Thursday, March 12, 2015

“ውድ ኮሚቴዎቻችን ለውሳኔ 1 ወር ብቻ መቀጠራቸው የጓሮ ውሳኔ ለመሰጠቱ ማሳያ ነው” – ድምፃችን ይሰማ -

“ውድ ኮሚቴዎቻችን ለውሳኔ 1 ወር ብቻ መቀጠራቸው የጓሮ ውሳኔ ለመሰጠቱ ማሳያ ነው!!!
ፍ/ቤቱ ፖለቲካዊውን ውሳኔ ባለመቀበል በነጻ ሊያሰናብታቸው ይገባል!!!” 
ድምፃችን ይሰማ
ሐሙስ መጋቢት 3/2007
ከህግ የበላይነት ይልቅ የደህንነትና የመንግስት ባለስልጣናት ፍላጎት ተፈፃሚ በሚሆንበት መንግስታዊ ስርዓት ውስጥ ፍትህን ማድበሰበስና ማስተጓጎል የተለመደ ሆኗል፡፡ መንግስት ይህንን ለማድረግ የተገፋፋበት ምክንያት ደግሞ ‹‹በሽብርተኝነት ተጠርጥረዋል›› የተባሉት ንፁሃን ለእስር የሚበቁት ተጠርጥረዋል በሚባሉበት ወንጀል ሊያስጠይቃቸው የሚችል አንዳችም ህጋዊ ማስረጃ ሳይኖር በመሆኑ ነው፡፡
yisema dimstachin
ህዝበ ሙስሊሙ የመረጣቸው እንደራሴዎቹ በግፍ በታሰሩበት ማግስት በማዕከላዊ ከደረሰባቸው አካላዊ በደል ባልተናነሰ በፍትህ ችሎቱ ውስጥ በሚሰሩ ተውኔቶች የሥነ-ልቦና በደል ደርሶባቸዋል፡፡ በደሉ መደበኛ ክስ ተመስርቶባቸው ችሎት ፊት የቀረቡ ዕለት ከተነበበው የክስ መዝገብ ይጀምራል፡፡ በሀገሪቷ ከፍተኛ የሆነ ቅጣት በሚያስከትለው የሽብር ክስ የተከሰሱ ሲሆን ክሱ የተዋቀረበት የሀሰት ትብታብ እርስ በእርሱ እንኳ ተደጋግፎ መቆም የማይችል፣ ብሎም የቅጥፈትን ትክክለኛ ገጽታ ለተመልካች ሁሉ ማሳየት የሚችል ነበር፡፡ ከሁለት ዓመታት በላይ የዘለቀው የፍርድ ሂደትም ከአንድ ምንጭ በተቀዱት አቃቤ ህግ፣ ዳኛና ምስክሮች ቁርኝት የኮሚቴዎቻችንን የሞራል ልዕልና ለመስበር፣ አካላቸውን በማሰቃየት ያልተሳካውን የነፃነት ስሜታቸውን ለመቅበር፣ ተስፋቸውን ለማጨለም ተደራራቢ ትንኮሳዎች በሚደረጉበት የዕለታዊ ስነ ልቦናዊ ቅጣት ማዕከል በሆነው ፍርድ ቤት ውስጥ የሚደረግ ቅርፁ እንጂ ይዘቱ ያልተለየ ቅጥ ያጣ ተውኔት ሆኖ ቆይቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ ፍትህ የምትንገላታበት የተውኔት መድረክ ከመሆንም ባሻገር የኢትዮጵያዊው ሙስሊም ሰላማዊ ትግል አሁንም በህገ ወጥነት፣ ህዝቡም በሽብርተኝነት የሚፈረጅበት፣ ለሚደርሱ በደሎች ሁሉ የህግ ሽፋን የሚፈለግበት አውድማ ነው፡፡ የህዝበ ሙስሊሙ እንደራሴዎች የፍርድ ሂደት መጠናቀቁን ተከትሎ ለመጨረሻ ብይን የአንድ ወር ቀጠሮ የተሰጠበት የመጨረሻው ችሎት በራሱም ለዚህ እውነታ ሌላ ተጨማሪ ማሳያ ነው፡፡ ከሁለት ዓመታት በላይ የዘለቀውና ከ5 ሺህ በላይ የፅሁፍ፣ የምስል፣ የድምፅና፣ የቪዲዮ ማስረጃዎች የቀረቡበት የፍርድ ሂደት የመጨረሻ መከላከያ ከተሰማበት ቀን ጀምሮ ሂደቱን ሙሉ ገምግሞ እና ከህግ፣ አዋጅና ደንቦች አንፃር መርምሮ ብይን ለመስጠት የአንድ ወር ቀጠሮ መስጠት ስላቅ ብቻ ሳይሆን ከችሎቱ መጋረጃ ጀርባ ባሉት የመንግስት አካላት ውሳኔው ቀድሞ ማለቁን አመላካች ነው፡፡
በዚህ ዓይነት በርካታ ተከሳሾች ባሉበት ሰፊ፣ ውስብስብና ረጅም የክስ ሂደት ውስጥ ቀርቶ የአንድ ግለሰብ ተራ ክስ እንኳ ሂደቱን መርምሮ ብይን ለመስጠት የሚሰጠው ቀጠሮ ከወር ከፍ ያለ ነው፡፡ ሆኖም ግን በኮሚቴዎቻችን የፍርድ ሂደት ውሳኔው የሚተላለፈው የቀረቡትን መረጃዎች መርምሮ፣ ከጭብጡ ጋር ያላቸውን ተያያዥነት አስልቶ፣ የተቀዱትን የአቃቤ ህግ ምስክርና የኮሚቴዎችን መከላከያዎች በሚገባ አድምጦ፣ በጠበቆችና በአቃቤ-ህጉ መካከል የተደረጉ ክርክሮችን አመዛዝኖ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን የመብት ጥያቄ ለማፈንና የበደሉን ግፊት ለመጨመር በሚረዱ የፖለቲካ ውሳኔዎች በመሆኑ ከተለምዶው የፍርድ ቤት ሥርዓት ያነሰ እጅግ አጭር ጊዜ በመስጠት መንግስት በፍትህ ስርዓቱ ቁልቁል ጉዞ ላይ ፍጥነት ጨምሮበታል፡፡ ታዲያ ይህ ለአንድ አገር ውድቀት አይደለምን?
ዛሬም ሕዝበ ሙስሊሙ በጀግኖች መሪዎቹ ላይ የሚሰጥን የሐሰት ፖለቲካዊ ብይን በጭራሽ አይቀበልም! በጽኑም ይታገለዋል!!!
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!
http://www.zehabesha.com/amharic/archives/39667

No comments:

Post a Comment