Friday, November 8, 2013

የኢትዮጵያዉያን ስቃይና መከራ በሳዉዲ አረቢያ

(በሳዲቅ አህመድ)

የመጣኸዉ ባዶህን ነው! ባዶ ሆነህም ትመለሳለህ!…ኢንተ-ጃኢ-ፋዲ ወተርጃእ-ፋዲ…የሳዉዲዎች አመለካከት!
የፈለጋቹበት ዉሰዱን ግን አትደብድቡን…ይላል ኢትዮጵያዊዉ…ለካስ አትደብድቡን ማለቱ የሚያስደበድብ ነበር…
አይደለም የሰዉ ልጅ እንስሳ እንኳ እንደዚህ አይደረግም። የምታዩአቸዉ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች በሳዉዲ ዜጎች ተይዘዉ ወደ ጀዋዛት (የስደተኛ መምሪያ) ሲወሰዱ ነዉ። እነዚህን ደሃና ከርታታ ኢትዮጵያዉያን በቁጥጥር ስር ያዋለዉ ያገሪቱ ፖሊስ ሳይሆን ያገሪቱ ዜጎች ናቸዉ።”እክስር የዱ!…እጁን ስበረዉ!…” ይላል አንዱ። ከታች ሆኖ የጣር ድምጽን የሚያሰማዉ ኢትዮጵያዊ “ሐላሊ…ሐላሊ… ላቤን ያፈሰስኩበት የልፋቴ ዋጋስ? በማለት ሲጠይቅ ዱላዉ ይጠነክርበታል።
ሰዉ የመሆን ማእረግን የተነፈገዉ ሌላኛዉ ኢትዮጵያዊ ደግሞ ዱላዉን እርግጫዉን እየዋጠ ስቃዩን ለመቀነስ “ኻላስ-አነ-ገልጣን…በቃ! በቃ! እኔ-ነኝ-ጥፋተኛ” ይላል። ከሳዉዲ ዜጎች አንደኛዉ ኢትዮጵያዉያኑ በመያዛቸዉ ባይከፋም ዱላዉን እንዲህ እያለ ይቃወማል “ተራ ኤይብ-መጅሙዓ-ተድርቡነ?… ይህ ነዉር ነዉ በህብረት ትደባደባላችሁ?” ግን ማን ሊሰማዉ። የኢትዮጵያዉያኑን የሰራ-አካል ማሰቃየት ብቻ ሳይሆን የሚያራግፉባቸዉም የቃላት ናዳ ስነልቦናን ይሰብራል።The Misery of Ethiopians in Saudi Arabia
አገር ዉስጥ ካለዉ ስቃይ ለመዳንና የተሻለን ህይወት ለራስም ለቤተስብም ለማምጣት የሚሰደዱት ኢትዮጵያዉን የሚደርስባችዉ መከራና እንግልት ተቆጥሮ አያበቃም። የሳዉዲ መንግስት የመኖሪያ ፈቃድ (ኢቃማ) የሌላቸዉ ወይም ከአሰሪያችዉ ጋር የማይሰሩ (ከፊል) በመጡበት የስራ ዓይነት (ሚህና) የማይሰሩት ከአገር እንዲወጡ ወይም የመኖሪያ ፈቃዳቸዉን እንዲያስተካክሉ የሰጠዉ ግዜ ስላበቃ ሰዎችን በዜግነት በሐማኖት ሳይለዩ ማፈሱን ተያዘዉታል። ባንጻሩ እነዚህ ሰደተኞችን ወደ ሳዉዲ በማስገባት ህገወጥ ተግባር የሚፈጽሙን የሳዉዲ ዜጎች መንግስቱ ወጥ የሆነ እርምጃ ሲወስድባቸዉ አይስተዋልም። ስለዚህ የሳዉዲ ዜጎችም ይሁኑ መንግስቱ ተጠያቂ ከመሆን አይድኑም።
ሰዎች ወደ ሳዉዲ እንዴት ይገባሉ የሚለዉን ስንቃኝ…
1) በሐሃጅና በኡምራ(ጸሎት)
ሰዎች ከተለያዩ አገራት ጸሎት እናደርጋለን በማለት ወደ ሳዉዲ ከደረሱ በሗላ እዚያዉ ይቀራሉ። እነዚህን ሰዎች ቀጥሮ በማሰራትም ይሁን ከቦታ ቦታ በድብቅ በማመላለስ ህገወጥ ተግባር ላይ የሚሰማሩት የሳዉዲ ዜጎች ናቸዉ። በነዚህ የሳዉዲ ዜጎች ላይ መንግስቱ በቂ የሆነ እርምጃ አይወስድም፤ የርምጃዉ ሰለባ የሚሆኑት ስደተኞቹ ብቻ በመሆናቸዉ መንግስቱ ተጠያቂ ነዉ።
2) የኮንትራት ስራ (ጠለብ)
በኮንትራት የሚመጡት ሰራተኞች ከዘመናዊ ባርነት ባልተናነሰ መልኩ ከፍተኛ ስቃይ ይደርስባቸዋል። ረጅም ሰዓታትን መስራት ብቻ  ሳይሆን ከኮንትራቱ ዉል ዉጪ ለዘመድና ለጎረቤት በተጨማሪ እንዲሰሩ የሚገደዱ አሉ። የጠለብ (የኮንትራት) ሰራተኞች ድብደባ፣ግርፋት፣አስገድዶ መድፈር (rape)ወዘተ ይደርስባቸዋል፤ በዚህም ሳቢያ ከአሰሪያቸዉ በመጥፋት በግል ተቀጥረዉ መስራት ይጀምራሉ።የሳዉዲ መንግስት ዜጎቹ የሰራተኛን መብት እንዲያከብሩ በቂ ግንዛቤን ባለመፍጠሩና  ይሕንን መስል ኢሰብዓዊ ድርጊት የሚፍጽሙትን ዜጎች ሕግ ፊት በተገቢዉ መልኩ ባለማቅረቡ ተባባሪ ያስመስለዋልና ተጠያቂ ነዉ።
2) በባህርና ድንበር አቋርጦ መግባት
የሳዉዲ ጎረቤት ከሆነችዉ የመን በኩል ብዙ ስደተኞች ወደ ሳዉዲ ይገባሉ። በተለይም ጀዛን የሚባለዉ የሳውዲ ግዛት ቀድም ሲል የየመን የነበረ ሲሆን ድንበሩን አንድ አይነት ጎሳዎች ብቻ ሳይሆን ቤተሰቦችም ይጋሩታል፤ በሁለቱም አገራት ያሉ የህግ አስከባሪ አካለት የሚዛመዱበት አጋጣሚ ብዙ ነዉ። በተቀነባበረ የኮንትሮባንድ ስራ ፖሊሶችና ድንበር ጠባቂ ሐይላት ሰዎችን በህገወጥ መንገድ በማስገባት ይተባበራሉ። የሳዉዲ መንግስት በድንበሩ ላይ ባሉ የህግ አስከባሪ ሐይላት ላይ በቂ ቁጥጥር ባለማድረጉ ተጠያቂ ነዉ።
ስደተኞች ወደ ሳዉዲ ሲገቡ የአገሪቱን ግዛቶች አቋርጠዉ ከቦታ ቦታ እንዲዘዋወሩ የኮንትሮባንድን ስራ የሚሰሩት የሳዉዲ ዜጎች ናቸዉ። ለምሳሌ አንድ ስደተኛ ከየመን ድንበር-ጀዛን ወደ ሪያድ ወይም ወደ ጂዳ መግባት ቢፈልግ በጭነት መኪና ከእቃ ጋር ተደብቆ እንዲገባ ይደረጋል፤ካልያም ወንዱ እንደሴት ቀሚስ-ሻሽ-የፊት መሸፈኛ እንዲለብስ ይደረግና የሳዉዲ ዜጎች እንደ ሚስት ወይም ልጆች ጭኖ በኮንትሮባንድ ሰዎችን ከቦታ ቦታ ያመላልሳሉ። በዚህ የኮንትሮባንድ ተግባር ፖሊስ (ሹርጣ) ተባባሪ የሚሆንበት አጋጣሚ ብዙ ነዉ። ለዚህ ህገ ወጥ ተግባር ከሳዉዲ መንግስት ሌላ ማንም ተጠያቂ ሊሆን አይችልም።
ወደ ሳዉዲ ለምግባት ኢቃማ (የመኖሪያ ፈቃድ) በዉድ ገዝተዉ የሚገቡ ስደተኞች አንዳንዴ የውሸት አሰሪያቸዉ (ከፊል) ጠፍቶባቸዉ የመኖሪያ ፍቃድ ለማዉጣት የሚቸገሩበት አጋጣሚ አለ። አንዳንዴም የመኖሪያ ፍቃዱን ቢያገኙም ፈቃዳቸዉ ሲቃጠል ለማደስ (ተጅዲድ) አሰሪያቸዉ ጠፍቶ ወይም ፍቃደኛ ሳይሆን ይቀርና ሳይወዱ በግድ ህገወጥ ይሆናሉ። ለዚህ ህገወጥና የተዝረከረከ አሰራር ከሳዉዲ መንግስት ሌላ ማን ተጠያቂ ሊሆን ይችላል?
በሳዉዲ ከተሞች ዉስጥ በስፋት ያሉት ጉዳይ ማስፈጸሚያ ቢሮዎች (መክተበል ሙአቂብ) የመኖሪያ ፍቃድን በተመለከተ የተለያዩ የማጭበርበር ስራዎች (ተዝዊር) በመስራት ይታወቃሉ። እነዚህን ጉዳይ ማስፈጸሚያ ቢሮ ከፍቶ ለመስራት የሳዉዲ ዜጋ መሆኑ ግዴታ ነዉ። በነዚህ ቢሮዎች የዉሸት የመኖሪያ ፍቃድን ከማዘጋጀት ጀምሮ፤ስደተኞች ያለ አሰሪያቸዉ (የዉሸት አሰሪም ቢሆን) ፍቃድ ከአገር ወጥተዉ እንዲመለሱ (ኹርጀል አዉዳ) እስክማድረግ ይሰራል። በነዚህ ቢሮዎች ዉስጥ ሌላዉ ቀርቶ ከስራ ሰዓት ዉጪ ከኢምግሬሽን (ጀዋዛት) በመመላለስ ባዶ ኢቃማ የመኖሪያ ፈቃድ በማምጣት የዉሸት የምኖሪያ ፍቃድ የሚሰጡ የመንግስት ሰራተኞች በርካታ (ነበሩ)ናቸዉ። በዉሸት ከአንድ አሰሪ ወደ ሌላ አሰሪ (ተናዙል-ነቅለል-ከፋላ) በማድረግም የሳዉዲ ህግ አስከባሪ አካላት በመተባበር ህገወጥነትን ያስፋፋሉ። ለዚህ ሁሉ ምስቅልቅል ተጠያቂዉ ዛሬ በየመንገዱ እንደ እንስሳ እየታደኑ ኢሰብዓዊ ተግባር የሚፈጽምባቸዉ ስደተኞች ሳይሆኑ የሳዉዲ መንግስት ነዉ። ከሳዉዲ መንግስትም ባሻገር አገሪቷን የተቆጣጠሩት የንጉስ አብድልአዚዝ ቤተሰቦች ያንበሳዉን ደርሻ ይይዛሉ።
በሳዉዲ ዉስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን በተለያየ የሙያ ዘርፍ የተሰማሩ ሲሆኑ በትክክለኛዉ መንገድ ሰርትዉ የከበሩ፤ላገር፣ለቤተሰብ፣ለወገን የተረፉ በርካታ ናቸዉ። ባንጻሩም እንደ ወጡ የቀሩ፤ ጤነኛ ሆነዉ ታመዉ የተመለሱም ይኖራሉ። በህገወጥ መንገድ አረቄና አስካሪ መጠጥን በመጥመቅ ብሎም በዝሙት የሚተዳደሩም ይኖራሉ። በሺዎች የሚቆጠሩ እዚያዉ-ሳዉዲ የተወለዱ ኢትዮጵያዉያን ህጻናት ሲኖሩ በአገሪቱ ደንብ መሰረት ሁለተኛ ደረጃን ከጨረሱ በሗላ የኮሌጅ ትምርት የማግኘት እድላቸዉ የመነመነ ነዉ (አይቻልም ማለት ይቻላል)። አቅም ያለዉ ልጆቹን ወደ አዉሮፓ እና አሜሪካ ለከፍተኛ ትምርት ሲልክ ዉስን አቅም ያለዉ ልጆቹን ወደ ኢትዮጵያ ልኮ በተለያዩ ኮሌጆች ያስተምራል። ሁለቱንም ማረግ ያልችለ ልጆቹ ያለትምርት የሚባክኑበት አጋጣሚ ሰፊ ነዉ።የባህረ ሰላጤዉን ስደት አስመልክቶ ብዙ ግዜ የሚነገረዉ ለአቅመ አዳምና ሔዋን ለደረሱት ኢትዮጵያዉያን ሲሆን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የወደፊት እጣ ፈንታቸዉን የማያዉቁ ሕጻናት ስለተዘነጉ ለነርሱም ማሰቡ ታላቅ ሰብዓዊ ግዴታ ነዉ።
በዚህ መከራና ስቃያ ዉስጥ ላሉ ኢትዮጵያዉን ለመታደግ ለዜጎቹ የሚቆረቆር ሁነኛ መንግስት ቢያሻም ሪያድ ያለዉ የሳዉዲ ኤምባሲና ጅዳ ያለዉ የቆንስላ ጽ/ቤት በመጣመር ዜጎችን የሚበድሉ ቢሆኑ እንጂ ለዜጎች ደራሽ ሲሆኑ አይታይም። ከተወሳሰበዉ የሳዉዲ ህግ ለመዳንና የመኖሪያ ፍቃድን ለማደስ ለፓስፖርት እድሳት ኤምባሲ የሚሔዱ ኢትዮጵያዉን ከፍላጎታቸዉ ዉጪ ለአባይ ቦንድ ግዙ ተብለዉ እንደሚቸገሩ ቀደም ሲል የተዘገበ እዉነታ ነዉ።ኤምባሲዉ ኢትዮጵያዉያንን በዘር በብሔር እየመተረ በልማት ስም አፍን ብልጓም ሲዘጋ ኢትዮጵያዉያን በየመንገዱ ላይ ከእንስሳ ባነሰ መልኩ እየተደበደቡ እየተገረፉ ክብራቸዉ ተገፎ ወደ ማጎሪያ ቤት (ተርኺል) እየተወረወሩ ነዉ።
ይህ ኢሰብዓዊ ተግባር አለም አቀፋዊ ትኩረት እንዲያገኝ ለተለያዩ የስብዓዊ መብት ድርጅቶች ማሳወቁ ተገቢ ሲሆን ጉዳዩ ከፍትኛ የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኝ ኢትዮጵያዉያን በያሉበት መንቀሳቀስ አለባቸዉ።የፖለቲካ ድርጅቶችም ኢትዮጵያዉያኑ የሚደርስባቸዉን በደል በማዉገዝ ለጉዳዩ ልዩ አትኩሮትን በመቸር አቅማቸዉ በቻለዉ መጠን ሊንቀሳቀሱ ይገባል። የተለያዩ የሐይማኖትና የሲቪክ ማህበራትም ይሁኑ አክቲቪስቶች በመጣመር የሳዉዲ ኤምባሲዎች በሚገኙበት አገራት ሰላማዊ ሰልፍን ቢያረጉ መግለጫዎችን ቢያወጡ የወገኖቻንን ስቃይና መከራን ማስቆም ባይችሉ እንኳ ሊቀንሱት ይችላሉና-ወገን ለወገን መድረሱ ግድ ይላል።
የመጣኸዉ ባዶህን ነው… ባዶ ሆነህም ትመለሳለህ…(ኢንተ፡ጃኢ፡ፋዲ ወተርጃእ፡ፋዲ) ለሚባሉት ኢትዮጵያዉይን ከኛ  ሌላ ደራሽ የላቸዉምንና እንድረስላቸዉ። ልብ ያለዉ ልብ ይበል!

Wednesday, November 6, 2013

የትኛውን‹‹አሸባሪ›› እንጠቁማችሁ? የኢህአዴግ ታጋይና ካድሬዎች ለፈንጅና ሽብር ቅርቦች ናቸው፡፡

Image
Nov5,2013
ትናንትና ኢቲቪ ‹‹የእኛ ጉዳይ›› ብሎ ስለ አልሻባብ ውይይት አቅርቧል፡፡ በእርግጥ እነ ኃ/ማሪያም ለገንዘብ ማግኛም ይሁን ለኢህአዴጋዊ ጀብድ በየ መድረኩ ‹‹አልሻባብ ተንኮታኩቷል›› ከሚሉት በተቃራኒ አልሻብብ አሁንም አስፈሪ፣ ስራ አጥነት መቅረፍ የግድ መሆኑን፣…..ሌላም ሌላም ከኢቲቪ የተለዩ የሚመስሉ ሀሳቦች በተወያዮቹ ተነስተዋል፡፡ እውን እነ ኃ/ማሪያም ከሰሙ ‹‹የአሸባሪዎች ስልታቸው እንጅ ጥያቄያቸው ተገቢ (ሌጅቲሜት) ነው››ም ተብሏል፡፡ ነገሩ ተወያዮቹ ከነ ሽመልስ፣ በረከት፣ ኃ/ማሪያም እንደሚሉዩ ማየት የሚቻለው ስለ ኢትዮጵያ ‹‹ሽብርተኛ›› ብዙም አለማለታቸው ነው፡፡
ሆኖም በስተመጨረሻ ‹‹ሽብርን ለመግታት አስቀድሞ መረጃ ስለመስጠት፣ ከፖሊስ ጋር ስለመስራት….›› የተሰጠው ማሳሰቢያ ከእነ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ጉትጎታ ጋር የው ተመሳሳይ ነው፡፡ ምክንያቱም የኮሚኒቲ ፖሊስ፣ ደህንነትም ሆነ ሌሎቹ ‹‹አሸባሪ›› ብለው መረጃ አሰባሰብን ብለው ያሰሯቸው ኢትዮጵያውያን ፈንጅ ለማፈንዳት ይቅርና ፈንጅ እንኳን በእጃቸው ነክተው የማያውቁ ናቸው፡፡ እስክንድር ነጋ የታሰረው ፌስ ቡክ ላይ እየጻፈ በነበረበት ወቅት ነው፡፡ ርዕዮት አለሙ አሸባሪ ተብላ የተያዘችው ‹‹በቃ!›› በሚል አዲስ አበባ ውስጥ የተለጠፈን ጽሁፍ ፎቶ ስታነሳ በመገኘቷ መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡ አቡበክርና ሌሎች የኮሚቴው አባላት፣ ውብሸት ታዬ፣ በቀለ ገርባ…… ይልቅ የኢህአዴግ ታጋይና ካድሬዎች ለፈንጅና ሽብር ቅርቦች ናቸው፡፡
እውነቱን ለመናገር ፌስ ቡክ ወይንም ድህረ ገጽ ላይ ጽሁፍ ሲለጥፍ አሊያም ሲያነብ የተገኘን ሁሉ ይጠቆም ማለት ሌላ መንግስታዊ ሽብር፣ ሌላ እብደት ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ በይፋ ኢንተርኔትና ኢንተርኔት ቤቶችን መዝጋት ይቀላል፡፡ ካልሆነ የአቶ መለስን ፎቶ ለማየት፤ አይጋ ፎረፍም፣ ኢርታን አሊያም ሌላ የፓርቲውን ፕሮፖጋንዳ የሚያሰራጩትን ለማንበብ የሚገባ ጀማሪ ካድሬም ካልሆነ የሚገኝ አይመስለኝም፡፡
በእርግጥ ‹‹መረጃ የማሰባሰቡን›› ስራ ከጀመሩት ቆይተዋል፡፡ ኢንተርኔት ቤት ባለቤቶችና ሰራተኞቻቸውን ‹‹የተለየ ነገር የሚጽፍ ሰው ካጋጠማችሁ ሪፖርት አድርጉ!›› እንደሚሏቸው ብዙዎቹ አረጋግጠውልኛል፡፡ እንግዲህ የተለየ የሚጽፈውን ለማወቅ ‹‹ቻት›› የሚያደርገውን ሁሉ ለአልሻባብ ይሆን ለሌላ መሆኑን ማለት ሊኖርባቸው ነው፡፡ ፌስ ቡክ፣ ቲውተር…ብቻ ኢንተርኔት ላይ የተለየ የሚጽፍን ሰው እንዴት ማወቅ ይቻላል? ራሱ የተለየ ማለትስ ምን ማለት ይሆን? መቼም ደህንነቶቹ ስለ ሽብር ከሚያወራ ይልቅ የባለስልጣናትን አስቂኝ ፎቶ የለጠፈን ‹‹አሸባሪ!›› ብለው ከረቼሌ እንደሚከቱት አያጠራጥርም፡፡
ታዲያ በአዜብ መስፍን፣ አባዲላ፣ በረከት፣ ሽመልስ…….የቀለደ፣ ፎቷቸውን ያጣመመ፣ ያጣመሙት ሀሳብ ላይ ትችት ያቀረበ ሁሉ ‹‹አሸባሪ›› ተብሎ መረጃ ከተሰባሰበበት የሚቀረው ማን ነው? የሴቶች፣ የወጣቶች…..ሊግ አባላትማ ከፌስ ቡክ ይልቅ ስብሰባ ማዕከል፣ ቀበሌ ውስጥ ነው ተሰብስበው የሚውሉት፡፡ ተዘግቶም ቢሆን ኢቲቪን ቢያፈጡበት ይወዳሉ፡፡ እንዲያው ኢንተርኔት ቤት ቢያዘወትሩስ ማን መረጃ ያሰባስብላቸዋል? ሌላ አካባቢስ ማን ጆሮ ይጠባላቸዋል? የድጋፍ ሰልፉስ? አሸባሪነት ካድሬ በመሆንና ባለመሆን፣ ድምጽን ከፍ አድርጎ በመጠየቅና ባለመጠየቅ፣ ስለ ሰብአዊነት በመቆምና ባለመቆም መካከል የተቀመጠ ማሸማቀቂያ ካልሆነ በስተቀር ምን ሊባል ይችላል?
‹‹በቃ›› የሚልን ብቻ ሳይሆን ፈንጅ የሚያጠምድን አሸባሪ ፎቶ ማንሳት ወይንም ስለ ጉዳዩ መጻፍ የጋዜጠኛ ስራ ነው፡፡ እኔ በበኩሌ በዚህ ጉዳይ መረጃ መስጠት የሚደፍር ጤነኛ ሰው ይኖራል ብዬ አላምንም፡፡ መስጠትም አያስፈልገውም፡፡ መስጠት ቢያስፈልግ ግን አሸባሪ መባል ያለባቸው ለምን ‹‹በቃ›› ተብሎ እንደተጻፈ ሳያውቁ ጉዳዩን ሽብር አድርገው የሚቆጥሩት ናቸው፡፡ እውነተኛና ሽብርን የሚዋጋ መንግስት ቢሆር ‹‹በቃ›› ያለውን ሲያጡ በንዴት ፎቶ ግራፉን የሚያነሱትን ጋዜጠኞች የሚያስሩት ካድሬዎች ላይ ነው መረጃ መሳባሰብም መጠቆምም ያስፈልግ የነበረው፡፡
በግልጽ የሚታየው ‹‹አሸባሪነት›› መጀመሪያ መቀረፍ ይኖርበታል፡፡ ይልቁንስ ‹‹በቃ›› ከሚባለውና ለኢህአዴግ ከፈንጅም በላይ ከሚያስበረግገው ጉዳይ በስተጀርባ ያለው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጭቆና እና ኢፍትሃዊነት ጥቆማ መስጠት ቢቀድም የተሻለ ነው፡፡ ከዚያም በኋላ ስለ አሸባሪ ማውራት ይቻል ይሆናል፡፡ ምዕራባዊያን ዜጎቻቸው ትምህርት ቤትም ሆነ ሌላ ቦታ ሰው ሲፈጁ ንክ፣ እብድ እንጅ አሸባሪ ብለው አይጠሯቸውም፡፡ አንድ ከመካከለኛው ምስራቅ የመጣ ሸክ መስጊድ ውስጥ ምዕራባዉያንን የሚያጥላላ ሰበካ ሲያደርግ ግን አሸባሪ ይሉታል፡፡ ኢህአዴግ ይህን ወደ ተቃዋሚና አባልነት አውርዶታል፡፡ ከወራት በፊት ባህርዳር ላይ ንጹሃንን የጨፈጨፈው ፖሊስ ለስርዓቱ የቀመ ስለነበር አሸባሪ አልተባለም፡፡ ለፖለቲካው ይጠቅም ዘንድ የሸክ ኑሩ ሞት ሽብር ተደረገ፡፡ ድራማ ነው የሚባለው እንዳለ ሆኖ ኢህአዴግ ባህርዳር ላይ ንጹሃንን የቀጠፈው ፖሊስ አንድ ቀን ከተቃዋሚዎች ስብሰባ ላይ መገኘቱ መረጃ ቢሆረው ተቃዋሚዎቹን በቀጥታ ከአልቃይዳ ጋር አገናኝቶ ለመውቀጥ ጊዜ አይፈጅበትም ነበር፡፡ የባህርዳሩም ሆነ የሸህ ኑሩው ድራማ ላለመሆኑ ምንም ማስረጃ አልተገኘም፡፡ ሽብርተኝነትን በንጹሃን ላይ የሚተውነውንና ‹‹ጠቁሙን›› የምትሉንን ሽብርተኛ በምን መለየት እንችላለን? ለኢህአዴግን የስልጣን ጥያቄ፣ ሰብአዊ መብት፣ ዴሞክራሲ፣ የአገር ጉዳይ፣ የሀይማኖት ጉዳይ፣ ሰላማዊ ሰልፍ…..ማንሳት ሽብርተኝነት ነው፡፡ ከእስክርቢቶ ውጭ ይዘው የማያውቁትን ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች፣ ሰልፈኞችና ሌሎችም ፈንጅና መሳሪያ ከያዙት በላይ ያስፈሩታል፡፡ አገር ውስጥ ካሉ ተቃዋሚዎች ይልቅ በየ ቀኑ ‹‹ ተስማማ፣ ተፈራረመ…›› ሲባል የምንሰማው መሳሪያ አንግተው አብረውት ካደጉት ኦብነግና ኦነግ ጋር ነው፡፡ ምክንያቱም አንድ አይነት ቋንቋ ይናገራሉ፡፡ ይግባባሉ፡፡ አልሻባብም ቢሆን ለመደራደር ስላልፈለገ ይሆናል እንጅ ኢህአዴግ ከሰማያዊ፣ አንድነት፣ መድረክ ቀድሞ ሊደራደረው እንደሚችል የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ የኦብነግንና የኦነግን መሪዎች ‹‹ምህረት›› ተደርጎላቸው፣ ቤትና መኪና ተሰጥቷቸው እየኖሩ እነ ርዕዮት፣ በቀለ፣ እስክንድር፣ አቡበክር ላይ ጥቆማም ሆነ እስራት ሲደረግ ‹‹ሽብር›› ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ልክ እንደ እነ ርዕዮት፣ በቀለ፣ አንዱአለም፣ አቡበክር፣ እስክንድር የሰብአዊ መብቱ እንዲከበርለት ይፈልጋል፡፡ በእምነቱ ጣልቃ የሚገቡበትን አጥብቆ ይቃወማል፡፡ ፍትህ ይፈልጋል፡፡ መብቱ እንዲከበርለት ይከራከራል፡፡ ይህን ሁሉ ታዲያ ጮህ ብሎ ሲናገር ለኢህአዴግ አሸባሪ ነው፡፡ ታዲያ ይህን ሁሉ መብት ጠያቄ፣ የፌስ ቡክ፣ ቲውተር፣….ኢንተርኔት ተጠቃሚ ላይ እንዴት ጥቆማ ማድረግ ይቻላል? ስንቱን አሸባሪ ላይ መረጃ ተሰጥቶበት ያልቃል? ለምንስ ተብሎ?
የሚያሳዝነው ደግሞ እንዲህ አዘናግተውን፣ እንዲህ የሽብርን ትርጉም አጥፍተውብን እውነተኛዎቹ አሸባሪዎች ሲመጡ የምንጎዳው እኛው መሆናችን ነው፡፡ መቼም መንገድ አስዘግተው የሚጓዙት ባለስልጣናት ላይ ፈንጅ ሊፈነዳ አይችልም፡፡ ቤተ መንግስት ውስጥም ቢሆን የፓርቲው ልዩነት ካልሆነ በስተቀር (ሲጠበቅ በጣም ዘገየ) ፈንጅ አይፈነዳም፡፡ እነሱማ ምን ይሆናሉ?

ህወሀት በእነ አቶ ስየ ላይ የጀመረውን ዘመቻ ቀጥሎበታል



 ኢሳት ዜና :-ህወሀት በውስጡ የተነሳበትን መከፋፈል ለማስቀረት በእነ አቶ ስብሀት ነጋ የሚመራው ቡድን የቀድሞ ታጋዮችን በማሰባሰብ ህወሀትን ለማዳን በሚረባረብበት ጊዜ፣ በአቶ ስየ አብርሀ እና ቤተሰቦቻቸው ላይ የተጀመረው ዘመቻ ግን እንደቀጠለ መሆኑ ታውቋል። አቶ ስየ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴያቸው በእጅጉ የተገታ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ( ኢቲቪ) ” የነቀዙ ሀይሎች” በሚል በእርሳቸውና በአቶ ታምራት ላይኔ ላይ የዶክመንታሪ ፊልም ሰርቶ ማዘጋጀቱ ታውቋል። ፊልሙን ለምን አሁን ለመስራት እንደተፈለገ የታወቀ ነገር የለም። ይሁን እንጅ በህወሀት እና በመንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሀሳብ አመንጭነት ፊልሙ መዘጋጀቱን ለማወቅ ተችሎአል።

የአቶ ስየ ታናሽ ወንድም አቶ ምረተአብ አብርሀ በሙስና ተከሰው በእስር ላይ ከሚገኙት ከአቶ ገብረውሀድ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብሎ ዘብጥያ ቢወርዱም፣ ሰሞኑን በዋለው ችሎት ግለሰቡን በሙስና የሚያስከስስ መረጃ ሊገኝ አልቻለም። አቃቢ ህግ አቶ ምርተአብን ለመልቀቅ ባለመፈለጉ ፣ በምርመራው ወቅት ታክስ እንዳጭበረበሩ ተደርሶበታል በሚል ከሙስና ጋር ባልተያያዘ ክስ ተመልሰው እንዲታሰሩ አድርጓል። ፍርድ ቤቱ ጉዳዩ ምክር ያስፈልገዋል በማለት አቶ ምረተአብን ለመፍታት ሳይደፍር ቀርቷል።
በጉዳዩ ላይ አቶ ስየ አስተያየት የሚሰጡ ከሆነ ለማነጋገር ዝግጁ መሆናችንን እንገልጻለን።

Monday, November 4, 2013

የውጭ ሃገር ዜጎች ውጥረት ጭንቀት እና ስጋት በሳውዲ አረቢያ !


ኖቬበር 4 2013 የምህረት አዋጁ መጠናቀቅ ተከትሎ በውጭ ሃገር ዜጎች ላይ የሚደረገው የቤት ለቤት አሰሳው አይቀሬነት እይተነገረ ነው ።
ለ 3 ወር የተራዘመው የሳውዲ አረቢያ መንግስት የስደተኞች ምህረት አዋጅ የፊታችን ሰኞ ኖቬበር 4 2013 መጠናቀቁን ተከትሎ ጭንቀት ስጋት እና ውጥረት በትለያዩ ሃገራት ዜጎች ላይ ነግሷል። ይህ አዋጅ ቀደም ብለው ከወጡት የሳውዲ አረቢያ የስደተኞች ህግ የንጉሱ ትዕዛ ያረፈበት አሊያ « አምረል መሊክ » መሆኑ የተፈጻሚነቱ አይቀሬነት በውጭ ሃገር ዚጎች ላይ ያለውን ስጋትን ከወትሯው ለየት እንዲል አድርጓታል ።
ከእንግዴህ ሳውዲ አረቢያ ውስጥ በፈለጉት የስራ ዘርፍ እንዳሻቸው ተሰማርተው መንቀሳቀስ እንደማይችሉ ህጉ እንደማይፈቅድላቸው ቀደም ብለው የተረዱ አያሌ የውጭ፡ሃገር ዜጎች ቤተስቦቻቸውን ወደ ሃገራቸው ሸኝተዋል አሊያም ላይመለሱ ጎዛቸውን ጠቅልለው ከሃገሪቷ በመውጣት ላይ መሆናቸው እይተነገረ ነው።
በተለይ ያለመኖሪያ ፈቃድ ወልደው የከበዱ ኢትዮጵያውያን ሪያድ እና ጅዳ ላይ በብዛት እንዳሉ እይተነገረ ባለበት በዚህ ቀውጢ ወቅት የነዚህ ዜጎቻችን እጣፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል በህብረትሰባችን ውስጥ ያለው ጭንቀት ከመቸውም ግዜ የከፋ አድርጎታል። ጅዳ እና ሪያድ ኢትዮጵያውያን በብዛት ይኖሩባቸዋል ተብለው የሚነገርላቸው አካባቢዎች በሳውዲ ጸጥታ ሃይሎች ፍተሻ እንደሚካሄድባቸው ውስጥ አዋቂ ምንጮች በመግለጽ ላይ ናቸው ።
ከጅዳው ይልቅ በብዛት በተለምዶ ባህር ሃይል እይተባሉ የሚነገርላቸው ድበር አቋርጠው ህገወጥ በሆነ መንገድ ወደ ሳውዲ ምድር የገቡ ዜጎቻችን ሪያድ ከተማ ውስጥ በተለምዶ መንፉሃ ኡም ሃማም ነስሪያ እና ነሲም የከተሙ በመሆናቸው በአካባቢው ባሉ ኢትዮጵያውያን ላይ ያለው ስጋት ጨምሯል። ትላንት ምሽት ሪያድ ከተማ መንፉሃ እና ነሲም አካባቢ አልፎ አልፎ ፍተሻ እንደነበር የሚጠቁሙ ምንጮቻችን ከግዜው ገደብ መጠናቀቅ ጋር ተዳምሮ ውጥረትን መፍጠሩ ይነገራል።
በአብዛኛው ሪያድ ውስጥ በንግድ እና በት/ቤት አውቶብስ ትራንስፖርት አገልግሎት ስራ ላይ እንደተሰማራ የሚነገርላቸው ዜጎቻችን የሳውዲ መንግስት ያወጣው ህግ ብዙም እንዳልተመቻቸው ይናገራሉ። በዚህም መስረት ከፊታችን ኖቬበር 4 2013 የምህረት አዋጁ የግዜ ገድብ መጠናቀቁን ተከትሎ በእለት ተዕለተ እንቅስቃሴያቸው ላይ አሉታዊ ተጸኖ ስለሚኖረው አብዛኛው የንግድ ቤቶች ተዘግቶ ሊውሉ እንደሚችል እና አብዛኛው የት/ቤት ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ የአውቶብስ ባለቤቶች የስራ ገበታቸው ላይ ሊገኑ እንደማይችሉ እየተነገረ ነው። ይህ በዚህ እንዳለ በባህር ወደ ሳውዲ አረቢያ ህገወጥ፡በሆነ መንገድ እንደገቡ የሚነገርላቸው ዚጎቻችን በየጎዳናው ያለ ስራ ለመባዘን ተገደዋል። እንዚህ ዜጎች የመኖሪያ ፈቃድ ካላቸው ዜጎቻችን ይልቅ ያለምንም ስጋት በነጻነት ሪያድ ከተማ ላይ በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸው የነገራል።
በመጨረሻም የግዜ ገድቡ መጠናቀቁን ተከትሎ በሚደረገው አሰሳ ጉዳያቸው በሂደት ላይ ያሉትን ወገኖች እንደማይመለከት የሚናገሩ የሳውዲ ጸጥታ ሃይል ምንጮች የምህረት አዋጁን መራዘም አስመልክቶ እስካሁን ምንም ያሉት ነገር እንደ ሌለ ለማረጋገጥ ተችሏል ።
ከዚህ በታች የሚታየው ሰዕላዊ መግለጫ በሪያድ በተለምዶ መንፉሃ እየተባለ የሚጠራ አካባቢ የትላንት ውሎ ነው።
Ethiopian Hagere ጅዳ በዋዲ

Saturday, November 2, 2013

“አንድነት” በአባላቶቹ ላይ የሚደርሰው ጥቃት መባባሱን ገለፀ


“አንድነት” በአባላቶቹ ላይ የሚደርሰው ጥቃት መባባሱን ገለፀ
አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) በአባላቱና በደጋፊዎቹ ላይ የሚደርስባቸው ጥቃትና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ መባባሳቸውን ገለፀ፡፡

ከትላንት በስቲያ ፓርቲው በፅ/ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት፤ ከ2003 አንስቶ በአባላቱና ደጋፊዎቹ ላይ የደረሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በዝርዝር አቅርቧል፡፡ ፓርቲው “የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሪፖርት” በሚል ባወጣው ሰነድ፤ ከተዘረዘሩ ጥቃቶች መካከል:- በድብደባ አካል ማጉደል፣ በህገወጥ መንገድ በቁጥጥር ስር ማዋል፣ ማሰቃየት፣ ማስፈራራትና መዛት እንዲሁም በማስገደድ መረጃ ከፓርቲያቸው እንዲያመጡ ማድረግ፣ የመኖሪያ ቦታን በህገወጥ መንገድ መበርበር፣ ይዞታና ንብረትን ያለ ካሳ ነጥቆ መውሰድ… የሚሉት ይገኙበታል፡፡

አቶ ደምሴ መንግሥቱና አቶ ገበየሁ ይርዳው የተባሉ የፓርቲው አመራሮች፤ በአባላትና ደጋፊዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደመጣ ጠቁመው፣ ጥቃት የደረሰባቸው አራት አዛውንት አባላቶቻቸው ጉዳታቸውን በአካል በማሳየት በህገመንግስቱ እውቅና የተሰጣቸውን:- በህይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነት እንዲሁም በህግ ፊት እኩል የመታየት ተብለው የተዘረዘሩት መብቶች መጣሳቸውን ገልፀዋል፡፡

http://www.addisadmassnews.com

አሳዛኝ ዜና- ስደተኞቹ በሙሉ አለቁ!


ከኒጀር ተነስተው ፣ ሰሃራ በረሃን በማቋረጥ አልጄሪያ ለመድረስ፣ ከዚያም ወደ ሌላ አገር ለመሻገር አንድ መቶ የሚሆኑ ስደተኞች በአንድ መኪና ታጭቀው ጉዞ ይጀምራሉ።
ሰሃራ በረሃን እንዳጋመሱ የተጫኑበት መኪና ይበላሻል። በዚያ በረሃ፣ መኪና ጠጋኝ ቀርቶ ፣ ቀና ቢሉ ሰማይ፣ ጎንበስ ቢሉ ድንጋይ ካልሆነ ምንም አልነበረም። የሚያደርጉት ጠፋቸው። ማንም የሚደርስላቸውም አልነበረም። በዚህ ሁኔታ ቀናት ተቶጠሩ። የቋጠሯት ጭብጦና እፍኝ ውሃ አለቀች። ቀስ በቀስም አንድ በአንድ እያሉ በውሃ ጥምና በረሃብ ይሞቱ ጀመር።
በመጨረሻም አንድ ዘላን ድንገት ሲያልፍ ያየውን በመናገሩ በሂሊኮፕተር ከስፍራው ሲደረስ ሁሉም፣ አንድም ሳይቀር፣ በውሃ ጥም ሞተውና ወድቀው፣ አንዳንዶቹም ባልታወቀ አውሬ ተበልተው ተገኙ። የበለጠ የሚያሳዝነው 92ቱ ሴቶችና ህጻናት ናቸው። ዜናውን ሲ ኤን ኤን ዛሬ ኦክቶበር 31 አወራው -

Friday, November 1, 2013

ህወሓት አይድንም፤ እያቃሰተ ነው (አስገደ ገብረስላሴ ከመቀሌ)


272d8-599201_480729571949477_370096823_n
‹‹የህ.ወ.ሓ.ት  ትንሳኤ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ድላችን የማይቀር ነው ›› ስብሓት ነጋ

በጌታቸዉ  አረጋዊ  የህ.ወ.ሓ.ት ኣባልና የድምፅ ወያነ ጋዜጠኛ  «ውራይና » የሚል በትግርኛ ቋንቋ የተዘጋጀ ለአራተኛ ጊዜ በነሃሴ ወር 2005 ዓ/ም የታተመ መፅሄት ስብሓት ነጋ  የህ.ወ.ሓ.ት   ፈላስፋ ቃለ መጠይቅ ያደረገበት መፅሄት በፅሞና  ኣነበብኩት። የመፅሄቱ ዋና ይዘት   ‹‹ህ.ወ.ሓ.ት እናድናት›› ነዉ የሚለዉ ስብሓት ነጋ በመፅሄቱ የተካተቱ ብዙ ስንክሳራዊ  ሃተታ ተናግሯል ።
  • አሁን ማለት የፈለግኩት በመፅሄቱ የተካተቱ በሙሉ መልስ ለመስጠት አይደለም፡፡ ምክንያቱም የስብሓትን ስንክሳር መልስ ለመስጠት  ከፈለኩ ግዜ አይገኝም  መፅሃፍም  ሊሆን የሚችል ነዉ። በመሆኑም አለፍ አለፍ በማለት  የስብሓትን አንኳር አንኳር ነጥቦች መልስ ለመስጠት እሞክራለሁ።
ሌላ ይህ ፅሁፍ መልስ ለመስጠት የተገደድኩት የ ህ.ወ.ሓ.ት መሪዎች ለትግርኛ ቋንቋ  ማዳበርን  በትግርኛ ስነ-ፅሁፍ ለማስፋት ብለዉ በፅሁፍ ቢናገሩ እጅጉን የሚደገፍና የትግራይ ህዝብ መስዋእት ነበር። ይህ ደግሞ ማንም ኢትዮጵያዊ  ይድግፈዋል፤፤
የ ህ.ወ.ሓ.ት መሪዎች ግን ከረጅም ጊዜ ጀምረዉ ለትግራይ ህዝብ በጠባብነት ለመነሳሳት ሲፈልጉ ወይ መምቻ ሃይል ሊጠቀሙበት ሲፈልጉ የሚናገሩት  የሚፅፉበት ኢትዮጵያዊ አጀንዳ እያለና  ያለ ትግራይ ህዝብ የሚነገር የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጉዳይ አድርገዉ እንደመናገር ፈንታ በድብቅ ይናገራሉ።
ስብሓት ነጋም በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ሃገራችን ብዙ ደንቃራ ሁኔታዎች ተደቅነውባትና ህዝቡ በብዙ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፖለቲካዊ  ችግሮች አጋጥመውት እያሉ ለትግራይ  ለአንድ ክልል ከ4-5 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ለብቻዋ የሚወከል ህ.ወ.ሓ.ት ትንሳኤ መተንበይ ሌላዉ የኢትዮጵያ ህዝብና ክልሎች … በሂወት ካሉት በታች ከሞቱት  በላይ የሆኑ ህዝቦችና ክልሎች እንደማሰብ ትግራይን ጨምሮ ማለት ነዉ። ለትግራይ ብቻ  ማሰብ ለስብሓት ነጋ ጠባብ ሊያስብላቸዉ የሚችል ይመስለኛል።
በሌላ በኩል የስብሓት ነጋ ትንሳኤ ሙዉታን ሲለን የህ.ወ.ሃ.ት ትንሳኤ ሙታን ለመመለስና የህ.ወ.ሃ.ት  መሪዎች  ከመሰነጣጠቅና ከመክሰም እንዴት እናድነዉ ጭንቀቱ እንጂ የትግራይ ህዝብ ባጠቃላይ የሃገራችን ህዝቦች ብሄር ብሄረሰቦች ከዲሞክራሲና  ሰብኣዊ መብቶች ነፃነትና አፈና አስተዳደር እንዴት እናድናት አይደለም ጭንቀቱ፤፤ ይህ ካልኩ በኃላ ወደ መፅሄቱ ላይ የሰፈረዉ አንዳንድ መልስ ለማስቀመጥ እሞክራለሁ።
ስብሓት ነጋ በአሁኑ ጊዜ ያለዉ  የህ.ወ.ሓ.ት አመራር ለነዚህ ለአመታት እያጠራቀማቸዉ የቆየ ችግርን በፍፁም ነፃነት በፍፁም አባታዊነት በትክክል ከተረዳቸዉ  መረዳትም ያለበት ነዉ።‹‹የ ህ.ወ.ሓ.ት ትንሳኤ ጊዜ ይወስዳል እንጂ ድላችን የማይቀር ነዉ።›› ይላል ውራይና መፅሄት ነሃሴ 2005 ገፅ 4 ሶስተኛ  አምድ አዲስ መስመር ሁለት
ስብሃት ነጋ ከእንግዲህ ወዲህ የምናውቀዉ  ህ.ወ.ሓ.ት ከነበሩበት ብዙ ችግሮች ሲያሳየዉ የነበረ መገላበጥ የተሳሳቱ ሃገራዊና አህጉራዊ አቋሞች በተለይ ደግሞ በሃገር ሉኣላዊነት የሚመለከት ሃገራዊ ሃላፊነት የጎደለዉ ብዙ ስህተትና ጥቁር ነጥብ  ቢሰራ በፀረ-ደርግ የነበረዉ አቋም የኃላ ኃላ ለስልጣኑና የግዛቱን ማስፋፋት ሲል ያመጣዉ አገር አቀፍ አመለካከት ለኢትዮጵያ ህዝብ ለጊዜዉ ከፋሽስታዊ   ደርግ አፈና አድኖታል። ተነፃፃሪ ሰላም ያመጣ ይመሰል ነበር ሆኖም ግን   የህ.ወ.ሓ.ት  አመራርና እሱን እሚመስሉ እሱ የፈጠራቸዉ የህ.ዋ.ሓ.ት ስሪት ፓርቲዎች ልክ ደርግ መጀመሪያ ወደ ስልጣን ሲመጣ  ኢትዮጵያ ትቅደም ያለ ምንም ደም እንዳለና  ቀስ በቀስ ወታደራዊ ባህሪዉ አገርሽቶበት ፍፁም ለኢትዮጵያ ህዝብ  ፋሽስትና ፀረ ህዝብ የሆነዉ የህ.ዋ ሕ.ት መሪዎች የትግራይ ህዝብና ልጆቹ በሃገር ደረጃ ደርግ ከተደመሰሰ ብቻ ነዉ ሰላም፣ ፍትህ፣ ዲሞክራሲ፣ ነፃነት፣ የህግ የበላይነት ይመጣል እያለ በመቶ ሺዎች ዜጎች የሰጡትን ደርግን አስወግዶ ወንበሩን ከተቆናጠጠ በኃላ ትላንትና ሽሮ  አለ መረቅ አለ እያለ ወደ እሳት እየማገደዉ የመጣ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከዳ የትግራይ ህዝብ ነበር። ውጤቱ ደግሞ የትግራይ  ህዝብ ሳይሆን መላዉ የኢትዮጵያ ህዝብ በአሁኑ ጊዜ አግኝቶት ያለ ምንድነዉ ?
ስደት በየአህጉሩ ተበታትኖ ሞት መታረድ በባህር የአሳ ቀለብ መሆን ሁሉም አይነት መብቶች ማጣት አንድነት መላላት ሉአላዊነቱን መደፈር ነዉ። በተለይ ደግሞ የህ.ወ.ሓ.ት መሪዎች አመራር ትንሳኤ መውታን ካልተረጋገጠ የትግራይ ህዝብ አይኖርም  የምትሉት 22 አመት ሙሉ ለውጥ ያላመጣ ችሎታ አሁን በሁሉም ነገር ከፈረጃችሁ በኃላ ‹‹ከገባንበት አዘቅት  አውጡን››  ብትሉን  አቶ ስብሃት ማን ያምንሃል የትግራይ ህዝብ ለናንተ ተንከባክቦ  አምጥቶ ምን ጥቅም አገኘ ። የትግራይ ህዝብ ልጆች ተምረዉ ስራ አጥተዉ የሚላስ የሚቀመስ አጥተዉ የስብሓትና  የጓደኞቹ ልጆች ግን ዘር መንዘራቸዉ በቻይና  በእንግሊዝ፣ ኣሜሪካ  በሌሎች ምእራብ አገሮች ተምረዉ በተቀማጠለ ኑሮ  ነዉ የሚኖሩት፤፤ ይህ እኮ የኢትዮጵያ ህዝብ አበጥሮ ያውቀዋል። ስለዚህ በኔ እምነት በአሁኑ ጊዜ  ስብሓት እንደ ምትለዉ የ.ህ.ወ.ሓ.ት  መሪዎች ትንሳኤ ሙታን    በአሁኑ ጊዜ አያስፈልግም፡፡ አዲስ ትውልድ የአዲሱ ትውልድ የህ.ወ.ሓ.ት አመራር ንኪኪ ያልተበላሸ  ኢትዮጵያዊ አመራር ያስፈልጋል። ይህ ነዉ ሃቁ።
« ስብሃት ነጋ የህ.ወ.ሓ.ት አመራር እዚህ ግባ የማይባለዉ አቅም ተነስቶ ለትግራይ ህዝብ አሳልፎ እጅጉን ጥልቀት ካለዉ አድሃሪ አሰላለፍ አሸንፎ  ለማመን የማይቻል ሃገራዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት በመፍጠር ወሳኝ ሚና ተጫውቷል። አሁንም አሁን ያለዉ የህ.ወ.ሓ.ት አመራር  የትግራይ ህዝብ  በመያዝ ህ.ወ.ሓ.ት አይፈጠርም አንልም። ‹‹በመሆኑ ቅድምና በቅርቡ ከህ.ወ.ሓ.ት ማ/ኮሚቴ የወጡ የህ.ወ.ሓ.ት አመራር ነበር እንደ አዲስ በመደራጀት አሁን ላለዉ ማ/ኮሞቴ የሚያግዝበት መንገድ መፈለግ አለበት ይላል»
‹‹ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ›› ይባላል አይደለ አቶ ስብሃት የህ.ወ.ሓ.ት አመራር 40 አመት ሙሉ ቆይቷል፤፤ ስብሃት ነጋም 39 አመት በአመራር ቆይተሃል በህ.ወ.ሓ.ት   ከ1967፣ 1969፣1970 ዓ/ም  የነበሩ የህ.ወ.ሓ.ት  የሃሳብ ልዩነት በፀረ ዲሞክራሲ የግጭት አፈታት   ስብሃትም ነበርክ  በ 1982 ዓ/ም አባይ ፀሃዬ ከስልጣን በማውረድ መለስን ወደ ስልጣን  ካስወጡ አንዱ አንተ ነበርክ ።በ1993 ዓ/ም ከህ.ወ.ሓ.ት መሰናጠቅ  ጋር ተያይዞ  ህ.ወ.ሓ.ት በሁለት አንጃ  ሲሰናጠቅ አንተም ስልጣን ከያዘዉ አንጃ  ጋር ሆነህ ለወጣዉ አንጃ በማውገዝ በዋናነት አንተ ነበርክ። አሁንም በቅርቡ የነበረዉ የህ.ወ.ሓ.ት መተካካት የሚባልም የተኩ ይሁኑ የተተኩ በሁሉም ነገር እዚህ ግቡ የማይባሉ ናቸዉ፤፤ መሪ የነበረ ሲወርድ አንጃ የነበረዉ ነዉ ወንበሩን የያዘዉ፤፤ ስለዚህ  ህ.ወ.ሓ.ት ከሲቪል ብቁ መሪ አላፈራም ብቁ ምሁር የማስጠጋት ባህል አልነበረውምና፤፤ በቅርቡ  ከህ.ወ.ሓ.ት የወጡ አመራሮች በመሰረቱ የሚበቃቸው ነገሮች ስለያዙ ነዉ እንጂ ስልጣን ጠልተዉ አይደለም፤፤ እነሱ ቢመለሱም እያቃሰተ ያለዉ ህ.ወ.ሓ.ት ሊያድኑት አይችሉም። አቶ ስብሃት ወንበር ብትይዝም አንደኛ ተቀባይነት የለህም፡ ሁለተኛ እድሜዉም ገፍቷል እነርሱም  በቅን ይሁን በተንኮል እየሰሩ አቅማቸው ተጨርሷል። ስለዚህ በቅርቡ ከ ህ.ወ.ሓ.ት የተቀነሳችሁ ህ.ወ.ሓ.ት ልታገግም ለማድረግ አትችሉም፤፤ ህ.ወ.ሓ.ት እኮ በስም እንጂ በአካል የለችም ይህ ትክክልኛ ነዉ።
በ 1993 ዓ/ም የተገነጠሉ አንጃዎች በስብሀት አይን እነሱ ከተመለሱ ህ.ወ.ሓ.ት ትነሳለች ነዉ እያለ  ያለዉ?
በኔ እምነት የወጡ አንጃዎች አብዛኞቹና የቀረዉ አንጃ የስልጣንና የሃብት ማካበት ልዩነት እንጂ መሰረታዊ የሆነ የህዝብ ጥያቄ አልነበራቸዉም እነዛ የህዝብ ጥያቄ የሃገር ሉአላዊነት አልተከበረም ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች አልተከበሩም በኢኮኖሚ ፖሊሲ፣በፖለቲካዊ አስተሳሰብ(አይዶሎጂ) ልዩነት የነበራቸውና አሁንም ለህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ.ኣ.ዴ.ግ እየታገሉ ያሉ  ከ3 ሰዎች አይበልጡም።
ሌሎች ግን ትላንትና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ወጣት ግቡ እያሉ ወደ ጦርነት እያስገቡ አዲስ አበባ እንደገቡት እንደጥርስ መፋቂያ ተጠቅመዉ የጣሉት አሁን  በወጣቱ መስዋእት ስማቸዉ ገኖ በአለም አቀፍ ታዋቂነት አግኝተዉ በንግድ አለም ተሰማርተዉ ከነቤተሰቦቻቸዉ በመላዉ አለም እየናጠጡ  ይገኛሉ። በሃገር ውስጥ ያላቸዉ ሃብትም ለዘር መንዘራቸዉ የሚበቃቸዉ ነዉ። ስለዚህ  ስብሃት እያልከን ያለሀዉ እነዚህ አንጃዎች ተመልሰዉ ወደ ህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ  ከመጡ ህ.ወ.ሓ.ትን አድነዉ በሃገራችን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ያመጣሉ ነዉ እያልከን ያለሀዉ ? ይህም የዋህነት ይመስለኛል አሁንም 1ኛ የመንግስትን ያህል ሃብት የሰበሰቡ ናቸዉ ፤
ሁለተኛ እድሜም ገፍቷል፤ ሶስተኛ ተቀባይነት የለም፤፤ ስለሆነም እዚህ ላይም የስብሃት አባባል ውድቅ ነዉ።
እነዚህ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ህዝብ ዲሞክራሲ ልማት ፍትህ አጥቶ ከላይ እንደገለፅኩት ህዝቡ ተቸግሮ በአለም ተበታትኖ የከፋ ኑሮ ሲገፋ ስለህዝብ ችግር አጀንዳ አንስተዉ ሊነጋገሩስ ይቅርና ጭራሹም በዚህች  አገር ምን ችግር እንዳለ ግምት ላይ አያስገቡም እንዳውም ከዚህ ድሃ ህዝብ የተወለዱ አይመስሉም፤፤ ከልዩ ፍጥረት የተፈጠሩ  ነዉ የሚመስሉት ። እነዚህ  በኔ እምነት በተለያዩ ጊዜ ከህ.ወ.ሓ.ት ተገንጥለውና በመተካካት የተቀነሱ በስልጣን ያሉ  የህ.ወ.ሓ.ት  መሪዎች ቢሰባሰቡ ህ.ወ.ሓ.ትን አክመዉ ለሞት ከመቃሰት አያድኑትም። ስብሃት ነጋ ያልተረዳዉ ነገር ቢኖር ህ.ወ.ሓ.ት የምትባል ፓርቲ አቶ ስብሃት ያለበት ፈራጅ ቡድን በ 1985 ዓ/ም የዲሞክራሲ ጥያቄ የሉአላዊነት  ጥያቄ በማስነሳቱ በግፍ የታሰሩ የተባረሩ በዛ እንደወጡ የቀሩ እለት ነዉ ህ.ወ.ሓ.ት የሞተች  መለስም አንተም በ1993 ዓ/ም ለነበረ  የህ.ወ.ሓ.ት የሁለተኛ አንጃ መሰንጠቅ ለመምቻ ተብሎ ያመናችሁበት ነበር እሱም የ1985 ዓ/ም ታጋዩ ያስነሳዉ ጥያቄ ትክክል ነበረ  ግን ምን ይሁን ኮለፍነዉብላችሃል።
« ስብሃት ነጋ አሁን ደግሞ የ ህ ወ.ዋ.ሓ.ት አባልና የትግራይ ህዝብ ታግሎ  ያመጣውን ስርአት ማክበር ብቻ ሳይሆን ታግሎ ለመጣዉ ስርአት ቀዳሚ ግንባር በመሰለፍ ሊከብርና ሊያስከብር  ሊያገኝ ሌሎችም እንዲያገኙ ማክበር አለበት» በገፅ 4 ሶስተኛ አምድ አንቀፅ ሁለት መስመር 25፤፤                       አቶ ስብሃት የትግራይ ህዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ወገኖች ጋር ታግሎያመጣዉ ስርአት ነበር ግን በናንተ ተቀምቷል፤፤ አይቶ አጥቷል የትግራይ ህዝብ የደርግን ሁሉም አይነት ግፍ ያልፈራ በእናንተ ግን የመግስት ሰራተኛ ነጋዴዉ ፣ አርሶ ሰደሩ ፣ ወዛደሩ፣ ተማሪዉ ፈርቶ ተሸማቅቆ እንዲኖር ተርቦ እያለ አልራበኝም ታሞ እያለ አልታመምኩም ውሃ ጠምቶት አልጠማኝም እንዲል አድርጋችሁታል፤፤ ለባለስልጣን መውቀስ ሂስ  ካደረገ ወደ ላይ አትንጠራራ ብሎ  ጭንቅላቱን ደፍቶ እንዲሄድ  ተደርጓል። ሌላዉ አቶ ስብሃት የትግራይ ህዝብ ታግሎ ያመጣውን ስርአት ፊት ተሰልፎ መጠበቅ አለበት ተብሏል፤፤ የማንና የማን ሃብት ህንፃ ሊጠበቅ ነዉ ይህ ማታለል ነዉ። የትግራይ ህዝብ በአሁኑ ጊዜ በወንዝ ተከልሎ ማሰብ ትቶ ተሻግሮ በሩቅ አይቶ የኢትዮጵያ አንድነትና ሉኣላዊነት ነዉ ሚታየዉ ያለዉ እምቢ ለጠባብነት እያለ ያለዉ።
የአቶ ስብሃት ጠባብ አመለካከት  አልፏል ድሮም የህ.ወ.ሓ.ት አፈና ደርግን ለመጣል ሲባል ተሸፍኖበታል እንጂ ስለ አንድነት ጉዳይ ስለ ባህር በር ስለ ኤርትራ ጉዳይ ብዙ ጥያቄ አንስቶ እነ ስብሃት ምን አይነት መልስ ትሰጡት እንደነበራችሁ ራስህም ታውቀዋለህ። ስለዚህ የትግራይ ህዝብ ሃሳብህን አይቀበልህም።
ሌላዉ የትግራይ ህዝብ ይሁን መላዉ የኢትዮጵያ ህዝባችን  የህ.ወ.ሓ.ት በ1983 ዓ/ም ደርግን አስወግዶ ወንበሩን ሲቆነጠጥ የህ.ወ.ሓ.ት  መሪዎች ህዝቡ ታግሎ ባመጣዉ ድል ተጠቅማችሁ ከደርግ ተለይታችሁ ለመታየት ብዙ ዲሞክራሲ የሚመስሉ መግለጫዎች ትሰጡ ነበር።በመሬት ላይ የነበራችሁ ፖሊሲም ለምእራብ ሃገሮች ፖለቲካ ፍጆታ ብላችሁ ነፃ ኢኮኖሚነት መብት የምትጠብቁ ትመስሉ ነበር ቀስ በቀስ ግን የፀረ ዲሞክራሲ ባህሪያችሁ አገርሽቶበት እንደ ወትሮ ሆናችሁ የቻይና ታማኝነታችሁ አረጋግጣችሁ መሬት ለምን የህዝብ አላችሁ።
በአሁኑ ጊዜ የህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ መሪዎች የከተማም ሆነ የገጠር መሬት የኔ ነዉ 90 ሚሊዮን ህዝብ የመሬት ጢሰኛ ነህ ብላችሁ ፍፁም ዜግነቱ ቀምታችሁታል፤፤ ኢትዮጵያዊ ዜጋ መሆኑ እንዲጠራጠር አድርጋችሁታል፤፤ ታዲያ ስብሃት ነጋ የትግራይ ህዝብ የታገሉለት  አላማ እንዳይቀማ ፊት ተሰልፎ ለህ.ወ.ሓ.ት ይጠብቃት ስትለን በ 17 አመቱ የትጥቅ ትግል የከፈለዉ ሂወትና ቁሳቁስ ያልጠቀመዉ አሁን እንደገና የህ.ወ.ሓ.ት መሪዎች ልጆቻቸዉ እንዲሁም ምንጩ የማይታወቅ የሰበሰቡት ሃብት ሊጠብቅ ነዉ የምትፈልገዉ? አይታሰብም ዋና ችግራችሁ ለሁሉም ስራችን መስተዋታችን ህዝብ ነዉ ስትሉ የነበረ በመክዳት በአሁኑ ጊዜ ህዝብ ምን ይላል የሚል መረጃ አለመኖራችሁ ነዉ እንጂ ህዝቡ ለውጥ ፈልጓል የህ.ወ.ሓ.ት መሪዎች ልክ ከባህር እንደወጣ አሳ ከልብ አውጥቶ ጥሏቹሃል። አሁን ግን ትልቁ ችግር ሆኖበት ያለዉ የመንግስት የፍትህ አካላት በደህንነት በፖሊስና ፌዴራል ፖሊስ በአቃቤ-ህግ ታፍኗል፤፤ በአሁኑ ጊዜ በሃገራችን ያለዉ አስተዳደር በአዋጅ ወታደራዊ አስተዳደር ስላልተባለ ነዉ እንጂ በተግባር ወታደራዊ አንባገነናዊ ስርአት ነዉ ያለዉ። ታዲያ ስብሃት ነጋ ለትግራይ ህዝብ ለዚህ ስርአት ጠብቀዉ  ነዉ እያለ ያለዉ  ደግሞ በባዶ ሆዱ እንዴት ብሎ ይታሰባል;
« የትግራይ ህዝብ ታግሎ የሚያታግለዉ  የሚጠቅመዉ አብዮታዊ መሪ ድርጅት ያስፈልጋል›› ስብሃት ነጋ ገፅ 4 በአርእስት የተፃፈ» (በትግርኛ ህዝቢ ትግራይ ተቓሊሱ ዘቃልስ ዝጠቕሞ ወያናይ ውድብ ክረክብ ይግበኦ)
ስብሓት ነጋ  እያልከን ያለሀዉ የትግራይ ህዝብ ታግሎ የሚያታግለዉ አብዮታዊ  ፓርቲ ያስፈልገዋል ነዉ። በዚህ አባባል እኔም እስማማለሁ አዎን አብዮታዊ ፖለቲከዊ ድርጅት ያስፈልገዋል ።ግን የትኛዉ አብዮታዊ ፓርቲ; ህ.ወ.ሓ.ት ከማቃሰት እናድነዉ ከሆነ በትግራይ ክልል ህዝብ ይሁን ባጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ. ኣ.ዴ.ግን አይፈልግም፤፤ በወታደራዊ አስተዳደር ስለታፈነ በምርጫ ጊዜ ለፈለገዉ ቦታ የመረጠዉ ካርድ ስለተቀማ ከክልል እስከ ጎጥ  በአንድ ለአምስት የደህንነት መዋቅር ስለታፈነ ብቻ ነዉ። ስለዚህ ከእንግዲህ  የትግራይ ህዝብ ለስብሃትና ጓዶቹ ሎሌ ሆኖ አይኖርም፤፤ በሰላማዊ መንገድ ትግሉን በማስቀጠል የኢትዮጵያ ህዝብ የስልጣን ሉአላዊነቱ ሊያረጋግጥ ነዉ።
ግን አቶ ስብሀት ነጋ ሁሉ ግዘ ለትግራይ ህዝብ እየተቆረቆርክ መስለህ የጠባብንት አመለካከት ታሰራጫለህ፤፤
ይህንን ያልኩበት ምክንያት 90 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብ በአስከፊው የህ.ወ.ሀ.ት ኢ.ህ.አ.ደ.ግ መሪዎቹና ካድረዎቹ አፈና መዳፍ ገብቶ እያለ ለኢትዮጵያ ህዝብ እንደ ማሰብ ፋንታ የትግራይ ህዝብ ለብቻው ነጥለህ ለበሰበሰ ስርአታችሁ ዘበኛ ማድረግ አያዋጣም፤፤ የትግራይ ህዝብም አይቀበለውም፤፤ ለአንድነቱ የቆመ ነውና፤፤
‹‹ «ስብሃት ነጋ ሙስና ዋነኛዉ የስርአታችን አደጋ ነዉ›› ብሎ የተነሳ ፓርቲና መንግስት ለምን ወደዚህ የተበላሸ  ሙስና አደጋ ደረሰ የሚል ጥያቄ በብቃትና በቆራጥነት  ካለተፈታ  በዚህች አገር ምን ሊፈጠር ነዉ? ሙስናና ብልሹነት ከቁጥጥር እየወጣ ነዉ የሚል ጥቆማ ከአገር ውስጥም ከውጭ አገር ለሚመለከተዉ ጥቆማዉ እንደ ጎርፍ ይፈስ ነበር በጊዜዉ ግን ሰሚ ጆሮ አላገኘም » ›› ውራይና መፅሄት ገፅ 3  አንቀፅ አንድ መስመር ሰባት፤፤
አቶ ስብሃት እንደምትለዉ    ህ.ወ.ሃ.ት ከ1984 ዓ/ም ጀምሮ በስብሰባ በብዙሃን መገናኛ ስለሙስና ብዙ ይናገር ነበር፤፤ በተለይ ደግሞ የህ.ወ.ሃ.ት አመራሮች ሙስና በናንተ ነበር የተጀመረዉ፤፤ ምርጥ ቤት ለራስህ ለዘር መንዘርህ ለአንድ መሪ ከሁለት እስከ 3( 4 መኪና) መያዝ ነዳጅ ያለገደብ መጠቀም የራስህና የቤተሰብ ህን ኑሮ ማሻሻል ከውርሃዊ ገቢህ ጋር የማይመጣጠን በየቀኑና በየሳምንቱ በሂልተን በሶደሬ መዝናናት የቤት እቃዎች በሚሊዮን  የሚቆጠር ገንዘብ ወጭ ማድረግ ከባለሃብቶች ገፀ በረከት ስጦታ መቀበል፣ በየጊዜዉ ብዙ ወጭ  በማውጣት ግብዣ ማድረግ ልዩ ፍጡር ሆነህ መታየት ረጅም ሳይጓዙ  ወደ ይኩራሩበት የነበሩ  የንጉሳዊ ቤተሰብ ቅምጥል ኑሮ እነሱን አልፈዉ ሄደዉ በየምሽቱ  በአስር ሺህ ብር የሚቆጠር  ገንዘብ ማባከን በልጅ ጥምቀት ፣ የልደት ቀን ሰንጋዎች ማረድ በዊስኪ መራጨት  ጊዜ እየገፋ ሲሄድ በግልፅ የማይታወቅ  ሃብት  ማካበት በተለያየ መንገድ ሰማይ ጠቀስ ህንፃዎች መገንባትና ስም ቀይሮ ብዙ የደረቅና የፍሳሽ የጭነት መኪና መግዛት ሌላ ቀርቶ የመሪዎች ሚስቶች ውጭ አገር ሄደዉ እንዲወልዱና  ለወደፊት በዛው የውጭ አገር ዜግነት ይዘዉ ቆይተዉ መሸሻ ቦታ  ማዘጋጀት ብሎም ቤት መስራት ስልጣንህ ተጠቅመህ ዘርመንዘርህ ውጭ መላክ ነበር። ለዚሁ ማረጋገጫ በቻይና በ10 ሺህ  የሚቆጠሩ የመሪዎች ልጆች የሚማሩ ኣሉ። ሌላ ዋነኛዉ በመንግስት ስራ አመዳደብ በሞያ እንደመሆን በዘመድ አዝማድ በጋብቻ በጓደኝነት አድርገህ ስራው በሞኖፖል መያዝ ሌላ ስራተኛ እንደ ሁለተኛ ዜጋ ማየት ነበር።
ኣቶ ስብሃት ይመሩት የነበረ የኢፈርት ድርጅቶች በአስር ቢሊዮን የሚቆጠር ካፒታል ያላቸውም ለስሙ በህዝብ ስም እየተነገደባቸው ለሙሰና ብልሹነት የተጋለጡ ሆነው የሄዱት ስፍር ቁጥር የላቸውም፤፤ ሁሉም   ለስሙ በህዝብ ስም እየተነገደባቸዉ ለሙስናና ብልሹነት የተጋለጡ ሆነዉ የኦዲት ቁጥጥር የለባቸዉም፤፤ ሁሉም ገንዘቡን የሚያውቀዉ ስብሃት ነጋ ነበር፤፤ ቁልፉም እሱ ነበር ኃላም ስብሃት ሲለቅ ስዬ አብርሃ ቀጥሎ ኣባዲ ዘሞ በመጨረሻም አዜብ መስፍን የበላይ ጠባቂ ጠ/ሚኒስቴር መለስ ነበሩ።ስብሃት ነጋም እስከአሁን የግዙፍ ካምፓኒ የወጋገን ባንክ ቦርድ ዳይሬክተር ነህ፤፤ ይህ ባንክ ከፍተኛ  አክሲዮን የህ.ወ.ሃ.ት ሃብት ነዉ ስንት ካፒታል አለዉ ማን ይቆጠቀጠረዉ የሚለዉ መልሱ ለስብሃት ነጋ ነዉ።
እንግዲህ የሙስና ጉዳይ ከተነሳ በዘመነ ህ.ወ.ሃ.ት ስርአት ሙስና በኢትዮጵያ አደጋዉ እንዲስተካከል አስተያየት የሚሰጡ ቅን አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የውጭ አንባሳደሮች መንግስታት የአለም ባንክም ምክር ይሰጡ ነበር፤፤ ለዚህ አስተያየት ከአቶ ስብሃት ጀምሮ ሁሉም የህ.ወ.ሃ.ት መሪዎች ሰሚ ጆሮ አይሰጡትም ነበር። ምክንያቱም ሁሉም የተነካኩ  ናቸዉና።  ስለዚህ ስብሃት ነጋ ‹‹የሙስና መረጃ እንደጎርፍ ይፈሱ ነበር ግን ሰሚ ጆሮ አልነበረም፤፤›› ስትለን አንተስ ሙስና ኣለ ብሎ መረጃ የሰጠህ ቅን ኢትዮጵያዊ እንደ ጠላት አይተህ ከስራ አላባረርክም ? በጥላቻ እንዲታይ አላደረክም ይህ አባባል ማታለያ ነዉ ። አንድ ነገር በዚሁ እድሜ በገፋበት በምፅተአለም ዋዜማ አገራችን በሰዉ ሃብት የሃገር ሃላፊነት የማይሰማቸዉ ጅቦችና ከወደመችና የአገራችን አንጡራ ሃብት ውጭ አገር ከሰፈረ በኃላ ሆነ ራሱ ግን የስብሃት ልግም እንጂ አብዮታዊ ነት አያሳይም።
ስብሃት ነጋ ‹‹የተበላሸ ሙሰኛ ሁሉ በየደረጃዉ መታረም አለበት ስርአቱን  በመጣስ ቤት ከፍቶ የሰረቀ መሆኑ እያወቀና እየሰማ  እርምጃ ያልወሰደ በከፍተኛ ደረጃ ጥፋት መጠበቅ አለበት። ያ ቤት ከፍቶ አግኝቶ ትንሽ የቀመሰ ደግሞ በሁለተኛ ደረጃ የሚስተካከል መሆኑ ህዝቡን ለማረጋጋት ያስችለዋል» ውራይና መፅሄት ገፅ 5 3ኛ አምድ አንቀፅ 3 መስመር አንድ
አቶ ስብሃት ነጋ አንደኛ ነገር አንተን ከሙስና ነፃ እንደሆንክ  በሁለተኛ ደግሞ ቢሊየን የሰረቀና ሚሊዮን የሰረቀ እኩል መታየት  የለባቸዉም፤፤ ምክንያቱም ትንሽ ለሰረቀ ቀላል ቅጣት ከሰጠኸዉ ህዝብ ሊረጋጋ ይችላል ብለሀናል። የትኛዉ ህዝን ነዉ? ግልፅ አይደለም፤፤ አሁን እኮ ዋና ሌባ የሚባለዉ ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ያለዉ ባለስልጣን በሙስና ተራክሷል፤፤ ይህ መዋቅር ከህዝቡ ከ3 እስከ 5%  ነዉ የሚሆነዉ ቅጣቱ ይቀላል  ምትለዉ ያለህ ለማነዉ? ለምስ ነዉ የሚቀልበት? በኔ እምነት አቶ ስብሃት የምትለን ያለ ታች  ሆኖ ህዝብ ያሰቃዩ ሎሌዎች ከተመቱ ለወደፊቱ በየመድረኩ እጅ እያወጣ የስ እያለ የሚውል ሰዉ አናገኝም፤፤ በምርጫ ጊዜ ኮረጆ የሚሰርቅ የለንም፤፤   ከሚል የመነጨ ነዉ ትንሽ  የሰረቀ ይማር የምትለን ያለህ በሌላ በኩል ትልቁ ብልሹ ሙሰኛም ይመታ ስትለን ቁርጠኝነትህን አይደለም የሚያመለክት፤፤  አቶ ስብሃት ነጋ ትልቁ የሙስና ግንድ  ከተመታ አንተም ልትመታ መሆንህ በመረዳትህ ነዉ የተድበሰበሰ ትንታኔ የተናገርከዉ። በኔ እምነት ግን በኢትዮጵያ ትልቁ ጠላት ሙስናና ብልሹ አስተዳደር ከግንዱ ብቻ ሳይሆን ከስሩ ከቀበሌ ጀምሮ መቆረጥ አለበት እላለሁ። እዚህ ላይ ግን የስብሃት አሰራር እማውቀዉ ነገር አለ፤፤ ስብሃት በስሙ ገንዘብ ይሁን ንብረት የለዉም። ብዙውን ጊዜም የሆነ ወጭ አይፈርምም ነበር፤፤  ሁሉም ነገር በውክልና ነበር የሚያሰራዉ ። ስለዚህ ትንሽ የሰረቀ ይማር ሲለንም  እነዛ ወኪሎቹ እንዳይቆረጡ ካለዉ ስጋት ነዉ። የገንዘቡ ጎተራም ከነሱ ነዉ በስብሃት ወንድሞች ዘርመንዘሩ ስም የተሰሩ ህንፃዎች ምንጫቸዉ የማይታወቅ ሃብትም አላቸዉ።
ሌላዉ ስብሃት ነጋ ስለ ሙስና መረጃ ሲሰጥ ሰሚ ጆሮ አልነበርንም ብለህናል፤፤ ማነዉ የማይሰማ በግልፅነት ልትነግረን አትችልም ማነዉ ለሙስና ጨካኝ ያልሆነ ጠ/ሚኒስቴር? ውጭ ጉዳይ? መከላከያ ሚኒስቴር? የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ? ደረጃ መዳቢዎች? ያገር ውስጥ ገቢ ደህንነት? የከተማ ልማት? የአዲስ አበባ ከንቲባ ዳይሬክተር? እመቤትዋ የጥረት ዳይሬክተር? የወጋገን ዳይሬክተር? የመከላከያ ኢንጅነሪንግ ሚኒስትሮች? የክልል ውሃ ሃብት ኢንተርፕራይዝ ሃላፊዎች ? የስኳር ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር? የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ፓርቲዎች ናቸዉ ታዲያ አቶ ስብሃት ከፍተኛዉ ሙሰኛ ( ትልቁ) ቦታ ነዉ የሚገኘዉ  ብለሃል፤፤ ከነዚህ የተኞቹ ናቸዉ ሙሰኞች፤፤ የአቶ ስብሃት አሽሙር አነጋገር 40 አመት ጊዜ ስለፈጀብህ በአንድ አረፍተ ነገር ይቅርና የማያውቅህ እኔም  በአስር የሚቆጠሩ አመታት  አብረን  ተቀምጠን አሽሙርህ ሊረዳኝ አልቻለምና ለዚህ ትውልድ አሽሙር ከምናወርሰዉ ግልፅነትን እናውርሰዉ።
አቶ ስብሃት አንድ ጥያቄ ግን ልጠይቅህ  በዚህ ፅሁፍ ላይ ያሰፈርከዉ ለትግራይ ህዝብ ብቻ ታግሎ የሚያታግለዉ መሪ ድርጅት ያስፈልገዋል ብለሃል በሌላ በኩል ደግሞ ህ.ወ.ሓ.ት እናድን ትላለህ እዚህ ላይ ሁለት ነገር እንድመለከት አድርጎኛል።
1 ለትግራይ ህዝብ ብቻ ለምን አዲስ መሪ ድርጅት ያስፈልገዋል ? ተበላሽቶ ያለዉ የኢትዮያ ህዝብ መሪ ነኝ የሚለዉ ህ.ወ.ሓ.ት  ኢ.ህ.ኣ.ዴ.ግ ክህመሙ ካላጋገመ  ህ.ወ.ሓ.ት ብቻውን አክመህ ይድናል ወይ ? በሙሉ ተሟል ነውና ወይስ አዲስ የትግራይ መሪ ፓርቲ በመመስረት ወደ ዱሮ የነበርክበት አስተሳሰብ ነፃ  ( ትግራይ ትግርኚ) የሰሜን ኢትዮጵያ መንግስት ለመመስረት አስበህ ይሆናል የሚል ጥርጣሬ አድሮብኛል፤፤ አባባልህ ለብዙ ዜጎች  የተብራራ እይደለም፤፤ ደግሞ በቅርብ ጊዜ አሜሪካ ሄደህ ኤርትራዊ ነኝ ከማለትህ እጅጉን ተጠራጠርኩህ፤፤
2 ለምን ህ.ወ.ሓ.ት  ኢ.ህ.ኣ.ዴ.ግና አጋሮቹ እናድን ተበላሽተዋልና ብለህ በሃገር ደረጃ ላሉ ጓዶች ችግር ማየት ለምን ተሳነህ ? ወይ  የህ.ወ.ሓ.ት  መሪዎች ብቻ ነዉ የታመማችሁት ? አሁን ያለዉ ችግር እኮ  የህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ.ኣ.ዴ.ግ መሪዎች በሙስና መበላሸትና የመበስበስ አደጋ ነዉ አጋጥሟችሁ ያለዉ፤፤         አቶ ስብሃት በጥልቀትና በስፋት ብታስብበት፤፤ በአሁኑ ጊዜ  ህ.ወ.ሓ.ት   ብዙ ነገር ተበላሽቶባቸዋል፤፤ አንድ እርምጃ ለመራመድ ተስናችሁ በመቃሰት ላይ ናችሁ፤፤ በሰለጠኑ አገሮች እንደምናየው ከሆነ ይቅር እና እናንተ በስብሰባችሁ እንዳላችሁት ስብሰባዉ አንድ ቃል በውሸት ተናግረዉ ህዝብ ካወቃቸዉ ወይ ባገራቸዉ ከባድ ወንጀል ከተፈፀመ ከስልጣን ይወርዳሉ፤፤ እናንተ ግን አገር ያህል የባህር በር የሌላት አስቀርታችሁ የዘሂግ  ፍርድ ቤት ውሳኔ ተሸንፋችሁ እያላችሁ አሸንፈናል ውሳኔዉ የኛ ነዉ ብላችሁ በመድረክ ዋሽታችሁ ይሀው ቁማችሁ ትሄዳላችሁ። በተጨማሪ የመላው ህዝብ ተቃውሞ እልባት ለማድረግ አልቻላችሁም፤፤ ይህም ከስልጣን ያወርዳል፤፤ እንደ ጃንሆይ ተጎትታችሁ ከወንበሩ ከምትወርዱ ለምን ይቅርብን ብትሉና ህዝብ የፈለገዉን መሪ ቢመርጥስ ?
ስብሃት ነጋ  ከአሁን በኃላ የህ.ወ.ሓ.ት መሪዎች ከህመማችሁ አገግማችሁ ህ.ወ.ሓ.ት እናድናት ማለትህ የዋህነት ነዉ። ዋና ችግርህ የህዝብን ፍጎትና ልብ ትርታ ኣለመረዳትህና የትግራይ ክልል ህዝብ ከህ.ወ.ሓ.ት መሪዎች የተፋታ መሆኑን አልደረስክበትም፤፤ በሸራተን ሆነህ ስለ የትግራይ ህዝብ ከመናገር እስቲ ወደ ገጠር ህ/ሰብ ስሜቱን አጥና ።  እናንተ  ህዝቡን ለማደናገር ብላችሁ የምትናገሩትና የምትሰሩት  አበጥሮ ያውቃልና።