ወ/ሮ ገነት ዘውዴ (ዮዲት ጉዲት) ይቅርታ መሳደቤ አይደለም ሰው የሚያውቃቸው በዚህ ስም በመሆኑና የሚኮሩበትም በመሆኑ እንጅ፡፡ እናም ወ/ሮ ገነት በቅርቡ በሸገር የኤፍ ኤም ሬዲዮ (ነጋሪተ- ወግ) “የሸገር እንግዳ” በተባለው ዝግጅት እንግዳ ሆነው አዘጋጇ ጋዜጠኛ ወ/ሮ መዓዛ ሦስት ቅዳሜ አዋይተዋቸው ነበር፡፡ በዚያ ጨዋታቸው ወ/ሮ ገነት ከተናገሩት ብዙው ነገር ከንክኖኝ ከጊዜ አንጻር ባይሆን በጥቂቶቹ ላይ ጥቂት ነገር ለማለት አስቤ እየጫጫርኩ እያለሁ እንዲያውም በወ/ሮዋ በሐሰት ስማቸው ከጠፋ ወገኖችና ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው አንደኛው በጥሩ ምሁራዊ ተዋስኦ የተዋዛ ምላሽ ሰጥተው አሻሩልኝ፡፡ ይሁንና ወ/ሮዋ የተናገሩት አጉል ነገር በርካታ በመሆኑ ሁሉንም ለመዳሰስ ከጊዜና ከቦታ አንጻር የማይቻል በመሆኑ ዶክተሩ ለሁሉም አጉል ነገር መልስ ሳይሰጡ ቀሩ፡፡ እኔም እንማማርባቸው ዘንድ ይጠቅማሉ ብየ ባሰብኳቸው በዚያ በወይዘሮዋ ወግ በተነሡ ሁለት ዐበይት አጉል ጉዳዮች ላይ አተኩሬ የተቻለኝን ያህል ለማለት ፈለኩ፡፡ እነኝህ ወ/ሮዋ የተናገሩት ሁለት ዐበይት አጉል ነገሮችም አንደኛው ወይዘሮዋ “የግራ ዘመም የፖለቲካ (የእምነተ-አሥተዳደር) አስተሳሰብ አራማጅ በመሆኔ” እያሉ የተናገሯቸው ነገሮች ሲሆኑ ሁለተኛው ደግሞ ሀገራችንን የሴቶች ሲዖል አድርገው ያቀረቡት ነገር ነው፡፡
ወ/ሮ ገነት ግራ ዘመም የፖለቲካ (የእምነተ አሥተዳደር) እምነትን ወይም አሥተዳደርን (left political belief) የተረዱት በተሳሳተ አረዳድ ነው፡፡ ለወ/ሮ ገነት ግራ ዘመም ፖለቲከኛነት (እምነተ-አሥተዳደሬነት) ማለት ነባሩን አስተሳሰብ ሙሉ ለሙሉ መቃረን መቃወም ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ግራ ዘመም እምነተ አስተዳደር ማለት የራስን መጣል መተው መቃረን ማለት ሳይሆን የሶሻሊዝምን (የኅብረተሰባዊነትን) የፖለቲካ (የእምነተ-አሥተዳደር) ርዕዮተዓለም (Ideology) መከተል ወይም መቀበል ማለት ነው፡፡ ይህ ችግር የወ/ሮ ገነት ችግር ብቻ አይደለም በዚያ ዘመን የነበረው ትውልድ ሁሉ ሊባል በሚችል ደረጃ የነበረውን የፖለቲካ ማዕበል ይንጠው የነበረውም እንጅ፡፡
በስለው ከማይበስሉት ከጥቂቶቹ በስተቀር ብዙዎቹ ዛሬ ላይ ሰክነው ሲያስቡት በዚያ ጊዜ የነበራቸው አስተሳሰብ የተሳሳተ እንደነበረ ከመረዳታቸው የተነሣ ያ ዘመን የእብደት ዘመን እንደነበር ሐፍረት እየተሰማቸው ይናገራሉ፡፡ ይህ የጸጸት ስሜት ከግለሰቦችም አልፎ በዚያ የስሕተት ማዕበል ይናጡ የነበሩ ሀገራትም ተጋርተውታል፡፡ የግራ ዘመም ፖለቲከኞች (እምነተ-አስተዳደራዊያን) በነበራቸው የተሳሳተ ግንዛቤ የተነሣ ያራምዱት የነበረው የግራ ዘመም አስተሳሰብ የዜሮ (የባዶ) ብዜት ማለት ነበር፡፡ የነበረውን ነገር አጥፍቶ ከዜሮ የመጀመር የድንቁርና ሥራ ማለት ነው፡፡ በተለይም እንደኛ ጥንታዊና ለሌሎችም የተረፈ ሥልጣኔ ባለቤት በነበረች ወይም በሆነች ሀገር ላይ የነበረውን ብዙ የተለፋበትን የተደከመበትን መሥዋዕትነት የተከፈለበትን ነገር ሁሉ በዜሮ አጣፍቶ ከዜሮ መጀመር ምን ያህል እብደትና ድንቁርና እንደሆነ ቢያንስ አሁን ላይ የማይረዳ ሰው ይኖራል ብየ አላስብም፡፡ አሀ! ለካ እነ ወ/ሮ ገነት አሉ እሽ ከእነሱ ውጭ በሚል ይስተካከልልኝ፡፡
አንድ ሀገርና ማኅበረሰብ ታሪካዊና ጥንታዊ ከሆነ በረጅም ጊዜ ቆይታውና ሒደት ማንነቱን ባሕሉን ሃይማኖቱን አየር ንብረቱን ሳይቀር መሠረት በማድረግ የሚያፈራው በርካታ የተለያዩ ዓይነት እሴቶች ይኖሩታል እነዚህ በሒደት በሞክሮ ማየት (trial and error) የሚጠቅመውን በመያዝ የማይጠቅመውን በመተው ሒደት የሚያዳብራቸው ብዙ ዓይነት አስተሳሰቦች መኖራቸው የማይቀር ነው፡፡ ታዲያ አንድ ትውልድ ድንገት ተነሥቶ ከባዕድ በተጫነው አስተሳሰብ ሳቢያ የነበረውን ሁሉ እንዳለ ጠቅልሎ ልጣል በሚልበት ሰዓት ሊደርስ የሚችለው ኪሳራ እጅግ ከግምት በላይ ነው፡፡ ከስልሳዎቹ እስከ ሰማኒያዎቹ አጋማሽ (1950-1975ዓ.ም.) የነበረው ተማሪውና ተራማጅ ነኝ ይል የነበረው ትውልድ (የደርግ የኢሐፓና ከእነሱ የወጡት የወያኔ ሌሎችም የዚያን ዘመን ፖለቲካ ተዋንያን) በምዕራቡ የሶሻሊዝምና ኮሚኒዝም ርዕዮተ ዓለም ራሳቸውን አጥምቀው የሀገራችንን እሴቶች ከባሕል እስከ ሃይማኖት ከታሪክ እስከ ትምህርት ከወግ እስከ ሥርዓት የነበረውን ሀብታችንን ዋጋ አሳጥተና ጥለው ለገዛ ማንነታቸው ታሪካቸው ቅርሶቻቸው ጠላቶች ሆነው እንደ አዲስ ሀገርና ኅብረተሰብ ከዜሮ ነበር እንድንጀምር ይሟሟቱ የነበሩት፡፡ የእነሱ ጥረትና ፍልስፍና ግን የት እንዳደረሰን ሁሉም በግልጽ የሚያየውና የሚረዳው መረጃ የማያስፈልገው ኪሳራ ነው፡፡
ያ ሁሉ አለፈና ምን አለፈና ይሄው ዛሬስ የሚያዳክረን እሱው አይደል? እሽ ከእኛ ውጭ ባለው ዓለም ግን ዛሬ ሌላው ቀርቶ የዚያ ርዕዮተ ዓለም (Ideology) ቃፊር የነበረችው ሩሲያ እንኳን ተለውጣ ተጸጽታ ያኔ የሰበረቻትን ያደቀቀቻትን አንቅራ ተፍታት የነበረችውን የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ከጣለችባት አንሥታ ክብር በመስጠት ከዚያ ሁሉ ቀውስ በኋላ ዛሬ ላይ የሩሲያ መንግሥት መሪዎች ያለ ፓትርያርኩ ቡራኬ የሚከውኑት መንግሥታዊ በዓላትና ታላላቅ ክንውኖች የሌለበት ሁኔታ ሊታይ ግድ ብሏል፡፡ መሪዎቿም ቤተክርስቲያን ሳሚዎች የሆኑበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡
እንግዲህ ወቅታዊ የዓለም አቀፍ ሁኔታ እንዲህ በሆነበት ሁኔታ ነው “ሞኝና ወረቀት ያሲያዙትን አይለቅም” እንዲሉ የኛዋ ግራ ዘመም ፖለቲከኛ ወ/ሮ ገነት ያኔ ያውም በተሳሳተ ግንዛቤ የጨበጡትን ሙጭጭ አድርገው ይዘው ከስንት ዐሥርት ዓመታት በኋላም በዕድሜ በልምድ በተሞክሮ ብዛት በትምህርትም ሳይለወጡ አሁንም “ግራ ዘመም ስለሆንኩ እንደዚህ ዘንደዚህ ዓይነቱን አልፈልገውም ደሞ የምን ምንትስ ነው እንደ ዛ የድሮው ደጅ አዝማች ቀኝ አዝማች!” እያሉ በዚያ ዘመን ቅኝት ማውራታቸው በጣም ነበር የደነቀኝ፡፡
አንዴ አንድ መድረክ ላይ ዶክተር ዳኛቸው (የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምህርና ወያኔ በሀገራችን ላይ ያደረሰባትንና የጋረጠባትን ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ በተቻለው መጠን ባጋጠመው መድረክ ሁሉ እያጋለጠና እየሞገተ ያለ ምሁር) በኢሕአፓ ዘመን በነበረው ትውልድ ትግል ዙሪያ ላይ የተጻፈን መጽሐፍ በገመገመልን ወቅት ለዚያ ዘመን ትውልድ ያለኝ ግምት ወይም አቋም ከዶክተር ዳኛቸው ጋርም አጨቃጭቆጫል፡፡ ዶክተር ዳኛቸው እንደማንኛውም የዚያ ዘመን ሰው ሁሉ በተለይም እንደ የትግሉ አጋርነቱ ያን ትውልድ እያወደሰ እያሞካሸ መቸም ሊደገም የማይችል ትውልድ እያለ ነበር አቅርቦቱን (ፕረዘንቴሽኑን) ያቀረበው፡፡ በውይይቱ ላይ ሐሳብ አስተያየት እንዲሰጡ ዕድል ከተሰጣቸው ሰዎች አንዱ ነበርኩና ሐሳቤን ስሰጥ “እኔ የዚያ ዘመን ትውልድ ጀግና ምናምን በሚባለው ጉዳይ አልስማማም ስላልነበርኩበት ግን አይደለም ለኔ ጀግና ማለት ሞትን የሚጋፈጥ ሞትን የማይፈራ ማለት ሳይሆን የሚሞትለት ዓላማ ከሀገሩ ከማንነቱ አንጻር ሲታይ ባለው ጠቀሜታ የሚወሰን ነው ለኔ ያትውልድ ስሩን ከሀገሩ ከገዛ ከማንነቱ ነቅሎ አውሮፓ ላይ የተከለ ለገዛ ማንነቱ ሥልጣኔው ጠላት የሆነ ርዕዮተዓለሙም ኢትዮጵያዊ ያልነበረ ነውና በፍጹም ጀግና አልነበረም አባጭ የሚለው ስም ግን ይስማማዋል፡፡ ይሄው የጣለው የተከለብን ጠንቅም እስከዛሬ አልለቀቀንም ወደፊትም ገና ብዙ ያዳክረናል” አልኩ፡፡ አለዛ እኮ እነዮዲት ጉዲትን፣ እነ ግራኝ አሕመድን፣ በድፍረት መግደል ማጥፋት ማውደም የሚችሉበትን ዕድል ለራሳቸው የፈጠሩትን፣ ክፉ የጭካኔ እርኩስ መንፈስ ተጠናውቶት ያለምንም ምክንያት እየተነሣ በድፍረት የሚገለውን ሁሉ እኮ ጀግና ልንል ነው!
ይህ አስተያየቴ ለዶክተር ዳኛቸው በጣም አልተመቸውም ነበር “ያ ትውልድ ጀግና ካልተባለ ማን ሊባል ነው?” አለ “አንተን ደስ እንዲልህ ፈሪ ነው ልበል? ርዕዮተዓለሙ ኢትዮጵያዊ አይደለም ትላለህ መሬት ላራሹ ኢትዮጵያዊ አይደለም? የብሔር ጥያቄ ኢትዮጵያዊ አይደለም?” ሲል ጠየቀኝ መልስ ለመስጠት ዕድሉ እንዲሰጠኝ ጠየኩ አወያዩ አልፈቀደም እናንተ በግል ተወያዩ ያለንን ሰዓት በቀሪ ሐሳቦችና ጥያቄዎች ላይ እናተኩር በማለቱ ቀረ፡፡
በእርግጥ ወ/ሮ ገነት ዛሬ የዚያ ርዕዮተዓለም አፍላቂዎች በተውበት ዘመን የወደቀውን የነጭ ውራጅ አስተሳሰብ በተንጋደደ አረዳድ ጨብጠው ይዘው ዛሬም ማውራታቸው ወ/ሮዋ ለአሁኑ ትውልድ አርአያ የመሆን አቅም ኖሯቸው ይህ ትውልድም ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጥር በመፍራት አይደለም በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት መስጠቴ፡፡ ነገር ግን የዚያን ዘመን እብደት እንዲገነዘብ እንዲታዘብ እንጅ፡፡ ወ/ሮ ገነት ግራ ዘመም ስለሆንኩ እያሉ በመንቀፍ ሊከተሉት እንደማይሹ ከገለጹት ነባር ባሕል ወግ ሥርዓት አንዱ ለጋብቻ ሽምግልና መላኩን ነው፡፡ ከዓመታት በፊት ይሄንን ጉዳይ አንድ እንደሳቸው ግራ ዘመም ወይም ተራማጅ ነኝ ባይ በሬዲዮ (በነጋሪተ ወግ) በሚተላለፍ ዝግጅት ላይ እየተቸ እንዲቀርም እየመከረ አሳች ሐሳቡን በጽሑፍ አስተላልፎ ስለነበርና ይህ ጉዳይ ዝም ተብሎ የሚታለፍ ስላልሆነብኝ በዚያው ዝግጅት ላይ ሰጥቸው የነበረው ምላሽ ይሄንን ይመስል ነበር፡፡
“ሌላው አቶ ተራማጅ ስለጋብቻ ሽማግሌ የመላክም ባሕል ኋላ ቀር ነው በማለት አጣጥለው ነቅፈዋል፡፡ ኋላቀሩ ባሕሉ ወይስ እርስዎ የሚለውን በአጭሩ እንይ አቶ ተራማጅ ምክንያት አድርገው ያቀረቡት በጣም አስቂኝ ነገር ነው የሆነብኝ፡፡ ምክንያትዎ ምን ነበር? 1ኛው ሽማግሌዎቹ ሄደው የሚያወሩት ነገር አብዛኛው ውሸት ስለሆነ የሚል ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ተጋቢዎቹ መጀመሪያ ተዋውቀው ተፈቃቅደው የጨረሱት ጉዳይ ነው፡፡ የሚለው ደግሞ ሌላኛ ውምክንያታቸው ነው፡፡
አቶ ተራማጅ ታዲያ በምን ሒሳብ ነው መፍትሔው ባሕሉን ማጥፋት ሊሆን የሚችለው? በትዳር ውስጥ የሚማግጡ ሰዎች አሉና ተብሎ ትዳር ይጥፋ ወይም ይቅር ይባላል እንዴ? ይሄስ ከበሰለ ጭንቅላት የፈለቀ በሳል የመፍትሔ ሐሳብ ነው? ነው ወይስ በትዳር ላይ የሚማግጡ ሰዎች እንዳይኖሩ የሚያስችሉ የማኅበራዊ ግንኙነትና አስተዳደር ሥራዎችን መሥራት? የትኛው ነው የበሰለ እና ማስተዋል የታከለበት የመፍት ሔሐሳብ? እንደዚሁም ሁሉ በሽምግልና የሚዋሹ ሰዎች አሉ ተብሎ ሽምግልና ይቅር አይባልም በሽምግልና ውሸት እንዲቀር መሥራት እንጂ፡፡ በዚህ ላይ አሁን ያለው ሽምግልና የሚላክበት ሁኔታ እና ሽምግልናን የፈጠረው የቀደመው ባሕላችን ሁኔታ ይለያያል፡፡ አንዱ ይሄ ነው ለሁለተኛው ምክንያትዎ ደግሞ እንደው እርስዎ ሲያስቡት አይደለም ልጅን ያህል ነገርና መርፌም እንኳ ቢሆን ሳይጠይቁ እና ሳያስፈቅዱ ከሰው ይወስዳሉ ይዋሳሉ እንዴ? ምን ነካዎት አቶ ተራማጅ? ምንም እንኳን ተጋቢዎቹ አስቀድመው የጨረሱት ጉዳይ ቢሆንም የወላጅ ፈቃድ ይሁንታና ቡራኬ እንዴት አያስፈልግም ጃል? ልጅን ያህል ነገር ማንነቱ ላልተነገረዎትና ለማያውቁት ሰው ባለቤት እንደሌለው እቃ ብድግ አድርጎ ሲወስድ ዝም ይሉታል እንዴ? ወይም ደግሞ ከሱቅ ገዝተው እንደሚተኩት እቃ ዝም ብለው ብድግ አድርገው ይሰጡታል እንዴ? ኧረ ከሱቅ የገዙት እቃም ቢሆን እንኳ ለማያውቁት ሰው ዝም ተብሎ ብድግ ተደርጐ አይሰጥም፡፡ አቶ ተራማጅ ለመሆኑ ሴት ልጅ አለዎት እንዴ? ይሄን ሲሉ እሷን አስበዋል? ምን ያህልስ ይሳሱላታል?
ለዚህ ዓይነት ስሕተት የዳረግዎትና ወደፊትም የሚዳርግዎት ምን እንደሆነ ልንገርዎት? እርስዎ ለማንነትዎ ለመለያዎ ያለዎት ግምትና የሚሰጡት ዋጋ ዝቅተኛ ወይም የተበላሸ ነው፡፡ በመሆኑም ይህ የውስጥ የተበላሸ እምነትዎ የሆነ ነገራችንን ለመተቸት ሲያስቡ ትክክለኛ መመዘኛ እንዳይኖርዎ ከባድ ተጽእኖ ያሳድርብዎታል በመሆኑም ነገሩን በትክክል ለመረዳት ከስሩና ከተለያየ አቅጣጫ ማየት እንዳይችሉ ያደርግዎታል፡፡ እናም እናማ ከእንደዚህ ዓይነት ራስን ከባድ ትዝብት ላይ ከሚጥል ስሕተት ላይ ይጥልዎታል ማለት ነዋ፡፡ አቶ ተራማጅ ይህንን መልስ ለመስጠት የሚያስችል ጊዜ አልነበረኝም ተመሳሳይ ዓይነት የተሳሳተ አስተሳሰብ ያላቸው ዜጐች ብዙ በመሆናቸውና የተላለፈውም በፌዲዮ (በነጋሪተወግ) በመሆኑ ሊያሰናክሏቸው የሚችሏቸው ሰዎች ብዛት አሳስቦኝ በእርስዎ ምክንያትነት ማድረግ ያለብኝን አድርጌ በአጭሩ መልስ መስጠት እንዳለብኝ ስለተረዳሁእንጂ፡፡ ወደፊት እንደ ሁኔታው ለሚያቀርቧቸው ተመሳሳይ ጽሑፎች በተቻለኝ መጠን በሆደሰፊነት መልስ ለመስጠት እሞክራለሁ፡፡ ነገር ግን እባክዎትን ለሚተቹት ነገር ጥልቅ የሆነ ምርመራ እና ግንዛቤ ደርዝ ያለው ምክንያታዊነት ይኑርዎት፡፡ በተቻለዎ መጠን ሚዛናዊ ይሁኑ እንደዚህኛው ዓይነት ጽሑፍዎት ግልብ አይሁን እንዲያም ሲል ደግሞ ለማንነትዎ ለመለያዎ ተቆርቋሪነትን ይጨምሩበት በትክክለኛ አተያይ ይሁን እንጂ የሚተች ወይም የሚነቀፍ ነገር ካለብንም ሳይሳቀቁ ይተቹ ይንቀፉ ነገር ግን የሚተቹብን ወይም የሚነቅፉብን ነገር የእኛ እንከን ብቻ ወይም ከሌሎች አንጻር ስንታይ የባስነው እኛ መሆናችንን እርግጠኛ ይሁኑ፡፡ በተረፈ እንደወረደ ስሜታዊነት በተንፀባረቀበት ሁኔታ ጽሑፉን ስለጻፍኩ ወይም መልስ ስለሰጠሁ ይቅርታዎ አይለየኝ” ብየ ነበር የመለስኩት ለወ/ሮ ገነትም ተስማሚ ሆኖ ስላገኘሁት ነው እዚህ ላይ ማንሣቴ፡፡
በጣም የገረመኝ ነገር ቢኖር ሌላው ቀርቶ ወ/ሮ ገነት ግራ አዝማች ቀኝ አዝማች ደጅ አዝማች የማሳሰሉት አገርኛ የጦር መሪዎች ሥያሜዎችን መጥላት ለወ/ሮ ገነት ግራ ዘመምነት ነው፡፡ ጋዜጠኛ ወ/ሮ መዓዛ ውይይታቸውን ሲጀምሩ ወ/ሮ ገነትን በቅርቡ ፒ.ኤች.ዲዎን ሠርተዋልና ዶክተር እያልኩ ልጥራዎት ወይ? ብላ ብትጠይቃቸው ወ/ሮዋ ምን አሉ? ከህክምና ዶክተሮች በቀር ያሉ ባለ ፒ.ኤች.ዲዎች ዶክተር ተብለው መጠራታቸው ትክክል እንዳልሆነ ተናግረው ሲያበቁ “አሁንማ በምህንድስና የመጀመሪያ ዲግሪ ያለው ሁሉ ኢንጂኒየር እየተባለ ይጠራ ጀመር እኮ!” ሲሉ አሸሞሩ ቀጠሉና “እኔ ዶክተር እከሌ ኢንጂነር እከሌ ሲባል እንደድሮው ደጅ አዝማች እከሌ ቀኝ አዝማች እከሌ የተባሉ ነው የሚመስለኝ” በማለት ያልበሰለና አስገራሚ አስተሳሰባቸውን ገለጡልን፡፡ ቆይ እኔን የሚገርመኝ ወ/ሮ ገነት በዛሬው ዘመን ጄኔራል እከሌ ኮሎኔል እከሌ ሲባል ግን ይመችዎታል አይደል? በባዕድ ቃል የሚጠራው የጦር መሪዎች ሥያሜ ሲስማማዎት ሀገርኛው ግን ያቅለሸልሽዎታል ለምን? ግራ ዘመም በመሆንዎ የራሳችንን መጥላት ስላለብዎ ይሆን? ለመሆኑ የዚህችን ሀገር ነጻነት ያለእነዚህ የጦር መሪዎች ለማሰብ ይችላሉ? አዎ በእርግጥ ታሪክ ሠሪው ሰፊው ሕዝብ ነው ነገር ግን ንብ ያለ አውራው ይሰማራል ይዘምታል እንዴ? የትኛው ሕዝብና የት ነው ያለ መሪ ታሪክ የሠራ? ለምንም ጉዳይ ቢሆን ሲያስቡት አመራር ሳይኖር ሕዝብ እንዴት ሊሠማራና ሥራውን ጉዳዩን ሊከውን ይችላል? የጥላቻዎ ምንጭ ምን እንደሆነ ልንገርዎ? ከቅጥረኛነትዎ የተነሣ እውስጥዎ ያለው የጸረ ኢትዮጵያ ስሜትዎ ነው እንዲህ እንዲያስቡ የሚያደርግዎት፡፡
ለዚህም ነው ኢትዮጵያን ለ40 ዓመታት ያህል ወራ አማራን (የነገሥታቱንና የክርስቲያኑን ወገን) ከአክሱምና አካባቢው መንጥራ ባጠፋችው የተቀረውንም እንዲሰደድና እንዲበተን ባደረገችው፣ አብያተመንግሥታቱንና አብያተክርስቲያናቱን በውስጣቸውም የያዙትን ቅርሳቅርሶች አቃጥላ አፈራርሳና አውድማ የሀገሪቱን ሥልጣኔ ሀብትና የሰው ኃይሏን አጥፍታ ሀገሪቱን ለከፋችግር በዳረገችው ከዚህ ክፉ ሥራዋ በስተቀር አንዲት እንኳን መልካም ሥራ የሚጠቀስ ነገር በሌላት የጥፋት ልጅ በዮዲት ጉዲት ሲጠሩ ኩራት የተሰማዎት፡፡ በቀረቡበት መድረክ ሁሉ ዮዲት ጉዲት ስለ መባልዎ በተጠየቁ ቁጥር መልካም ሥራ ሠርታ እንዳለፈች ሁሉ “እሷ እኮ ታሪክ አላት” እያሉ የሌላትን መልካም ገጽታ ለማስያዝ ጥረት የሚያደርጉት፡፡ ለመሆኑ ምንድን ነው ይሄ ታሪኳ? ተብለው ቢጠየቁ ምን ብለው ሊመልሱ ነው? እርስዎ እኮ አያፍሩም “ሀገር ስላቃጠለች” ይሉ ይሆናል፡፡ ሌላ ሊባል የሚችል ነገር የላትማ! አየ ወ/ሮ ገነት፡፡ እንዴ! እንዴ! አንድ ነገር ትውስ አለኝ ይሄ ባለፈው ሰሞን “እኔ ተሰውሬ የነበርኩት ነቢዩ ኤልያስ ነኝ ከብሔረ ሕያዋን መጣሁ” እያለ ስንት የዋሀንን ያጃጃለው አይሑድ “ዮዲት ጉዲት ሀገር አልሚ እንጅ ታሪክ አለ እንደምትሉት ሀገር አጥፊ አይደለችም ስሟን ሲያጠፉ ነው” እያለ እንዲሰብክ ያደረጉት እርስዎ ይሆኑ? መቸም አያደርጉም አይባሉም እኮ ጠረጠርኩ፡፡
እናም ለዚህ ነው በእሷ ስም መጠራትዎት ሊያኮራዎት እንጅ ሊያሸማቅቅዎት ያልቻለው፡፡ ከወያኔም ጋር እንዲያብሩና ከዚህ የጥፋት ጎጠኛ ቡድን ጋር ተሰልፈው ማጥፋትዎ ቅንጣት ሊሰማዎት ያልቻለውና መልካም እንደሠራ ሰው የሚያንቀባርርዎት፡፡ አየ ድንቁርና፡፡ ወ/ሮ መዓዛ “ፕሮፌሰር ዐሥራት ዮዲት ጉዲት ብለው ስም አወጡልዎት” ብላ ስትጠይቅዎት እኔ በዐይነ ሕሊናየ እንዴት እንደሚሆኑ የሣልኩዎት እንደተኮነነች ነፍስ ሽምቅቅ እንደሚሉ አድርጌ ነበር፡፡ ቢሉም ግን ይሄንን የተሰማዎትን መጥፎ ስሜት ደብቀው ምንም እንዳልተሰማዎት አስመስለው የሆነ ነገር ይመልሳሉ ብየ ስጠብቅ እርስዎ ግን እውነተ ጉዲት አስደሳች ነገር እንደሰሙ ሁሉ እየተፍነከነኩና ኩራት እየተሰማዎት “እሷ እኮ ታሪክ ያላት ናት” ብለው ሲመልሱ አሁን እኒህ ሴትዮ ምናቸው ነው የተማረው? ብየ ነበር እራሴን የጠየኩት፡፡
በነገራችን ላይ ፕሮፌሰር ዐሥራት እርስዎን ዮዲት ጉዲት ብለው ስም ሲያወጡልዎት እርስዎ እሽ እያሉ ለምን? እንዴት? ሳይሉ በፍጹም ታዛዥነት ለጥፋት ቡድኑ መጠቀሚያ በመሆን ወያኔ እርስዎን ብዙ ያስጠፋዎታል ብለው በማሰብ እንጅ በራስዎ በጭንቅላትዎ አስበው የመወሰን ሥልጣን ኖሮዎት የሚያደርጉት ነገር ይኖራል ብለው ያንን ከመፍራት እንዳልሆነ ጠንቅቀው የሚያውቁት ይመስለኛል፡፡
ለምሳሌ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተባረሩት የ41ዱን ዶክተሮችና ፕሮፌሰሮች በእርግጥ የተባረሩት 42 ነበሩ አንደኛው ግን አቶ ማንትስ የተባለው ሳይገባው ከእነሱ ጋር ተቆጥሮ የተባረረና ወዲያውም የወያኔ ቀንደኛ ደጋፊ የሆነ በመሆኑ የእሱ መቀነስ ትክክል ነው፡፡ እናም እነኝህ 41 ዶክተሮችና ፕሮፌሰሮች ሲባረሩ የእርስዎ የግል ውሳኔ ሊሆን እንደማይችል ማንም ሊረዳው የሚችለው ጉዳይ ነው፡፡ የዚህም ማረጋገጫ የሚሆነው እነሱን ካባረሩ በኋላ እነሱ ይሰጧቸው የነበሩትን ኮርሶች እነሱ ባስተማሯቸው በፍሬሽ (ደራሽ) ተመራቂዎች እንዲሸፈኑ መደረጉና ከፊሎቹ ዲፓርትመንቶችም (ክፍል ጥናቶች) ከናካቴው ተዘግተው መቅረታቸው ነው፡፡ ይህ የደነቆረ ፖለቲካዊ ውሳኔ መሆኑን እንጅ አሥተዳደራዊ ውሳኔ መሆኑን አያሳይም፡፡ የሚገርመው ይሄንን ካደረጋቹህ በኋላ የተከተለው ችግር እውነቱ ፈጦ እየታየ የብቃት ማነስ ብላቹህ መናገራቹህ ነው፡፡ ይሄ ምላሻቹህ የእነሱ ጉዳይ በተነሣ ቁጥር የምትሰጡት አሳፋሪ ምክንያት እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ከ12 ዓመታት በፊት በፋና ሬዲዮ የቀጥታ የስልክ ውይይት ላይ ይሄንን ጉዳይ አንስቸ ወያኔን በምወቅስበት ጊዜ አንድ የወያኔ ሹም የሥራ ኃላፊ የመለሰው መልስ አሁን እርስዎ የተናገሩትን ነው፡፡ የብቃት ማነስ የተባውን ክስ ሐሰተኛነት እንዲያጋልጡ አስከትየ ላቀረብኩለት ጥያቄዎች ግን ከመርበትበት በስተቀር ሊያቀርበው የቻለው በልስ አልነበረም፡፡
እርስዎም እንዲህ በይ ተብለው ያኔ የተሰጥዎትን መልስ ሳይረሱ ከስንት ዓመታት በኋላም ያችኑ ሳይጨምሩ ሳይቀንሱ ተፏት፡፡ ሞጋች ጋዜጠኛ ስላላጋጠምዎት ዕድለኛ ነበሩ ሐሰተኛ ምክንያት ሰጥተው ተሳድበውም ለማለፍ ቻሉ፡፡ ከዚህ ውጭ ያለው ምክንያት እውነተኛውና ትክክለኛው በመሆኑ ሰዎቹ እንደዜጋና እንደምሁር በሀገራቸው ጉዳይ ላይ በያገባኛል ስሜት ምሁራዊ አስተዋጽኦ ለማበርከት መጣራቸው ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው በመሆኑና በዚህ ምክንያት ሰውን ከሥራ ገበታው ማባረር አንባገነንነታቹህን የሚያጋልጥ ስለሆነ ከመዋሸት ውጭ አማራጭ አልነበራቹህም፡፡ ባይሆን የምትሰጡት ሐሰተኛ ምክንያት በቅጡ (ቴክኒክሊ) ሲታይ ሐሰትነቱ በቀላሉ ሊታወቅ የማይችል ማድረግ ግን ነበረባቹህ፡፡ በነገራችን ላይ ይህች አሁን እርስዎ ያሏት ምክንያት እኮ ተሽራ ተሳስተን ነው በሚል በ1997ዓ.ም. በአቶ መለስ ተቀይሯል አልሰሙም ማለት ነው? ወ/ሮ ገነት እንዲያው ግን ሌላው ሌላውን ይተውትና ደርግን “ምሁራንን እንዲሰደዱ ያደረገ የተማረው ክፍል ጠላት ነው!” እያሉ ለሚከሱና ለሚንገበገቡ ዱላውንም ለቀመሱ ለእርስዎ ለሕሊናዎ ይሄንን የማባረር ውሳኔ እንደምን በጸጋ ሊቀበሉት ቻሉ፡፡ ነው ወይስ ያ ስሜትዎ የውሸት ነበር? አዎ በእርግጥም የውሸት ነው፡፡ ስለ ሰብአዊ መብቶችና ደርግ በዜጎች ላይ ስለፈጸመው ግፍ እንደዚያ በስሜት የሚናገሩት የውሸትና የማስመሰል ነው፡፡ ልጅዎ ምን አድርጎ ሥልጣንዎን መከታ በማድረግ ኃይልዎን አላግባብ በመጠቀም ምን እንዳይደረግ እንዳደረጉ የሚረሱት አይመስለኝም፡፡ ወ/ሮ ገነት እስኪ ለአንድ አፍታ እራስዎን በሰለባ ቤተሰብ ቦታ አድርገው ያን አደጋ ለማሰብ ይሞክሩ? ምን ተሰማዎት? ሲጀመር የሰብአዊና የዜጎች መብት የሚያንገበግበው የሚቆረቁረው የሚሰማው ቅንና ስስ ልብ ቢኖርዎት ኖሮ በምንም ተአምር ወያኔ ሊሆኑና ወያኔነት ሊስማማዎት ባልቻለ ነበር፡፡ በዚህ ላይ ደሞ አማራ ሆነው! አይ ወ/ሮ ገነት አማራ ነኝ ሲሉ ግን ትንሽ አያፍሩም? መቸም ወያኔ ለአማራ ምን አስቦለት ሥልጣን ከያዘ ማግስት ጀምሮ ምን ሥልጣን ከያዘ ገና በረሀ እያለ ጀምሮ ምን አስቦበት እስከአሁንም ምን እያደረገው እንደሆነ በገሀድ በአደባባይ የሚታይ ነገር ነውና ከሆድዎ ሻገር ብሎ ማሰብ የሚችል ጭንቅላት ስለሌለዎት እንጅ ነጋሪ የሚያስፈልግዎ አልነበረም፡፡ እባክዎን አማራ ነኝ አይበሉ እንዳልሆኑ እኔ እነግርዎታለሁ፡፡ ስለዚህ ወ/ሮ ገነት የሚያስብ ጭንቅላት ካለዎት እርስዎ ምንም ሊሉ የሚችሉበት አፍ የለዎትምና ነውረኛ ማንነትዎን እንደታቀፉ ነግቶ ውርደትዎን እስኪከናነቡ ድረስ አርፈው ይቀመጡ እሽ?
እስከአሁን ድረስ እኔ በእርግጠኝነት የድንቁርና ምንጩ ምን እንደሆነ አላውቅም፡፡ በተፈጥሮው ደንቆሮ የሆነ እንደሌለ ግን እርግጠኛ ነኝ፡፡ የድንቁርና ካፋቱ ልክን አለማሳወቁ ሰውን ያለ ፍርሐትና ሐፍረት በድፍረት ማናገሩ ነው፡፡ ወ/ሮ ገነት “የኢትዮጵያ ሴቶች” ብለው አጠቃለው በመጀመል ሀገራችን ኢትዮጵያ ሴቶችን በተመለከተ ተስተካካይ የሌለውን ቀና አስተሳሰብና በሀገራችን ታሪክ ሴቶች ምን ያህል ቦታ እንደነበራቸው ማጤን ይገባቸው እንደነበር መጽሐፍ ለመጻፍ የተነሣ ሰው አይደለም የቡና ወሬ ለሚያወራ ሰው እንኳ የሚዘነጋ ጉዳይ አልነበረም፡፡ ወ/ሮ ገነትን ግን ይሄ ጉዳይ ጨርሶ አላሳሰባቸውም እንዲያው ብቻ አፋቸው እንዳመጣላቸው “ሴቶች በኢትዮጵያ እንደሰው አይቆጠሩም” ሲሉ በውይይታቸውም ያውም አእላፋት እየሰሙ ይሄ የቅጥረኛነት አጀንዳቸው እውነት መስሎ እንዲታሰብላቸው በሀገራችን የሴቶችን ገናናነት የሚመሰክረው ታሪክ የያዘው የሀገራችን ታሪክ ድራሹ እንዲጠፋላቸው እየተመኙ የደደረ ድንቁርናቸውን በሚቀፍ መልኩ ሲያሳዩን ቅንጣት እንኳን አልተሰማቸውም፡፡ ወ/ሮ ገነት እርስዎ እንደሰው ሳይቆጠሩ ኖረው ከሆነ ይሄ ከራስዎ ከግል ማንነትዎ ጋር በተያያዘ የራስዎ ችግር እንጅ የሀገሬና የወገኔ ችግር እንዳልሆነ ላረጋግጥልዎት እወዳለሁ፡፡
ወ/ሮ ገነት ለመሆኑ ሀገራችን ኢትዮጵያ ሴቶች ብቃት እንዳላቸው አውቃ በታሪኳ ከ15 በላይ ሴቶችን ለመጨረሻው የሥልጣን ደረጃ ያበቃች ሀገር እንደሆነች ያውቃሉ? ግራ ዘመም ስለሆንኩ ነባሩን የሀገር ማንነት ባሕል እሴቶችን በሙሉ መጥላት አለብኝ ብለው እያሰቡ እንዴት ብለው ሊያውቁ ይችላሉ? ይሄንን የሀገሬን ስኬት እርስዎን ቀጥረው የራሳቸውን ችግር የእኛ ችግር እንደሆነ አድርገው በእርስዎና በመሰሎችዎ አፍ የሚናገሩት አውሮፓውያን እንኳን አግኝተውት ያውቃሉ? አይደለም 15 አንድ እንኳን አይደለም በጥንት ዘመን አሁን ሠለጠን በሚሉበት ዘመን እንኳን ያሳኩ ሀገራትን ሊጠቅሱልኝ ይችላሉ? እኔ ግራ ዘመም ነኝና ይሄንን ታሪካቹህን መቀበል መመስከር አልችልም ብለው የሚያምኑ ቢሆንም እንኳን ዝም ይባላል እንጅ ታዲያ እንደሌለ አድርገው ያወራሉ እንዴ! ነውር አይደለም? ለነገሩ እርስዎ ነውር የት ያውቁና፡፡
ወ/ሮ እርስዎ እያሉ ያሉት “ሀገራችን ሴቶች ሴት በመሆናቸው ብቻ የሚጠቁባት ሀገር ናት” ነው የሚሉት እኔ ደግሞ ፍጹም ሐሰት ነው እያልኩዎት ነው ያለሁት፡፡ ምክንያቱም ሴቶችን የሚያጠቁ ወይም የሚበድሉ ባሎች ወይም ጓደኞች ወይም ወንድሞችን ስናይ ሴቶቻቸውን የሚያጠቋቸው ሴት ስለሆኑ ወይም ወንድ ስላልሆኑ አይደለምና፡፡ ሴት ስለሆነች ወይም ወንድ ስላልሆነች ብቻ ጥቃት የሚያደርስ ሰው ካለ እስካሁን ሰምቼ ዐይቸም አላውቅም ይኖራል ብዬም አልገምትም አለ ከተባለ ግን ይህ ሰው ጤነኛ ባለመሆኑና ለየት ያለ (Exceptional) በመሆኑ ጉዳዩ መታየት ያለበት በተለየ ሁኔታና ቦታ እንበል ለምሳሌ በአእምሮ ሕሙማን ማዕከላት ዓይነት ቦታ ነው፡፡
ጉዳዩ ወይም ችግሩ ግን ፈጽሞ የማኅበረሰቡ ተደርጎ መታየት የለበትም፡፡ ይህንን ካደረግን ግን ማኅበረሰቡን መስደብና ማዋረዳችን ነው፡፡ በደል የተፈጸመባቸውን ሴቶች የበደል ዓይነቶች ያየን እንደሆነ እነዚያ የተፈጸሙ በደሎች ሁሉም በተመሳሳይ ሁኔታ በወንዶችም ላይ የሚፈጸሙ ናቸውና፡፡ በመሆኑም በደሉ የተፈጸመባት ሴት ያ በደል የተፈጸመባት ሴት በመሆኗ አይደለም ማለት ነው፡፡ ታዲያ ምንድነው? ያልን እንደሆነ በጉልበትና በመሳሰሉት ነገሮች በደል ከሚያደርሰው ሰው ያነሰች ስለሆነች ነዋ! በማነሷም በጉልበት ከእሱ ማነሷን ምቹ ሁኔታ ተጠቅሞ ከእሷ የሚፈልገውን ነገር ለማግኘት ወይም ለመበዝበዝ ነው፡፡ ወንዶች ያላቸውን ጉልበት የሴቶች ሴቶች ያላቸውን የአቅም ውሱንነት ለወንዶች አድርገን ብናስበው ይህ አሁን በሴቶች ላይ እየተፈጸመ ነው ያሉት ችግር ሁሉ የሚታሰብ ባልሆነም ነበር፡፡ በመሆኑም ጉዳዩ የጉልበተኞች እና የአቅመ ውስኖች ጉዳይ እንጂ በፍጹም የጾታ ጉዳይ ወይም ሴት እና ወንድ የመሆን ጉዳይ አይደለም ማለት አይመስልዎትም ወ/ሮ ገነት? በወንዶችም ላይ የሚፈጸመው ይሄው ነውና፡፡ ጉልበተኛው አቅመ ቢሱን ወይም ደከም ያለውን ሲጎዳው ሲያጠቃው ሲበድለው ሲበዘብዘው እንደሚታየው ሁሉ ማለት ነው፡፡ ሕፃናት ወንዶች አንዳንዴም አዋቂ ወንዶች ለመግለጽ የሚቀፍ የጥቃት ሰለባ እየሆኑ ባሉበት ሁኔታ የጥቃት ዓይነቶችን በፆታ ወስነን እንዴት ነው የሴቶች እንደዚህ ልንል የምንችለው? ፆታ የለየ ጥቃት ከሌለስ እንዴት ነው ጥቃትንና ፆታን ልናያይዝ የምንችለው?
በዚህም ምክንያት የሴቶች ምንትስ የሴቶች እንደዚህ አሁንም የሴቶች ቅብርጥስ የሚባሉ ነገሮች ሁሉ ችግሩንና ጉዳዩን በትክክል ማየት መግለጽ መወከል ካለመቻላቸው የተነሣ ሥያሜዎቹ ፈጽሞ አይመቹኝም፡፡ ይሄ እንዲያውም የእናንተ ቁማር ይመስለኛል፡፡ ኅብረተሰቡን በተገቢው መንገድ ማስተዳደር ሲያቅታቹህ ወይም ከማኅበረሰቡ ለሚሰነዘሩ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ሲሳናቹህ የማኅበረሰቡን ትኩረት ማስቀየሻ እና ከእናንተ ላይ ዞር ማድረጊያ ለዚያ ማኅበረሰብ እዚያው ባለበት የሚይዝላቹህን ፆታን እና የመሳሰሉትን ርእሰ ጉዳዮች መሠረት ያደረጉ የተለያዩ የቤት ሥራዎችን ሆን ብላቹህ ትፈጥራላቹህ፡፡ ይሄም እንግዲህ ከቤት ሥራዎቹ አንዱ መሆኑ ነው፡፡ ይህን ስል ግን ለተገፉ ወይም ለተጠቁ ሰዎች ጥብቅና አይቆም ይረሱ ይገለሉ ማለቴ እንዳልሆነ መረዳት የሚችል ጭንቅላት ያለው ሰው ሁሉ ይረዳኛል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ነገር ግን ዓላማችን የተገፉትን ወይም የተጠቁትን ሰዎች መብት ማስከበር ወይም ማስጠበቅ ከሆነ፤ይሄንንም ለማድረግ አቅምን አይቶ ወይም ገምቶ በአቅም ውስንነት ምክንያት በተወሰኑ የማኅበረሰብ ክፍል ላይ ብቻ አትኩሮ መሥራት ካስፈለገ ወይም ግድ ካለ፤ በተሳሳተ ሚዛን ጾታን መሠረት ባደረገ ሥያሜ በጅምላ የሴቶች መብት በማለት ሳይሆን የተጠቂ ሴቶች ጉዳይ ወይም የተበደሉ የግፉአን ማለትም የተገፉ ሴቶች መብት ተከራካሪ ወይም አስጠባቂ ቢባል ትክክለኛ ሥያሜ ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም የማይጠቁና ያልተጠቁ ሴቶች አሉና፣ ያልተገፉና የማይገፉ ሴቶች አሉና፣ የተከበሩ እና የሚከበሩ ሴቶች አሉና ለእኛ ለሐበሾች ይሄ ሊነገረንና በዚህ ልንታማ ጨርሶ የሚገባ ጉዳይ አልነበረም፡፡ ከተሞከረም ድፍረት ነው፡፡
ማንም ነጭ ለእኛ ለሐበሾች አፍ አለኝ ብሎ እና ደፍሮ በዚህ ርእሰ ጉዳይ ላይ ሐበሻን እንደ ሐበሻ ሊነቅፍ ወይም ሊኮንን የሚችልበት የሞራል (የቅስም) አቅም ብቃትና ነፃነት ከቶውንም የለውም፡፡ በታሪኩ የሴት መሪ አይቶ ወይም አግኝቶ ወይም አብቅቶ የማያውቅ ድኩም ኅብረተሰብ ከቀዳማዊት ሳባ (ከዛሬ 4380-4370 ለ10 ዓመታት የነገሠች) ጀምሮ እስከ ቀዳማዊት ዘውዲቱ ከ15 በላይ ገናና ብልህ አስተዋይ ብቁ ሴቶችን ያፈራንና ያበቃን ሕዝብ እና ሀገር ሊነቅፍ ሊመክር ሊኮንን ሊተች የሚችልበት ኧረ በየትኛው ሒሳብ ይሆን ወ/ሮ ገነት? እንደ አለመታደል ሆኖ በዚህ ዘመን ካለን ሐበሾች ጥቂት የማንባለው አፈር ያብላንና ለነገሩ በልተናል ከዚህ በላይ አፈር መብላት የት አለና፡፡ ክብራችንን ዋጋችንን (ቫልዩአችንን) ባለማወቅ የዚያ ችግር ባለቤት ወይም ተጠቂ የሆኑ የበርካታ ምዕራባዊያን ሀገሮች ጩኸት ሴቶችን ለመሪነት ማብቃት አይደለም ለሴቶች እንደ ሰው የሰውነት መብት ከሰጡ እንኳን ከአንድ የእድሜ ባለጸጋ እድሜ የማያልፉትን፣ የሴቶችን ሰብአዊ መብቶች ሕገ መንግሥቶቻቸውን ጨምሮ በተጻፉ ሕጎቻቸው ሁሉ በይፋ የደፈለቁትን ኅብረተሰቦች ወይም ሀገሮች ጩኸት የሴቶችና የወንዶች የሚል ልዩነት ሳታደርግ እስከ የመጨረሻው የሥልጣን ደረጃ አብቅታ ባረጋገጠች ሀገር፣ ሴት ልጅ ክብሯን ለመጠበቅ ካልሆነ በቀር ጾታዋን እንደበደል እንደእርግማን በመቁጠር ምንም ዓይነት ገደብ አድርጎ በማያውቅ ኅብረተሰብና ሀገር ኢትዮጵያ ውስጥ በእኛው በሐበሾች አፍ ስንጮኸው ጉዳዩ ምን ያህል አሳዛኝና ልብ የሚሠብር እንደሆነና በዚህ ዘመን ያለነውን ሐበሾች ያለንበትን የሞራል (የንቃተ ወኔ) ዝለት፣ ኪሳራና ዝቅጠት የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡
ምንአልባት አንዳንድ የሚታዩ የሚመስሉ ነገሮች ካሉ ወይም ቢኖሩ እነኚህ የድህነት ገጽታችን የፈጠራቸው ሳንኮች የድሀነታችን መገለጫዎች እንጂ በፍጹም እንደ ሐበሻ የባሕላችን አካል ወይም የአስተሳሰባችን ደረጃ ሆነው አይደለም፡፡ አስተዋይ ልቡና ያለው ማንኛውም ሰው ይህንን በሚገባ ይረዳል፡፡ ሀገራችን ለሴቶች ያላት ክብርና ቦታ ተወዳዳሪ የሌለው ነው ይሄንንም አድርገን አሳይተናል፡፡ በሀገራችን እግዚአብሔር እንኳን በወንድ ብቻ አይጠራም በሴትም እንጅ ቅድስት ሥላሴ ተብሎ፡፡ ሀገርም እራሷ የምትጠራው በሴት ስም ነው እናት ሀገር በመባል፡፡ ሌሎች የሚወደዱ ነገሮች ሁሉ በሴት ስም ነው የሚጠሩት፡፡ ከዚህ በላይ የጾታ እኩልነት የት አለ? እስኪ ይሄንን የአስተሳሰብ ጣራ እንደኛ አንድ ሳያጓድል በቋንቋው በባሕሉ በሥልጣኔው የያዘ ሀገርና ሕዝብ ይጥሩልኝ?
ይሄን ይሄን እኮነው ድንቁርና የምልዎት ወ/ሮ ገነት፡፡ የምለው ነገር ሁሉ ይገባዎታል ግን? በእርግጥ ድንቁርና እኮ የሌለበት ሰው የለም ምን ያህል በማን ላይ ይጠናበታል ይገንበታል የሚለው ነው የሚለያየው እንጅ ሁሉም ሰው እኮ ድንቁርና አለበት፡፡ ምን ሰብስቦ አንድ ላይ እንዳጎራቹህ እንጃ እንጅ በወያኔ ቤት ያለው ድንቁርናና የደናቁርት ዓይነትና ብዛትማ ለጉድ ነው!
ድንቁርና አነስተኛም ሊሆን ይችል ይሆናል እንጅ የቀለም ቀንድ የበቃ ምሁር በሚባል ሰውም አይጠፋም፡፡ በትምህርት የሚወገድ የድንቁርና ዓይነት አለ በሌላ በኩል ደግሞ ፕሮፌሰር ተብሎም ፊደል ካልቆጠረ መሐይም በማይሻል መልኩ ድንቁርናውን ትምህርት የማያጠፋለት የሰው ዓይነትም አለ፡፡ የእርስዎ ድንቁርና መገለጫዎችን ልንገርዎት? በካፈርኩ አይመልሰኝ ፈረስ ሽምጥ መጋለብዎት፣ በእልሀቸው እያሉ በጥፋት ላይ ጥፋት በመደረብ ጌቶቸ ለሚሏቸው ምቹ አጋሰስ መሆንዎ፣ ምክንያታዊ አለመሆንዎ፣ ከተኮነንኩ አይቀር በሚል አስተሳሰብ በየትኛውም ቦታ በመቸም ሰዓት ገዢ ለሆኑ እውነቶች ለመገዛት አለመፍቀድዎ ለሞራል (ለቅስም) ድንጋጌዎች ጨርሶ ለመገዛትና ለመዳኘት አለመፍቀድዎና ጭራሽም ዐይንዎን በጨው አጥበው ሰው ምን ይለኛል ሳይሉ እየፈጠሩ እየቀጠፉ እየዋሹ ማውራትዎ ወዘተ. ናቸው፡፡ ያው ወያኔ ሆኖ ሕሊናንና ጭንቅላትን መጠቀም አይቻልም አይደል? እንዴት ብለው ታዲያ ከዚህ የድንቁርና በሽታ ይድናሉ? ያው መቸስ ቢጤ ከቢጤው ጋር አይደል የሚቧደነው? ወያኔ ሊሆኑ የቻሉትስ እንዲህ ዓይነት ሰው በመሆንዎም አይደል? እንጅ አሁን ማን ይሙትና የወያኔ ማንነት ማንን መማረክ ማንን ማታለል ይችላልና ነው ወያኔ የሆኑት? ደርግ የፖለቲካ ተቃዋሚዎቸ ናቸው በሚላቸው ላይ ግድያን ለሁለትና ሦስት ዓመታት የፈጸመውን ግፍ ወያኔ በዚህኛው ላይ ጠላትና መጥፋት ያለበት ብሎ የፈረጀውን ብሔረሰብ ጨምሮበት በከፋ መልኩ በግልጽም በስውርም ለ23 ዓመታት እየፈጸመው ያለውን ግፍ በደል ኢሰብአዊ ድርጊቶች ሳያውቁ ሳይሰሙ ቀርተው አይደለም፡፡ ዛሬ እነሱ እንኳን በሥራቸው አፍረው ሞራልም (ንቃትም) አጥተው እንደ ድሮው ደፍረው ማውራት በተውበት ዘመን ይህ ሥርዓት ለፍትሕና ለዲሞክራሲ ለእኩልነት የቆመ እንደሆነ አድርገው የሚወሸክቱት፡፡
ስለ ትምህርት ሥርዓቱ በሌላ ጽሑፍ እመጣልዎታለሁ ነገር ግን “ላለው የትምህርት ጥራት ማሽቆልቆል ተጠያቂው መምህሩ ነው ፖለቲካዊ በሆነ ምክንያት የትምህርት ሥርዓቱን ስላልተቀበለው” ማለትዎ ያልተቀበለበት ምክንያት ፖለቲካዊ ብቻ አይደለም እንጅ እውነትነት አለው፡፡ እንዲህ ከፊል እውነት መናገርዎም ጥሩ ነው ይበርቱ፡፡ ስለዚህ ወ/ሮ ገነት በሕዝብ ዘንድ ያላቹህን ተቀባይነት በሚገባ ያውቁታል ማለት ነው፡፡ መምህሩ ብቻ አይደለም የማይቀበላቹህ፡፡ መምህሩ ከሌላው ማኅበረሰብ ተነጥሎ ሊጠላቹህ ላይቀበላቹህ የሚችልበት ምክንያት ሊኖር አይችልም፡፡ ምክንያቱም መምህራን የኅብረተሰቡ አንኳር አካል እንጅ ከሌላ ዓለም የመጡ ልዩ ፍጥረቶች አይደሉምና፡፡ ሕዝብ ወዶ መርጦን እያላቹህ የምትወሸክቱት ውሸት መሆኑን ስላረጋገጡልን እናመሰግናለን፡፡ ስለዚህ በሌላ ጊዜ ሕዝብ መርጦን ፖሊሲያችንን (መመሪያዎቻችንን) ወዶልን ነው እያሥተዳደርን ያለነው ብለው ደግመው እንደማይዋሹን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ አይደል ወ/ሮ ገነት?
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
http://www.goolgule.com/genet-zewdie-is-it-really-how-it-is/