Tuesday, March 5, 2013

ኢህአዴግ አሣ አስጋሪዎችን ጨፈጨፈ


የአሜሪካዊው አስከሬንና አሟሟት ሊመረመር ነው

fisherman


የመከላከያ ሰራዊት በድንገተኛ ከበባ ከገደላቸው ንጹሃን ዜጎች መካከል የአሜሪካ ዜግነት ያላቸውን የአቶ ኡሞት ኡዶል ግድያ አስመልክቶ የአሜሪካ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ ምርመራ እንደሚያደርግ አስታውቋል። ግድያው ከተፈጸመ በኋላ የሰራዊቱ አባላት አስከሬን አደባባይ በማውጣት ለህዝብ እያሳዩ ደስታቸውን ሲገልጹ የተመለከቱ የጋምቤላ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ክፉኛ መበሳጨታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በጋምቤላ የደረቁን ወቅት ወይም በጋውን በወንዞች ዳር ውሃ ተንተርሶ መኖር የተለመደ ነው። ከቋሚ የመኖሪያ ቀዬ ወደ ወንዝ ዳርቻ በመሄድ አድኖ መመገብና አሳ አስግሮ ዕለትን ማሳለፍ የባህል ያህል ነው። በአገሬው ልምድ መሰረት ከቋሚ መኖሪያቸው ወደ ውሃ ዳር የሚሄዱት ወንዶች ሲሆኑ ጉዞውም የሚደረገው በቡድን ነው።
በዚሁ መሰረት በጋምቤላ ክልል የጎክዲፓች ነዋሪዎች የደረቁን ወቅት ለማሳለፍ በጊሎ ወንዝ ዳርቻ ወደምትገኘው አብሌን ያመራሉ። በቡድን ወደ አብሌን ያመሩት ሰዎች ከወንዝ አሳ በማስገርና ያገኙትን በማደን ቀን እየገፉ ሳለ የካቲት 21፤2005ዓም (28/2/13) በድንገት የመከላከያ ሰራዊት ከበባቸው። ተኩስ ተከፈተ። ለጊዜው ስድስት ሰዎች ህይወታቸው ማለፉንና የቆሰሉ እንዳሉ ለተጎጂዎቹ ቅርበት ያላቸው ያስረዳሉ።
ሰዎቹ ከጋምቤላ ከተማ 120 ኪሜ ርቀት ላይ በምትገኘው አብሌን ተቀምጠው ኑሯቸውን እየገፉ ሳለ በድንገት የተከበቡት በጥቆማ እንደሆነ ለጎልጉል የደረሰው መረጃ ያመለክታል። “አቶ ኡሞት ኡዶል እና ሌሎች መሳሪያ የታጠቁ አብሌን ታይተዋል” የሚል ጥቆማ የደረሰው ኢህአዴግ፤ ሰራዊቱን ሰዎቹ በቋሚነት ወደሚኖሩበት ጎክዲፓች በመላክ ቤተሰቦቻቸውን በመያዝ፣ በማሰርና፣ በመግረፍ ሰዎቹ ያሉበትን ቦታ እንዲያሳዩ አስገደዱ።
ኡሞት ኡዶል (ፎቶ: ጎልጉል: የድረገጽ ጋዜጣ)
አቶ ኡሞት በዋሽንግተን ዲሲ ነዋሪ የነበሩ ሲሆን የአሜሪካ ዜግነትም አላቸው። ኢህአዴግ ከመሬት ነጠቃ ጋር በተያያዘ በክልሉ ህዝብ ላይ እየፈጸመ ያለውን ግፍ አጥብቀው በግልጽ የሚቃወሙ ሰው መሆናቸውን የሚያውቋቸው ይናገራሉ። አቶ ኡሞት ከመሬት ነጠቃ ጋር በተያያዘ ህዝብን የሚያስተባብሩና ለዓመጽ የሚያነሳሱ ናቸው በሚል ኢህአዴግ ቢወነጅላቸውም ውንጀላውን በማስረጃ ማቅረብ እንደማይችል እነዚሁ ክፍሎች ይገልጻሉ። ስለተፈጸመው ግፍ የተሞላበት ግድያና ከግድያው በኋላ ስለተከናወነው “አረመኔያዊ የእንስሳ ተግባር” ሲያስረዱ በቁጣ ነው።
በተጠቀሰው ቀን ቤተሰቦቻቸውን ቀበሌያቸው ድረስ በመሄድ በመግረፍና በማስፈራራት ወደ አብሌን ለከበባ በጠቋሚ የመጡት የመከላከያ አባላት ሰዎቹን እንደተመለከቱ ተኩስ ከፈቱ። በድንገት የተከበቡትና ዛፍ ሥር ተቀምጠው የነበሩት አንዳችም ጥያቄ ሳይቀርብላቸው በጥይት የተደበደቡት ሰዎች የአልሞት ባይ ተጋዳይ ትግል ቢያደርጉም አልሆነም። ተደራጅቶ በሶስት የወታደር ካሚዮን ከባድ መሳሪያ ታጥቆ የመጣው ሰራዊት ጨፈጨፋቸው። ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ እንደተናገሩት ወዲያው ህይወታቸው ካለፈው ስድስት ንጹሃን መካከል አቶ ኡሞት መሞታቸው ሲታወቅ የሰራዊቱ አባላት አውካኩ፤ በደስታ ጨፈሩ። አስከሬኑንን ጭነው ፉኙዶ ወደሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት ካምፕ በመሄድ ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ደስታቸውን አበሰሩ።
አስከሬን በመኪና በመጫን ከተማ እየዞሩ ደስታቸውን ገለጹ። በማግስቱ በጋምቤላ ከተማ ስታዲየም አስከሬኑን ህዝብ እንዲመለከተው ታዘዘ። ህዝብ ስታዲየም ተገኝቶ የአቶ ኡሞትን አስከሬን እንዲሳለም፣ ኢንቨስተሮችም ያለስጋት የመሬት ነጠቃቸውንና “ልማታቸውን እንዲቀጥሉ”፣ መሞታቸውን አይቶ ሕዝቡ እንዲያምንና ሞራሉ እንዲጎዳ የተላለፈው ውሳኔ ባልተጠበቀ ሁኔታ ተስተጓጎለ። ለጎልጉል መረጃውን ያስተላለፉ እንዳሉት አቶ ኡሞት አሜሪካዊ መሆናቸው ሲታወቅ ማዕከላዊ መንግስት ከአዲስ አበባ አስቸኳይ ትዕዛዝ አስተላለፈ። አስከሬኑን ባስቸኳይ እንዲቀብሩ መመሪያ ሰጡ። ሁሉም ነገር በመመሪያው መሰረት ተጠናቀቀ። የአቶ ኡሞት አስከሬን ባልታወቀ ቦታ ተቀበረ። አስከሬኑንን ለማየት በግዳጅ ተሰባሰበው ህዝብም ምንም ነገር ሳይመለከት ወደ ቤቱ ተመለሰ። ሁኔታውን ተከትሎ በተፈጠረ አለመረጋጋት የኢህአዴግ ሠራዊት በጎክ አካባቢ ነዋሪ የሆኑ የጋምቤላ ተወላጆች በተለይም ወንዶችን እያሠሩና እያሰቃዩ እንደሆነ ከሥፍራው የደረሰን ዜና ያረጋግጣል፡፡
የአኙዋክ የፍትሕ ምክርቤት ጉዳዩን ለአሜሪካ መንግስት እንዳሳወቀና የአሜሪካ መንግስት ጉዳዩን ከስር መሰረቱ ጀምሮ እንደሚመረምረውና እስከ መጨረሻው የመንግሥት አካል እንደሚደርሱ ማረጋገጡ ታውቋል። ኢህአዴግ አቶ ኡሞትን የገደለበትን ምክንያት በማስረጃ ማቅረብ እንደሚጠበቅበትም አስታውቀዋል። አቶ ኡሞት የሚጠረጠሩበት ድርጊት እንኳን ቢኖር በቁጥጥር ስር አውሎ በህግ መጠየቅ እየተቻለ እንዲገደሉ መደረጋቸው ተቀባይነት የሌለው እንደሆነ የሚከራከሩላቸውና ጉዳያቸውን ይፋ ያደረጉት ክፍሎች ይናገራሉ።
በወቅቱ ህይወታቸው ያለፈው ንጹሃንና የደረሱበት ያልታወቀው ሰዎች ስም ዝርዝር ከስፍራው የደረሰን ሲሆን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
  1. ጎጎ ኦቻላ
  2. ቻም ኦቻላ
  3. ዑከች አቻው
  4. አኳይ ኦሞት
  5. ኦሞት ኦባንግ
  6. አጂባ አኳይ
  7. ኦሞት ኡጁሉ ኦጎታ
  8. አንበሳው ኡጁሉ
  9. ቱወል ኦሎክ
  10. ኦችዋል ኦባንግ
  11. ኦዋር ቻም
  12. ኒሙሉ አጎሌ
  13. አብራች ኒሙሉ
  14. አኩኔ ኦሞት
  15. አግዋ ቻም
  16. ኦዋር ኒግዎ አጋክ
  17. ኦሞት ኡዶል (አሜሪካዊው)

Sunday, March 3, 2013

አቡነ ማትያስ ለፓትርያሪክነት የተመረጡበት ከፍተኛ ድምፅ አነጋጋሪ ኾኗል


አቡነ ማትያስ ለፓትርያሪክነት የተመረጡበት ከፍተኛ ድምፅ አነጋጋሪ ኾኗልበስደት ላይ የሚገኘው ሲኖዶስ ሢመት ፕትርክናውን አውግዟል
‹‹ዕርቀ ሰላሙ ቅዱስ ሲኖዶስ በተናገረው መሠረት ይቀጥላል››
/ተመራጩ ፓትርያርክ/
አምስት ዕጩ ፓትርያርኮች ለውድድር በቀረቡበት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የስድስተኛው ፓትርያርክ ምርጫ÷ ብፁዕ አቡነ ማትያስ 500 ድምፅ በማግኘት ሌሎች ዕጩዎችን በሰፊ ልዩነት ያሸነፉበት ውጤት የምርጫውን ተሳታፊዎችና ተከታታዮች እያነጋገረ ነው፡፡
አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው የምርጫው ተሳታፊዎችና በተለያዩ መንገዶች የምርጫውን ሂደት የተከታተሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮችና ምእመናን÷ የምርጫው አሸናፊ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ሊኾኑ እንደሚችሉ ከወራት በፊት በሰፊው ሲነገር የቆየ ነበር፡፡ ይኹንና በምርጫው ድምፅ ከሰጡ 806 መራጮች መካከል ከ60 በመቶ በላይ ድምፅ በማግኘት ያሸነፉበት ውጤት÷ በዕጩነት ከተካተቱትና ለፓትርያርክነት ይበቃሉ የተባሉት ሌሎች ዕጩ ፓትርያሪኮች በተናጠል ካገኟቸው አነስተኛ ድምፆች አንጻር የምርጫውን ሂደት መለስ ብለው ለማጤን እንዳስገደዳቸው ይገልጻሉ፡፡
ስማቸውና የተወከሉበት አህጉረ ስብከት እንዳይገለጽ የጠየቁ ሁለት መራጮች፣ ከትላንት በስቲያ በመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ የተከናወነውን የስድስተኛው ፓትርያርክ ምርጫ ከጅምሩ እስከ ፍጻሜው በቅርበት መከታተላቸውን፣ በአፈጻጸሙ ግልጽና ቀልጣፋ ከመኾኑም ባሻገር ለትችት የሚዳርግ የጎላ ችግር እንዳላዩበት አስረድተዋል፡፡ ይኹንና ከምርጫው ቀን በፊትና ምርጫው ከተካሄደበት አዳራሽ ውጭ ተፈጽመዋል የሚሏቸው ተግባራት ለተጠቀሰው የውጤት መራራቅ በምክንያትነት አስቀምጠዋል፡፡
አስተያየት ሰጭዎቹ በቅድመ ምርጫው ተፈጽመዋል ከሚሏቸው ተግባራት መካከል÷ መንግሥት አሸናፊው ዕጩ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ‹‹ቀጣዩ ፓትርያርክ እንዲኾኑ ይደግፋል›› በሚል በሰፊው መወራቱና ይህንንም ተከትሎ በመራጮች ውሳኔ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ተፈጽሟል የሚሉት መጠነ ሰፊ ቅስቀሳ ነው፡፡ ቅስቀሳው በተወሰነ መልኩ ‹‹ብፁዕነታቸውን ባትመርጡ…›› የሚል ማስፈራሪያም የተቀላቀለበት እንደነበር መራጮቹ የራሳቸውንና የሌሎች ጓደኞቻቸውን ተሞክሮ በመጥቀስ ይናገራሉ፡፡
በርካታ የካህናትና ምእመናን ጥቆማ ካገኙና በዕጩ ፓትርያሪክነት ለመወዳደር ይበቃሉ ያሏቸው ሊቃነ ጳጳሳት በዕጩነት አለመካተታቸው ቅር እንዳሰኛቸው የገለጹት እኒህ አስተያየት ሰጭዎች÷ በምርጫው ለቀረቡት ዕጩዎች በአስመራጭ ኮሚቴው የተሰጠው ትኩረትም ምክንያታዊና ሚዛናዊ አለመኾኑንም ለውጤቱ መራራቅ በመንሥኤነት ጠቅሰዋል፡፡ በድምፅ መስጫው ወረቀት ላይ አሸናፊው ዕጩ ብፁዕ ማትያስ በመጀመሪያ ደረጃ መቀመጣቸው በሢመተ ጵጵስና ዘመነኛቸው ከኾኑት፣ በዕድሜ ከሚበልጧቸውና በሁለተኛ ደረጃ ከተቀመጡት ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ አንጻር የራሱ ተጽዕኖ አሳርፏል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡
የሁለቱን አስተያየት ሰጭዎች አስተያየት የሚተቹትና ድምፃቸውን ለአሸናፊው ዕጩ መስጠታቸውን ገልጠው የተናገሩ ሌሎች መራጮች በበኩላቸው÷ ብፁዕ አቡነ ማትያስ በአባታዊ ሞገሳቸው፣ በአገልግሎት ልምዳቸውና በዓለም አቀፍ ተሞክሯቸው ያገኙት ድምፅ ውጤት የሚያንሳቸው እንጂ የሚበዛባቸው እንዳልኾነ ይከራከራሉ፡፡ በቅድመ ምርጫው በየአቅጣጫው በብፁዕነታቸው ላይ ሲሰጡ የቆዩ ትችቶችን መከታተላቸውን የገለጹት መራጮቹ÷ በመጨረሻ ለውጤቱ ወሳኝ የሚኾነው መራጩ የሚወስደው አቋም ነውና በዕጩነት ከቀረቡት ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕነታቸው በሰፊ ድምፅ መርተው የተመረጡበት ውጤት ተቺዎቻቸውን ጭምር ያስደነቀ መኾኑን በምርጫው ስፍራ ማረጋገጣቸውን መስክረዋል፡፡
በምርጫው በዕጩ ፓትርያሪክነት የተወዳደሩት ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ 98 ድምፅ፣ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ 98 ድምፅ፣ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል 70 ድምፅ እና ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ 39 ድምፅ ማግኘታቸው አስመራጭ ኮሚቴው ይፋ ባደረገው የምርጫ ውጤት ተገልጧል፡፡
ከምርጫው አንድ ቀን በፊት ከአዲስ አድማስ ዘጋቢ ጋር አጭር ቆይታ ያደረጉት ተመራጩ ፓትርያሪክ ብፁዕ አቡነ ማትያስ በዕጩነት መካተታቸውን ያወቁት በሀ/ስብከታቸው ኢየሩሳሌም ሳሉ ከኢትዮጵያ በተደረገላቸው ጥሪ መኾኑን ገልፀዋል፡፡ “መንግሥት እርሳቸው ስድስተኛው ፓትርያሪክ እንዲኾኑ ይፈልጋል ስለመባሉ ተጠይቀው÷ ‹‹ስለዚህ ጉዳይ ምንም የማውቀው ነገር የለም፤›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በሌላ በኩል በሰሜን አሜሪካ በስደት ላይ የሚገኘው ‹‹ሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ›› የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ.ም የሚካሄደው ሢመተ ፓትርያሪክ÷ ‹‹ኢ-ቀኖናዊና የቤተ ክርስቲያንን ክብር ዝቅ የሚያደርግ፣ ሥርዐተ አልበኝነትን የሚሰብክ፣ ቤተ ክርስቲያንን የሚከፋፍል ነው፤›› በሚል ቀደም ሲል ያስተላለፈውን ውግዘት ማጽናቱን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ በመላው ዓለም የሚገኙ ካህናትና ምእመናን ለቤተ ክርስቲያን ክብርና አንድነት፣ ሰላምና ሐዋርያዊ ተልእኮ መሳካት አብረውት እንዲቆሙና እንዲሠሩም ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
በውጭ በስደት ከሚገኙት የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች ጋር የተጀመረውን የዕርቀ ሰላም ንግግር ለፍጻሜ ከማብቃት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ተቋማዊ መሻሻል በማፋጠን አስተዳደራዊ ለውጥ እንዲመጣ ከመንቀሳቀስ አኳያ በርካታ ተግባራት የሚጠብቋቸው አሸናፊው ተመራጭ ፓትርያሪክ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ለአዲስ አድማስ እንደገለጹት÷ ‹‹ቤተ ክርስቲያኒቱ ቀጥተኛውንና ትክክለኛውን መንገድ እንድትይዝና መንፈሳዊነትን እንድትጎናጸፍ ነው ተስፋ የማደርገው፡፡ ዕርቀ ሰላሙ እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ ተናግሯል፡፡ በዚያው መሠረት ይቀጥላል፡፡ ከሲኖዶስ የተለየ ሐሳብ ሊኖረኝ አይችልም፤›› ብለዋል፡፡
በአስመራጭ ኮሚቴው በወጣው መርሐ ግብር መሠረት የስድስተኛው ፓትርያሪክ በዓለ ሢመት በነገው ዕለት የአኀት አብያተ ክርስቲያን ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም መገለጹ ይታወሳል፡፡
addis admas

ፍሬ-አልባ ጩኸት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም


አንሰ እቤ አምግዕዝየ ኵሉ ሰብእ ሐሳዊ ውእቱ!
(የዳዊት መዝሙር 115)
መስፍን ወልደ ማርያም
የካቲት 2005
አቶ ዳንኤልን አላውቀውም፤ ለካ ብዙ ጭፍሮች ያሉት ሰው ነው፤ በጣም ተንጫጩለት፤ የሎሌ ነገር ሆነና ጩኸታቸው አንድ ነው፤ ጉዳዩን ጭራሽ አያውቁትም፤ ያንገበገባቸው መሪያቸው መነካቱ ነው፤ ለሎሌዎቹ መልስ መስጠት ባልተገባ ነበር፤ ነገር ግን ያደረጉት ትክክል መስሎአቸው እንዳይኩራሩና በያዙት የመክሸፍ መንገድ አንዳይቀጥሉ አንዳንድ ነጥቦችን ላብራራላቸው ፈለግሁ፤ ውጤት ይኖረዋል ብዬ ሳይሆን ለኔው ለራሴና ለማኅበረሰባችን ጤንነት ነው፤ ራሴን ከአቶ ዳንኤል ጭፍሮች ለመከላከል ፈልጌ እንዳይመስል፤ አትኩሮት በጉዳዩ ላይ እንዲሆን ለመሞከር ነው።
አንዳንዶቹ ዲያቆን የሚል ቅጽል ባለመጨመሬ ሆን ብዬ መስሎአቸዋል፤ ባለማወቅ ነው፤ ራሴን ተጠራጥሬ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ከፈትሁና የማውቀውን ነገረኝ፤ — የተካነ፣ ምሥጢር ያየ፤ ቀዳሽ — የሚል፤ በዚህ መስፈርት እኔም ዱሮ ዲያቆን ነበርሁ፤ ዛሬም ይህንን የሚያሙዋሉ ወጣቶች በኢትዮጵያ ውስጥ በሚልዮን ባይሆን በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ይኖራሉ፤ በዚያ ላይ እኔ እንደማውቀው ዲያቆን ሦስት ደረጃዎች ሲኖሩት የዲያቆኖች አለቃ ሊቀ ዲያቆናት ይባላል፤ አቶ ዳንኤል ሊቀ ዲያቆናትም አልሆነም፤ የአቶ ዳንኤል ዲያቆንነት የቱ ዘንድ እንደሚወድቅና ምን ማለትም እንደሆነ አላውቅም፤ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም እንዲህ ያለ ማዕርግ መስጠት ጀምራ እንደሆነና ለነማን እንደምትሰጥ አላውቅም፤ እኔ ዱሮ የማውቀው ዲያቆን የቅስና ሥልጣን(በምድር ያሰራችሁት በሰማይም የታሰረ ይሆናል፤) ሲያገኝ መምሬ መባሉን ነው።
ወደተነሣሁበት ጉዳይ ልግባ — አንድ መጽሐፍ አሳተምሁ፤ አውቃለሁ የሚለው አቶ ዳንኤል ተነሥቶ ስለመጽሐፉም ስለሌላ ሌላም የማያውቀውን ጻፈ፤ ስድስት የግድፈት ነጥቦችን ለቅሜ በማስረጃ እያስደገፍሁ የማያዳግም መልስ ሰጠሁት፤ ይህንን ያደረግሁበት ምክንያት ጭፍሮቹ እንዳሉት ሥራዬን አትንቀፉት በማለት በመታበይ አይደለም፤ ማናቸውም ሥራ አደባባይ ሲወጣ መነቀፉ አይቀርም፤ ስሕተትም አይጠፋም፤ አንድ ሰው በአንድ የአገር ወይም የማኅበረሰብ ጉዳይ ላይ ሲጽፍ ወይም በአደባባይ ሲናገር ራሱን ማጋለጡ ነው፤ የአቶ ዳንኤል ጭፍሮች ይህንን የማያውቁትን ጉዳይ ለእኔ ለማስተማር መከጀላቸው ጨቅላነታቸውን ያሳያል፤ በእኔ ላይ ባወረዱት ውርጅብኝ እንኳን ጉድጓድ ቆፍረው ራሳቸውን ቀብረው ነው፤ እውነተኛ ማንነታቸውን ደብቀው ነው፤ እነዚህ ጭፍሮች ስለመጋለጥ የሚያውቁት የለም፤ ስለዚህም ጉርጓድ ውስጥ ተቀብረው ስለማያውቁት ነገር መጮሁ የመጀመሪያው ስሕተታቸው ነው፤ ለነገሩ ስሕተት አይደለም፤ ወኔ-ቢስነት ነው።
እነዚህ ሁሉ ጭፍሮች ለጩኸት ከመጠራራታቸው በፊት መጽሐፉን ለማንበብና የክርክሩ መነሻ የሆኑትን ነጥቦች ለመጨበጥ አልሞከሩም፤ ወደው አይመስለኝም፤ ንዴታቸውን ለመግለጽና ግዳይ ለመጣል ስለቸኮሉ ለእነሱ ችሎታ የሚቀልለውን
‹‹የአንተ አሽከር፣ የአንተ ቡችላ፣
ኩፍ ኩፍ ይላል እንደጉሽ ጠላ!
በማለት በአደባባይ አቅራሩ፤ የችሎታ ማነስና ችኮላ ተለውሶ ያንን ጫጫታ አስከተለ፤ ገና ይቀጥላል፤ ባገኙን ቦታ ሁሉ ይህንን ጀብዱአቸውን ሊገልጹልኝ የሞከሩም አሉ፤ ከመሀከላቸው አንድም አንኳን ጉዳዩን ለመገንዘብና በጉዳዩ ላይ አስተያየት ለመስጠት የሞከረ አለመኖሩ የአስተሳሰብ ደረጃቸውን በግልጽ ያመለክታል፤ የሁሉም ዘገባ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ነው።
  • ከመሀከላቸው ስለመጽሐፉ የተናገረ አንድም የለም፤
  • ከመሀከላቸው አንድም ሰው አቶ ዳንኤል ስለጻፈው የተናገረ የለም፤
    • መጽሐፉን ሳያነቡና የአቶ ዳንኤልን ጽሑፍ ሳያነቡ እንዴት ብለው   እኔ በጻፍሁት ብቻ እንደዚያ ያለ የንዴት ጫጫታ ማሰማት ቻሉ?
ለጭፍራዎቹ በመጽሐፉና በአቶ ዳንኤል ጽሑፍ መሀከል ምንም ግንኙነት እንዳላዩበት ግልጽ ነው፤ ሊያዩበትም አይችሉም፤ ስለዚህ የእውቀት ጉድለታቸውን በንዴት ተኩት፤ እነሱው ራሳቸው የተገነዘቡትን የእውቀት ጉድለታቸውን እያጋለጡ ስለመጽሐፉ ለመናገር ወኔ አላገኙም፤ የኢትዮጵያውያን ባህላዊ ማምለጫና መብለጫ በሆነው የብልጣብልጥ ዘዴ ተጠቅመው በእነሱ ግምት እነሱን ከፍ እኔን ዝቅ አድርገው ለማሳየት ሞከሩ፤ ጭፍሮቹ በሙሉ እውቀቱ ስለሌላቸው መጽሐፉን ረሱት፤ ስለዚህም ራሳቸውን የሥነ ምግባር ሊቃውንት አደረጉና ትንሽነታቸውን ወደበላይነት ለመለወጥ ጣሩ፤ ይህ ብልጣብልጥነት እንደማያዋጣ ስለገባቸውና የእውቀታቸውንም ጎዶሎነት ስለተገነዘቡ ማንነታቸውን ሳይገልጹ ስማቸውን ደብቀው በአደባባይ ደነፉ፤ ደስ አላቸው፤ አስደሰቱ፤  ‹‹ያንን ፕሮፌሰር ነኝ ብሎ የሚኮፈስ ሰውዬ ልክ ልኩን ነገርነው! ልኩን እንዲያውቅና ከእኛ የማይሻል መሆኑንም ነገርነው!›› አንዳንዶቹ የእውቀት ደረጃቸውን አዘቅት ሲያወርዱ ከመስፍን ጋር ፕሮፌሰርነትንም አብረው ይኮንናሉ! አይ ፕሮፌሰርነት! እንዲህ ከሆነ ይቅርብን! እያሉ ዘላበዱ።
ተመካክረው የተነሡት በእነሱ ሚዛን ስለመስፍን ወልደ ማርያም ምግባረ-ብልሹነት ለዓለም ለመንገር ነው፤ አዋጃቸውን እንቀበለው፤ ስለመስፍን ወልደ ማርያም አንድ እውቀት ያስጨብጠናል፤ ዋናው ጉዳይ ግን መስፍን ወልደ ማርያም አይደለም፤ ዋናው ጉዳይ መጽሐፉ ነው፤ እንግዲህ ስለመጽሐፉ ምንም የማያውቅ ሰው ስለመስፍን ወልደ ማርያም መናገር የሚችለው ስንት ገደሎችን ዘልሎ ነው? ሁሉም ያሉት መስፍን ወልደ ማርያም ለአቶ ዳንኤል የሰጠው መልስ ስድብ ነበር የሚል ነው፤ ነገር ግን ከመሀከላቸው አንድም ሰው ስድቡ ምን እንደነበረ አልተናገረም፤ አንዴም ደህና አድርጎ ያላነበበውን ደጋግሜ አንቤዋለሁ ብሎ ሐሰት የተናገረን ሰው ሐሰት ተናግረሃል ማለት፣ የማያውቀውን አውቃለሁ ብሎ የተናገረ ሰውን አታውቅም ማለት፣ የማያውቀውንና ያልሆነውን ነገር ሲለጥፍብኝና የተናገረውን መልሶ ምሥጢር በማድረጉ የደብተራ ተንኮል ማለት፣ ለእኔ ስድብ አይደለም፤ እውነትን መናገር፣ ወይም ፈረንጆች እንደሚሉት አካፋን አካፋ ብሎ መጥራት ነው፤ ማሰብ የሚችል ሰው ለተናገርሁት ማስረጃ እንዳይጠይቀኝ ማስረጃዎቼን ሁሉ ቁልጭ አድርጌ አቅርቤአለሁ፤ እንዲያውም ትልልቅ ግድፈት የምላቸውን ነገሮች አልገባሁባቸውም፤ እዚያ ብገባ የበለጠ አንጫጫ ነበር፤
ከጭፍሮቹ አንዱም እንኳን መጽሐፉን ያነበበ አይመስለኝም፤ ከጭፍሮቹ አንዱም እንኳን በአቶ ዳንኤል ጽሑፍ ውስጥ ምንም እንከን አላዩም፤ ሊያዩም አይችሉም፤ ከስድብም አልፎ ወንጀል ሊለጥፍብኝ ሲከጅለውም አልታያቸውም፤ ወንጀልን በሰው ላይ መለጠፍ አላዋቂነት፣ ተንኮል፣ ውሸት ቢባል ስሕተቱ ምኑ ላይ ነው? እውነት ከማይከበርበት ቤት የወጡ ጭፍሮች እውነትን አላዩም ብሎ መውቀስ ባይቻልም አለማየታቸውን መናገር ግን ተገቢ ነው።
የአቶ ዳንኤል ጭፍሮች የመጽሐፉን ቁም-ነገር መጨበጥ ስላቃታቸው የሥነ-ምግባር ጉድለት የመሰላቸውን የመመጻደቅ ስብከት አወረዱት፤ ነገራቸው ሁሉ እንደአህያ መልክ አንድ ዓይነት ነው፤ ራሳቸውን አፋፍ ላይ እኔን ደግሞ ገደል ውስጥ ጨምረው እንደናዳ ሊያወርዱብኝ ሞከሩ፤ ከጭፍሮቹ መሀል አንድም እንኳን እሱም ራሱ ሆነ ጓደኞቹ የጻፉት የምግባረ ብልሹነት መግለጫና ማረጋገጫ መሆኑን የመገንዘብ ችሎታ ያለው አልተገኘም፤ በነዚህ ጭፍሮች የማሰብ ችሎታ እውነት መናገርን እንደስድብ ከመውሰዳቸው በላይ እነሱ ግን ለመሳደብ ልዩ ፈቃድ ያላቸውና የሥነ ምግባር ደረጃቸውም  የተለየ ነው፤ እነሱ ሲሳደቡ የሥነ ምግባር ብልሽት አይታያቸውም! እውነትን በደረቅ ቋንቋ ከመስማት ይልቅ ውሸትንና ተንኮልን በለስላሳ ቋንቋ መስማት የሚበልጥባቸው ጭፍሮች አቶ ዳንኤል ለተናገረው ዓይኖቻቸውን ሸፍነው እኔ በሰጠሁት መልስ ላይ ማተኮራቸው ያጋደለ የሆዳምነት ሚዛናቸውን በገሀድ ያሳያል፤ ውሸት የተናገረን ውሸታም ማለት፣ ተንኮልን የሸረበን ተንኮለኛ ማለት ትክክል ነው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለእውነት የተራበ፣ ለእውቀት የተራበ ሆኖ ለብዙ ሺህ ዓመታት ባለህበት ሂድ ሲል የኖረው በእንደነዚህ ያሉ የእውነትና የእውቀት ጸር የሆኑ ጭፍሮች እየታገተ ነው።
ሳያውቁት የመክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ ዋናውን መልእክት በተግባር አሳዩ፤ እውነትንና እውቀትን (ሁለቱን መለየት አይቻልም፤ እውነትን የማይቀበል እውቀትን አያገኝም፤ እውቀትን የማይቀበል እውነትን አያገኝም፤) አርክሰው እነሱ ጨዋነት የሚሉትን አወጁ፤ አንዱ በማያሻማ መንገድ ገልጦታል፤ መስፍን ኃይለ ማርያም ነኝ የሚል እንዲህ አለ፤‹‹ከእርስዎ ምሁራዊ ስድብ የዳንኤል ክብረት ጨዋዊ መሃይምነት በእጅጉ ይሻላል፡፡›› ይህ ሰው እሱና ጓደኞቹ በያዙት ሚዛን ‹‹ስድብ›› ያሉትን ተቀብሎ ከመታረምና ወደእውነትና ወደእውቀት መንገድ ከመግባት ይልቅ ‹‹ጨዋዊ መሃይምነትን›› መርጦ ለመኖር መወሰኑ ያሳዝናል፤ የዳንኤል ክብረትን አስመሳይነት፣ ደፋርነት፣ አላዋቂነትና ተንኮል በማያሻማ ቋንቋ ለመግለጥ የወሰንሁት በእንደዚህ ያሉ ምስኪን ‹‹ጨዋዊ መሃይሞች›› ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ገምቼ ልከላከልላቸው ብዬ ነበር፤ ተመችቶናል ስላሉ እግዚአብሔር ያውጣቸው፤ ሌሎች ሕመሙ እንዳይጋባባቸው ይጠንቀቁ!
በመጨረሻ በእውቀት ጉዞ ይሉኝታ፣ መግደርደር፣ መሸፋፈን፣ ማድበስበስ፣ መቀላመድ፣ የተጠሉና የእውቀት ጸር በመሆን የሚፈረጁ ዝንባሌዎች ናቸው፤ ሀ ማለት ሁለት ነው፤ ለ ማለት ሦስት ነው፤ ከተባለ ሀ+ለ አራት ነው ሲል የተጻፈውን አላነበብህም፤ ወይም አልገባህም፤ ስለዚህም መልስህ ልክ አይደለህም ማለት መማር ለፈለገ ነውር አይደለም፤ እውነትንና እውቀትን ለማራመድ መንገዱ ይህ ነው፤ የተገነዘበው ይራመዳል፤ እውነትን የሚፈራው ወደኋላ ይቀራል፤ መክሸፍ ማለት እንዲህ ነው።
source: http://mesfinwoldemariam.wordpress.com

Saturday, March 2, 2013

የስዑዲ ማስጠንቀቂያና የኢትዮጵያ ምላሽ


ሞኑን አንድ ከፍተኛ የሳውዲ አረቢያ ባለስልጣን ኢትዮጵያ በአባይ ግድብ የተነሳ በግብጽና በሱዳን የአባይ ወንዝ አጠቃቀም መብት ላይ አደጋ እየጣለች ነው ማለታቸውን ሱዳን ትሪብዩን የተሰኘው ድረ ገጽ ዘግቧል። ባለስልጣኑ የተናገሩት የሳውዲ አረቢያ መንግስት
አቋም መሆን አለመሆኑን አጣርቶ የኢትዮጵያ መንግስት ሰሞኑን መግለጫ እንደሚያወጣ ተዘግቧል። ሱዳን ትሪብዩን የተሰኘው ድረ ገጽ ሰሞኑን ባወጣው ዘገባ የሳውዲ አረቢያ ምክትል የመከላከያ ምክትል ሚኒስትር ካሊድ ቢን ሱልታን ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ያለው ፕሮጀክት፣ ግብጽና ሱዳን በወንዙ ላይ ያለቸውን መብት አደጋ ላይ እንደሚጥል መናገራቸው ተሰምቷል። ከሱዳን ድንበር 12 ኪሎሜትር ርቆ እየተሰራ ያለው የህዳሴ ግድብ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ይልቅ ለፖሊቲካ አሻጥር የሚያገለግል ነው ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃለ አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የተባለው ዜና የሳውዲ አረቢያ መንግስት አቋም መሆኑን አጣርቶ የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ መግለጫ እንደሚሰጥ ተናግረዋል፣
ይህ በሰባ አራት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዶላር በመሰራት ላይ ያለው ግዙፍ የግድብ ፕሮጀክት ተፋጥኖ እየጨመረ ያለውን የኢትዮጵያን ህዝብ ለመመገብና በተደጋጋሚ የሚከሰተውን የምግብ እጥረት ለመቋቋም እንደሚረዳ የኢትዮጵያ መንግስት ይናገራል።
ኢትዮጵያና ሳውዲ አረቢያ ጥሩ የኦኮኖሚ ትስስር ያላቸው ሀገራት ናቸው። በርካታ የሳውዲ አረቢያ ባለጸጋዎች መዋለ ነዋያቸውን በኢትዮጵያ ውስጥ ያፈሳሉ። ታዋቂው የኢትዮጵያ ባለሐብት ሼ ሞሐመድ አል-አህሙዲም የሳውዲ አረቢያ ዜግነት አላቸው።
  ኢትዮጵያ በአብዛኛው ለቤት ውስጥ ሥራዎች ብዙ ሰራተኞችን በየዓመቱ ወደ ሳውዲ አረቢያ ትልካለች። የምክትል መከላከያ ሚኒስትር ካሊድ ቢን ሱልጣን መግለጫ ኢትዮጵያ ከሳውዲ አረቢያ ጋር ካላት ከዚህ ትስስር ጋር የማይሄድ ነው ይላሉ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤

በግብጽ የፕሬዞዳንት ሙርሲ መንግስት ስልጣን ላይ ከወጣ ወዲህ በሳውዲ አረቢያና ግብጽ ግንኙነት እያደገ መምጣቱ ይነገራል። የብሪታኒያውያኑ የፖሊቲካ ጥናት ተቋም ቻተም ሃውስ የአፍሪቃ ቀንድ የፖሊቲካ አዋቂ ጃተም ሞስሊ እንዳሉት የሳውዲ አረቢያ መንግስት የአባይ ወንዝ ጉዳይ አይመለከተውም ማለት ይከብዳል፤

«የግብጽ የውሃ ጉዳይ ለግብጽ ብሔራዊ ጸጥታ በጣም አስፈላጊ ነው። የአሁኑ የግብጽ መንግስት ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ግብጽና ሳውዲ አረቢያ ግንኙነታቸውን አሳድገዋል። ግብጽ ለሳውድ አረብያ ቅርብ ሀገር ናት። ስለዚህ በግልጽ እንዲህ ነው ባይባልም፣ በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይ የሳውድ አረቢያ ፍላጎት የለበትም ማለት አይቻልም።»
ግብጽ የአረቡን አቢዮት ተከትሎ በተከሰተው የውስጥ አለመረጋጋት ምክንያት በምስራቅ አፍሪቃ ያላት የፖሊቲካ ተጽዕኖ ቀንሷል። ሱዳንም የደቡብ ሱዳንና የዳርፉር ችግሮች ፊቷን ከአከባቢው ፖሊቲካ እንድታርቅ አድርጓታል። በሌላ ኢትዮጵያም የአባይ ወንዝ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለማስፈጸም በብርቱ እየገፋች ነው።
በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይ ንትርክ ከተጀመረ ከሃምሳ ዓመታት በላይ ሆኖታል። ግብጽ የአባይ ወንዝ አጠቃቀምን በተመለከተ እአአ በ1929 የተፈረመው የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነት ቀጣይነት እንዲኖረው ትፈልጋለች።

  ኢትዮጵያና የላይኛው አባይ ተፋሰስ ሀገራት ግን ሁሉን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምንነት እንዲፈረም ይሻሉ። እአአ በ2010 ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች አራት የአባይ ተፋሰስ ሀገራት በአባይን ውሃ ክፍፍል ላይ በዩጋንሳ ኢንቴቤ ከስምምነት ደርሰዋል። ከአንድ ዓመት በኋላም ጎራውን ተቀላቅላለች።

አባ ሳሙኤል እና አባ አብርሃም ብፁዕ አቡነ ማትያስ እግር ላይ ወድቀው ይቅርታ ጠየቁ


http://www.zehabesha.com/amharic/wp-content/uploads/2013/02/abune_samuel.jpg
ሐራ
ተዋሕዶ የተባለው ድረ ገጽ “አቡነ ማቴዎስ አቡነ ሳሙኤልና አቡነ አብርሃምን ከአቡነ ማቲያስ ጋር ለማስማማት ቤታቸው ውስጥ እያነጋገሯቸው ነው የሚል ዜና አስነበቦ ነበር። አባ ሰላማ የተባለው የኦርቶዶክሳውያን ድረ ገጽ ደግሞ በሰበር ዜናው “አባ ሳሙኤል እና አባ አብርሃም ብፁዕ አቡነ ማትያስ እግር ላይ ወድቀው ይቅርታ ጠየቁ” ይላል። ዜናው
እንደወረደ የሚከተለውን ይመስላል አባ ሳሙኤል እና የጉድ ሙዳዩ አባ አብርሃም አቡነ ማትያስን ይቅርታ መጠየቃቸው ተሰማ፡፡ ይቅርታ እንዲጠይቁ ያደረጉት በ6ኛው የፓትርያርክ ምርጫ ሁለት መለያ አጥልቀው ሲሻቸው ለማቅ ዞረው ደግሞ በሽምግልና ስም እየተጫወቱ የቆዩት የመንደሩ ቀኛዝማች ሀይሉ ቃለወልድ መሆናቸው ታውቋል፡፡
የመንደሩ ቀኛዝማች በሐዘን ድባብ የተዋጠውን የማቅን መንደር ባለበት ትተው “ኧረ ጉድ እንዳንሆን እነአባ ሳሙኤልን ከአቡነ ማትያስ ጋር እናስታርቃቸው” ብለው የማቅ እጩ ወደነበሩት (“ነበር እንዲህ ቅርብ ነው ለካ?” አሉ እቴጌ ጣይቱ) ወደአባ ማቴዎስ በመደወል ከአቡነ ማትያስ ጋር እንዲያስታርቋቸው ይጠይቃሉ፡፡ አባ ማቴዎስም ሌሎች ጳጳሳትን ይዘው ወደአቡነ ማትያስ እንደገቡና ይቅርታ እንዲጠይቁ እንዳደረጓቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከዚያም አባ አብርሓም እግራቸው ላይ ወድቀው ስቅስቅ ብለው በማልቀስ “ይቅርታ አድርጉልኝ አባቴ፣ እኔ እኮ በሽተኛ ነኝ የምለውንም አላውቅም” በማለት ይቅርታ ጠይቀዋል ተብሏል፡፡
አባ ሳሙኤልም
በተመሳሳይ መንገድ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ግን “እኔን ምን አደረጋችሁኝ? ይቅርታ መጠየቅ
ያለባችሁ እኔን ሳይሆን የደፈራችሁትን ሲኖዱሱን ነው፡፡ አልሰማ ያላችኋቸውን ሰብሳቢውን ነው ይቅርታ መጠየቅ
ያለባችሁ፡፡” ማለታቸውን ምንጮቻችን ተናግረዋል፡፡
አባ ሳሙኤል እንኳን ለውድድር ለዕጩነትም ብቁ ባለመሆናቸው ተናደውና አኩርፈው በምርጫው ዕለት አለመገኘታቸውን የገለጹት ምንጮች ከእርሳቸው ጋርም የጉድ ሙዳዩ አባ አብርሃምና የማቅ አንደኛ ዕጩ አባ ማቴዎስ አድመው እንዳልተገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የጉድ ሙዳዮቹ አድራጎት ከአንድ ጳጳስ ፈጽሞ የማይጠበቅና በቀጣይም ከብፁዕ አቡነ ማትያስ ጋር ሊያጋጫቸው እንደሚችል ስለተሰጋ ነው ይቅርታ እንዲጠይቁ የተደረገው ተብሏል፡፡ ወላዋዩ አባ ገብርኤልም በግል ወደ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ገብተው በተመሳሳይ “ደብዳቤው እውነት መሆኑን አረጋገጥኩ አባቴ ይቅርታ ያድርጉልኝ ሰዎች አሳስተውኝ ነው” ማለታቸው ታሰምቷል፡፡ አሳሳቱኝ ያሏቸው ምናልባትም በአዋሳ ምእመናን ጉዳይ ወዳጆች የሆኗቸው የማቅ ሰዎች ሳይሆኑ እንዳልቀረ ተገምቷል፡፡
በምርጫው ሕግ ውስጥ አቡነ ማትያስን ከጫወታው ለማስወጣት የእድሜ ገደብ በማድረግና የዜግነት ጥያቄን በማቅረብ የተንቀሳቀሱትና በቆፈሩት ጉድጓድ የገቡበት አባ ሳሙኤል፣ ከምርጫው አስቀድሞ 500 ሺህ ብር መድበው የምረጡኝ ቅስቀሳ በማድረግ ግርግር ለመፍጠር መሞከራቸውና ሕዝብ መርጦኛል በሚል በአስመራጭ ኮሚቴው ላይ ጫና ለማሳደር በከፍተኛ ሁኔታ ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸው የሚታወስ ነው፡፡ በተለይም የሥላሴ ኮሌጅ ተማሪዎችን በደካማ ጎናቸው ማለትም ከኮሌጁ ዲን ከአባ ጢሞቴዎስ ጋር ያላቸውን አለመግባባት እንደጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም መብታቸው እንዲከበርላቸው አባ ጢሞቴዎስን “ለምንድነው ተማሪዎቹ የሚጠይቁትን መብታቸውን የማያከብሩላቸው?” በማለት በተደጋጋሚ በመጠየቃቸው በዚህ ደስ ያልተሰኙት አባ ጢሞቴዎስ ፊት ነስተዋቸዋል፡፡ አባ ሳሙኤልም ይህን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም እርሳቸው ፓትርያርክ ከሆኑ ችግሮቻቸውን ሁሉ እንደሚፈቱላቸው ቃል በመግባት በተላላኪዎቻቸው በኩል ተማሪዎቹን አሳምነው ነበር ተብሏል፡፡
የሁለቱን ሲኖዶሶች እርቀሰላም እንደፈረሰ አድርገው እንዲያነቡ የወያኔ መንግስት የተጠቀመባቸው አቡነ አብርሃም ዛሬ ያሰቡት ሳይሳካ የተለየ አቋም ይዘዋል የሁለቱን ሲኖዶሶች እርቀሰላም እንደፈረሰ አድርገው እንዲያነቡ የወያኔ መንግስት የተጠቀመባቸው አቡነ አብርሃም ዛሬ ያሰቡት ሳይሳካ የተለየ አቋም ይዘዋል በዚህ ያልተወሰኑትና የፓትርያርክነት ሥልጣን ያሳወራቸው አባ ሳሙኤል ያኔ ከአቡነ ጳውሎስ ጋር ተጋጭተው ለዓመት ያህል ያለስራ ተቀምጠው በነበረ ጊዜ መሸሻ የሆኗቸውን ብፁዕ አቡነ ማትያስን ለመቀናቀን መሞከራቸውና በዕጩነት እንዳይቀርቡ በርካታ ክፉ ስራዎችን ሲሰሩ ቆይተው ሁሉም ከከሸፈባቸው በኋላ በመጨረሻው ይቅርታ የጠየቁት ጥፋታቸው ስለተሰማቸው እንዳልሆነና በቀጣይ ሊወሰድባቸው የሚችለውን እርምጃ ፈርተው እንደሆነ የአባ ሳሙኤልን ማንነት ጠንቅቀው የሚያውቁ ምንጮች ተናግረዋል፡፡
ይህ በእንዲህ የምርጫው ግርግር በትኩሱ እየተቃኘ ባለበት በአሁኑ ወቅት የአባ ሳሙኤል በጊዜ ከጨዋታ ውጪ መሆንን በማሰብ ሌላው የጉድ ሙዳይ አባ ሉቃስ “ለመሆኑ የእጅጋየሁ አማች አባ ሳሙኤል ቢመረጥ ኖሮ እርሱን እጅ ልንነሳ ነበር ወይ?” ሲሉ ተደምጠዋል፡

Friday, March 1, 2013

የኢትዮጵያ አንድነትና ነፃነት ኃይልና የኢሕአዴግ ጦር በጭርቆና በረሃ ውጊያ ገጠሙ ተባለ


የመከላከያ ሠራዊት ሕንጻ
የኢትዮጵያ አንድነትና ነፃነት ኃይል (Ethiopian Unity and Freedom Force – EUFF) በጎንደር ጭርቆና በምትባለ በርሃ ላይ ከወያኔ አንድ ሻምበል ጦር ጋር ባደረግኩት ውጊያ 25 ወታደሮችን መግደሉን እና 11 ማቁሰሉን አስታወቀ።
የነፃነት ኃይሉ ለዘ-ሐበሻ በላከው መግለጫ “ከፌብሩዋሪ 25 እስከ 27 2013 ዓ.ም በአካባቢው የመንግስት አጨብጫቢ ሚሊሻዎች እየተመራ ወደ ነፃ መሬታችን በመምጣት ጥቃት ሊያደርስብን የመጣነውን አንድ ሻምበል ጦር አሳፍረን መልሰነዋል” ብሏል።
በአርማጭሆና በአይከል መካከል በምትገኘው ጭርቆና በረሃ ለ3 ቀናት በተደረገው ውጊያ ከመንግስት ወታደሮች 25 ሰዎች መሞታቸውን፣ 11 መቁሰላቸውን እና 3 ወታደሮችን መማረኩን ያስታወቀው የኢትዮጵያ አንድነትና ነፃነት ኃይል (EUFF) ከራሱ ሠራዊትም 5 ወታደሮች በዚህ ውጊያ መሞታቸውን ለዘ-ሐበሻ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ አንድነትና ነፃነት ኃይል (Ethiopian Unity and Freedom Force – EUFF) ከወያኔ ጋር አትሥሩ በሚል ማስጠንቀቂያ ለሰጣቸውና ይህን ማስጠንቀቂያ አልሰማ አሉኝ ላለው ባለፈው ጃንዋሪ 13 ቀን 2013 ዓ.ም በመተማ የወረዳው አስተዳዳሪ፣ የከተማው የብአዴን ጽ/ቤት ኃላፊ፣ የከተማው የአቢሲኒያ ባንክ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅን ጨምሮ 18 ሰዎች በመኪና ላይ በተጠመደ ቦምብ ሕይወታቸው ወዲያዉኑ ሲያልፍ ሌሎች 4 ሰዎች መቁሰላቸውንና ለዚህም ኃላፊነቱን መውሰዱ ይታወቃል። ከዚህ ቀደም ይኸው ድርጅት “ከኢሕአዴግ ሥርዓት ጋር አትተባበሩ የሚል ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ላልሰሙ ደጋፊዎች ክምር ድንጋይ የሚባለው አካባቢ የነዳጅ ዘይት ማጠራቀሚያ ማጋየቱና፤ እንዲሁምጨጨሆ ላይ ላይ ደግሞ አውቶቡስ ማቃጠሉ መዘገቡ አይዘነጋም። አሁን የመንግስት አንድ ሻምበል ከዚህ ጥቃት ጋር በተያያዘ ይህን ኃይል ለማጥፋት ወደ ሠራዊቱ ነጻ መሬት (ጭርቆና በርሃ) በመሄድ ውጊያ የገጠመው ቢባልም፤ ከመንግስት ወገን በተለይም ወደ መከላከያ ሚ/ር ደውለን ይህንን ለማረጋገጥ ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም። – See more at:http://www.zehabesha.com/

ESAT Daily News Amsterdam 01 March 2013 Ethiopia