ወያኔ ባለፉት ሃያ ሁለት አመታት የአገራችንን የፍትህ ተቋሞች አንዴ አንደ ቂም መበቀያ ሌላ ግዜ ደግሞ እንደ ማጥቂያ መሳሪያ እየተጠቀመባቸዉ የፖለቲካ ተቀናቃኞቹንና ጥርስ የነከሰባቸዉን የህብረተሰብ አባላት እያሰረ፤ እያሳደደና እየገደለ ከርሞ ዛሬ ላይ ደርሷል። በተለይ ከግንቦት 1997ቱ ምርጫ በኋላ ወያኔ ብዕርና ወረቀት ይዘዉ በሃሳብና በአመክኖ የታገሉትን ሰላማዊ ዜጎች “ሽብርተኞች”፤ ድምጻችን ይሰማ ብለዉ የመብትና የነጻነት ጥያቄ አንግበዉ በሰላማዊ መንገድ የታገሉትን ኢትዮጵያዉያን የእስልምና እምነት ተከታዮች ደግሞ “አክራሪዎች” እያለ ፍርድ ቤት በማቅረብ በፍትህ ተቋሞች በኩል የፖለቲካ ዉሳኔ በማሳለፍ ሠላማዊ ዜጎችን ለረጂም ግዜ እስርና እንግልት ዳርጓል።
ወያኔ ለኢትዮጵያና ለዜጎቿ ደንታ የሌለዉ እና ከስህተቱ የማይማር የግብዞችና የዘረኞች ስብስብ ስለሆነ አሁንም የአገሪቱን የፍትህ ተቋሞች እንደ ማጥቂያ መሳሪያ እየተጠቀመ የኢትዮጵያን ህዝብ በፍርሃት ጨለማ ዉስጥ ሸብቦ እየገዛ ለመኖር የቆረጠ ይመስላል። ባለፈዉ ሳምንት አጋማሽ ላይ የወያኔ አገዛዝ ከአንድ አመት ተኩል በላይ እስር ቤት ዉስጥ አጉሮ ያቆያቸዉን የድምጻችን ይሰማ መሪዎች ከፊሎቹን በነፃ ተለቅቀዋል የሚል ከፊሎቹን ደግሞ ተከላከሉ የሚል ትርጉም የለሽ ብይን ሰጥቷል። በህወሀት ታጋዮች የተሞላዉ ፍርደ ገምድሉ የወያኔ ፍርድ ቤት እንኳን ተከሳሾቹ በተከሰሱበት ሽብር የመፈጸም ወንጀል ምንም አይነት ማስረጃ አልተገኘባቸዉም ሲል አገዛዙ ግን የፖለቲካ ክንዱን በመጠቀም ማስረጃ ያልተገኘባቸዉን ሠላማዊ ዜጎች የተከሰሱበትን መሰረተ ቢስ ክስ ተከላከሉ የሚል የፖለቲካ ዉሳኔ ሰጥቷል።
የወያኔ አገዛዝ የሙስሊሙን ህብረተሰብ የመፍትሄ አፈላላጊ ቡድን መሪዎች ፍርድ ቤት ያቀረባቸዉ ለምዕራባዉያን ለጋሾቹና ለአለም አቀፍ አበዳሪ ድርጅቶች ኢትዮጵያ ዉስጥ ፍትህ ያለ ለማስመሰል ነዉ እንጂ ወያኔ የድምጻችን ይሰማ መሪዎችን የፈረደባቸዉ ያሰራቸዉ ቀን ነዉ። የወያኔ የፍትህ ታሪክ በግልጽ እንደሚያሳየን ወያኔ ግለሰቦችን የሚያስረዉ ለክስ የሚያበቃ ማስረጃ አግኝቶባቸዉ አይደለም፤ ይልቁንም ወያኔ ማስረጃዎችን እየፈበረከ ለፍረድ ቤቶች የሚያቀርበዉ ግለሰቦችን ካሰረና ሰብዓዊ መብታቸዉን ከገፈፈ በኋላ ነዉ። ለምሳሌ የድምጻችን ይሰማ መሪዎችን አስሮ ብዙም ሳይቆይ የእነዚህን ሰላማዊ ዜጎች ተክለ ሰዉነት ጥላሸት የቀባና ግለሰቦቹን ያለ ማስረጃ ወንጀለኛ አድርጎ የፈረጀዉን “ጂሐዳዊ ሀረካት” የሚል የፈጠራ ድራማ ሰርቶ ለህዝብ አቅርቧል።
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሽብር በመፈጸም ወንጀል ተጠርጥረዉ የቀረቡለትን ግለሰቦች በተከሰሱበት ወንጀል ማስረጃ አላገኘሁባቸዉም ካለ በኋላ ሁሉንም በነጻ አለማሰናበቱ የሚያሳየን የወያኔ ፍርድ ቤቶች ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነጻ አለመሆናቸዉን ብቻ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያ ዉስጥ ፍርድ ቤቶች የገዢዉ ፓርቲ የማጥቂያ መሳሪያዎች መሆናቸዉን ጭምር ነዉ። የወያኔን አገዛዝ ከሌሎች አምባገነኖች ለይቶ አደገኛ የሚያደርገዉና በምዕራባዉያን መንግስታትና በቀላጤዎቻቸዉ እንዲወደስ ያደረገዉም ይሄዉ አገዛዙ የሚቃወሙትን ኃይሎች የሚያጠፋቸዉ እንደሌሎቹ አምባገነኖች በግልጽ ሳይሆን በህግ ሽፋን ዉስጥ በስዉር መሆኑ ነዉ።
የወያኔዉ ፍርድ ቤት በተመሳሳይ ወንጀል ተከስሰዉ የቀረቡለትን ነገር ግን ምንም መረጃ ያላገኘባቸዉን የድምጻችን ይሰማ መሪዎች ገሚሶቹን በነፃ ለቅቆ የተቀሩትን ጥፋተኛ አለመሆናችሁን አረጋግጡ ብሎ መወሰኑ የወያኔን ሁለት እኩይ አላማዎች ያሳየናል። የመጀመሪያዉ የወያኔ አላማ በአላማቸዉ ጸንተዉ የቆሙትን የድምጻችን ይሰማ መሪዎች መከፋፈል ሲሆን፤ ሁለተኛ አላማዉ ደግሞ የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች የቀረቡላቸዉን የክስ መዝገቦች በሚገባ አጣርተዉ ዉሳኔ የሚሰጡ መሆናቸዉን ለአለም አቀፉ ህብረተሰብ ለማሳየት ነዉ።
የኢትዮጵያ ህዝብ ግን እንደዚህ አይነቶቹን የወያኔ እኩይ ተግባሮች ካወቀ ዉሎ አድሯል፤ ስለሆነም ከወያኔ ፍትህ ጠብቆ አያዉቅም፤ ወያኔ የክፋትና የበቀል ምንጭ ነዉና ለደፊትም አይጠብቅም። የድምጻችን ይሰማ መሪዎችም ሆኑ ከእነሱ በፊት በግፍ ታስረዉ መከራቸዉን የሚያዩት የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፤ ጋዜጠኞችና የሲቪክ ማህበራት መሪዎች የታሰሩት ለቆሙለት የፍትህ፤ የነጻነትና የእኩልነት አላማ እንደ አለት ጸንተዉ በመቆማቸዉ ነዉ። እነዚህ ጀግኖች የታሰሩለት አላማ የሁላችንም አላማ ነዉና ፍትህ፤ እኩልነትና ነጻነት የጠማን ኢትዮጵያዉያን ክንዳችንን አስተባብረን የችግሮቻችን ሁሉ ምንጭ በሆነዉ በወያኔ ስርዐት ላይ ክንዳችንን በጋራ እናንሳ!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!
No comments:
Post a Comment