ፓርቲ ሊፈርስ እንደቻለ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው፡፡

ስለሆነም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለወደፊቱ የኢትዮጵያ ህዝብን ለመምራት ያበቃቸው ታሪካዊ አጋጣሚ የአንድ ግለ-ሰብን ራእይ በመከተል ብቻ ሊወጡት አይችሉም፡፡ የህዝብ ጥቅምንና ድምፅን የሚያስከብርና የድርጅታቸውን አባላት በነፃነት የሚያሳትፍ የራሳቸው ሕሊና ያስፈልጋቸዋል፡፡ በዚህ መሠረት እሰካሁን የነበሩትን የመንግስት፣ ማለትም የአቶ መለስ አቋሞች፣ ድርጊቶችና እቅዶች በመመርመር የሚተዉ፣ ተስተካክለው የሚቀጥሉና የሚጨመሩ ጉዳዮች መለያየት ያስፈልጋል፡፡

የቆየው የመንግስት ወሳኝ ሃሳብና አሰራር

ከአቶ መለስ ህልፈተ ህይወት በሁዋላም በሃሳባቸው ለመቀጠል መፈለግ ማለት ሌሎች ሃሳቦች እንዳይፈልቁና በቆየው ሃሳብ ውስጥ የነበሩ ስህተቶች እንዳይታረሙ መግታት ነው፡፡ የነበረውን አሰራር መቀጠል ማለት ደግሞ ሁሉም ሰው እንደ ሃይማኖት በአንድ ሃሳብ መመራቱን ለማረጋገጥ ቁጥጥር፣ ግምገማና መሸማቀቅ ያስከትላል፤ ያስቀጥላል፡፡ በእንደዚህ ዓይነት አስተሳሰብና አሰራር ላይ የተመሰረተ ስርዓት ነፃነትን በማሳጣት የመተራረም ዕድልን ስለሚዘጋ ለልማት እንደሚጠቅም ዋስትና የለውም፡፡

የቆየው ሃሳብ መለያው የሚወርደውም የሚቀየረውም ከላይ ከመሆኑ ሌላ አንድ ወጥነት አልነበረውም፡፡ አቶ መለስ የቆሙለት የተለመደ፣ አንድ ወጥ የሆነ ማህበራዊ ስርዓት፣ እንደ ካፒታሊዝም ወይም ሶሻሊዝም አልነበራቸውም፤ ከሁለቱ ስርዓቶች ተቀይጦ ሲቀርብም ቅንነት የጎደለውና የሚቀያየር ነበር፡፡ ሰውየው አንዴ ነጭ ካፒታሊዝም ያሉትን ሌላ ጊዜ ሶሻሊዝምን ያስመስሉት ነበር፡፡ ስታሊናዊ የቁጥጥርና የአፈና መዋቅር ተዘርግቶና ካድሬዎች ተሰማርተው ህዝብ በግምገማ እየተዋከበ የአንድ ሰው ፍላጎት ብቻ እንዲሰርፅበትና (indoctrinated እንዲሆንና) ሌላ ሃሳብ እንዳያፈልቅ ሲገደድ ቆይቷል፡፡ ይህ አሰራራቸው ከስታሊናዊ የጭቆና ስልት እንዳልተላቀቁ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡

ሆኖም ሟቹ፣ ከስታሊናዊነት አስከፊውን ያፈና ገፅታ እንደመረጡ ሁሉ ከካፒታሊዝምም አስከፊውን የሙስና ገፅታ አስፍነው ጥቂት ደጋፊዎቻቸው በአጭር ጊዜ ብዙ ሃብት እንዲያካብቱና ብዙ ህዝብ በድህነት እንዲራቆት አድርገዋል፡፡ ስርዓቱ አምባገነኑን ለሚደግፉት ሙስና፣ መብታቸው እንዲከበር ለሚፈልጉት አፈና ሆኖ ቆይቷል፡፡ በተለይ ጉልበትን በመጠቀምና ምርጫን በማጭበርበር ከ99% ያለፈው የፖለቲካው ሙስና ካለ አግባብ ስልጣንንና ሃብትን መቆጣጠር አስችሏል፡፡ ሌብነትንና ጉቦን ለሚያካትተው ሙስና መሰረቱ የፖለቲካ ሙስና እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

አቶ መለስ ከሳቸው የተለየ ሃሳብ እንዳይፈልቅ አጥብቀው ይቆጣጠሩ ነበር፡፡ እሳቸው ራሳቸው ግን ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮም የተወሰኑ ሰዎችን ለማጥቃት በፈለጉ ቁጥር የማደናገር መፈክራቸውን (በማኦ ዜዱንግ፣ በኢንቨር ሆጃ፣ በቦናፓርቲዝም፣ በነጭ ካፒታሊዝም፣ በኒዮ ሊበራሊዝም፣ በልማታዊ መንግስት ወዘተ) ስለሚቀያይሩ ተከታዮቻቸው በአንድ ሃሳብ እንዳይፀኑ የሚያደርግ ስሜት ፈጥረዋል፡፡ ስለዚህ የተከታዮቻቸው እጣ ፈንታ መፈክር ሲቀየር እየተከታተሉ ማስተጋባት ነበር፡፡

ስርዓቱ በፖለቲካ የማይደግፉትን በብዙ ዘርፍ እንዲሰቃዩ የማድረግ ጠባይ ስለነበረው አቶ መለስ መንግስታዊ ስልጣን እንደያዙ የማይፈልጓቸውን ዜጎች ከስራ አስወጥተዋል፡፡ ዜጎችን ከስራ ሲያባርሩ ግን ስታሊናዊ የመመንጠር እርምጃ እንደሚወስዱ (purge እንዳደርጉ) አልገለፁም፡፡ ስለዚህ ቢሮክራሲውን እንደሚቀንሱና አላስፈላጊ የሚሏቸውን ሰራተኞች እንደሚያባርሩ የገልፁት በኒዮ ሊበራል መርህ መሰረት ነበር፡፡ ያ መርህ ከዓለም የገንዘብ ድርጅትንና ከዓለም ባንክ የመጣ የመዋቅር ማስተካከያ መርሃ ግብር (Structural Adjustment Programme) ይባል ነበር፡፡ በወቅቱ አቶ መለስ ኒዮ ሊበራል የኢኮኖሚ መርህን ከስታሊናዊነት ጋር ቀላቅለው ከመተግበር አልቦዘኑም፡፡

የዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ በኒዮ ሊበራል መርሃ ግብራቸው በድሆች አገሮች ላይ ብዙ ቀውስ ካስከተሉ በሁዋላ አለም አቀፍ ተቃውሞ ሲበዛባቸው መርሃ ግብሩን ቀየሩት፡፡ የድርጅቶቹ ባለስልጣኖች ከነበሩት እንደነ ጆሰፍ ስቲግሊትዝ (Josef Stiglitz)፣ ኒዮ ሊበራል የኢኮኖሚ መርህን ተቃውሞው መፃፍ ጀመሩ፡፡ በ1998 በፈረንሳይ የተቋቋመውና ከ50 በላይ አገሮች ዜግነት ያላቸው አባሎች ያሉበት በገንዘብ ንግድ ላይ ግብር ለመጣልና የተሰበሰበውን ግብር ለዜጎች ጥቅም ለማዋል የቆመ ማህበር ማለት Attac (L’Association pour la taxation des transactions financières et pour l’action citoyenne) የሚባል ማህበር አለ፡፡ ማህበሩ የግሎባላይዘሽን ሂደት በኒዮ ሊበራሊዝም የነፃ ገበያ መርህ ድሃ አገሮችና ህዝቦች እንዳይጎዳ ይከራከራል፤ አቶ መለስም ኒዮ ሊበራል መርህ ይከተሉ እንዳልነበሩ መስለው ለካድሬዎቻቸው ከኒዮ ሊበራል ጋር የሚያያይዙትን ሙስና „ኪራይ ሰብሳቢነት“ እንዲባል ከትእዛዝ ጋር የተያያዘ ስብከት ሲያሰራጩ ቆይተዋል፡፡ በተግባር ባጭር ጊዜ በሙስና የተዘፈቁት ግን የአብዮታዊ ዴሞክረሲ ባለስልጣኖች ናቸው፡፡

አገዛዙ ያንድ ፓርቲ ስርዓት አራማጅ በመሆኑ ምክንያት እንዳይወገዝ ለመከላከል ሰውየው ኢሕአዴግን አውራ ፓርቲ ብለውታል፡፡ ይህ አውራ ፓርቲ ተግባሩ (ያንድ ፓርቲ ስርዓትነቱ) እንደ ቻይና ሆኖ፣ አጠራሩ አውራ ፓርቲ በመባል የካፒታሊስት ስዊድንና ጃፓን ዓይነት ፓርቲ እንዲመስል ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ ስርዓቱ የቻይና እንዳይመሰል ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲኖሩና ምርጫ እንዲደረግ ለይሰሙላ ቢፈቀድም፣ ያንድ ፓርቲ አገዛዙ እንዲቀጥል ደግሞ የህዝቡ የመምረጥና የተቃዋሚ ፓርቲዎቹ የመመረጥ መብቶች ተረግጧል፡፡

ብዙ ጊዜ እንደ አውራ ፓርቲ የሚጠቀሱት ፓርቲዎች ለረዥም ጊዜ ስልጣን ላይ የቆዩት የስዊድን ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲና የጃፓን ሊበራል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ናቸው፡፡ የስዊድን ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ በመቶ ዓመት ውስጥ ከ1911 እስከ 2010 ድረስ ከ50% በላይ የህዝብ ድምፅ ያገኘው በ1940 ዓ/ም 53.8% እና በ1968 ዓ/ም 50.1% ሁለት ጊዜ ብቻ ነው፡፡ የጃፓን ሊበራል ዴሞክራቲክ ፓርቲም ከ1955 እስከ 2009 ድረስ (ከ1993/94 በስተቀር) ስልጣን ላይ ቢቆይም፣ ፓርቲው ከ50% በላይ ድምፅ ያገኘበት ጊዜ በ1958፣ በ1960 እና በ1963 ብቻ ነበር፡፡ ስለዚህ ሁለቱም ፓርቲዎች ለብዙ ጊዜ ስልጣን ላይ የቆዩት፣ አንደኛ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንጂ በጉልበትና በማጭበርበር አልነበረም፤ ሁለተኛ ሁለቱም ፓርቲዎች አብዛኛውን ጊዜ ተቃዋሚዎቻቸውን አግልለው ህዝቡን ለመግዛት የሚያስችላቸው በቂ የህዝብ ድምፅ ማግኘት ስላልቻሉ ስልጣናቸውን ከሌሎች ጋር እንዲጋሩ ይገደዱ ነበር፡፡ እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ትልቁ ቁምነገር ጃፓንና ስዊድን ነፃ የሆኑ ዴሞክረሲያዊ ተቋማት ያሏዋቸው ዴሞክራሲያዊ ስርኣት የገነቡ አገሮች መሆናቸው ነው፡፡ በዚህ መሰረት ኢህአዴግ አምባገነናዊ ፓርቲ እንጂ በአውራ ፓርቲነት ከሚታወቁት ድርጅቶች የሚያገናኝ ዴሞክራሲያዊ ይዘት የለውም፡፡

አብዮታዊ ዴሞክረሲ ባንድነት ጥያቄ

በኢትዮጵያ አውራ ፓርቲው ልማታዊ መንግስት እንደሚመሰርት ተገልፀዋል፡፡ አቶ መለስ ዴሞክራሲና የምጣኔ ሃብት እድገት እንደማይገናኙ ቢገልፁም፣ ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ የህልውና ጥያቄ እንደሆነ ይገልፁ ነበር፡፡ በአገዛዙ ዴሞክራሲ ሲባል ግን በስታሊናዊ ማእከላዊነትና በግለ-ሰብ አምባገነንነት ላይ የተመሰረተው አብዮታዊ ዴሞክራሲ ነው፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚባለው ብሄር/ብሄረሰቦችን ከፋፍሎ ለመግዛት እንዲያመች የተደረገ፣ በመገንጠል አገርን የመበታተን አደጋን የሚጋብዝ አካሄድ ነው፡፡

ይኸው አብዮታዊ ዴሞክራሲ ደግሞ በተገላቢጦሽ ኢትዮጵያን ከመበታተን እንዳዳነ ይነገርለታል፡፡ ለመሆኑ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ባይኖር ኖሮ ከኢትዮጵያ ማን ይገነጠል ነበር? ሻዕብያ በከፍተኛ ያቶ መለስ ትብብር ኤርትራን ገንጥሏል፤ ኢትዮጵያ የባህር በር አጥታ ለፀታ አደጋና ለምጣኔ ሃብታዊ ኪሳራ ተጋልጣለች፡፡ ሌሎቹ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ድርጅቶች መገንጠል የሚያስችላቸው ወታደራዊ አቅም ስላልነበራቸውና እስካሁንም ስለሌላቸው አንዱን የኢትዮጵያ አካል መገንጠል አልቻሉም፡፡ አንድን ብሄር ከኢትዮጵያ ለመገንጠል አቅም የነበረውና በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ምክንያት የመገንጠልን ዓላማ እንደተወ የሚገልፅ ራሱን ችሎ የቆመ ድርጅት ህወሓት ብቻ ነው፡፡ እውነት ግን የህወሓት አመራር መገንጠልን ያልመረጠው በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ምክንያት ነው ወይስ በስልጣንና በኢትዮጵያ ደረጃ ከስልጣን የሚገኝ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥቅም እንዳይቀርበትና የትግራይ ህዝብ የመገንጠል ፍላጎት እንደሌለው ስለሚያውቅ? ዓላማቸው የትግራይ ዴሞክረሲያዊ ሪፑብሊክ ለመመስረት መታገል እንደሆነ በ68 ማኒፌስቶ በይፋ አውጀው የነበሩት አቶ መለስና ግብረ አበሮቻቸው የኢትዮጵያ አንድነት ራእይ አልነበራቸውም፡፡

የምእተ ዓመቱ የልማት ግቦችና የብዙ ኢትዮጵያውን የልማት ራእይ

ልማት የሁሉም ያገራቸውን ሁኔታ የሚከታተሉ ኢትየጵያውያን ራእይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በከፋ ደረጃ ተደጋግሞ የተከስተውና እስካሁን ማስወገድ ያልተቻለው ራሃብ የብዙ ወገኖቻችን ህይወት ቀጭቷል፤ ህዝብን አሰቃይቷል፤ ለልመናና ሃፍረት አጋልጧል፤ ዘውዳዊውንና የደርግን መንግስታትን እንዲወድቁ አሰተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ስለዚህ በዚህ ችግር ያለፉና ይህን ችግር የሚያውቁ ኢትዮጵያውያን ችግሩን ማስወገድ ይፈልጋሉ፡፡

ሁዋላ ቀርነትን የማስወገድ ራእይ ዓለም አቀፍ ራእይም ስለሆነ የምእተ ዓመቱ የልማት ግቦች በ1993 ዓ/ም ሚስተር ኮፊ አናን የዓለም የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሃፊ በነበሩበት ጊዜ በ193 አገሮችና ብዙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ለልማት ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ ስለተስማሙ በ1994 የሚከተሉት የልማት ግቦች እስከ 2015 (2007 በኢትዮጵያ አቆጣጠር) እንዲሟሉ ተስማምቷል፡፡
1.ከመጠን ያለፈ ድህነትንና ራሃብን ማጥፋት
2.የ1ኛ ደረጃ ትምህርትን ለሁሉም ማዳረስ
3.የፆታ እኩልነትን ማሳደግና የሴቶችን የመወሰን መብት ማስከበር
4.የህፃናት መሞትን መቀነስ
5.የእናቶችን ጤንነት ማሻሻል
6.ኤይድስን፣ ወባንና ሌሎች በሽታዎችን መታገል
7.ያየር ንብረት ዘላቂነትን ማረጋገጥ
8.የልማት ግቦቹን ለማሳካት ዓለም አቀፍ ትብብርን ማጠናከር

ስምንተኛው የልማት ግብ እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያም የልማት ግቦቹን ለማሳካት ከሃብታም አገሮች እርዳታ ታገኛለች፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ህዝብም ልማት የግለ-ሰብ ራእይ፣ ማለትም የመለስ ራእይ ተደርጎ ከሚነገረው፣ ልማት ዓለም አቀፍ የጋራ ራእይ መሆኑ ማወቁ ግልፅነት ላለው አሰራር ይጠቅማል፡፡

„የመለስን ራእይ“ ከመከተል መወገድ ያለባቸው አቋሞችና ድርጊቶች

የግለ-ሰብ ፈላጭ ቆራጭ አምባገነንነት፡

የግለ-ሰብ ፈላጭ ቆራጭ አምባገነንነት ከድህነትም ከማሃይምነትም የባሰ የሁዋላ ቀርነት መገለጫ ነው፡፡ በእንደዚህ ዓይነት አምባገነንነት በህዝብ ላይ ግፍ እንደሚፈፀም በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፤ በአምባገነንነት የኢኮኖሚ እድገት እንደሚመጣ ግን ዋስትና እንደሌለ በብዙ የአፍሪካ አገሮች አምባገነኖች ተረጋግጧል፡፡ ስለዚህ አቶ ሃይለማርያም በኢትዮጵያ ህዝብ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አመባገነን ያልሆኑ መሪ ቢሆኑ መሠረታዊ የሆነ ታሪካዊ ለውጥ ይሆናል፡፡ እዚህ ላይ የጋራ አመራር የሚል አገላለፅ በአቶ መለስ ስር እንደነበረው ዓይነት ከሆነ እውነት እንዳልነበረ ግልፅ ስለሆነ የጋራ አመራሩ በቅንነት መተግበር አለበት፡፡

የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አለመከበር

በአቶ መለስ አገዛዝ ስር የኢህአዴግ አባሎችና ብዙ ባለስልጣኖች እንኳንና ተራው ዜጋ እነሱም ራሳቸው ነፃ ዜጎች እንዳልነበሩ ነፃነት እንዳልነበራቸውም ደፍረው መናገር እንዳልቻሉ ያውቃሉ፡፡ የግዲያ ወንጀሎች ከፈፀሙትና በሙስና ከተዘፈቁት የኢህአዴግ ባለስልጣኖች በስተቀር ግን ሌሎቹ አባላት ነፃነት፣ ግልፅነትና ፍትህ የማይፈልጉበት ምክንያት ሊኖር አይችልም፡፡ የኢህአዴግ አባላት ነፃነት ቢፈልጉም በተገዥነት ተሸማቅቀውና እርስ በርሳቸው እንዳይተማመኑ ተደርገው ስለቆዩ ለመብቶቻቸው መታገል መቻላቸው ያጠራጥራል፡፡ ኢህአዴግ በስልጣን እስካለ ድረስ የራሱ አባላት ነፃ ሳይሆኑ ሌሎች ዜጎች ነፃ ሊሆኑ ስለማይችሉ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ስልጣናቸውን ተጠቅመው ለድርጅታቸው አባላት ነፃነት ቢያጎናፅፉ ለሁሉም ይጠቅማል፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሌላቸው አቋም ማውገዝ

የልማት ጥያቄ ሲነሳ ለአገራችን ልማት በጣም እንደሚያሰፈልጋት ባሏቸው አቋሞች በኢህአዴግና በቂ የህዝብ ተቀባይነት ባላቸው ተቃዋሚ ድርጅቶች ማኽል መሠረታዊ ልዩነት የለም፡፡ ርሃብ በኢትዮጵያ እንዲጠፋ፣ ተቃዋሚዎችም መንግስት በኢኮኖሚው በጥናት ላይ የተመሰረተ ሚና እንዲኖሮው እንደሚፈልጉ ይገልፃሉ፤ ለነፃ ገበያ ብቻ የቆሙ አይደሉም፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ በተቃዋሚዎቹ ላይ ኒዮ ሊበራሊዝምን ለጥፎ ባገር ውስጥ ከሌለ ሃሳብ ጋር ከሚከራከር፤ ተቀዋሚዎቹ የራሳቸውን አቋም ራሳቸው ቢገልፁ ይሻላል፡፡

እንደዚሁም የሚከተሉትን ልመዶችና አሰራሮች ማስወገድና የሚስተካከሉትን ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡

- የአንድ ፓርቲ አገዛዝን ማስፈንና በአውራ ፓርቲ ስም ማጭበርበር፣

- ዜጎችን በፖለቲካ ምክንያት በውሸት ማሳሰር፣ ማስከሰስ፣ ማስፈረድ፣ ማሰቃየት፣ የውሸት ሽምግልና መላክ፣ ተከሳሾች ራሳቸውን እንዲወነጅሉና ተሸማቅቀው ይቅርታ እንዲጠይቁ ማድርግ፣

- ለብሄር/ብሄረ ሰብ ልዩነት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ፤ ባደረጃጀት( የነገድ ድርጅቶች መፈልፈል)፣ ባጠራር (የኢትዮጵያ ህዝብ በማለት ፈንታ በተንዛዛ „ብሄር፣ ብሄረሰብና ህዝቦች የሚል አጠራር መጠቀም) ህዝብን መከፋፈል

- የፖለቲካ ሙስና> ጉልበትን በመጠቀም ምርጫን ማጭበርበር፣ የፍርድ ተቋምን፣ የመገናኛ ብዙሃንን፣ የምርጫ ቦርድን፣ የሰራዊትንና የፀጥታ ሃይሎችን ገለልተኛ ሆነው ህዝቡን በእኩልነት እንዳያገለግሉ መከልከልና የስልጣን መሳሪያ ማድረግ

- የኢኮኖሚ ሙስና

- በህገ መንግስቱ የተዘረዘሩትን መብቶችና ሕጎች አለመተግበርና ዜጎችን ለማሰቃየት አጣምሞ መተርጎም

- ዜጎችን በጉልበት ማፈናቀልና መሬት ለውጭ ኩባኒያዎች ማከራየት

- በርካሽ የውጭ ዕቃዎች ገበያውን በማጥለቅለቅ የአገር ፋብሪካዎች እንዳያድጉ ወይም እንዲጠፉ ማድረግ፣

- ጥሬ ምርቶች እንደነ ሰሊጥና ኑግ ባገር ውስጥ ፋብሪካዎች እንዲሰሩ በማድረግ ፈንታ ለውጭ ገበያ መላክ፣ ባገር ውስጥ በፋብሪካ እንዳይሰሩ ማድረግ

አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የጠቅላይ ሚኒስትር ስልጣን ከተረከቡ ቀን ጀምሮ ነጋ ጠባ ያቶ መለስን ራእይ እከተላለሁ ሲሉ ቢደመጡም አቶ መለስ የፈጠሩት ሁኔታ ለጥቂቶቹ ገነት ለሚሊዮኖቹ ሲኦል እንደሆነ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት እስከሌለና በሃገር ገዳይ ላይ ትችት ማቅረብ እንደ ወንጀል ተቆጥሮ ወሕኒ ቤት የሚያስወርድ እስከሆነ ድረስ አቶ ሃይለማርያምና ጥቂቶቹ ባለደረቦቻቸው የዚህ በሽተኛ ራእይ እስረኞች ሆነው ይቀጥላሉ፡፡ የአንድ አምባገነን ፓርቲ አገዛዝ ያንድ ግለ-ሰብ ፈላጭ ቆራጭነትና ባንድ ግለ-ሰብ አምልኮ መጠመድን እንዳስከተለው ሁሉ፣ በድህነትና ባፈና የሚማቅቁት ሚሊዮኖች ሲነሱበት አገዛዙ ይደመሰሳል፡፡

የህሊናና የፖለቲካ እስረኞች ካለ ቅድመ ሁኔታና አሁን ይፈቱ!!

ESAT Daliy News Amsterdam Nov 22 2012 Ethiopia


በምስራቅ ኢትዮጵያ ከባድ ዉጊያ እየተካሄደ ነው!


በምስራቅ ኢትዮጵያ ከባድ ዉጊያ እየተካሄደ ነው!!!
አምባገነኑ የወያኔ መደብ ለአመታት በኬንያ መሽጎ ድርድር ሲያደርግበት የነበረው ውይይት ከተኮላሸ በኋላ በምስራቅ ኢትዮጵያ ከባድ ዉጊያ እየተደረገ መሆኑን የመከላከያ ሰራዊት ምንጮች ጠቆሙ::

በኦጋዴን ቀላፎ እና ጎዴ በሚባሉ ቦታዎች የታጠቁ ሃይሎች  በወያኔ ወታደሮች ላይ በከፈቱት ድንገተኛ ጥቃት ከባድ ጥፋት አድርሰው መሰወራቸዉን የገለጡት እነዚህ ምንጮች ወያኔ በምክር ቤቱ አሸባሪ እያላቸው የሚከሳቸዉን የኦብነግ አባላት  ከህዝብ ተደብቆ ሲደራደር ከቆየ በሁዋላ ድርድሩ መክሸፉን ተከትሎ የተነሳው ዉጊያ ማብረጃ አላገኘም ሲሉ ዉስጥ አዋቂ ምንጮች ተናግረዋል::

ለቀጠና ጥበቃ በተሰማሩ የወያኔ ወታደሮች ላይ የተደረገውን ጥቃት የቀሰቀሰው ውጊያ በጦሩ ላይ ለደረሰው ጥቃት ተጠያቂ ናችሁ ተብሎ መስመራዊ የጦር መኮንኖች ወደ እስር ቤት ተልከዋል;

በጦሩ ላይ ለደረሰው ጥቃት ራሳቸዉን ነጻ ማድረግ የፈለጉት የምስራቅ እዝ የጦር ኣዛዥ አብርሃ ወ/ማርያም እና ተከታዮቹ ግንባር ላይ ተሰልፈው የነበሩትን መስመራዊ የጦር መኮንኖች ጥፋተኛ በማድረግ ከያሉበት ተለቅመው ሐረር ከተማ በሚገኘው የምስራቅ እዝ ዋና ማዘዣ በሆነው እስር ቤት ዉስጥ መታሰራቸውን ምንጮቹ ተናግረዋል::

በምስራቅ እዝ ዋና አዛዥ የሚመራ አንድ ግብረ ሃይል/ቡድን/ ተቋቁሞ እነዚህን የመስመር መኮንኖች ለመዳኘት እና የጥፋተኝነት ዉሳኔ ለመስጠት በስራ ላይ መሆኑን ዉስጥ አዋቂ ምንጮቹ አመልክተዋል::

የባለሥልጣናቱ ውይይት ታፈነ!!!!!


የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ስም ሲነሳ አቶ በረከት ስምዖን በግንባር ቀደም ይጠቀሳሉ። የአቶ በረከት ንብረት ሆኖ የመለስን አመራር በታማኝነት ሲያገለግል የኖረው ይህ ተቋም ቆርጦ በመቀጠል፣ የዜጎችን ሃሳብ በማዛባት፣ ወሬን ባለማመጣጠንና የሃሰት ፕሮፓጋንዳ በማስተላለፍ የሚታወቅ ነው። ስለሚጠየፉት የማይመለከቱት እንዳሉ አፍ አውጥተው የሚናገሩም አሉ።
ለሙያው ቅርብ የሆኑ አስተያየት ሰጪዎች “ወገንተኛ እንኳን ቢኾን መሰረታዊ የሙያው ግዴታ ሳይጣስ ሊሆን ይገባል። አንድ መገናኛ ማመጣጠን ካልቻለ በራሱ ሙት ነው። እያደር ብቻውን ይቀራል” ሲሉ ኢቲቪን ይገልጹታል። እንደነሱ አባባል ኢቲቪ ከህዝብ ሳይሆን ከራሱ ጌቶችም ጋር ተነጥሎ የአንድ ወገን (ግለሰብ) ሎሌ የሆነ በድርጅት ቅርጽ የሚከላወስ ሱቅ በደረቴ አይነት ነው።
ኢቲቪ ሃሳባቸውን፣ ንግግራቸውን፣ አቋማቸውን፣ ጥቆማቸውንና ተቃውሟቸውን እየቀረጸ በማዛባት ከህዝብና ከሚወዱዋቸው ወገኖቻቸው ጋር እሳትና ጭድ ያደረጋቸው፣ ለተራ የፖለቲካ መጠቀሚያ ሰለባ የሆኑ ወገኖች ኢቲቪን “በደለን” በማለት መውቀስ የሚችሉበት አግባብ የላቸውም። ኢቲቪ “በአልቤርጎ ውለታ” የግል ሳሎናቸው ያደረጉትን ጨምሮ “ልማታዊ” የሚባሉት በግብር ጸረ ልማት የሆኑ ውስን ጋዜጠኞች ሎሌ ሆነው እንዳሻቸው የሚንፈላሰሱበት ቤት ስለሆነ ጠያቂም ከልካይም እንደሌለባቸው ስለ ተቋሙ የሚያውቁ ይመሰክራሉ።
ተቋሙ ከድርጅት ደረጃም ወርዶ የግለሰብና የተወሰኑ ቡድኖች መፈንጫ እንደሆነ በየጊዜው አስተያየት ቢሰጥም ማንም ደፍሮ ሊያስተካክለው አልቻለም። ኢህአዴግ መንግስት ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ አቶ በረከት ብቻቸውን የሚጋልቡት የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ጡንቻው የራሱን የኢህአዴግ ከፍተኛ የሚባሉትን ባለሥልጣናት ድምጽ የማፈን አቅም ያለው መሆኑ በእጅጉ አነጋጋሪ ሆኗል።
ከፍተኛ ባለሥልጣናት በጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት ያካሄዱት ስብሰባ ለህዝብ ይቀርባል ከተባለ በኋላ መታፈኑ ባለሥልጣናቱን ሳይቀር አስቆጥቷል። ካለፉት ሁለት ወራት ጀምሮ አወዛጋቢና አነጋጋሪ ዜናዎችን የሚዘግበው ሰንደቅ ጋዜጣ “ለህዝብ ይፋ ይሆናል” ተብሎ ማስታወቂያ የተነገረለት ስርጭት በማን ትዕዛዝ ታፈነ የሚለው ጉዳይ ባለስልጣናቱን እንዳበሳጫቸው ጠቅሶ ሰፊ ሪፖርት ይፋ ሲያደርግ አንድ የሥራ ኃላፊ ከማናገሩ ውጪ ወደ ላይ ከፍ ብሎ አላነጣጠረም።
ሰንደቅ ጋዜጣ 8ኛ ዓመት ቁጥር 376 ረቡዕ ህዳር 12 ቀን 2005 በፌስ ቡክ ባሰራጨው ዜና ስብሰባውን በመከታተል ሪፖርት ያዘጋጀው ጋዜጠኛ አዲሱ መሸሻን በማነጋገር “የባለሥልጣናቱ ውይይት የታፈነው ሆን ተብሎ ነው” በማለት ምላሽ መስጠቱን እንደሚከተለው አስነብቧል።
የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ባልደረባ የሆነው ጋዜጠኛ አዲሱ መሸሻ በዕለቱ ዝግጅቱን እንዲከታተል ተመድቦ ዜናው ከስድስት ደቂቃ ተኩል በላይ ሠርቶ በዕለቱ መተላለፉን፣ የዜናው ይዘትም አዎንታዊ ግብረ-መልስ ከውይይት ተሳታፊዎች እንደነበረው አስታውሷል። ይኸው የባለሥልጣናት ውይይት ሰፋ ባለ ፕሮግራም እንዲዘጋጅም ከድርጅቱ የሥራ ኃላፊዎች መታዘዙንና ይህንንም ተከትሎ በማግስቱ ቅዳሜ ዕለት ሰፊ ፕሮግራም አዘጋጅቶ እሁድ እንደሚተላለፍ የሚገልፀውን ማስታወቂያ (ስፖት) ሠርቶ አስረክቦ በግል ጉዳይ እረፍት መውሰዱን አስታውሷል።
ሆኖም እሁድ ጥቅምት 25 ቀን 2005 ዓ.ም ይተላለፋል የተባለው ፕሮግራም እሱ ለጊዜው ባላወቀው ምክንያት ሳይተላለፍ መቅረቱን፣ ነገር ግን ስብሰባውን በአካል ተገኝቶ ያልተከታተለው አቶ ሳሙኤል ከበደ በተባለ ባልደረባው አማካይነት ቀደም ሲል አዘጋጅቶት የሄደው የተሟላ ፕሮግራም ተጥሎ፣ ሆን ተብሎ የባለሥልጣናቱ ሃሳቦች ተቆራርጦ ማክሰኞ ጥቅምት 27 ቀን 2005 ዓ.ም እንዲተላለፍ መደረጉን ገልጿል።
ጋዜጠኛ አዲሱ “የባለሥልጣናቱ ውይይት የመንግሥት አቋም እንጂ የግለሰብ አይደለም። እኔ ጉዳዩን የተከታተልኩት ባለሙያ እያለሁ፣ ሳይነገረኝና ሳላውቅ ያዘጋጀሁት ፕሮግራም ተጥሎ፣ ተዛብቶና ተቆራርጦ እንዲቀርብ በመደረጉ ኃላፊነቱን መውሰድ ያለበት ጋዜጠኛ ሳሙኤል ከበደ እንጂ ተቋሙ አይደለም” ማለቱን የሰንደቅ ዘገባ ያስረዳል።
አቶ አባይ ጸሃዬ
የጎልጉል የአዲስ አበባ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢቲቪ ምንጮች እንዳሉት ጋዜጠኛ አዲሱ መግለጫውን እንዲሰጥ ከበላይ ትዕዛዝ ወርዶለታል። የባለሥልጣናቱ ውይይት ሙሉ በሙሉ ለህዝብ ይተላለፋል ከተባለ በኋላ አለመተላለፉ፣ በማስቀጠልም ፕሮግራሙ ተቆራርጦ መቅረቡ ካበሳጫቸው ባለሥልጣናት መካከል አቶ አባይ ጸሃዬ ኢቲቪ ማብራሪያ እንዲሰጥ መጠየቃቸውን እንደሚያውቁ የጠቆሙት ምንጮች “ፕሮግራሙ ተዛብቶ እንዲተላለፍ ትዕዛዝ የተቀበሉት ሃላፊዎች መመሪያውን ከማን እንደሚቀበሉ ይታወቃል” ብለዋል።
አቶ በረከትን በቀጥታ ያልገለጹት የኢቲቪ ሰዎች፤ “ኢቲቪ ውስጥ ከፍተኛ ጉዳዮች እርሳቸው ሳያውቁት አይተላለፉም። ጨዋታው ኢህአዴግ ኢህአዴግን ማፈን ጀመረ የሚያስብል ነው” በማለት ባለሥልጣናቱ ላይ ሲደርስ አዲስ ሆነ እንጂ በርካታ ዜጎች በተመሳሳይ ሃሳባቸው እየተዛባ ለፖለቲካ ቅስቀሳ እንዲውል ሲደረግ ማየት የተለመደ መሆኑን አስታውቀዋል። ኢቲቪ ከድርጅትም ወርዶ የግለሰብ “ሎሌ” እንደሆነ ሲነገር ለሚሰሙ ባለሥልጣናት ከዚህ በላይ ማስረጃ ሊቀርብ እንደማይችልም አመልክተዋል።

አሊ ሱሌማን
ጥቅምት 23 ቀን 2005 ዓ ም በተካሄደው የከፍተኛ ባለሥልጣናት ውይይት ላይ ባለሥልጣናቱ ምን ቢናገሩ ነው ድምጻቸው እንዲታፈን የተደረገው የሚለው ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኗል። በውይይቱ ወቅት ባለሥልጣናቱ ጠንካራና ባለሥልጣናትን እየለየ የሚያሳጣ አስተያየት መስጠታቸው፣ የጸረ ሙስና ኮሚሽነር አቶ አሊ ሱሌማን ኮሚሽኑ መረጃ ቢኖረውም ከሶ እንዳያስፈርድ ጫና እንዳለበት ለተሰነዘረባቸው ወቀሳ ምላሽ ሰጥተዋል። ህዝብ መማረሩና ሰሚ ማጣቱ፣ አደገኛ የማህበራዊና ኑሮ ውድነት ቀውስ መከሰቱ፣ የመንግስትን “ሌቦች” ለመቆጣጠር የተቋቋሙ መዋቅሮች ቅርንጫፎቹን እንጂ ግንዱን ገንድሰው ሊጥሉ አለመቻላቸው፣ የግንዱን ግድግዳ መገርሰስ ካልተቻለ ግንዶቹ እንደሚጠነክሩ፣ ኢህአዴግ ለራሱ ሲል ግንዱን መገርሰስ እንደሚገባው … ይህን ማድረግ ካልተቻለ አደጋ እንደሚሆን ከተለያዩ ባለስልጣናት ሃሳብ ተሰጥቷል።
“የግንዶቹን በር በርግዶ መግባት አልተቻለም” በማለት አቶ አባይ ጸሃዬን በመደገፍ የወደፊት የአቶ መለስ ምትክ እንደሚሆኑ የሚነገርላቸው የመገናኛና የኢንፎርሜሽን ሚኒስትሩ አቶ ደብረ ጽዮን ገ/ሚካኤል “ጊዜ መስጠት የለብንም።

በዚህ ከቀጠለ አደገኛ ነው” ሲሉ ስርዓቱን እየበላው ያለውን የሙስናና መበስበስ አደጋ አመላክተዋል። የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ “የችግሩ ምንጭ መዋቅራችን ነው” ሲሉ፣ ምክትል ጠ/ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው “ሰፊ ተጠያቂነት ይካሄዳል” ማለታቸው ተደምጧል።
ደብረ ጽዮን ገ/ሚካኤል
ዘጠነኛው መደበኛ ጉባኤውን ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ያለው ኢህአዴግ፣ እናት  ፓርቲዎቹና አጋር ፓርቲዎቹ በተናጠል ባካሄዱት ተከታታይ ግምገማ በተመሳሳይ ሰዉ ድርጅቱን አልቀበልም ስለማለቱ፣ በልማት ሰራዊት ግንባታ ስም ለቀረበው የመደራጀት ጥያቄ አዎንታዊ መልስ መከልከሉ፣ በአባላትና በካድሬዎች መካከል የመጠራጠርና የመከዳዳት ስሜት መጎልበቱ፣ ከሁሉም በላይ ሙስና ከቁጥጥር በላይ መሆኑ ስርዓቱን አደጋ ላይ እንደጣለው ከተሰብሳቢዎቹ መሰንዘሩ ተደምጧል። የየፓርቲው መሪዎችም በተመሳሳይ ችግር እንዳለ መልሰው ለካድሬውና ለበታች አመራሩ ማስተጋባታቸው ችግሩን ማን ይፍታው በሚል ጥያቄ እንዲያነሱ እንዳስገደዳቸው አስተያየት እየተሰጠ ነው።
ኢህአዴግ ባለስልጣናትን ሆን ብሎ በሙስና በማበስበስ “አቋም የሌላቸው ታዛዥ” እንደሚያደርጋቸው፣ እንዲህ ያለው ተግባር አገርንና ራሱን ኢህአዴግን ወደ “ታላቁ” ጉድጓድ እንደሚነዳቸው ከወራት በፊት “መለስ የቆፈሩት ጉድጓድ” በሚል ርዕስ ከጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ጋር ቃለ ምልልስ ያካሄዱ አንድ የኢህአዴግ አመራር ማስታወቃቸው አይዘነጋም። በቃለ ምልልሱ ኢህአዴግ ስለመበስበሱ በስፋት የተወሳ ሲሆን በተለይም አቶ መለስ ካለፉ በኋላ ስርዓቱ እንዴት ሊፈረካከስ እንደሚችል ተመልክቷል። በተመሳሳይ ከወር በፊት ሪፖርተር ጋዜጣ በርዕሰ አንቀጹ ኢህአዴግ ከፍተኛ በሚባል የንቅዘትና የመውደቅ አደጋ እንደተጋረጠበት በመጠቆም ከወዲሁ መስተካከል ስላለባቸው ጉዳዮች ማሳሰቢያ መስጠቱም ይታወቃል።
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተቆርቋሪ ተማሪ አለ ?


ድሮ ድሮ አዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲ የምንሰማው ዜና የሃገራችው ውስጥ ያለውን የመብት ረገጣ  በመቃወም  ፣ የምርጫ መጭበርበርን  ትከትሎ,,,,,  ወዘተ  ተቃወሙ ወይም ድምፃቸውን አሰሙ ሲባል ነበር ። ከተወሰነ ጊዜ በኃላ አዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲ አለ እንዴ  እስኪባል ድረስ ዝምታው ሰፍኑዋል ። ከምር ግን በአዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲ  ለ ኢትዮጵያ በህዝብ ላይ የሚደርሰው የሰብዓዊ መብት ረገጣ  የሚቆረቆር ዜጋ እንዴት ይጠፋል ። አንድ የ ፌስ ቡክ ጓደኛ ፖስት ያደረገው ነገር  ላስታውሳችሁ ምን አለ መሰላችሁ ¨አዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲ ወደ ካድሬ ማሰልጠኛነት ተቀይሯል  ¨ ነበር ያለኝ  ይህ ነገር እውነት ይሆን ? እንደሚታወቀው  በዮኒቨርሲቲዎች ውስጥ የወያኔ ቡችላዎች  ያነፈንፋሉ ፤ ግን እንዴት በወገናችን  ላይ የሚደርሰው   ኢ ሰብዓዊ መብት ረገጣ  በቃ የሚል ይጠፋል !!! እስኪ አለመታደል ሆኖ አዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲ የሚገኙ ተማሪዎች  በሃገሪቱ እየተባባሰ ያለውን የመብት ረገጣ ተቃውመው ድምጳቸውን አሰሙ የሚል አስደሳች ዜና  ለመስማት ባንታደልም ። ይህንን  ዜና እነሆ ፦
በአሁኑ ዝርፊያ ከ 50 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ንብረት አጥቷል
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የአይቲኤስሲ ላብራቶሪ ሰሞኑን ለሁለተኛ ጊዜ ተዘረፈ፡፡
ሪፖርተር ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው ለሁለተኛ ጊዜ ሰሞኑን የተዘረፈው የ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢንስቲትዩቱ ላብራቶሪ እጅግ በጣም ውድ የሆኑ፣ የዘመኑን ቴክኖሎጂዎች ያካተቱና በብዙ ሚሊዮን ብር የሚገመቱ ንብረቶቹን አጥቷል።
ዝርፊያው የተፈፀመው የዲፓርትመንቱን በር ቁልፍ በመስበር እንደሆነም ምንጮቹ ገልጸዋል።
የተወሰዱት ኮምፒውተሮችና የላብራቶሪ ዕቃዎች ግምት ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ሊበልጥ እንደሚችል ያመለከተው ጋዜጣው፤ጉዳዩን ፖሊስ ይዞ እየመረመረው መሆኑንም ጠቁሟል፡፡
በዝርፊያው ተጠርጥረው ከታሰሩት ውስጥ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በፍሪላንሰርነትና በቋሚነት የሚያገለግሉ ሠራተኞች እንደሚገኙበት ተመልክቷል፡፡
በዩኒቨርሲቲው ተከስቷል ስለተባለው ዝርፊያ ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ነፃነት ይልማ፦ ‹‹ጉዳዩን ፖሊስ ስለያዘው ምንም ማለት አልችልም፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
በዝርፊያው ተጠርጥረው በጃንሜዳ አካባቢ በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ስለታሰሩት ተጠርጣሪዎችና ፖሊስ ስለደረሰበት የምርመራ ውጤት ማብራሪያ ለማግኘት የተደረገው ጥረት አለመሳካቱም ተገልጿል፡፡

Wednesday, November 21, 2012


የመንግስት ጋዜጠኛው የሰራው የዜና ዘገባ ያለርሱ ፈቃድ ተቆራርጦ በቴሌቭዥን መቅረቡን አስታወቀ


ህዳር ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ባልደረባ የሆነው ጋዜጠኛ አዲሱ መሸሻ በጠ/ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ጥቅምት 23 ቀን 2005 ዓ.ም የተካሄደውንና ከፍተኛ ባለሥልጣናት የተሳተፉበት ውይይት አስመልክቶ በስፍራው በመገኘት ያጠናቀረው ፕሮግራም ያለአግባብ ተለውጦ እና ተቆራርጦ ለሕዝብ እንዲቀርብ መደረጉን አስታወቀ።
ሰንደቅ ጋዜጣ ይህንኑ አስመልክቶ ዛሬ እንደዘገበው፣ ጋዜጠኛ አዲሱ መንገሻ በዋናነት በመልካም አስተዳደር፣ በተጠያቂነት እና በሙስና ችግሮች ላይ ያተኮረውን ይህንኑ የስብሰባ ውሎ እንዲዘግብ ተመድቦ፣ ይህንኑ ውይይት በተመለከተ ከስድስት ደቂቃ በላይ የፈጀ የዜና ዘገባ ቢሰራም፣ ባላወቀው ምክኒያት እርሱ ያጠናቀረው ዜና ወደ ጎን ተትቶ፣ በስብሰባው ላይ በአካል ባልተገኘው ሌላ ባልደረባው የተሰራ ዜና ለሚድያ ፍጆታ መዋሉን አስታውቋል። ይኸው በጋዜጠኛ ሳሙዔል ከበደ የተከለሰው ፕሮግራምም ሆን ተብሎ የባለስልጣናቱ ሃሳቦች ተቆራርጠውነት ጥቅምት 27 ቀን 2005 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን እንዲተላለፍ መደረጉንም ጋዜጠኛ አዲሱ ገልጿል።
ይህንኑ አስመልክቶ እየቀረበ ያለውን ቅሬታ በተመለከተ የተሰማውን ስሜት የገለፀው ጋዜጠኛ አዲሱ “የባለሥልጣናቱ ውይይት የመንግሥት አቋም እንጂ የግለሰብ አይደለም። ውይይቱን በአካል ተገኝቼ የተከታተልኩት ባለሙያ እያለሁ፣ ሳይነገረኝና ሳላውቅ ያዘጋጀሁት ፕሮግራም ተጥሎ፣ ተዛብቶና ተቆራርጦ እንዲቀርብ በመደረጉ ኃላፊነቱን መውሰድ ያለበት ጋዜጠኛ ሳሙኤል ከበደ እንጂ ተቋሙ አይደለም”ሲል አስታውቋል።
“አቶ ሣሙኤል ያልተከታተለውን ዝግጅት በራሱ ተነሳሽነት ብቻ ቆርጦ ያመጣል? ወይንስ እንዲያቀርብ የታዘዘው በበላይ ኃላፊዎች ቢሆንስ?” በሚል ለጋዜጠኛ አዲሱ ለቀረበለት ጥያቄ “ይህንንም ቢሆን እኔ እንዳውቀው መደረግ ነበረበት። በአለቆች ታዞ ከሆነ አዘውኝ ነው ማለት ነበረበት። በእውነትና ታዞ ከሆነ የተቋሙ ኃላፊዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ኃላፊነት ሊወሰዱ ይገባል” ሲልምላሽ ሰጥቷል።
ጋዜጠኛ አዲሱ አያይዞም ይህን መሰል ችግር የሚፈጠረው በቢሮክራሲ ውስጥ ከኢሕአዴግ በላይ ኢሕአዴግ ነን የሚሉ ሰዎች በመኖራቸው ነው። በስብሰባው ውስጥ ተሳታፊ ከነበሩት መካከል ፕሮግራሙ እሁድ ባለመተላለፉ ቅሬታቸውን ለድርጅቱ ኃላፊዎች ማቅረባቸውንም ሰምቻለሁ ብሏል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ባለቤትነት በጠ/ሚኒስትሩ ቢሮ ጥቅምት 23 ቀን 2005 ዓ.ም የተካሄደው ስብሰባ በመልካምአስተዳደር፣ በተጠያቂነት፣ በሙስና ችግሮችና በመሳሰሉት ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት የተካሄደ ሲሆን በዚህ ውይይት ላይ የኢፌዲሪ ምክትል ጠ/ሚኒስትርና የትምህርት ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጨምሮ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ በሚኒስትር ማዕረግ የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይ ፀሐዬ፣ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል፣ የእምባ ጠባቂ ተቋም ዋና እምባ ጠባቂ ወ/ሮ ፎዚያ አሚን፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዓሊ ሱሌይማን፣ የአ/አ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አበባው ስጦታው እና ሌሎችም የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ይኸው ውይይት በኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ሊተላለፍ ታቅዶ የነበረው ሰፋ ያለ ፕሮግራም በተያዘለት ዕለት ካለመተላለፉም በተጨማሪ በተላለፈበት ዕለትም ተቆራርጦ መቅረቡ፣ በአገራችን ውስጥ ዋነኛ አነጋጋሪ ጉዳዮች ሆነው ከሰነበቱት ጉዳዮች አንዱ ነው በማለት ባልደረባችን ቅዱስ ሀብት በላቸው ከአውስትራሊያ ዘግቧል።