Sunday, January 27, 2013

የዋልድባ መነኮሳትን ከፍተኛ ግፍና መከራ እየተፈጸመባቸው መሆኑን ገለጹ


የጸለምት ወረዳ ባለስልጣናት፣ በዋልድባ ያለዘር ልዩነት ለዘመናት የኖሩ መነኮሳትን ትግሬ ካልሆናችሁ በዚህ ገዳም ውስጥ መኖር አትችሉም በማለት ከፍተኛ ግፍና መከራ እየፈጸሙባቸው መሆኑን ዘጋቢያችን መነኮሳቱ የጻፉትን አቤቱታ ዋቢ በማድረግ በላከልን ዘገባ ገለጸ።
እንደ ዘጋቢያችን ሪፖርት መነኮሳቱ ለክልሉ የወያኔ ባለስልጣናትና ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በጻፉት አቤቱታ እንዳሉት ባለስልጣናቱ ግፍና በደል የሚፈጽሙባቸው በጣት የሚቆጠሩ የነሱን መነኮሳት፣የአካባቢውን ታጣቂዎችና ሚሊሺያዎች በመጠቀም ነው። በሃይማኖትም ሆነ በሀገሪቱ ህግ መንፈሳዊ ቦታ ማንም ያለዘር መድልዎ የሚገለገልበት ቦታ ቢሆንም እነርሱ ግን በማንነታቸው ምክንያት የዘር መድልዎ፣ እስራትና ድብደባ እየተፈጸመባቸው ነው – እንደ አቤት ባዮቹ መነኮሳት። ከዚህም ሌላ ከገዳሙ ውጪ በነጻነት ለመንቀሳቀስ የትግራይ ክልልን መታወቂያ የመያዝ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፤ የገዳሙ ማህተም ያለበትን መታወቂያ ይዘው ሲንቀሳቀሱ ይህ ተቀባይነት ስሌለው መንቀሳቀስ አትችሉም በማለት አካባቢውን ለቀው እንዲሄዱ ግፊት እየተደረገባቸው ነው።
በመሆኑም መነኮሳቱ ይህን አቤቱታ ለማቅረብ ወደ ጎንደር ሲጓዙ ቀጥታውን መንገድ በመተው የሁለት ቀን መንገድ ለመጨመርና በረሃ ለበረሃ ለመንከራተት ተገደዋል።ቀጥታውን መንገድ ለመጠቀም የመረጡትም ለእስር ተዳርገዋል።
በአቤቱታው እንደተገለጸው የደረሰባቸውን ግፍና በደል ለማሰማት የተንቀሳቀሱት መነኮሳት ሰላሳ አንድ ሲሆኑ፣ በርካቶች የዘርኝነት ጥቃቱ ሰለባዎች ገዳሙን በመልቀቅ ተሰደዋል። ባለስልጣናቱም መነኮሳቱን በማዋከብ፣በመደብደብና በማሰር ከበታተኑ በኋላ ወደ ገዳሙ በመሄድ በማንአለብኝነት የራሳችን የሚሏቸውን ሰዎች በልዩ ልዩ የሃላፊነት ቦታ በመመደብ የገዳሙን ስርዓት አፋልሰው ሄደዋል ሲሉ አቤቱታ አቅራቢዎቹ አማረዋል።
በመጨረሻም በተደጋጋሚ በደረሰባቸው በደል፣ግፍና የዘረኝነት ጥቃት በገዳማቸው መኖር አለመቻላቸውን፣ የሌላ ሃገር ዜጋ ይመስል በገዛ ሃገራቸው በመንፈሳዊ በዓታቸው እንዳይኖሩ የማያውቁትን ፖለቲካ ተገን ባደረገ ዘረኛ አስተሳሰብ ህልውናቸው አደጋ ላይ መውደቁን በመግለጽ ይህ ችግር በእነርሱ ላይ ብቻ የሚቆም ባለመሆኑ ውሎ አድሮ ችግሩ ከመባባሱና ጠባሳ ከመተው በፊት የሚመለከታቸው አካላት አፋጣኝ መፍትሄ እንዲፈልጉ አሳስበዋል።

“መናገር የማልፈልገው ብዙ ነገር አለ” ብጹእ አቡነ ሕዝቅኤል


  ከላይፍ መጽሄት የተወሰደ
  (ቅጽ 7 ቁጥር 99 … ጥር 2005 እትም)
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ለቀናት ያደረገው ስብሰባ በመጠናቀቅ ባሳለፍነው ሳምንት ባወጣው መግለጫ አሜሪካን ሀገር የሚገኝው ሲኖዶስ ያቀረበውን ጥያቄ ለመቀበል ሕገ ቤተክርስቲያን እንደማይፈቅድለት በመግለጽ  ስድስተኛውን የቤተርክርስቲያን ፓትርያርክ ለመምረጥ መወሰኑን ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ የላይፍ መጽሄት አዘጋጆች ከመግለጫው በኋላ ወደ ሲኖዶስ ዋና ጸሀፊ አቡነ ሕዝቅኤል ቢሮ በማምራት አቡኑን ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡ አቡነ ሕዝቅኤል የስራ ጫና ውስጥ የነበሩ ቢሆንም  መጠነኛ ጊዜ መስዕዋት በማድረግ ጥያቄዎቻችንን በመቀበል ተገቢ ነው ያሉንን ምላሽ  ሰጥተውናል፡፡ ነገር ግን አቡኑን በምናነጋግርበተ ሰዓት ማንነቱ ያልለየነው አንድ ሰው ቢሮ ውስጥ ተቀምጦ ጥያቄና መልሱን ይከታተል ነበር፡፡ ለብጹእ አቡነ ሕዝቅኤል የምናቀርብላቸው ጥያቄ እኛን እየተመለከቱ ምላሽ መስጠት ይገባቸው የነበረ ቢሆንም በእያንዳንዱ አረፍተ ነገር  ግለሰቡን እየተመለከቱ ማረጋገጫ እንደሚጠይቅ ሰው አይናቸውን ገጽታው ላይ ያንከራትቱ ነበር፡፡ ጥያቄያችን ጨርሰን ከቢሮ ልንወጣ ስንልም “አቡኑን ለማስለፍለፍ ሞክራችሁ ነበር እሳቸው ግን ብልጥ በመሆናቸው አንዳች ነገር አልተናገሩም” ብሎናል፡፡ ለማንኛውም ቃለ ምልልሱን እነሆ፡፡
ላይፍ፡- የአገር ውስጥ ሲኖዶስ ባወጣው መግለጫ በቀጥታ ስድስተኛውን ፓትርያርክ ወደ መምረጥ እንደሚገባ አስታውቋል ፡፡ በዚህ ዙሪያ ከግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የምትወስዱት ትምህርት ምንድነው ?
አቡነ ሕዝቅኤል፡- እኛ ከግብጽ ኦርቶዶክስ እንለያያለን ፤ ምናልባት ልዩነታችን በቋንቋ ብቻ አይደለም፡፡ በሐይማኖት በኩል አንድ ነን፡፡ በፓትርያርክ ምርጫ በኩል የራሳችን መንገድ አለን፡፡ ቤተክርስቲያናችን ከግብጽ ባርነት ወጥታ  ራሷን ችላ እየተራመደች በመሆኗ ከእነሱ የምትዋሰው ነገር የላትም፡፡
ላይፍ፡- “ሲኖዶስ የሚያደርገው ስብሰባም ሆነ የሚያስተላልፈው ውሳኔ የእምነቱ ተከታይ የሆኑትን ከ40 ሚሊየን በላይ ምዕመናንን አያሳትፍም፡፡ የእነሱ ድምጽ በሲኖዶስ ውሳኔ ላይ ተጽህኖ የለውም” የሚሉ ወገኖች በስፋት ይደመጣሉ፡፡ ለመሆኑ ሲኖዶስ የምዕመናንን ድምጽ የሚያዳምጥበት አሰራር አለው?
አቡነ ሕዝቅኤል፡- ምን መሰለህ እኛ የምንመራበት የስርዓት መጽሐፍ አለን፡፡ መጽሐፉ ይህንን በግልጽ ያስቀምጠዋል፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ ነገሮችን በግልጽ የምታስኬድበት መመሪያ አላት፡፡ ሲኖዶሱ የሚመራው በእነዚህ መመሪያ ነው፡፡ ነገር ግን የምዕመናንን ድምጽ  ሲኖዶስ አያዳምጥም ማለት ተገቢ አይደለም ፡፡ ድምጻቸው የሚደመጥበት የራሱ የሆነ መንገድ አለው፡፡
ላይፍ ፡- ለምሳሌ የትኛው መንገድ ?
አቡነ ሕዝቅኤል፡- የፓትርያርክ ምርጫውን ውሰድ ፡፡ በዚህ ወቅት ምዕመኑ እንዲሳተፍ ይደረጋል፡፡ የፓትርያርክ አስመራጭ ኮሚቴ ውስጥም ምዕመናኑ ይገኛሉ፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ ንፍገት የለባትም፡፡
ላይፍ፡- ቤተክርስቲያኒቱ የተፈጠረላት መልካምና ወርቃማ አጋጣሚ በመጠቀም በስደት አሜሪካን ከተመሰረተው ሲኖዶስ ጋር እርቅ ትፈጽማለች በማለት የሚጠብቅ አማንያን ብዙ ነበሩ፡፡ ነገር ግን መግለጫው በአጋጣሚው እንዳልተጠቀማችሁበት ምልክት ሰጥቷል፡፡
አቡነ ሕዝቅኤል፡- አልተጠቀማችሁበትም አትበል ተጠቅመንበታል ፡፡ ምንድነው ሳንጠቀም ያመለጠን ?
ላይፍ ፡- ለምሳሌ አንድ ፓትርያርክ በህይወት እያለ ሌላ እንደማይሾም የቤተክርስቲያኒቱ ህግ ይደነግጋል  ፤ ይህ በአንድ ወቅት ተጥሷል ፤ አሁን በድጋሚ ጥፋቱን ለማረም የሚያስችል አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር፡፡ እናንተ ግን በአቡነ መርቆሪዎስ መንበራቸው መመለስ ፈቃደኛ አልሆናችሁም፡፡
አቡነ ሕዝቅኤል፡- አቡነ መርቆሪዎስ ክብራቸው እንዳለ እዚህ መኪና ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡ ገዳም መቀመጥ ከፈለጉም በገዳም እዚህ ከተማ ውስጥ ከሆነም እዚህው ከተማ ውስጥ እንዲቀመጡ ቦታ ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡ ሲኖዶሱ ይህንን ወስኗል ፡፡ ሌሎች ሊቃነ ጳጳሳትም ወደ ሀገራቸው መግባት ከፈለጉ ሀገረ ስብከት እንሰጣቸዋለን በማለት ሲኖዶሱ አስተላልፏል፡፡  ከዚህ ውጪ ሲኖዶስ ምን ማድረግ ይችላል? ይምጡና አብረው ባለቤት ይሁኑ  ፤ ከውጭ ሆነው ሌላ ነገር ሳይሉ በሂደቱ በመሳተፍ ይምረጡ ይመረጡ ይጠቀሙ ነው የተባለው፡፡ ከዚያ ወዲያ ቤተክርስቲያን ምን ልታደርግ ኖሯል ?
ላይፍ ፡- አቡነ መርቆሪዎስ አራተኛ ፓትርያርክ በመሆናቸው  እንዴት ይጠቁሙ ይጠቆሙ በድጋሚ ምርጫ ውስጥ ይግቡ ይባላሉ የሚሉ ሰዎች  ብዙ ናቸው፡፡ ለዚህ የመሞገቻ ጥያቄ የምትሰጡት ምላሽ ምንድነው ?
አቡነ ሕዝቅኤል፡- ይህንን ቀኖና ይከለክላል ፤ አንተ የምትለው የገባህበት በር እያለ ግድግዳውን  አፍርሼ ካልወጣው ነው፡፡ በበሩ በመንገዱ እንጂ በግድግዳው እወጣለሁ ካልክ ብዙ ችግር ይፈጠራል፡፡ መመሪያችን የቤተክርስቲያኒቱ በመሆኑ ነው ሲኖዶስ ያዘዘው፡፡ ይህንን ፍትሐ ነገሥቱም አያዝም፡፡ አቡነ መርቆሪዎስ ሳይወዳደሩ በቀድሞ የፕትርክና ስልጣናቸው ይቀጥሉ ማለትም መንፈሳዊው ህግ አይደግፈውም፡፡
ላይፍ፡- በውጭ ሲኖዶስ ጋር ያላችሁ ግንኙነት ከአሁን በኋላ በምን ሁኔታ የሚቀጥል ይሆናል?
አቡነ ሕዝቅኤል፡- እኛ እንታረቅ ብለናል ፤ መስመራችንም መንገዳችንም ክፍት ነው፡፡ ይምጡ ብለናል ሌላ ነገር የለም፡፡
ላይፍ ፡- ከዋና ጸሀፊነትና ከፓትያርክ ምርጫው ራስዎን ማግለልዎ እና  የመልቀቂያ ደብዳቤ ስለ ማስገባትዎ ሰምተናል፡፡ ይህ የሀገር ውስጥ ሲኖዶስ እየሄደበት የሚገኝው መንገድ ደስተኛ ላለመሆንዎ ማሳያ አይሆንም ?
አቡነ ሕዝቅኤል፡- ማነው እንደዚህ ያለው? እንግዲህ እናንተ ብዙ ታወራላችሁና እኔ የምጨምረው ነገር የለኝም፡፡ ትንሽ ፍንጭ ይዛችሁ ያችን ማስፋት ትፈልጋላችሁ ፡፡ እኔ እኔ ነኝ፡፡ ከየትስ ነው ራሴን የማገለው? እኔ ከቤተክርስቲያን ውጪ ነኝን?
ላይፍ ፡- እኛ የሰማነውን በመያዝ ማረጋገጫ ጠይቀንዎታል፡፡ የተባለውን ውሸት ወይም እውነት ነው የማለት ፋንታ ግን የእርስዎ ነው?
አቡነ ሕዝቅኤል፡- ራሴን ከቅዱስ ሲኖዶስ አግልዬ ብሆን ኖሮ እዚህ አታገኙኝም ነበር፡፡
ላይፍ ፡- ከፓትርያርክ ምርጫ በፊት እርቅ መቅደም አለበት ከሚሉ የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች የመጀመሪያ ስለመሆንዎ ይነገራል፡፡ ምናልባት እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ምክንያት የሆንዎት እርቁ ባለመሳካቱ ይሆን ?
አቡነ ሕዝቅኤል፡- እርቁ መቼ በሲኖዶስ ሳይፈለግ ቀረና ነው እኔ እንዲህ ማለት የምችለው፡፡ ሲኖዶሱ እንታረቅ አንድ እንሁን ብሏል፡፡ ስለዚህ እኔ ከሲኖዶስ ውጪ መሆን አልችልም፡፡
ላይፍ፡- የአገር ውስጡ ሲኖዶስ ያሳለፈው ወይም የደረሰበት መደምደሚያ ያለ ሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት የተከናወነ ነው ብለው በግልዎ ያምናሉ?
አቡነ ሕዝቅኤል፡- የምን ጣልቃ ገብነት?
ላይፍ ፡-ለምሳሌ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት እርቁ ያልተሳካው መንግሥት በአሜሪካው ሲኖዶስ ደስተኛ ባለመሆኑ ነው ይባላል፡፡ ስድስተኛው ፓትርያርክ ለመምረጥ የምታደርጉት እቅስቃሴ የመንግሥት ረዥም እጅ እንዳለበት ይነገራል፡፡ ይህንን ያስተባብላሉ?
አቡነ ሕዝቅኤል፡- ምንድነው ይህ?
ላይፍ፡- የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ታምራት ላይኔ የአቡነ መርቆሪዎስን መሰደድ የመንግሥት እጅ እንደነበረበት በመግለፅ በይፋ ይቅርታ እንደጠየቁ ተናግረዋል፡፡ ይህ መንግሥት በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ እጁን ለማስገባቱ አይነተኛ ማስረጃ ተደርጎ ይጠቀሳል፡፡
አቡነ ሕዝቅኤል፡- እንዲህ ለማለቱ መረጃ አቅርቡልኝ፡፡ ይህንን መናገሩን እኔ አላውቅም፡፡ እኔ በዚህ አልነበርኩም፡፡  አንተም በዚያን ወቅት ጋዜጠኛ አልነበርክም፡፡ ስለዚህ ተወኝ፡፡
ላይፍ ፡- የቀድሞ ይቅር እሺ አሁን ነጻ ነን ብለው ያምናሉ ?
አቡነ ሕዝቅኤል፡- መንግሥት እኔ እስከማውቀው ድረስ እዚህ ውስጥ አልገባም ፡፡ ሕገ – መንግሥቱም አይፈቅድለትም፡፡ እነርሱ በእኛ እኛም በእነርሱ ጣልቃ አንገባም፡፡  መንግሥት ገብቶ ምን አደረገ ተባለ?  አልገባንም፡፡ እኔ ለራሴ እስከ አሁን ድረስ ነጻ ነኝ ፡፡ የሌላውን አላውቅም፡፡
ላይፍ፡- የእርቁ ጥያቄ ተቀባይነት ያጣው በየትኛው በኩል ነው ?
አቡነ ሕዝቅኤል፡- እኛ ከዚያን ወገን ጋር እየተቀራረብን ነው እርቁ እንደሚፈጸም ተስፈኞች ነን፡፡
ላይፍ፡- ከኢህአዲግ አመራሮች አንዱ የሆኑት አቶ አባይ ጸሀዬ ሲኖዶሱ በሚያደርገው ስብሰባዎች በመገኘት የመንግሥትን አቋም ግልጽ ስለማድረጋቸው መረጃዎቻችን ይገልጻሉ፡፡
አቡነ ሕዝቅኤል፡- በፍጹም እኔ በተገኘሁበት ስብሰባ የምትለውን ሰው ተመልክቼው አላውቅም፡፡ ከሲኖዶስ ስብሰባ ተለይቼ አላውቅም፡፡ ዝም ብለን የመንግሥትን ስም ባናጠፋ መልካም ነው፡፡
ላይፍ፡- አሜሪካን ሀገር ለሚገኝው ሲኖዶስ ሆነ ጉዳዩን በቅርበት ሲከታተሉ ለቆዩት የቤተክርስቲያን አባላት የሚስተላልፉት መልዕክት ምንድነው?
አቡነ ሕዝቅኤል፡- መልዕክት ሳስተላልፍ አይደል እንዴ የኖርኩትኝ ? ስንት መጽሐፍ ጽፌአለሁኝ ፤ የሚሰማኝ የለም እንጂ፡፡  አሁንም እየተናገርኩ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ምን እንድል ትፈልጋለህ ? መናገር የማልፈልገው ብዙ ነገር ያለኝ በመሆኑ ከዚህ በላይ ምንም መናገር አልፈልግም፡፡ ይህው ነው፡፡
ላይፍ፡- ለጥያቄዎቻችን ተገቢ ያሏቸውን ምላሾች በመስጠትዎ በአንባቢያችን ስም እናመሰግናለን
አቡነ ሕዝቅኤል፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

ESAT Ye Ehud Weg 27 January 2013 Ethiopia


Saturday, January 26, 2013

ጀግንነት ፈፅሞ አለመሸነፍ አይደለም። ተሸንፎ መነሳት ነው ለብሔራዊ ቡድናችን ፣ለአሰልጣኞች እና ለደጋፊዎች ሁሉ


ለናይጀርያው ግጥምያ ዝግጅት ላይ
ትናንት አርብ ጥር 17/ 2005 ዓም በ ኢትዮጵያ የ ሰዓት አቆጣጠር ከ ምሽቱ ሶስት ሰዓት ጀምሮ ከ ደቡብ አፍሪካ የተላለፈው የ ኢትዮጵያ እና ቡኪናፋሶ የ እግር ኳስ ውድድር የኳስን መሰረታዊ ባህሪ በያዘ መልኩ ማለትም ማሸነፍ ወይንም መሸነፍ አንዱን መርጦ አብቅቷል። አዎን በ ኢትዮጵያ በኩል አራት ጎሎች ተቆጥረዋል። ጫወታው እንዳበቃ በመጀመርያ በጣም ተናደድኩ ትንሽ ቆይቼ ነገሩ አለመሞቱ ግን የ ቡድኑ ሞራል ምን ያህል ይሆን? የሚለው ብቻ አሳሰበኝ።ዛሬ ቅዳሜ ጫወታውን ደግሜ አየሁት።በ እውነት ትናንት ያልታዩኝ የተጫዋቾቻችን ድንቅ ጥበብ ታየኝ።ሰው አንድን ነገር ለመመልከት የረጋ ልቦና ይሻል የሚባለው ልክ ነው።ዛሬ ከስሜት ውጭ ሆኘ ስመከት ቡድናችንን የሚያስደንቁ ጥበቦቹ ታዩኝ።እናም የሚከበር ቡድን ግን አኛ ተመልካቾች ልናከብረው እና ልናደንቀው የሚገባ ነው ብዬ አሰብኩ።
በአንድ ወቅት ከ አስራዎች አመታት በፊት ግብፅ ውስጥ የ ብሔራዊ ቡድናችን (ለማጣርያ ይመስለኛል)ሲጫወት ቡድኑን ለማዋከብ የነበረው የ ተመልካች ዘዴ በጣም መጮህ እና ከ እዚህ በፊት በ ሰማንያ አና ዘጠና ሺ ሕዝብ የተሞላ ስታድዮም ውስጥ ተጫውቶ የማያውቀውን ተጫዋች ማዋከብ ነበር። በወቅቱ ቡድናችን የ አለም አቀፍ ጫወታ ተሞክሮ ስሌለው እና የ ሰላሳ ሺ ሕዝብ የሚይዝ የ አዲስ አበባውን ስታድዮም ብቻ ስለሚያውቅ ትልቅ ችግር ፈጥሮ ነበር። አሁን ያ አቅም ተፈጥሮ የ ጫወታው ቴክኒክ ሁሉ ጥሮ መስመር ላይ ነው ያለው። የተሞከሩት የ ጎል ሙከራዎች የ ዕድል ጉዳይ እንጂ ምርጥ ተጫዋቾች እንዳሉን ለመረዳት አይናችንን የሚከፍቱ ናቸው።አሁን የቀረን አንዲት ነገር ነች። ጀግንነት፣እራስን ማወቅ፣ካለምንም ጉራ ታላቅ ተጫዋቾች እንዳሉን ማወቅ፣ይህንንም ለቡድኑ መንገር።ሽንፈት የሚጀምረው እራስን ዝቅ አድርጎ ማየት ሲጀመር ነው።ቡክናፋሶች የ ጎል ዕድል ቢያገኙም፣በ ጫወታ ቢገዳደሩንም፣ አሁንም የማሸነፍ እድላችን እጃችን ውስጥ መሆኗን ማወቅ አለብን። መሸነፍ፣ፈተና፣ተስፋ መቁረጥ አንዳንዴ ተደጋግመው የተጫኑ የሚመስሉበት ጊዜ አለ። እዚህ ላይ ነው ጀግና የሚያስፈልገው። ”ቁርጥ ቀን ባይመጣ ሁሉም ጀግና ነበር” የሚባለው የ እዚህ ቀን ነው። ቡድናችን አሰልጣኞቻችን ሁሉ በአንድ መንፈስ ቀጣዩን ጫወታ እንደሚያሸንፉ በ ሙሉ ልብ እራሳቸውን ከማወቅ እና ከማክበር ጋር ይጫወቱ ይመኑ ታምር ይሰራሉ።
እዚህ ላይ በቡድናችን የሞራል መጠበቅ ላይ እክል ፈጥረዋል የተባሉ ወደፊት ጥብቅ ምርመራ የሚፈልጉ እና በቀላሉ
የማይታዩ ጉዳዮች እንደነበሩ ይወራሉ። ይህንን በተለይ አስልጣኝ ሰውነትም ሆኑ ምክትላቸው ተመሳሳይ ስህተት እንዳይሰሩ ለፖለቲካው አካላትም ሆነ ለሕዝቡ በድፍረት እንዲነግሩልን እንጠብቃለን። በእዚህ ዘመን ”የተሰወረ የማይታይ ያልታወቅ የማይገልጥ” የለምና። ለሁሉም ግን አሁን መደረግ ያለበት ቢያንስ ቀጣዩ ጫወታዎች እስከሚጠናቀቁ በትዕግስት የቡድኑንም ሆነ የደጋፊውን ህብረት እንዲጠበቅ ማድረግ ይመስለኛል።
ጀግንነት ፈፅሞ አለመሸነፍ አይደለም። ተሸንፎ መነሳት ነው። ጀግናን ጀግና የሚያሰኘው ፈፅሞ የማይሸነፍ ምትሃታዊ ፍጥረት ስለሆነ አይደለም በ ዕድል ወይንም በ ትንሽ ስህተት አልያም ችላ ብሎት ጀግና የመጀመርያ ሽንፈት ይሸነፋል። ሁለተኛ እና ሶስተኛ ላይ ግን የሚያስደነግጥ ብቻ ሳይሆን የሚያርበደብድ ይሆናል።የዓለማችን ጀግኖች ተሸነፉ ሲባሉ እንደገና ተነስተው ስለሚያሸንፉ ያለፈውን ሽንፈታቸው ከቶ ማን ሊያስበው ይቻላል? እንግሊዝን እስኪ በ አለም ዋንጫ ላይ የሚደርስባትን እንመልከት።እንዲያ ድንቅ ክለቦች ያላት ሀገር በዓለም ዋንጫ ላይ ግማሽ መድረስ ሲያቅታት ለ እንግሊዝ ሕዝብ እና መንግስት ሰቀቀን የማይሆን ይመስለናል ? ግን እንግሊዞች ኳስ ስለማይችሉ ነው የተሸነፉት? አይደለም። ኳስ እንዲህ ስለሆነች ነው። የ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ጫወታ ዛሬ አለፍ አለፍ እያልኩ ከ ቡክናፋሶ ጋር ያደረገውን ጫወታ ስመለከት እጅግ ድንቅ ተጫዋቾች እንዳሉን ግን እኛ ልናከብራቸው፣ልናደንቃቸው፣ ታላቅ ችሎታ እንዳላቸው አንዳንድ ቴክኒካዊ ስራዎችን እያስተካከሉ እንዲሄዱ እራሳቸውን ዝቅ እንዳያደርጉ መንገር በ ባለዑያዎች ብቻ እንደሚገባ አመንኩ። ይህ ደግሞ ለሽንገላ ሳይሆን ቀድሞ የነበረው ”እኛ ኳስ አይሆንልንም” የሚባልበት ጊዜ ላይ ላለመሆናችን ችሎታቸውን በ ልዩ አቀራረብ ያሳዩን ተጫዋቾች ምስክር ናቸው። ዛሬ ኢትዮጵያ የ እግር ኳስ ደረጃዋ ለ አለም አይደለም ለ እኛ ለ ኢትዮጵያውያንም ያስደነቀን ጉዳይ ነው። ወደ ኋላ ፈፅሞ መመለስ የለም!
በመጪው ማክሰኞ ከ ናይጄርያ ጋር በሚኖረው ውድድር ተአምር የመስራት ብቃቱም ሆነ አቅሙ አላችሁ።በ አንድ በኩል ናይጀርያ በትናንትናው ከ ቡክናፋሶ ጋር በተደረገው ጫወታ ቡድናችንን ዝቅ አድርጎ የማየት ሁኔታ ሊኖር እንድሚችል ይገመታል።ይህ ጥሩ ዕድል ነው።
በ እርግጥም ከ ቡክናፋሶ ጋር የሆነ አምላክ ከ እኛ ጋርም አለ። ከ ናይጄርያ ጋር ያለ አምላክ ከ እኛ ጋርም አለ። ቀጣዩን ከ ናይጄርያ ጋርም ሆነ ቀጥለው በሚከፈቱት ዕድሎች ቡድናችን እንዲያሸንፍ እኛ ተመልካቾች የምናደርገው ሁለት ነገር ነው። አንድ በ ስታድዮም ተገኝቶ መደገፍ ሁለተኛው እና ዋናው ማንም ችላ ሊለው ወይንም ሊረሳው የማይገባው ከልብ የሆነ ቢያንስ የ ጥቂት ደቂቃዎች ልመና ወደ እግዚአብሔር ማቅረብን ነው። ያኔ ሁሉም ግዴታውን ተወጣ ማለት ይቻላል።የ ኢትዮጵያን ቡድን ያወደሱ ብእሮች እንደገና ይቀረፃሉ።ዋልያዎች በርቱ!
ጀግንነት ፈፅሞ አለመሸነፍ አይደለም። ተሸንፎ መነሳት ነው። ጀግናን ጀግና የሚያሰኘው ፈፅሞ የማይሸነፍ ምትሃታዊ ፍጥረት ስለሆነ አይደለም በ ዕድል ወይንም በ ትንሽ ስህተት አልያም ችላ ብሎት ጀግና የመጀመርያ ሽንፈት ይሸነፋል። ሁለተኛ እና ሶስተኛ ላይ ግን የሚያስደነግጥ ብቻ ሳይሆን የሚያርበደብድ ይሆናል።
ኢትዮጵያ ለ ዘላለም ትኑር!
ጌታቸው
ኦስሎ

ከአሜሪካ የህወሓት ሰላዮች ዛቻ – (ከኢየሩሳሌም አርአያ)


አሜሪካ የመሸጉ የሕወሐት ሰላዮች ዛቻና ማስፈራሪያ መሰንዘር ጀምረዋል። አልፈው ተርፈው «ክስ» እንመሰርታለን ብለዋል። ለማስፈራሪያቸው የሚበረግግ ባይኖርም – ነገር ግን ነፃነት ባለበት አሜሪካ ያሉ የፍትህ አካላት በብርሃነ፣ ስብሃት፣ በረከት፣ አዜብ አሊያም ሽመልስ….የሚሽከረከሩ መስሎዋቸው ያለሃፍረት አንደበታቸውን ሞልተው ሲደነፉና ለማሸማቀቅ ሲሞክሩ መታየታቸው …ምን ያክል የሞራል ድቀት እንደተጠናወታቸው ያሳያል። ባለፉት ወራት ከተሰነዘሩ ተራ ስድቦችና ዛቻዎች የትላንቱ ለየት የሚያደርገው ነጥብ ስላለ ነው፥ ይህችን መልክት ለመፃፍ የተገደድኩት። እነዚህ ሰዎች አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ የመሸጉ የሕወሐት ሰላዮች እንደሆኑ ላሰምርበት እወዳለሁ። ከጀርባቸው ብርሃነ እንዳለ በግልፅ በአንደበታቸው አረጋግጠውልኛል። ዋናው አላማቸው ደግሞ « ሳንጋለጥ..ቀድመን እናሸማቅ፤..» ከሚል ከንቱ አስተሳሰባቸው የመነጨ ነው።
እናንተ በንፁሃን ደም የታጠባቹ ወንጀለኛ የብርሃነ ጀሌዎች፥ የፈለጋችሁትን ብትደረድሩ እናንተን ከማጋለጥ ወደኋላ የሚያፈገፍግ ብዕር የለም!! በአሜሪካ ተቀምጣችሁ ከምትፈፅሙት የስለላ ወንጀል ባሻገር ያለው የጀርባ ጉድፍ ታሪካችሁ ገና አልተነካም። ከአገራችን ባህል ውጭ በሚያሳፍር ፀያፍ ተግባር ተዘፍቃችሁ … በሴት እህቶቻችን ላይ ስትፈፅሙ የነበረው የቡድንና የተናጠል…የአመንዝራ -ሴሰኛ ድርጊታችሁ የማይታወቅ መስሎዋችሁ ከሆነ ተሳስታችኋል። በመንግስት ቢሮዎች ጭምር ምን አይነት ርካሽ ተግባር ስትፈፅሙ እንደነበረ የተሟላ ማስረጃ እንዳለ ልትገነዘቡ ይገባል። የምታመልኳቸውና የምታገለግሏቸው አገር ቤት ያሉ አለቆቻቹ ሁለት እህትማማቾችን በአንድ ሌሊት ከተገናኙዋቸው በኋላ አንገታቸውን በሰይፍ ቀልተው እልም ካለ ገደል ውስጥ የጨመሩ አረመኔዎች እንደሆኑና እናተም የእነርሱ«ዱካ» ተከታዮች እንደሆናችሁ ተግባራችሁ ይመሰክራል። ይህና ሌላው የወንጀል ተግባራችሁ በዝርዝር ለአደባባይ የሚበቃበት ጊዜ እሩቅ እንደማይሆን ልታውቁት ይገባል። ..ትላንት በአገር ቤት የተጀመረው እናንተን የማጋለጥ ሂደት ከማስጨነቅ፡በገንዘብ ለመደለል ከመሞከር ባለፈ የፌዴራል ፖሊሶችን በማሰማራት የግድያ ሙከራ ፈፅማችኋል። ለረጅም ወራት ለአልጋ ብትዳርጉም… ለተለመደው አረመኒያዊ ተግባራችሁ የተንበረከከ እንዳልነበረ ሁሉ ዛሬም የሚንበረከክ እንደሌለ ልታውቁ ይገባል። በጣም የሚገርመው «ክብራችን ተነካ» ለማለት መዳዳታቸው ነው፤ ለመሆኑ ክብር ምን እንደሆነ ያውቁታል?..ለሌላው ክብር የሌለው ስለ ክብር አንስቶ መናገር እንዴት ይቻለዋል?..በአገሪቱ የተለያዩ ስፍራዎች ያፈሰሳችሁትና አሁንም የምታፈሱት የንፁሃን ደም …ክብር ያለው የሰው ልጅ እንደሆነ አታውቁም?…ለነገሩ<ጥፋት> ብቻ ከተጠናወተው አዕምሮ ፥ ምንም መጠበቅ አይቻልም።
የዚህ መጣጥፍ መነሻ ወደሆነው ክስተት እንሻገር፤ በቅርቡ በወጣውና « ፍቅረኛሞቹ አዜብና ብርሃነ» በሚል ርዕስ ለንባብ ከበቃው ፅሁፍ ጋር በተያያዘ ነው፤…
ትላንት ሐሙስ ጃንዋሪ 24 2013 ከምሽቱ8፡14 ሰዓት “ሎዮላ” ሆስፒታል ውስጥ እያለሁ በBlocked Number ስልክ ተደወለልኝ፤ …ማንነቴን ካረጋገጠ በኋላ ..« ግርማ እባለለሁ» አለኝ፤ ..ማን አልከኝ?…ስል መልሼ ለማረጋገጥ ጠየኩት። « ግርማይ እባላለሁ» ሲል በትዕቢት አይነት መለሰ።(ልብ በሉ…ሁለት ስሞች ነው የነገረኝ).. ከንግግሩ ማለትም ከቃላት አጠቃቀሙ በመነሳት.. ማንነቱን ለመለየት አያስቸግርም።
…ስለ አለቃው ብርሃነና አዜብ ከደሰኮረ በሁላ በቁጣ « ማነው የነገረህ?» ሲል ሊያስፈራራ ሞከረ።…ፍ/ቤት እንኳ የመረጃ ምንጭህን አስገድዶ መጠየቅ እንደማይችል ያለማወቁ ብዙም አላስገረመኝም፤.የተለያየ ምልልስ አደረግን፤.ከዛም ጠንካራ ቃላት ከተለዋወጥን በኋላ «  ማወቅ አለብህ » ያለኝን በዛቻ መልክ ሰነዘረልኝ፤ ብርሃነ ኪ/ማሪያም (ማረት) እንዲሁም የአዜብ ወኪሎች የሆኑ ክስ ሊመሰርቱ እንደሆነ ተናገረ።…በበኩሌ ያለአንዳች ፍርሃት መልስ ያልኩትን ሰጠሁት፤ ስልኩንም ዘጋሁት።
እናነተ በወንጀል የተጨማለቃችሁ፥ አንድ ልታውቁት የሚገባ ነገር ..ተግባራችሁን ከማጋለጥ የሚያፈገፍግ ብዕር እንደሌለና እንደማይኖር በድጋሚ ልጠቁማችሁ እወዳለሁ!!..መረጃ ለሰፊው ወገን ማድረሱ ይቀጥላል!!
ኢትዮሚድያ – Ethiomedia.com – January 25, 2013

ድምጻችን ይሰማ የሚል ቲ-ሸርት ያደረጉ ሙስሊሞች ከስታዲየም ተባረሩ

በትላንትናው ጨዋታ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ለመደገፍ የታደሙት በደቡብ አፍሪካ የሚገኙት የሙስሊሙ ማህበረሰቦች ድምጻችን ይሰማ እና እንዲሁም መሪዎቻችን ይለቀቁ የሚሉ ቲሸርቶችን ለብሰው በመታየታቸው በሰኩሪቲ ፖሊስ እየተለቀሙ ከስታዲየም ግቢ እንዲወጠ ተደርገዋል ። አብዛኞቹን ለጥያቄ እንፈልጋችኋለን በማለት የወሰዷቸው ሲሆን ሌሎቹን ደግሞ ይህንን ለብሳችሁ እዚግ ስታዲየም ውስጥ መቆም አትችሉም በማለት አስረግጠው ነግረረዋቸዋል ።ከደቡብ አፍሪካ የማለዳ ታይምስ ዘጋቢ እንደአቀረበው ሪፖርት ከሆነ ማንኛውም የተቃውሞ የሚያሰሙ ነገሮችን በመንግስት ሃይሎች እና በኢትዮጵያ ኤምባሲ ትብብር ህብረተሰቡን ለመቆጣጠር እና መብቱ እንደተጋፉት ገልጾአል ። ይህ ለምን ሆነ በማለት የማለዳ ታይምስ ዝግጅት ክፍል አስተባባሪ ላቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ቢቆጠቡም በድጋሚ እናንተ ይህንን የማገድ ስልጣን የላችሁም ይህ ትእዛዝ ሊመጣ የሚችለው ከፊፋ አስተዳደር በደቡብ አፍሪካ ስፖርት ፌደሬሽን ስር ብቻ ሊሆን ይገባዋል እንጂ በሃገሪቱ መንግስታቶች የሚሰጥ ላይሆን ይገባዋል ብሎ ሲያነጋግራቸው  ይህ ያንተ ጉዳይ አይደለም በማለት የጥበቃ ክፍሎቹ ሲመልሱ በማስከተልም ከሙስና ጋር የተያያዘ ስራ እየሰራችሁ እንጂ ይህ ህገ ወጥ እንደሆነ ልባችሁ ያውቃቸዋል ሲላቸው ከስታዲየሙ ለማባረር እንደሞከሩ እና ከዚያም በጥበቃዎቹ ዋና ሃላፊ ጋር በመነጋገር ጉዳዩን ትኩረት እንዲሰጥበት እና እንደዚህ አይነት ነገሮች በግዴለሽነት ሊታዩ እንደማይገባ እና በአለም አቀፍ ህግ ሊያስቀጣቸው እንደሚችል ጠቅሶ ተመልሶ ወደ ስታዲየሙ ለመቀላቀል መብቃቱን ሪፖርተራችን ከስፍራው ያደረሰን ዘገባ ያመለክታል ። ከጨዋታም በኋላ የኢትዮጵያን ሽንፈት በስታዲየም የሰሙ ወገኖች እንደተናገሩት ከሆነ ይህ ጉዳይ እልባት ካላገኘ በሚቀጥለው ከናይጀሪያ ጋር ለሚደረገው ጨዋታ ሁሉንም ነገር ያዩታል እንዲያውም ከጨዋታ ውጭ ሊሆኑም ይችላሉ ስለዚህ የሰው ልጅ የሚፈልገውን ለማድርግ የሚችልበትን ነገር መንፈግ የለባቸውም በሃገራችን የነፈጉንን ነጽነት በሰው አገር አይሞክሩት ሲሉ ገልጠዋል ። አንዳንዶቹም በመሸነፋቸው ደስ ብሎናል ሲሉም ቁጭታቸውን ገልጸዋል ። በሌላም በኩል በትላንትናው እለት የሞአ አንበሳው ምልክት የያዘውን እና ልሙጡን ባንዲራ ይዘው እንዳይገቡ ከመከለከሉም ውጭ በስታዲየሙ ውስጥ በልሙጡ ባንዲራ ማስታወቂያ የተሰራባቸው ሬክላሞች እንዲነሱ መደረጉን የዝግጅት ክፍላችን ሪፖርተር ከስፍራው ዘግቦአል ።

በዳውሮ ዞን የህዝቡን ተቃውሞ መርተዋል የተባሉ ሰዎች ታሰሩ


ጥር ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በዳውሮ ዞን በማረቃ ወረዳ ከወረዳ እና ከሌሎች ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን ግጭት መርተዋል ከተባሉት መካከል አቶ ዱባለ ገበየሁ፣ አቶ ጎሳሁን ዶሳ ዶሻና አቶ ግዛቸው ታደሰ ከበደ በትናትናው እለት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቋል።
በዞኑ የሚታየው አለመረጋጋት ያሳሰበው መንግስት ግለሰቦቹ በአካባቢው የሚደረገውን ተቃዎሞ በማደራጀት በኩል እጃቸው አለበት በሚል እንዳሰራቸው፣ ቤቱ ለፍተሻ በሄደበት ወቅት ያነጋገርነው በአሁኑ ጊዜ በእስር ላይ የሚገኘው፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሀይሎች ድርጅት የደቡብ ክልል ዋና አደራጅ አቶ ዱባለ ገበየሁ ገልጸዋል።
አቶ ዱባለ በክልሉ ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር እርሳቸው የኢህአዴግ አባል በነበሩበት ጊዜ በተለይም የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት የደኢህዴግ የፖለቲካ ጉዳይ ሀላፊ የሆኑት አቶ አለማየሁ አሰፋ ቤተሰቦቹን እያሾመ ነው በማለት ገምግመዋቸው እንደነበርና አሁን የሚደርስባቸው ነገርም የዚያ በቀል መሆኑን ገልጸዋል
በአሁኑ ጊዜ ከአቶ ዱባለ ጋር በእስር ላይ የሚገኙት የማረቃ ወረዳ አቃቢ ህጎች መሆናቸውን አቶ ዱባለ ገልጸዋል
በማረቃ ወረዳ በማሪ አካባቢ ሰሞኑን በተነሳው የሕዝብ አመጽ ሕዝቡ በፖሊስ ላይ እርምጃ መውሰዱ ይታወሳል።  ሻለቃ በዛብህ ገዝሙ የተባሉ የዞኑ ፖሊስ ከፍተኛ አመራርና አንድ ወታደር በድንጋይ ተደብድበዋል።  አንድ የመንግሥት መኪና ተሰባብሮ ከጥቅም ውጪ መሆኑና የመኪና መንገድ በመቆፈር ግንኙነት እንዲቋረጥ መደረጉ ይታወሳል።
የፌዴራል ፖሊስ ከትናንትና ጥዋት ጀምሮ አካባቢውን መቆጣጠሩ ታውቋል።
ለአሁኑ ግጭት መነሻ የሆነው የአካባቢው ካድሬዎች መንግስት ነው የማሪና የዋካ ከተማ ህዝብ እንዲጋጭ እያደረገ ያለው በማለት በመናገራቸው መሆኑ ታውቋል። ካድሬዎቹ ከዚህ ቀደም ለማሪ ነዋሪዎች ዋካ ወረዳ አይገባውም ብላችሁ ተቃወሙ በማለት ሲቀሰቅሱ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።  መንግስት የወረዳ ማእከልነቱ ለዋካ እንዲሰጥ መወሰኑን ተከትሎ፣ ካድሬዎች ዳግም ወደ ሕዝቡ በመንቀሳቀስ እኛ አይደለንም መንግሥት ነው እናንተን ከዋካ ሕዝብ ጋራ ያጣላው፤ እኛ በሉ የተባልነውን ነው ያልነው  በሚል በመናገራቸው ተቃውሞው ሊነሳ መቻሉ ታውቋል። በአሁኑ ጊዜ የፌደራል ፖሊሶች በኣካባቢው በብዛት እንደሚገኙ ታውቋል። የወረዳውን ባለስልጣናት አስተያየት ለማወቅ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።