Thursday, May 9, 2013

ወያኔ ሕወሃት ያልከበደው ኢትዮጵያዊ ማነው?



ሌቱ መሽቶ ይነጋል፤ ሳምንታት ወራት ዓመታት በፍጥነት መንጎዳቸውን አላቋረጡም፤ ክረምትና በጋ ይፈራረቃሉ፤ ወቅቶችም ማንም ሳይረብሻቸው ጊዜያቸውን ጠብቀው እያለፉ ነው፤ አፍጣጭ ገላማጭ ያለባቸውም ማዘዣ ጣቢያቸው ከእኛ አይደለምና። የክረምቱን ዝናብ ቀድሞ ለማምጣት፤ ፀሐይዋን ትንሽ ቀደም ወይም ዘግየት ብላ እንድትወጣና እንድትገባ ለማድረግ፤ የምንተነፍሰው አየር ባንድ አካባቢ ብቻ እንዲነፍስ ለማዘዝ፤ ብርሃን ብቻ እንዲሆን ወይም ጨልሞ እንዲቀር ማድረግ የሰው ልጅ የሚችል ቢሆን በተለይ እኛ ኢትጵያዊያን ምን ይውጠን ነበር? ለሀገርም ለሕዝብም ለታሪክም ለባህልም እንዴው ለምንም የማይጨነቅ ገዥ ሕወሃት ለተጫነብን።
“ሲለምኑ ማፈር ድሮ ቀረ” አሉ አድስ አበቤዎች። እንዴው ግን ሰራተኛው፣ ገንዘብ አስገቢና መላሹ፣ የሙስና ዘዋሪውና አስዘዋሪው፣ ቀጣሪውና አባራሪው፣ ባለስልጣኑና ባለፋብሪካው፣ ኢንቨስተሩና ነጋዴው፣ አምራቹ አከፋፋዩና ቸርቻሪው፣ መሬት ሰጭና ነሽው፣ አራሹና አሳራሹ ባጠቃላይ ሁሉም በሕወሃትና የአገዛዙ አባላት ቁጥጥር ስር በሆነበት ሀገራችን “ሲለምኑ ማፈር ቀረ” ቢባል የሚያስደንቅ አይሆንም። ህግን አክብሮ በራስ መንገድ መስራትና እራስን መደጎም አይቻልማ፣ ከህሊናው ጋር ሆኖ ከወያኔ ጋር መስራት የመጨረሻ እጣው ከስራ መባረርና ልመና ነዋ። ድሮ እኮ መስራት የማይወድ ነው የሚለምነው፣ ያኔ እኮ ቀን ከሌት ደክሜ በላቤ በደሜ ሀገሬን ሕዝቤን እራሴንም ላሻሻል የሚለው ሳይሆን መድከምን እየጠላ መጎሳቆልን እየሸሸ በምላሱ ስንቱን አውለብልቦ እራሱም ተውለብልቦ በመሽሞነሞን ለመኖር የሚፈልገው ነበር የሚለምነው። ስለዚህም በዚያ ዘመን መለመን ያሳፍር ነበር። አሁን ግን ቀረ።

ለነገሩ እኔ ልመናን አነሳሁ እንጅ በወያኔ ዘመን ምን ያልቀረ አለ፤ ድሮ ጀግና ያስብሉ ያስከብሩ ስለነበሩት የሀገር አንድነትና የባንዲራ ክብር ባደባባይ ማውራት ቀርቶ ማሰብ በራሱ ባሸባሪነት እያስከሰሰ ዘብጥያ ማውረድ ከጀመረ ወዲህ ባንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዘንድ በቀር መነገር ካቆመ ቆየ። ለስራ ለትምህርትና ለመሳሰሉት ካልሆነ በቀር ካገር መውጣት ማስገዘቱ ቢቀር ዘመድ አሰብስቦ ያሳዝንም የስለቅስም ነበር አሁን እቴ ሁሉ ቀርቷል። ወያኔ ከመጣ ምን ያልታየ አለ፤ አንድ ከተማ ነቅሎ የሚወጣ ያህል በየእለቱ ይሰደዳል። የአረብ አገር ጎረመሶች የግርፋት ስቃይና መከራ መለማመጃ ብንሆንም፣  ስቅላቱ ከፎቅ መወርወሩ በፈላ ውሃና ዘይት መተበሱ ሳያባራ ቢቀጥልም ሕወሃት ያማረረው ሕዝባችን ዛሬም ይሰደዳል። የሜድትራኒያንና የቀይ ባህር የአሳ ሲሳይ ብንሆንም በሕወት ብልሹ አገዛዝ ምክንያት ርሃብ የገረፈው መታረዝ የጠበሰው ማጣት ያንገበገበው ሕዝባችን አላቆመም ይሰደዳል። “ስደት ድሮ ቀረ”  በወኔ ሕወሃት ዘመን አይሰራም ባገዛዙ እንደባህል እየተወሰደ ያለ ነገር ነውና። ሀገሮች በኢኮኖሚ ሲያድጉና ሲሻሻሉ ባለሙያም ሆነ ጉልበት ሰራተኛ ከውጭ ያስገባሉ እንጅ የራሳቸውን አንቱ የተባሉ ባለሙያዎችና ሌሎች ሰራተኞችን አያባርሩም። ሕወሃት የተሻለ ፕሮፓጋንዳ ማዘጋጀት ሳይጠበቅበት አይቀርም።
“No free lunch” ይላሉ አሉ ፈረንጆች። ምንም ነገር በነጻ አታገኝም፤ አንድ ነገር ለማግኘት መስራት አለብህ መድከም አለብህ ለማለት ይመስላል አባባሉ። በኢትዮጵያችንና በወያኔ አገዛዝ ግን ይህን የሚሉት የአስፋልት ዳር ነጋዴዎች ናቸው። ከሚነፍሰው ንፋስ ጋር ከግራ ከቀኝ የሚመጣውን የተዘበራረቀ ሽታ እየማጉ፣ የሙሉ ቀን የፀሐይ ግለቱን ተቋቁመው፣ አቧራ ብርድና ዝናቡን ታግሰው ትነስም ትብዛ የዕለት ጉሮሯቸውን ለመድፈን፣ ቁርስ ያልበሉ ልጆቻቸውን ምሳ ወይም እራት አጉርሰው ለማደር ደፋ ቀና ከማለት በተጨማሪ ያችን የሚውሉባትን የአስፋልት ጥግ ቦታ ለማግኘት ወያኔ መሆን እንደ መስፈርት ሲቀርብላቸው “No free lunch” ቢሉ ችግሩ ያለው ሳይፈልጉ ከተጫነባቸው ሕወሃት እንጅ ከእሳቸው አይደለምና አያስፈርድም። የሚደንቀው ግን ከዚህ ሁሉም በሗላ ወያኔ ሕወሃት ከልክ በላይ የስራ እድል የከፈትኩ፣ የኢትዮጵያዊያንን በተለይም የሴቶችን መብት ያስጠበቅኩ እኔ ነኝ እያለ መዘባረቁ ነው።
ለድሮው ክቡር የነበሩት ገዳማትና መስጊዶች ሳይቀሩ በወያኔ ዘመን ተደፍረዋል።  ሳንፈልግ የወደቀብን ሕወሃት ያልከበደው ኢትዮጵያዊ ወገን የለም። ሕወሃትም በአገዛዙ ያላሸበረው የህብረተሰብ ክፍል ያልቀወጠው አካባቢ ተፈልጎ አይገኝም። ለባለራዕዩ ሬሳ ሽኝት ኮልኮሎ ያቀረባቸው የጎዳና ተዳዳሪዎችና የኔቢጤዎች ሳይቀሩ እንደ ነጋዴ መጋዘን ካርቱን አንዴ በዚያ በኩል ሌላ ጊዜ በዚህ እየተባሉ ይዋከባሉ። እነዚህ ሁሉ ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን ሕወሃት ማስታወስ አይፈልግም። እርዳታ መስጠትም አያስብም። ያቅም ማነስ ነው እንዳንል ደግሞ ሌሎች ወገኖች ለረዷቸው ላጎረሷቸው ሕወሃት ሲያውክ ማስተዋላችን ለምን ይሆን? ይህ እጣ ለቆሸ ሰፈር ገንዳ አራጆችም አልቀረላቸውም። ከሌሎች የአዲስ አበባ ክፍሎች ያገለገሉ እቃዎችንና የሆቴል ትርፍ ምግቦችን የያዙ ገንዳዎችን ከበው የሚያወራርዱት የቆሽ ሰፈር ገንዳ አራጆች ከወያኔ የሰፈር ጥበቃና ከፌደራል ፖሊስ የሚደርስባቸው ወከባ ቀላል አይደለም።
በእርግጥ ከነኝህ ገንዳዎች የሚገኝ ትርፍ ምግብ ለምግብነት የሚውል ሆኖ አልነበርም፤ ግን ምን ይደረግ ሰው የወደቀ ምግብ ይቅርና እራሱን ይበላል።  ሕዝባችን እኮ እራሱን በልቶ በልቶ ጨርሶ በጠኔና በክሳት እየተንጠራወዘ ነው ያለው። ከቁጥር ስላልጎደለ አልተጮኸም እንጅ ሞቷል ተብሎ ሊለቀስለት የሚገባው የማህበረሰባችን ክፍል ጥቂት አይደለም። ይህ ሁሉ በግፍ በወደቀብን ሕወሃት እየተሰፈረልን ያለ መከራ ነው። ግን ለምን? አንዳንዱ የሕወሃት ሰው ከትግራይ በመጣ በነጋታው የውስጥ ሱሪ እንኳ ለምንና እንዴት ማድረግ እንዳለበት ገና በቅጡ ሳያውቅ በዘረኛ ባለስልጣን ወገኑ በተሰጠ ቀጭን ትእዛዝ በሽዎች የሚቆጠር ኩንታል ሲሚንቶ ወይም ስኳር ያለ ወረፋ እንዲወስድ ይፈቀድለትና የፈቃድ ደብዳቤዋን ብቻ ለመርካቶ ነጋዴ በመሸጥ ፋብሪካዎቹን እንኳ ሳያይ ባንድ ቀን ባለ ሚሊዮን ይሆናል። ሌላው ደግሞ ከሊስትሮነት ስራው፣ ከቆሸ ሰፈር ትርፍ ምግብ ለቀማው፣ ከአስፋልት ዳር ልመናና ጎዳና ተዳዳሪነት ሲባረርና ሲዋከብ እናያለን። ለምን ብለን መጠየቅ የለብንም? ከዚህ የባሰ የመብት መደፈርስ አለ እንዴ? ሁላችንም ልናስተውል ይገባናል።
ችግሮች እንዲቆሙ የተመኘንባቸው ወይም የሞከርንባቸው ዘመናት ገና ያኔ ያኔ አልፈዋል። ወያኔ ግን በችግር ላይ ችግር በመከራ ላይ መከራ ደራረበብን እንጅ መፍትሄ አላገኘንም።  “እምብዛም ዝምታ ለበግም አልበጃት ሃምሳ ራሷን ሆና አንድ ነብር ፈጃት” ነው ብሂሉ። እኛ ለመብታችን መከበር እስቃልቆምን ድረስ ሕወሃት በየጊዜው ሌሎች አዳዲስ ምክንያቶችን እየፈጠረ ለማሰር ለማሰደድና ለመግደል አይቦዝንም። በፊት በፊት በ ኦነግ፣ በግንቦት 7፣ በአሸባሪነት፣ በአልቃይዳና በሌሎችም እያመካኘ የስርና ያንገላታ የነበረው ሕወሃት አሁን ደግሞ የግንቦት 7 ሕዝባዊ ሃይል መመስረትን ተከትሎና በዚሁ ሃይል እያመካኘ ወጣቱን እያሰረና እያሰደደ መሆኑ ይሰማል። እና እኛስ እስከ መቼ ነው እንደተገረፍንና እንደተሰደድን የምንቀጥለው? አንተም ከማባረር አልተመለስክ እኔም ሁሌ መባረር መሮጥ ሰለቸኝ የምንለውስ ዛሬ ሊሆን ካልቻለ ለመቼና ለእንዴት ያለ ጊዜ ይቆጠባል?
ህወሃት ከበቂ በላይ የስቃይና የጥፋት ማስጠንቀቂያዎችን ሰጥቶናል። የግድ በግል በራሳችን ለይ ደርሶ ማየት እንሻለን እንዴ? ለዚያውም ባለፉት የሕወሃት ያገዛዝ ዘመናት ችግር ያልዳሰሰው ቤት ካለ መለቴ ነው። ይህን የጥፋት ሃይል አንድ ሆነን ቆመን መመከት ካልቻልን ዝምታን ከመረጥናና ወያኔ ባዘጋጀልን ወጥመድ ተጠልፈን ከገባን ኢትዮጵያ የምትባልን ሀገርም ሆነ የሕዝባችንን ከብር እንደገና ለመመለስ በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። “ለሁሉም ጊዜ አለው” ሀገርንና ሕዝብን ለማዳንም ለኛ ለኢትዮጵያዊያን ረፍዷል ካልተባለ ጊዜው አሁን ነው። አንድ ላይ በመተባበር በውስጥ ሽኩቻ በአመራር ብቃት ማነስ በሕዝብ በመተፋት እና መጠላት የዘመመውን ሕወሃት ገፍተን እንጣለው።

የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ኢቲቪን ጨምሮ የመንግስትአካላትን ለመክሰስ ለፍርድ ቤት ያቀረቡት ጥያቄ


የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ኢቲቪን ጨምሮ የመንግስትአካላትን ለመክሰስ ለፍርድ ቤት ያቀረቡት ጥያቄ የፍርድ ቤቱ ሬጅስትራር የተለያዩ ምክንያቶችን በመፍጠር የክስ ፋይል አልከፍትም ማለቱ ተሰማ፡፡
በፌድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ተኛ ወንጀል ችሎት በሃሰት የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው የህዝበ ሙስሊሙ የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎች በጠበቆቻቸው አማካኝነት በጀሃዳዊ ሃረካት በተሰኘው ፊልም ለተፈፀመባቸው የሥም ማጥፋት ተግባር ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው፡
ሆኖም የቀረበውን ክስ እና ተከሳሽ የሆኑትን የመንግስት መስሪያ ቤቶች የፍርድ ቤቱ ሬጅስትራር ከተመለከተ ቡሃላ ከህግ አግባብ ውጪ በሆነ መልኩ ይህንን ክስ የፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ሊመለከቲት ይገባል በማለት ወደ ፕሬዝዳንቱ ከተወሰደ ቡሃላ ፕሬዝዳንቱም በሌላ ቀን ተመልሰው እንዲመጡ ጠበቆቻቸውን ቀጠሮ ይሰጣሉ፡፡ ቀጠሮውን አክብረው በተባሉበት ቀን ሲቀርቡም ፕሬዝዳነቱ ለግዜው ቢሮ አልገቡም በሚል ምክንያት የፍርድ ቤቱ ሬጅስትራር ቢሮ የክስ ፋይል ሊከፍትላቸው አለመቻሉን የኮሚቴዎቻችን ጠበቃ የሆኑት አለም አቀፉ የህግ ባለሙያ ዶ/ር ያዕቆብ ሃይለማርያም አስታውቀዋል፡፡
የኮሚቴዎቻችን ጠበቆች የቀረበው ክስ የጊዜ ገደቡ አልፎ እንዳይቃጠል በሚል ማቅረብ የሚገባቸውን ማስረጃዎች እና የህግ ሰነዶች አያይዘው ቢያቀርቡም ከተከሳሾቹ መካከል የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንትም በመኖራቸው የተለያዩ ምክንያቶችን በመፍጠር የክስ ፋይሉ እንዳይከፈት መደረጉን ምንጮች አስታውቀዋል፡፡ በክሱ መሰረት የኢትዬጲያ ራዲዬ እና ቴሌቪዥን ድርጅት፣የብሄራዊ ደህንነት እና መረጃ መረብ ኤጀንሲ፣የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እንዲሁም ሌሎች መስሪያ ቤቶች ሊከሰሱ የነበረ ሲሆን ጠበቆቹም ጃሃዳዊ ሃራካት በደንበኞቻቸው ላይ ባደረሰው የሞራል ጉዳት ተከሳሾች የ 8 ሚሊዬን አንድ መቶ ሺህ ብር የሞራከል ካሳ እንዲከፍሉ እንዲደረግላቸው ለፍርድ ቤቱ በክሱ ላይ አስፍረው እንደነበር የኮሚቴዎቻችን ጠበቃ ዶ/ር
ያዕቆብ ሃይለማርያም አስታውቀዋል፡፡
አላህ ፍትህን ያስፍንልን!!!

Tuesday, May 7, 2013

ከእሁድ እስከ እሁድ


(የሳምንቱ አጫጭር ዜናዎች)
state_department


አሜሪካ የሽብር ህጉ አሰጋኝ አለች
በሳምንቱ አጋማሽ በእነ አንዷለም አራጌና እስክንድር ነጋ ላይ የበታች ፍርድ ቤት የወሰነው ውሳኔ መጽናቱን ተከትሎ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተቃውሞ አሰምቷል። ቪኦኤ ድምጻቸውን ያሰማቸው የሚኒስቴሩ ተጠባባቂ ቃል አቀባይ ፓትሪክ ቬንትል “ውሳኔው በጸረ ሽብር ህጉ ላይ ያለንን ስጋት ያጠናክረዋል” ሲሉ ተደምጠዋል።
“በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና በእነ እንዷለም አራጌ ላይ የተላለፈው ፍርድ በመጽናቱ አሜሪካ በጥልቅ ቅር ተሰኝታለች” ያሉት ቃል አቀባዩ ውሳኔው መንግስት የሚተቹትን ሁሉ ለፍርድ እንደሚያቀርብ አመላካች ነው ብለዋል።
ሰዎች በነጻነት የመናገርና የማሰብ መብት እንዳላቸው የጠቆሙት ቃል አቀባዩ ኢትዮጵያ በህገ መንግስቷ ያሰፈረችውን የሰብአዊ መብቶችንና የዲሞክራሲ መብቶችን ማክበር የወደፊቱ ግቧ እንደሆነ አመልክተው “ኢትዮጵያ እነዚህን መሰረታዊ መብቶቻቸውን ስለተጠቀሙ ያሰረቻቸውን በሙሉ እንድትፈታ ደጋግመን እንጠይቃለን” ብለዋል። አሜሪካ በሽብርና ከሽብር ጋር ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ኢህአዴግን በግንባር ቀደም የምታግዝና ዘመናዊ የመረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያ የምታቀርብ አገር መሆኗ የሚታወቅ ነው።
የእስክንድር ነጋ ባለቤት ሰግታለች
ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርበው ከነበሩት መካከል አንዱ የሆነው እስክንድር ነጋን ወደ ዝዋይ ማረሚያ serkalemቤት ወይም ከአዲስ አበባ ውጪ ወደ ሌላ ማረሚያ ቤት ለማዛወር መታሰቡን ባለቤቱ ሰርካለም ስጋቷን እንደገለጸች ሪፖርትር አስታውቋል። ጋዜጣው ዝርዝር ባያቀርብም እስክንድር ወደ ዝዋይ ከተዛወረ ባለቤቱና ልጁ እሱን ለመጠየቅ እንደሚቸገሩና ምን አልባትም ችግሩ አሳሳቢ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። እነ እስክንድር ነጋ ላይ የ18 ዓመት ፍርድ ያጸኑት ዳኛ ዳኜ መላኩ ናቸው።
ዳኜ መላኩ ውሳኔውን ካሳወቁ በኋላ ከፍተኛ የሃዘን ስሜት ችሎቱ ውስጥ ይታይ ነበር። ፍርደኞቹ ወደ እስር ቤት ሲመለሱ ድምጽ አውጥተው ስሜታቸውን የገለጹላቸው እንደነበሩ ሪፖርትር በደፈናው ግለጿል። እስክንድር እጁን ወደ ፈጣሪው በማንሳት “እውነት ተደብቃ አትኖርም” ሲል መናገሩን የተለያዩ ሚዲያዎች ዘግበዋል”፡፡
 የሽብር ህጉ የፕሬስ ነጻነትን አውድሟል ተባለ
ባለፈው አርብ በዓለም ተከብሮ የዋለውን የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን አስመልክቶ መግለጫ ያወጣው ሂውማን ራይትስ ዎች “የኢትዮጵያ የሽብርተኞች ህግ የፕሬስ ነጻነትን አውድሟል” አለ። እስረኞች እንዲፈቱ ለማድረግ እንደሚሰራpress አስታውቋል።
ከመግለጫው በተጨማሪ የድርጅቱ የናይሮቢ ጥናት አቅራቢ ላቲቪያ ቤደር የሽብር ህጉ በረቂቅ ደረጃም ሆነ ህግ ሆኖ በስራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ የመናገር መብትን የሚነፍ መሳሪያ መሆኑን ተናግረዋል። ለቪኦኤ ቃላቸውን የሰጡት ላቲቪያ ድርጅታቸው የምዕራቡን ዓለም የኒዖ ሊብራል ሃሳብ አቀንቃኝ ስለሆነ ነው በተደጋጋሚ ኢህአዴግን የሚቃወመው በሚል ስለሚሰነዘረው ለተጠየቁት “ይህ በማንኛውም መልኩ ርዕዮተ አለማዊ ጉዳይ አይደለም፤ ጥሪያችን ስለ መሰረታዊው የሰብአዊ መብት መከበር ነው። ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የምናደርገው የመብት ጥሪ ነው። በኢትዮጵያ ይበልጥ የሚያሳስበን ጸረ ሽብር የተባለ ሀግ ጸድቆ ጋዜጠኞችን ለማፈን ጥቀቅም ላይ መዋሉ ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
የሂይውማን ራይትስ ዎች አጥኚ ላቲቪያ ቤደር ድርጊቱን ከመቃወም ባለፈ ጫና በመፍጠር የታሰሩት የፖለቲካ አስረኞችና ጋዜጠኞች እንዲፈቱ እንደሚሰሩ ተናግረዋል። ለቪኦኤ በሰጡት ቃል እንዳስታወቁት “አገራቱን በሚረዱ ወዳጅ አገሮችና ለነጻነት የሚቆረቆሩ ተጽዕኖ ፈጥረው እስረኞቹን እንዲያስፈቱ በየጊዜው እንወተውታለን” ብለዋል። በፕሬስ ነጻነት ቀን ይፋ እንደሆነው በኢትዮጵያ 11 ጋዜጠኞች በሽብር ህግ ተከሰዋል። ስድስቱ በሌሉበት ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን፣ አምስቱ ወህኒ ቤት የሚገኙት ናቸው። ከአምስቱ መካከል ሶስቱ ተፈርዶባቸዋል። ሁለቱ ዮሴፍ ጌታቸውና ሰለሞን ከበደ የፍርድ ሂደታቸውን እየጠበቁ ነው።
ኤርትራ ካሰረቻቸው ጋዜጠኞች መካከል የተገደሉ አሉ
የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ካሰሯቸው ከ10 በላይ ጋዜጠኞች መካከል እስር ቤት በሚያሳዝን መልኩ የሞቱ እንዳሉ ታማኝ ምንጮች እንዳረጋገጡለት የሂውማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ምክትል ሃላፊ ተናግረዋል። ሃላፊው ለቪኦኤ የናይሮቢ ዘጋቢ እንደነገሩት ኤርትራ ውስጥ የታሰሩት ጋዜጠኞች ጉዳይ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል።
Dawit
ዳዊት ይስሃቅ
እስረኞቹ ቤተሰቦቻቸውን አያገኙም፣ የት እንዳሉ በውል አይታወቅም፣ በዜግነት ስዊዲን የሆነው ዳዊት ይስሃቅን ጨምሮ ሁሉም እስረኞች በህይወት ስለመኖራቸው ቤተሰቦቻቸው ተስፋ በቆረጡበት ወቅት ሃላፊው ጉዳዩ ለአፍሪቃ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ስለቀረበ ይፈታሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።
በተመሳሳይ ከታህሳስ 2006 ጀምሮ ኢትዮጵያ ያሰረቻቸውን ተስፋ ልደት ኪዳኔና፣ ተስፋ እግዚ የተባሉትን ሁለት የኤርትራ ተወላጆች ጉዳይም ሃላፊው አንስተዋል “ጋዜጠኞቹ በኮሚኒካዶ ታስረዋል” ያሉት ሃላፊው እስረኞቹ በጠበቃ መወከልና በቀይ መስቀል ሊጎበኙ እንደሚገባ አመልክተዋል። ጋዜጠኞቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ኤርትራ ዘልቆ ከገባ በኋላ ነበር። በወቅቱ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከተከፈለና ጦርነቱ ከተጠናቀቀ በኋላ አቶ መለስ ጦሩ የያዘውን ቦታ ለቆ እንዲወጣ ማዘዛቸው አይዘነጋም።
በተዛማጅ ዜና በዓለም አቀፍ ደረጃ በ2012 ብቻ 121 ጋዜጠኞች መገደላቸውን በመግለጽ ለጋዜጠኞች ጥበቃ እንዲደረግ ዩኔስኮ ጥሪውን አቅረቧል። ዩኔስኮ ይህንን ጥሪ ያስተላለፈው የፕሬስ ነጻነት ቀንን አስመልክቶ ነው።
የአቶ አስግደ ገብረስላሴ ሁለተኛ ልጅ ታሰረ
የህወሀትን የበረሀ ትግል ታሪክ የሚዘክረውን ገሀዲ ቊጥር አንድ፣ ሁለት እና ሶስት የሚሉ መጽሀፎችን ከመጻፍ በተጨማሪ በትግራይ ውስጥ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በማጋለጥ የሚታወቁት አቶ አስገደ ገብረስላሴ ሁለተኛ ልጅ ታስሯል።
asgede
አቶ አስገደ ገብረስላሴ
የ28 አመቱ የማነ አስገደ ገብረስላሴ የሶፍት ዌር ኢንጂነረግ ምሩቅ ሲሆን፣ በውቅሮ በመምህርነት ሙያ ተቀጥሮ ነበር። አዲሱን ስራውን ሲጀምር አቶ አስገደ ልጅ መሆኑ በመታወቁ በቅጣት ወደ በረሀ ተመድቦ እንደነበር አባቱ አቶ አስገደ ገልጸዋል።
እናቱ ሻለቃ ግደይ ወ/ሚካኤል ልጃቸውን አያቱ ወደ ሚኖሩበት አዳህላይ ወደምትባል ቀበሌ ለህክምና መውሰዳቸውን ተከትሎ በቀበሌው የሚገኘው ትምህርት ቤት በመቃጠሉ የህወሀት ባለስልጣናት ህዝቡን ሰብስበው “ትምህርት ቤቱን ያቃጠለው አቶ አስገደ የሚባል የአረና ትግራይ ድርጅት አባል ልጅ ነው” በማለት ሊወነጅሉ ሲሞክሩ ህዝቡ “ሀሰት ነው ” በማለት በመቃወሙ ባለስልጣናቱ ሳይሳካላቸው እንደቀረ አቶ አስገደ ገልጸዋል። ስብሰባው ከተበተነና ህዝቡ ወደ ቤቱ ከገባ በኋላ ፖሊሶቹ ልጃቸውን አስረው መውሰዳቸውን ተናግረዋል።
ሌላው በእስር ላይ የሚገኘው የ26 አመቱ አክህፎም አስገደ 06 እየተባለ ከሚጠራው ድብቅ እስር ቤት ወጥቶ ወደ ሌላ እስር ቤት መዛወሩን አቶ አስገደ ገልጸው፣ አለም ባደረገው ጫና ትናንት ለመጀመሪያ ጊዜ ልጃቸውን በአይናቸው ለማየት እንደቻሉ እና ከወር በኋላም ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ አክለዋል።
አቶ አስገደ በትግራይ ክልል ውስጥ በርካታ ቤርሙዳ እየተባለ የሚጠራ እስር ቤት መኖሩን አውስተዋል። “የእነሱ ልጆች በህዝብ አንጡራ ሀብት ይማራሉ፣ የኛ ልጆች ይህን የተበላሸ ኑሮ ችለው በኖሩ በእንዲህ አይነት እስር ቤት ማሰቃየት ከዚህ በላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት የለም ብለዋል። (ዘገባው የኢሳት ነው)

የቃሊቲው ደብዳቤና የርዕዮት እውነቶች (በስለሺ ሀጎስ)


http://www.zehabesha.com/amharic/wp-content/uploads/2013/04/reyot-alemu.jpg

ጀግናዋ ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ
ሚያዝያ 23 2005 ዓ.ም ሪፖርተር ጋዜጣ በቅጽ 18 ቁጥር 44/1356 ዕትሙ “በህግ ታራሚ ርዕዮት ዓለሙ ላይ የደረሰ አንዳችም አይነት ችግር የለም!” በሚል ርዕስ ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት አስተዳደር የተላከ ደብዳቤ አስነብቧል፡፡ ደብዳቤው በቅጥፈትና በክህደት የተሞላ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ባልተነሳ ጥያቄና ባልተባለ ነገር ላይ በማተት የተነሳበትን ሀቀኛ ጥያቄ አደናብሮ ለማለፍ ከአንድ ህገ መንግስታዊ ተቋም የማይጠበቅ ጥረት አድርጓል፡፡
ይህ የሆነውም ርዕዮት ራሷን በማትከላከልበት ሁኔታ ውስጥ መሆኗን እንደ መልካም አጋጣሚ በማየት ይመስላል፡፡ በመሆኑም በደብዳቤው ላይ የሰፈሩትን አብዛኞቹን ጉዳዮች በቅርብ ስለማውቃቸው የርዕዮትን እውነቶች የማስረዳት ሞራላዊ ኃላፊነት እንዳለብኝ በማመኔ ይህን ጽሑፍ ለማዘጋጀት ተገድጃለሁ፡፡
በደብዳቤው ከታጨቁ ቅጥፈቶችና ማወናበዶች መሐከል ጸሐፊውን ጠልፈው የሚጥሉ እውነቶች ተሸሽገው ቀርበዋል፡፡ ከነዚህም መሐከል አንደኛው ርዕዮት ለብቻዋ እንድትታሰርና በጠያቂዎቿ እንዳትጎበኝ ለማድረግ ማረሚያ ቤቱ እንደተዘጋጀ ማረጋገጡ ነው፡፡ በደብዳቤው መጨረሻ ላይ፣
‹‹በማረሚያ ቤት አብረዋት ከሚኖሩ ታራሚዎች ለመረዳት እንደቻልነው ርዕዮት ያለምንም ጥረትና ልፋት ዝናን ለማግኘት በመሻቷ ከታራሚዎችና ከጥበቃ አባሎች ጋር በየጊዜው ትጋጫለች፡፡ ጤናማ የሆነ ግንኙነት የላትም፡፡ በተለያየ ጊዜ በታራሚዋ ላይ የዲሲፒሊን ግድፈት በመታየቱም ማረሚያ ቤቱ ጥፋቱን በማጣራት ላይ ይገኛል፡፡ ጥፋተኛ ሆና ከተገኘችም በፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የሕግ ታራሚዎች መተዳደሪያ ደንብ ቁጥር 138/1999 መሠረት ተገቢውን የዲሲፒሊን እርምጃ ተቋሙ እንደሚወስድ ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡››
የሚል ሀሳብ ሰፍሮ ይገኛል፡፡
በጽሑፉ ላይ እንደሚታየው ርዕዮት የዲሲፒሊን ግድፈት ማሳየቷን ማረሚያ ቤቱ ደምድሟል፡፡ ከዚህም በላይ ከጥበቃ አባሎችና ከታራሚዎች ጋር እየተጋጨች የዲሲፒሊን ግድፈቱን የምትፈጽመው ለምን እንደሆነ ሲገልጽ “ያለምንም ጥረትና ልፋት ዝናን ለማግኘት በመሻቷ ከታራሚዎችና ከጥበቃ አባሎች ጋር በየጊዜው ትጋጫለች፡፡ ጤናማ የሆነ ግንኙነት የላትም፡፡” በማለት በልቧ ምን አስባ ድርጊቱን እንደምትፈጽም ሁሉ መቶ በመቶ እርግጠኛ ሆኖ ነግሮናል፡፡
ታዲያ ማረሚያ ቤቱ የሚያጣራው ምንድን ነው? ጥፋተኝነቷን ከነ መንስዔው እርግጠኛ ሆኖ እየነገረን፤ መልሶ ደግሞ ጥፋተኛ ሆና ከተገኘች እርምጃ እወስዳለሁ ማለቱ አልሞ ለመተኮስ ሳይሆን፣ የሚፈልገው ላይ ተኩሶ ዒላማ ለማክበብ መዘጋጀቱን ያሳብቃል፡፡
አርሶ መራብና ተኩሶ መሳት፣
እያደር ይፈጃል እንደእግር እሳት! ሆነበት እንጂ ነገሩ፡፡
ማረሚያ ቤቱ ከሳሽም፤ አጣሪም፤ ፈራጅም፤ እርምጃ ወሳጅም ሆኖ መቅረቡ ደግሞ “በህግ ሽፋን ርዕዮት ብቻዋን እንድትታሰርና ጠያቂዎቿ እንዳይጎበኟት ለማድረግ እየሰራ ነው” የሚለው ስጋት እውነት መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ሲፒጄም ቢሆን ያለው ይህንኑ ነው፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በደብዳቤው ላይ፤
“በአንዳንድ ሚዲያዎች የተገለጸው ሌላው ጉዳይ ለሁለት ወራት በአንድ ክፍል ውስጥ ለብቻዋ እንደታሰረች የሚገልጸው ዘገባ ነው፡፡ ይህ ዘገባ ከርዕዮት ጋር የሚኖሩ የህግ ታራሚዎችን ከመናቅ ወይም እንደሰው ካለመቁጠር የመነጨ ይመስለናል፡፡ ሀሳቡ የርዕዮት ከሆነም ለራሷ ካላት የተጋነነ ግምት ወይም ማንነት የመነጨ ሊሆን ይችላል፡፡”
የሚል ውንጀላ ቀርቧል፡፡
እግዜር ያሳያችሁ! “ሊሆን ይችላል” ነው ያለው፡፡ ግምት ብቻ ተይዞ “ለራሷ ካላት የተጋነነ ግምት… እንደሰው ካለመቁጠር የመነጨ” የመሳሰሉ ሥነልቡናዊ ትንታኔዎች ውስጥ እንዴት ይገባል? ኧረ ጎበዝ አታሳፍሩን!
እርግጥ ነው ርዕዮት ለብቻዋ እንድትታሰር ሊያደርጋት በሚችል አንቀጽ (በፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የሕግ ታራሚዎች መተዳደሪያ ደንብ ቁጥር 138/1999) ክስ ተመስርቶባት ውሳኔውን (ውሳኔው ተግባራዊ የሚሆንበትን ዕለት) በመጠባበቅ ላይ ናት እንጂ በአሁኑ ሰዓት ለብቻዋ አልታሰረችም፡፡
ለዚህ ጉዳይ ሽፋን ከሰጡ በርካታ የሀገር ውስጥ የህትመት ውጤቶች መሐከል አንዱ (ሪፖርተር ጋዜጣ ቅጽ 18 ቁጥር 42/1352) ‹‹ርዕዮት ለብቻዋ ታስራ ትገኛለች›› ብሎ ሲፒጄ መናገሩን ጽፏል፡፡ ማረሚያ ቤቱን ለግምታዊ ስህተት የዳረገውም ይሄው ዘገባ ነው፡፡ ነገር ግን እንኳን አንድ ትልቅ ተቋም ቀርቶ፤ የዘገባው ስህተት ከምን የመነጨ እንደሆነ ማረጋገጥ የሚፈልግ ሰው የሲፒጄን ኦርጂናል መግለጫ ማንበብ፤ አሊያም ጋዜጣውን መጠየቅ ብቻ ይበቃዋል፡፡
እኔ ያነበብኩትና ለፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን በአድራሻው የተላከት የሲፒጄ ደብዳቤ “ርዕዮት ለብቻዋ ታስራለች” አይልም፡፡ በጉዳዩ ላይ መረጃ የሰጡ የርዕዮት ቤተሰቦችም በአንድም ሚዲያ ላይ ይህን አላሉም፡፡ ታዲያ ሪፖርተር ከየት አመጣው? የሚለውን ጥያቄም ከጋዜጣው በስተቀር ርዕዮትም ሆነች ማንም ሰው ሊመልሰው አይችልም፡፡
ከዚህ ሌላ ርዕዮት ማረሚያ ቤቱ እንዳለው አይነት ሰው አለመሆኗን ዓለም የሚያውቀው እውነት በመሆኑ ይህን ለማስረዳት አንዲትም ቃል ሳላባክን ወደ ቀጣዩ ርዕሰ ጉዳይ ልለፍ፡፡
ህክምናዋን በተመለከተም ምንም አይነት ችግር እንዳላጋጠማት በደብዳቤው ላይ ተገልጿል፡፡ “ማረሚያ ቤት በቆየችባቸው ጊዜያት በተለያዩ ቀናት ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተልካ ሕክምና ማግኘቷን ከግል ማህደሯ ማረጋገጥ ይቻላል” በማለትም እማኝ ይጠቅሳል፡፡
በተለያዩ ቀናት፣ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል መሄዷ እውነት ነው፡፡ ነገር ግን በጡቷ ላይ ሕመም እንደሚሰማት ተናግራ ሪፈር እንዲጻፍላት ብትጠይቅም፣ ከመንፈስ ጭንቀት ውጪ ምንም በሽታ እንደሌለባትና የእጅ ሥራ እንድትሰራ፤ ጥልፍ እንድትጠልፍ ስትመከር መሰንበቷ፤ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሄዳ ህክምናዋን ለመከታተል የቻለችውም ከብዙ አቤቱታ በኋላ ኦማር የተባለ የአፍሪካ ጋዜጠኞች ፌዴሬሽን ተወካይ ከአንድ ኢትዮጵያዊ ጋር ቃሊቲ ድረስ ሄደው በጎበኟት ወቅት በእነሱ በኩል በቀረበ አቤቱታ በማረሚያ ቤቱ ዋና አስተዳዳሪ ትዕዛዝ መሆኑ ቢታከልበት የተሻለ እውነት ይሆን ነበር፡፡
ሕክምናዋን በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል መከታተል ከጀመረች ወዲህም ብዙውን ጊዜ በቀጠሮዋ መሠረት ተገኝታ መታከም አለመቻሏ፤ ህመሟ ጊዜ የማይሰጥ በመሆኑ የተለየ ህመም ካጋጠማት ቀጠሮዋን ሳትጠብቅ ወደ ሆስፒታል እንድትመጣ በሀኪሞቹ ቢታዘዝም፤ ከጥር 10 ቀን ጀምሮ ክፍተኛ ደም ከጡቷ እየፈሰሰ እስከ የካቲት 07 ድረስ ህክምና ሳታገኝ በስቃይ መክረሟ፤ ከዚያ በኋላም ሀኪሟ በአስቸኳይ የናሙና ምርመራ ተደርጎ የዕጢው ደረጃ ከታወቀ በኋላ መለስተኛ ቀዶ ጥገና ማድረግ እንደሚኖርባት በመግለጽ ለየካቲት 13 ቀጠሮ ቢሰጥም መኪና የለም በሚል ሰንካላ ሰበብ እስከ መጋቢት 2 ድረስ፣ ከነስቃይዋ እንድትቆይ መደረጓና ሌሎች ታራሚዎች ህክምናቸውን ሲከታተሉ የቀጠሯቸው ቀን ከፍርድቤትና ከሌሎች ቀጠሮዎች ጋር እንዳይጋጭ የህክምና ቀጠሯቸውን እዚያው ሆስፒታል እያሉ እንዲያውቁት የሚደረግበት አሰራር የተለመደ ሆኖ እያለ ርዕዮት ከመጋቢት 2 ወዲህ መቼ ምን አይነት የሀኪም ቀጠሮ እንዳላት ለማወቅ ብትጠይቅም፣ በግልጽ ‹‹ለአንቺ አይነገርሽም›› መባሏ ተገልጾ ቢሆን ኖሮ ሙሉ እውነት ይሆን ነበር፡፡
ፍጹም እውነት እንዲሆን ደግሞ…
እንጂማ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል መሄዷ ብቻ ሳይሆን መለስተኛ ቀዶ ጥገና አድርጋ ከጡቷ ላይ ዕጢ ማስወጣቷም ጭምር ከወራት በፊት ሁሉም የሰማውና ያረጀ ዜና ነው፡፡
የትምህርቷን ጉዳይ በተመለከተ ከመነሻው ጀምሮ እስከ ክልከላው ድረስ እኔ ራሴ ስከታተለው የነበረ በመሆኑ፣ ማረሚያ ቤቱ ላከ በተባለው ደብዳቤ ላይ ያነበብኩት ነገር ክፉኛ አስደንግጦኛል፡፡ ጸሐፊው ትክክለኛ መረጃ ሳያገኝ በየዋህነት ተሳስቶ ካልሆነ በቀር እንዲህ አይነት አይን ያወጣ ቅጥፈት በአደባባይ እንዲነበብ ለመጻፍ በገዛ ህሊናው ላይ የሰለጠነ ልዕለ ኃያል ሰው መሆን ይጠይቃል፡፡
የሆነው ሆኖ “ትምህርቷን እንድትከታተል የሴቶች ቀጠሮና ማረፊያ ቤት ተገቢውን ድጋፍ እያደረገላት ይገኛል፡፡” ተብሎ የተገለጸው ፍጹም ሀሰት ሲሆን እውነቱ የሚከተለው ነው፡፡
የማረሚያ ቤቱን ይሁንታ ጠይቃ ካገኘች በኋላ ህዳር 29 2012 እ.ኤ.አ ያስመዘገብኳት እኔው ራሴ ነበርኩ፡፡ መመዝገቧን ካሳወቀች በኋላም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የማረሚያ ቤቱ ባልደረቦች ት/ቤቱ ድረስ በመሄድ እንዳረጋገጡ የሰማሁት ከራሳቸው አንደበት ነው፡፡ በየካቲት ወር መጨረሻ ትምህርቱ ሲጀመር የመማሪያ መጻህፍቶቿን ይዤ በሄድኩበት ጊዜ ግን የተሰጠኝ “እሷ እንድትማር አልተፈቀደላትም” የሚል ምላሽ ነው፡፡ ጉዳዩ እስካሁን ድረስ እልባት ባለማግኘቱ ትምህርቷን መጀመር አልቻለችም፡፡ የመማሪያ መጻሕፍቱም እስከ ዛሬ ድረስ በእጄ ይገኛሉ፡፡
በመጨረሻም መሽቶ በነጋ ቁጥር በሁሉም መስክ የባሰ ነገር መጋፈጥ ልማዳችን ነውና ለማረሚያ ቤቱ ደብዳቤ ይህን ያህል ጊዜና ጉልበት ከፈጀን በቂ ነው፡፡ ነገ ለሚመጣው የባሰ ነገር ጊዜና ጉልበት መቆጠብ፣
ያምናን ቀን አማሁት ላፌ ለከት የለው፤
የዘንድሮው መጣ እጅ እግር የሌለው፡፡
የሚል ቁዘማ ውስጥ ከመዘፈቅ ሳያድነን አይቀርም፡፡
ቺርስ!!

 http://www.zehabesha.com/

Sunday, May 5, 2013

ኦባንግ የኢህአዴግ ደጋፊ ስደተኞችን አስጠነቀቁ



“በአስመሳይ ስደተኞች ላይ በቂ መረጃ አለ”

obang


“ክፉን በክፉ መመከት ባያስደስትም ወቅቱ ያስገድደናል” ሲሉ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር ኦባንግ ሜቶ በተለይ ለጎልጉል ተናገሩ። አገዛዙን ሸሽተው በተለያዩ አገራት ከለላ አግኝተው በስደት የሚኖሩም ሆኑ ጉዳያቸው እየታየ ያሉ ወገኖች አካሄዳቸውን እንዲያስተካክሉ አስጠንቅቀዋል።
የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናትና ህግ አውጪዎች፣ የጀርመን የኢሚግሬሽን ሃላፊዎችና ከፍተኛ የፖለቲካ ሰዎች፣ ከኖርዌይ የኢሚግሬሽን ጉዳይ ሃላፊዎችና ተዛማጅ ሃላፊነት ካላቸው የህግ ክፍሎች፣ በካናዳ በተለያዩ ደረጃ ካሉ ባለስልጣናትና ወትዋቾች (አክቲቪስቶች)፣ በስዊድን አንዲሁም በእንግሊዝ በተመሳሳይ ግንኙነት ፈጥረው እየሰሩ መሆኑንን ያመለከቱት አቶ ኦባንግ “አገራቱ የስደት ፈቃድ ካገኙ በኋላ ለስደት ዳረገን ከሚሉት መንግሥት ጋር በቅርብ እየሰሩ ስላሉ አስመሳይ ስደተኞች አስገራሚ መረጃዎች መሰብሰባቸውን አውቃለሁ” ብለዋል።
አቶ መለስ በሞቱ በወር ጊዜ ውስጥ ብቻ በካናዳ ቫንኮቨር 27 አንድ አይነት ቋንቋ ብቻ የሚናገሩ ወጣቶች ጥገኛነት መጠየቃቸውን ጉዳዩን በጥብቅ እየመረመሩት ካሉ ክፍሎች ማረጋገጣቸውንና የምርመራውን ውጤት በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ያመለከቱት አቶ ኦባንግ፣ “ወጣቶቹ ካናዳ የገቡት ለእያንዳንዳቸው 75 ሺህ ዶላር በማውጣት ነው። ይህን ገንዘብ ማን ሰጣቸው? እንዴት አገኙት? እንዴት ከአንድ አካባቢ (ክልል) ብቻ ሊሆኑ ቻሉ? የሚሉት ጉዳዮች ምርመራውን በያዙት ወገኖች ላይ ግራሞት የፈጠረ ትልቅ ጉዳይ ነው” በማለት የጉዳዩን አሳሳቢነት ከገንዘብ ማሸሽ ጋር በማያያዝ አመላክተዋል። ለምሳሌ አንድ ጉዳይ አነሱ እንጂ በመላው ካናዳ በተመሳሳይ የምርመራ ስራ እየተሰራ መሆኑንን ተናግረዋል።

የካናዳው አንድ ማሳያ ሲሆን በአሜሪካ ግዙፍ ቪላዎችን እየገዙ ያሉት ክፍሎች ጉዳይ ከገንዘብ ማሸሽ ጋር ተያይዞ እየተመረመረ እንደሆነ አቶ ኦባንግ አስረድተዋል። ጥገኝነት ካገኙ በኋላ “ሊገለን ሲል አመለጥነው” ያሉትን ኢህአዴግን የሚደግፉ ክፍሎች ላይም ለሚመለከታቸው ባለስልጣናትና ተቋማት ከሚቀርበው መረጃ በተጨማሪ ከፍትህ ወዳድ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ጋር ድርጅታቸው በጥምረት እየሰራ መሆኑን አቶ ኦባንግ አልሸሸጉም፡፡
በጀርመን ኑረንበርግ በኢሚግሬሽን ጉዳዮች ዙሪያ የሚሰሩ ባለስልጣናት በተመሳሳይ የምርመራ ስራ እያከናወኑ እንደሆነ ያመለከቱት አቶ ኦባንግ፣ በግል በጉዳዩ ዙሪያ መነጋገራቸውን አስታውቀዋል። የጥገኝነት ፈቃድ ካገኙ በኋላ ዲያስፖራውን በመከታተልና አገር ቤት የሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ለችግር እንዲዳረጉ የሚያደርጉትን ክፍሎች ማንነት ነቅሰው እንደሚያውቋቸው ባለሥልጣናቱ በግንኙነታቸው ወቅት እንዳረጋገጡላቸው አመልክተዋል።
“ኢህአዴግ ለጊዜው የጠመንጃ ሃይል አለው። የገንዘብ አቅም አለው። ወዳጆችም አሉት። እኛ ደግሞ በየአቅጣጫው ፍትህ ወዳድ አጋሮች አሉን። ከነሱ ጋር እየሰራን ነው” በማለት አስረግጠው የተናገሩት ኦባንግ በማንኛውም መስፈርት ስደት ላይ ያሉ ወገኖችን መከታተልና መሰለል ተቀባይነት የለውም ብለዋል።
“አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ኖርዌይ፣ እንግሊዝ፣ ስዊድንና ጀርመን አገር ባለስልጣናቱ ከበቂ በላይ መረጃ አግኝተዋል። እኛም እየሰራንበት ያለ ተከታታይ ስራ አለ። በየአቅጣጫው የሚደረገው ትግል በቅርቡ ፍሬው መታየት ይጀምራል” የሚሉት ኦባንግ ርምጃው መወሰድ ሲጀምር ከስድስት እስከ አስራ ሁለት ዓመት እስር እንደሚያስከትል፣ ከዚያም የከፋ አደጋ እንዳለው ጠቁመዋል።
በትምህርትና በተለያዩ ስልጠናዎች ወደ ተለያዩ ዓለማት የሚሰማሩ የአገዛዙ አገልጋዮችም ቢሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው የሚያሳስቡት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር “አገዛዙ መድቧቸው በየኤምባሲው ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች፣ የስለላ ሰዎች፣ ከፍተኛ ባለስልጣናት ምስላቸውንና ማንነታቸውን ባደባባይ አይገልጹም። በኤምባሲዎች ድረ ገጽ ላይ እንኳ ስለማንነታቸው በቂ መረጃ ለመስጠት ድፍረት የላቸውም። የስርዓቱ ባህሪና የወንጀለኛነቱ መጠን ራሳቸውን እንዲገልጹ አይፈቅድላቸውም” በማለት በተራ መደለያና ጥቅማ ጥቅም ደረታቸውን እየሰጡ ያሉ ወገኖች አካሄዳቸውን በመመርመርና የሚያስከብራቸውን ተግባር እንዲፈጽሙ ጥሪ አስተላልፈዋል።
“ምክር በመለገስ ሰፊ ጊዜ የወሰድነው ክፉን በክፉ የመመለስ እምነት፣ ክፉ እንድናደርግ የሚገፋን  ድርጅታዊ አቋም ስለሌለንና የሚጠሉንን ጭምር ነጻ የሚያወጣ ግዙፍ ራዕይ ስላለን ነው” የሚል ጥልቅ አስተያየት የሰነዘሩት አቶ ኦባንግ፣ በአገራቸው መኖር ያልቻሉ ወገኖች ተሰደውም ሰላም ሲያጡ መመልከት ግን የማይቻልበት ደረጃ መድረሱን አመልክተዋል። ከዚህም በተጨማሪ እሳቸው በግል፣ ድርጅታቸው በመርህ የሚታገሉለት የሰዎች መብት መከበር ብሩህ አጀንዳ በዝምታ እንዲቀመጡ እንደማይፈቅድላቸው ተናግረዋል።
ከኖርዌይ የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት ጋር በተገናኙባቸው ወቅቶች ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ በግልጽ እንደነገሯቸው ያመለከቱት ኦባንግ ሜቶ፣ አሁን ስሙንና ዝርዝር ጉዳዩን ለመናገር ፈቃደኛ ካልሆኑት ክፍል ጋር በጋራ እየሰሩ መሆኑንን ጠቁመዋል። አኢጋን ያቋቋመው የግልጽነትና የተጠያቂነት ግብረ ሃይል አንዱና ትልቁ ስራው እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን መርምሮና አጣርቶ ለሚመለከታቸው በማቅረብ ፍትህን መጠየቅ መሆኑንን ያመለከቱት አቶ ኦባንግ “ዝርዝሩን መናገር ቢከብድም ብዙ ስራ እየሰራንበት ያለው የስደተኞች ጉዳይ የሌሎችንም ተሳትፎና ትብብር ይጠይቃል” ብለዋል።
“በስሜት መታገል አያዋጣም” የሚል የትግል ማስተካከያ ሃሳብ ፈንጠቅ ያደረጉት አቶ ኦባንግ የስደት ማመልከቻቸው ተቀባይነት አግኝቶ የመኖሪያ ፈቃድ ካገኙ በኋላ አገር ቤት በመመላለስ፣ ህግ በመተላለፍ ለአገዛዙ የሚሰሩ በሙሉ “ብልጥና አዋቂ ነን፣ ባለጊዜዎች ነን” በሚል አስተሳሰብ የሚንቀሰቀሱ አንደማያዋጣቸው ሲያሳስቡ “ለእንደዚህ አይነቶች ሁሉም ዓይነት መንገድ አይሰራላቸውም። ግለሰቦችንና ባለስልጣናትን ሳይሆን አሰራርን በማጭበርበር ይጠየቃሉ። አገራቱ እንደ ኢትዮጵያ ሳይሆን ስራ ላይ የሚውል ህግ አላቸውና ይተገብሩባቸዋል። አሰራራቸው ሲጭበረበር ዝም የማይሉት ለማንም ሲሉ ሳይሆን ለራሳቸው ሲሉ ነው። አሰራር / ሲስተም/ ሲበረዝ የሚያስከትለውን አደጋ ስለሚረዱ የሚታገሱ ካልሆነ በቀር በዝምታ አያልፉም። በኖርዌይም ሊሆን የታሰበው ይህ ነው። አሁንም ዝርዝር መረጃ ለመስጠት እቸገራለሁ” በማለት ነው። አቶ መለስ ህይወታቸው ባለፈ ወቅት በስደት ካምፕ የሚኖሩ ጭምር ለቅሶ መቀመጣቸው በኖርዌይ ሚዲያዎች አስገራሚ ተብሎ መዘገቡ፣ በህዝቡና በፖለቲከኞች ዘንድ መነጋገሪያ አጀንዳ እንደነበር አይዘነጋም።
በርካታ አሳዛኝና ህሊናን የሚፈታተኑ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነ ያወሱት ኦባንግ ሜቶ፣ ህጻናትን በጉዲፈቻ ስም በመቸብቸብ፣ ሴት እህቶቻችንን አረብ አገራት ያለ ዋስትና በመላክ ከፍተኛ ገበያ እየሰሩ ያሉት የህወሃት ሰዎች እንደሆኑ በበርካታ ማስረጃዎች መረጋገጡን ያስታውሳሉ። አያይዘውም አገራቸውን ለቀው ለስደት የሚወጡትን ወደ ኬኒያ፣ ታንዛኒያና ደቡብ አፍሪካ ብሎም በጅቡቲና በሶማሌ በኩል ገንዘብ እያስከፈሉ የሚያሻግሩት አሁንም እነሱ ናቸው ሲሉ አስቀድመው ስለ ጠየቁት ትብብር ማሳሰቢያቸውን ያጠናክራሉ።
“በማስተዋል እንስራ” የሚሉት ኦባንግ በየአቅጣጫው መረጃ ላይ የተኙና፣ በምን አገባኝ ስሜት ዝምታን የመረጡ ወገኖች ያላቸውን መረጃ በመስጠት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ከተለያዩ አካላት ጋር እየሰራ ያለውን ስራ እንዲያግዙ አሳስበዋል። ይህንን ማድረግ አቶ ኦባንግንና እርሳቸው የሚመሩትን ድርጅት መርዳት ሳይሆን ራስንና አገርን መርዳት እንደሆነም አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።aba
ከተቋቋመ 135ዓመታትን ያስቆጠረው የአሜሪካ ሕግ ባለሙያዎች ማኅበር (ABA) እየተባለ በሚጠራውና 400 ሺህ በላይ አባላት ባሉት የህግ ባለሙያዎች ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ከሁለት ሳምንት በፊት ንግግር እንዲያደርጉ በተጋበዙበት ወቅት አቶ ኦባንግ ሜቶ በርካታ ጉዳዮችን በማንሳት ድጋፍ ጠይቀው አዎንታዊ ምላሽ እንዳገኙ ጠቅሰዋል፡፡ በርካታ የህግ ባለሙያዎች በተገኙበት ስብሰባ ላይ በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ፣ ኢህአዴግ ህግን ከለላ በማድረግ በዜጎች ላይ የሚፈጽመውን ወንጀል፣ ለእንደዚህ ዓይነት ተግባሩ ማስፈጸሚያም የጸረ ሽብርተኝነትን፣ የመያዶችን፣ ወዘተ ህጎች በማውጣት ዜጎችን ለእስር፣ ለስደት፣ ለስቃይ መዳረጉን፣ የፍትህ አካላቱን ህግን በሚያከብሩና ፍትህ በሚያስፈጽሙ ሳይሆን ራሱ በመሠረተው ተቋም እያመረተ ለፖለቲካ መጠቀሚያ እያደረገ መሆኑን፣ ከዚህ አልፎ ደግሞ በስደተኛነት ስም ደጋፊዎቹን ወደ ውጪ በመላክ በሃሰት የኢህአዴግ ሰለባ በማስመሰል በየምዕራቡ ዓለም የመኖሪያ ፈቃድ እንዲያገኙ በማስደረግ መልሶ ስደተኛውን እዲሰልሉና ለሥርዓቱ እንዲሰሩ እያደረገ መሆኑን፣ ወዘተ በስፋት አብራርተዋል፡፡ የባለሙያዎቹ ማኅበር ጉዳዩን በጥልቀት እንደሚያየውና ያለውን ከፍተኛ የሰው ኃይል በመጠቀም ከአኢጋን ጋር እንደሚሰራ ከሌሎች ማኀበራት ጋር በመሆንም በተለይ በምዕራቡ ዓለም የተሰገሰጉትን አስመሳይ ስደተኞች ወደ ፍትህ የማምጣቱ ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን ለአቶ ኦባንግና ለድርጅታቸው አረጋግጠዋል፡፡

Saturday, May 4, 2013

አንድነት ፓርቲ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በአፋጣኝ እንዲፈቱ ጠየቀ


ሚያዚያ ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ፓርቲው ባወጣው መግለጫ ሚያዚያ 24 ቀን 2005 ዓ.ም ይግባኝ ሰሚ ችሎት በእነአንዷለም አራጌ ፍርድ ላይ የሰጠው ውሳኔ ፍ/ቤቶች የገዥው ፓርቲ ጉዳይ አስፈፃሚዎች እንጅ ገለልተኛ ተቋማት አለመሆናቸውን ያሳየ ነው ብሎአል።
ፓርቲው  “ሽብርተኝነት በናይጀሪያ፣ በአፍጋኒስታን እና በፓኪስታን በእየለቱ የምንሰማው እንጅ የኢትዮጵያ ችግር አይደለም በማለት ገልጾ የከፍተኛው ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ወጣቱን ፖለቲከኛና ከፍተኛ አመራር አንዱአለም አራጌንና ናትናኤል መኮንን ን ሽብርተኞች እንደሆኑና በሰላማዊ ትግል ሽፋን ሽብርተኝነትን እንሚያራምዱ አድርጎ ያቀረበው ሀተታ የፓርቲውን  ጠንካራ መዋቅር ያላገናዘበ፣ የፓርቲውን መልካም ስም የሚያጎድፍ ነው ብሎአል።  እነ አንዷለምም ሰላማዊ ታጋዮች እንጅ ሽብርተኞች አለመሆናቸውንም ጠቅሷል።
የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ የኢህአዴግ የዕድሜ ማራዘሚያና መጠቀሚያ ከመሆን በዘለለ ፋይዳ የሌለው መሆኑን የገለጸው አንድነት፣ በሽብርተኝነት ስም ዜጎችን ማሰር እንዲቆም  እና የፖለቲካና የህሊና እስረኞ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቋል።
በሌላ ዜና ደግሞ የግንቦት 7 አባል በመሆን የፈንጂ ስልጠና ሰጥተዋል በተባሉት ሻለቃ ማሞ ለማና አቶ አበበ ወንድማገኝ ላይ የቀረበው ክስ ከትላንት በስቲያ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት መሰማቱን አዲስ አድማስ ጋዜጣ ዘግቧል። በእለቱ በተነበበው የክስ መዝገብ ላይ አቶ አበበ ወንድማገኝ፤ በእንግሊዝ ሃገር ከሚገኙት ሻለቃ ማሞ ለማ ጋር በተደጋጋሚ በዱባይና ለንደን በመገኘት የፈንጂ ጥቃት ለማድረስ የሚያስችል ስልጠና በኤርትራ መውሰዳቸውን ያትታል።
አቶ አበበ ግለሰቦችን በመመልመል የትጥቅ ትግል ለማድረግ በማሰልጠን ለሽብር ተግባር ማነሳሳታቸውን የአቃቢ ህግ ክስ አመልክቶ፣  ጥር 15 ቀን 2005 ዓ.ም ቦሌ ሰሚት አካባቢ መኪና ውስጥ 10 “ C4” የተሰኙ ፈንጂዎችንና ማቀጣጠያ ገመዶችን ይዘው ተገኝተዋል ብሏል፡፡ የተከሳሽ ጠበቃ ባቀረቡት መቃወሚያ፤ የአቃቤ ህግ ክስ በየትኛው አዋጅ እንደቀረበ ክሱ እንደማያመለክት ጠቁመው፤ ደንበኛቸው የፈንጂ ስልጠና መስጠቱን እንዳልካደ በመግለፅ፤ አቃቤ ህግ ያቀረበው የክስ አንቀፅ እንዲያሻሽል ፍ/ቤቱን ጠይቀዋል፡፡
አቃቤ ህግ በበኩሉ፤ የተከሳሽ ድርጊት በሰው ህይወት፣ በአካልና በንብረት ላይ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል እንደነበር የሚያካትት ክስ እንዳቀረበ ገልጿል፡፡ “ተከሳሹ ስልጠና ብቻ ነው የሰጠው” የሚባለው ጉዳይ በማስረጃ የምናረጋግጠው ነው በማለት አቃቤ ህግ አክሎ ገልፀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ብይን ለመስጠት ለፊታችን ሰኞ ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ጋዜጣው ዘግቧል።

ESAT Daily News Amsterdam May 04, 2013 Ethiopia ed