Sunday, April 27, 2014

ጥቂት ስለ ማዕከላዊ! (አክመል ነጋሽ)

ማዕከላዊን በከፊል አውቀዋለሁ፡፡ ትናንት ሰባት የሚሆኑ ጋዜጠኞች፣ ብሎገሮችና አክቲቪስቶች መታሰራቸውን ተከትሎ ወደ ማእከላዊ መወሰዳቸውን ሰምተናል፡፡ በቀጣዮቹ ቀናት ምን ሊፈጠር እንደሚችል ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ጨለምተኛ ልመስል እችል ይሆናል፤ እውነታው ግን ይኸው ነው፡፡
መጀመሪያ ክሱ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው አጓጊ ጥያቄ ነው፡፡ ይህን ለማወቅ ወሳኝ ፍንጭ የሚሰጠው የቤት ፍተሻው ነው፡፡ የታሰሩትን ሰዎች ቤት የሚፈትሹት ፖሊሶችና መርማሪዎች ቤቱን የሚፈትሹት ለጥቂት ሰዓታት (ቢበዛ ለሁለት ሰዓታት) ከሆነና በጣም ብርበራ ያልበዛበት ከሆነ አለቆች በጸረ ሽበር ሕግ ለመክሰስ እንዳላሰቡና አስፈራርተው ብቻ በዋስ ለመልቀቅ እንዳሰቡ ፍንጭ ይሰጣል፡፡ በተቃራኒው ፍተሻው በትንሹ ከስድስት ሰዓታት በላይ የሚረዝምና በቤቱ የተገኘውን ወረቀት፣ መጽሐፍ፣ ሲዲ፣ ኮምፒውተርና ሞባይሎች ምንም ሳይስቀሩ ሰብስቦ የሚያስኬድ ከሆነ ጉዳዩ በጸረ ሽብር ሕግ ከመክሰስ ጋር የተያያዘ እንደሆነ መጠርጠር ያሻል፡፡
ይሄ የቤት ፍተሻ የቤቱን ኮርኒስ መቅደድና ወለሉን እስከመቆፈር ይደርሳል፡፡ በዚህ ጉዳይ ውስጥ ዋናው ግንዘቤ መወሰድ ያለበት ነገር ሰዎቹ የሚያስሩት ማስረጃ በመያዝ ሳይሆን፤ ማስረጃ ሊሆን የሚችል ማንኛውም ነገር በፍተሻው አግኝቶ እሱን ቀባብቶና አሳምሮ መክሰስ መቻላቸው ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ መርማሪዎች፣ አቃቢ-ሕጎችና ተሰያሚ ዳኞች ተገናኝተው እንዲያወሩ ስለሚደረግ ነገሩን ፍርድ ቤት አድርሶ የሚፈለገውን ውሳኔ ለማስወሰን መንገዱ ጨርቅ ነው፡፡
በማእከላዊ ከተወሰዱ በኋላ ቢያንስ ለሦስት ቀን ያህል ከቤተሰብም ሆነ ከማንም ጋር መገናኘት የማይተሰብ ነው፡፡ ይህ ታሳሪዎቹንም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን የበለጠ ለማደናገጥና የሥነ-ልቦና ጫና ውስጥ ለመክተት ወሳኝ ነው፡፡ ታሳሪዎቹ በቀጥታ የሚወሰዱት ‹‹ጣውላ ክፍል›› ወደሚባሉ የእስር ክፍሎች ነው፡፡ በዚህ ክፍል የሚታሰሩ ሰዎች በ24 ሰዓት ውስጥ ለ15 ደቂቃ ያህል የሚቆይ ጸሀይ መሞቂያና መጸዳጃ ቤት መሄጃ ፈቃድ ይሰጣቸዋል፡፡ እነዚህ ከፍሎች በግምት አራት በአራት ስፋት ያላቸውና ወለላቸው ከጣውላ ጣሪያና ግድግዳቸው ከኮንክሪት የተሠራ ሲሆን፤ ቦታው ሻል ካለው የእስር ኮሪደር ‹‹ሸራተን›› እጅግ ያነሰ ነጻነት ያለውና፤ በጣም ከባሰው ጨለማ ክፍል ‹‹ሳይቤሪያ›› የተሻለ ቦታ ነው፡፡ ምርመራው ለእስር በገቡበት ምሽት ይጀመራል፡፡ የኢ-ሜይልና ሌሎችም አካውንቶች ፓስወርዶች በግድ እንዲሰጡ ይደረግና የኮምፒውተር ሀ ሁ በማያውቁ ‹‹መርማሪዎች›› አካውንታቸው ይበረበራል፡፡
ከዚሁ ጎንለጎን ቀለል ያለ ምርመራና ጥያቄና መልስ ይካሄዳል፡፡ በቀጣዮቹ አምስት እና አስር ቀናት ‹‹ጠቃሚ ውጤት በምርመራ አላገኘንም›› ብለው ካሰቡ ወደ ሌላኛው የእስር ክፍል ወደ ‹‹ሳይቤሪያ›› ያዘዋውሯቸዋል፤ በዚህ ወቅት የምርመራ ስልቱና አጠቃላይ ሁኔታውም ይለወጣል፡፡ ታስረው መቆየት ‹‹አለባቸው›› ወይም ‹‹የለባቸውም›› የሚለውን የሚወስኑት በዚህ ጊዜ ነው፡፡ ውሳኔው ይፈቱ ከሆነ ወደ ‹‹ሸራተን›› የእስር ክፍል ያዘዋውሯቸዋል፡፡ ይህ ከቤተሰብ ጋር መገናኘት የሚያስችል የእስር ቦታ ሲሆን፣ በጊቢው ካሉት የእስር ክፍሎች ሁሉ የተሻለ አንጻራዊ ‹‹ነጻነት›› ያለው ነው፡፡
በጥቅሉ ሳይቤሪያ ከአንድ ሜትር ስኩዌር ብዙም የማይበልጥ፣ ጨለማ፣ በጣም ቀዝቃዛና አምስት ቀናት ቢቆዩቡት መላው አካልን ወደ አመድነት (ነጭነት) የሚለውጥ ዘግናኝ ቦታ ነው፡፡ በዚህ እስር ክፍል ውስጥ ሰዎች የሚታሰሩት ያላደረጉትን ነገር አድርገናል ብለው እንዲያምኑ ወይም የያዙትን ‹‹ሚስጥር›› ‹‹እንዲያወጡ›› ነው፡፡ በዚህ ክፍል የሚታሰሩ እስረኞች አንዳንዴ ያልተቋረጠና እስከ 14 ሰዓት የሚደርስ ምርመራ በፈረቃ በሚቀያየሩ መርማሪዎች ይደረግባቸዋል፡፡ በምርመራው እንደ እስረኛው ሁኔታ የሚላላና የሚጠነክር ድብደባና ቶርች መጠቀም የተለመደ ‹‹አሠራር›› ነው፡፡ ቶርች የተደረጉ ሰዎች ቁስላቸው እስከሚያገግም ከቤተሰብም ሆነ ጠበቃ ጋር ማገናኘት የማይታሰብ ነው፡፡ በእነዚህ ሁሉ ወቅቶች ቤተሰብ ምግብ ለማድረስ፣ ጠበቆች ደንበኞቻቸውን ለማግኘት የሚደርጉት ጥረት ውጤት አልባ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ይቺ ነች፡፡
By Akemel Negash
http://ecadforum.com/Amharic/archives/12025/

ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ያልተሰበሰበ ከ2.3 ቢሊዮን ብር በላይ ያልተሠራበት በጀት ከ785 ሚሊዮን ብር ሕጋዊ ያልሆነ ወጪ ተጋለጠ (ሪፖርተር)

የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ላለፉት በርካታ ዓመታት ለፓርላማ ሲያቀርበው እንደቆየው ሁሉ፣ ለብክነት የተጋለጠ በቢሊዮኖች የሚቆጠር የመንግሥት ሀብት መኖሩን ባለፈው ሚያዝያ 14 ቀን 2006 ዓ.ም.ለፓርላማው ይፋ አድርጓል፡፡ ተመሳሳይ ሪፖርቶችን ሲሰማ የቆየው ፓርላማው ፈጣን ዕርምጃ ከመውሰድ ይልቅ የአንድ ዓመት ገደብን መስጠት መርጧል፡፡በዝቅተኛ የደመወዝ ክፍያ ምክንያት ሠራተኞችን ለማቆየት መቸገራቸውን የገለጹት የፌደራሉ ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ፣ ችግሩን ለመቅረፍ ራሳቸው ጭምር በቡድን መሪነት በተሳተፉበት የ130 የፌደራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶችን የ2005 ዓ.ም. በጀት ኦዲት በማድረግ፣ እንዲሁም በኦዲት ሰርቪስ ኮርፖሬሽን የስምንት መሥሪያ ቤቶችን ኦዲት በማሠራት፣ በአጠቃላይ የ138 መሥሪያ ቤቶችን ኦዲት በመተንተን የኦዲት ግኝቱን ለፓርላማ አቅርበዋል፡፡ከቀረበው የፋይናንስ ሕጋዊነትን የተመለከተ የኦዲት ሪፖርት ውስጥ አንድ ቢሊዮን 527 ሚሊዮን ብር ተሰብሳቢ ሒሳብ መኖሩን፣ ሕጋዊ ሥርዓቱን በልተከተለ መንገድ የተለያዩ የመንግሥት ድርጅቶች 785 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጋቸውን፣ የተፈቀደው በጀት በትክክል ሥራ ላይ መዋሉን ለማረጋገጥ በተደረገ ኦዲት ደግሞ 2.3 ቢሊዮን ብር ያልተሠራበት በጀት መገኘቱን ይፋ አድርገዋል፡፡ውዝፍ ተሰብሳቢ ሒሳብ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት በወቅቱ ካልተወራረደ ወይም ካልተሰበሰበ በቆየ ቁጥር የመሰብሰብና ወደ ሀብትነት የመለወጥ ዕድሉ አሳሳቢ መሆኑን የገለጹት ዋና ኦዲተሩ፣ ኦዲት ከተደረጉት መሥሪያ ቤቶች 77 በሚሆኑት ላይ 877.1 ሚሊዮን ብር በደንቡ መሠረት ሳይወራረድ መገኘቱን አስረድተዋል፡፡ከላይ ከተጠቀሰው ያልተወራረደ ውዝፍ ተሰብሳቢ ሒሳብ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ ከያዙት መካከል በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ቴክኒክ ሙያና ትምህርት ሥልጠና ማስተባበሪያ 173.6 ሚሊዮን ብር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር 149.5 ሚሊዮን ብር፣ የትምህርት ሚኒስቴር 100 ሚሊዮን ብር ይገኙበታል፡፡ዋና ኦዲተር የመንግሥት ገቢ በአግባቡ መሰብሰቡን ለማጣራት ባካሄደው ኦዲት 32.2 ሚሊዮን ብር ከገቢ ግብር፣ ከቀረጥና ታክስ እንዲሁም ከሌሎች ገቢ መሰብሰብ በሚፈቅዱ ደንቦች መሠረት አለመሰብሰቡን አረጋግጧል፡፡ገቢ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶችና ድርጀቶች አግባብ ባለው ሕግና ደንብ መሠረት የመንግሥት ገቢ በአግባቡ መሰብሰባቸውን ለማረጋገጥ በተደረገ ኦዲት 326.7 ሚሊዮን ብር ያልተሰበሰበ ውዝፍ ገቢ መኖሩ ተረጋግጧል፡፡ አብዛኛው ይህ ውዝፍ ያልተሰበሰበ ገቢ የሚመለከተው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንን እንደሆነ ከኦዲት ሪፖርቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንን በጊዜያዊነት ወደ አገር የሚገቡ ዕቃዎች የጊዜ ገደባቸውን ካጠናቀቁ በኋላ፣ የጊዜ ገደቡ በሕግ አግባብ እንዲራዘም ካልተደረገ በስተቀር በዋስትና የተያዘውን ገንዘብ የመውረስ መብት በሕግ ተሰጥቶታል፡፡ ነገር ግን በጊዜያዊነት ገብተው የመቆያ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ በድምሩ 222.5 ሚሊዮን ብር የዋስትና ገንዘብ አለመሰብሰቡን የኦዲት ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡‹‹የሚሰበሰብ ገቢ መንግሥት ለሚያከናውናቸው የልማትና ማኅበራዊ አገልግሎቶች መስፋፋትና ለአገሪቱ የዕድገትና ትራንስፎሜሽን ዕቅድ መሳካት ወሳኝ ሚና የሚኖረው በመሆኑ፣ የመንግሥት ሕግና ደንብ ተከብሮ መሠራት አለበት፤›› ሲሉ ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ አሳስበዋል፡፡ሕጋዊነት የጎደላቸው ወጪዎችን በተመለከተ ባቀረቡት ሪፖርት 785 ሚሊዮን ብር አግባብነት የጎደላቸው ወጪዎች መኖራቸውንም አስረድተዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ በዋነኝነት የሚጠቀሰው በ25 መሥሪያ ቤቶች በወጪ ተመዝግቦ ነገር ግን የወጪውን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ማስረጃ ሊቀርብበት ያልቻለ 202.6 ሚሊዮን ብር በወጪ ተመዝግቦ ተገኝቷል፡፡የግዥ አዋጁን እንዲሁም ደንብና መመርያን ያልተከተሉ ግዥዎችን በተመለከተ ደግሞ፣ 43 መሥሪያ ቤቶች 165.9 ሚሊዮን ብር ደንብና መመርያን በመጣስ ወጪ አድርገዋል ብለዋል፡፡ ሌሎች 41 መሥሪያ ቤቶች ደግሞ 76 ሚሊዮን ብር ደንብና መመርያን በመጣስ ክፍያ መፈጸማቸውን በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡ሒሳቦች በወጪነት የሚመዘገቡት የሚፈለገው አገልግሎት መገኘቱን ወይም የሚፈለገው ንብረት በአግባቡ በእጅመግባቱ ሲረጋገጥ ቢሆንም፣ 13 መሥሪያ ቤቶች አገልግሎቱን ወይም ንብረቱን ሙሉ በሙሉ ሳያገኙ የከፈሉትንየ234.8 ሚሊዮን ብር ቅድመ ክፍያ በወጪ መዝገብ ይዘው ተገኝተዋል፡፡ በመሆኑም የተፈለገው አገልግሎት ወይምንብረት ሙሉ በሙሉ እስኪፈጸም ድረስ በተሰብሳቢ መያዝ ይኖርበታል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡በ104 መሥሪያ ቤቶች ደግሞ ለተለያዩ ግዥዎች አራት ሚሊዮን 471 ሺሕ ብር ያላግባብ በብልጫ መከፈሉን የኦዲት ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡በተጨማሪም በአሥር መሥሪያ ቤቶች የንብረት ገቢ ደረሰኝ ያልቀረበለት 22.6 ሚሊዮን ብር ወጪ መኖሩን፣ በሌሎች ሰባት መሥሪያ ቤቶች ደግሞ 1.6 ቢሊዮን ብር ቀረጥ የተከፈለባቸው ንብረቶች ገቢ መሆናቸውን ለማረጋገጥ አልተቻለም፡፡ቀረጥ ተከፍሎባቸው ንብረቶቹ ገቢ ለመሆናቸው ለማረጋገጥ ካልተቻለባቸው መሥሪያ ቤቶች ትልቁን ድርሻ የያዘው፣ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክቶሬት ሲሆን፣ በቀጣይነት ደግሞ ጤና ጥበቃና ትምህርት ሚኒስቴር ተጠቅሰዋል፡፡በ23 መሥሪያ ቤቶች የወጪውን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ያልተቻለ 90.9 ሚሊዮን ብር መኖሩን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡የፌደራል መንግሥት ግዥ አፈጻጸም መመርያ በግንባታ ቦታ ላይ ላሉ ዕቃዎች፣ ወይም ግንባታ ላይ ላልዋሉ ክፍያ መፈጸምን የሚከለክል ቢሆንም፣ 11 መሥሪያ ቤቶች ይህንን በመጣስ 168.6 ሚሊዮን ብር መክፍላቸውን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡ መንግሥት የግንባታ ዕቃዎችን በብድር ሲያገኝ የተገኘው ቁስ መጠን ተሰልቶ ከግንባታ ወጪ ላይ መቀነስ የሚገባው ቢሆንም፣ አራት መሥሪያ ቤቶች ግን 18.3 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ በብድር የተገኙ የግንባታ ዕቃዎች ወጪን ሳይቀንሱና ለመንግሥት ካዝና ሳያስገቡ በኦዲቱ ተገኝተዋል፡፡የተፈቀደላቸውን በጀት በትክክል ለሥራ አውለዋል ወይ የሚለውን ለማጣራት በተደረገ ኦዲት ደግሞ፣ በ96 መሥሪያ ቤቶች 2.3 ቢሊዮን ብር ያልተሠራበት በጀት ተገኝቷል፡፡ ይህ ሪፖርት ከቀረበ በኋላ መድረኩ ለውይይት ክፍት የነበረ ቢሆንም፣ የፓርላማው አባላት በቁጭትና በእልህ እንዳለፈው ዓመት ሲናገሩ አልተስተዋሉም፡፡ብቸኛው የፓርላማ የግል ተወካይ የሆኑት ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ የኦዲት ሪፖርቱን አስመልክተው፣ ‹‹በዚህ አገር ማንም ምንም ሊያደርግ አይችልም የሚሉ ባለሥልጣናት ያሉ ይመስለኛል፡፡ እርስዎ እንደዚያ ያስባሉ ወይ?›› የሚል ጥያቄ ዋና ኦዲተሩን አቶ ገመቹ ዱቢሶን ጠይቀዋል፡፡አቶ ገመቹ ዱቢሶ በሰጡት ምላሽ፣ እንዲዚህ ዓይነት አስተሳሰብ ይኖራል ብለው እንደማይገምቱ፣ ነገር ግን ችግር መኖሩን እያወቁ የማያስተካክሉ ኃላፊዎች መኖራቸውን፣ አንዳንድ ጊዜ በሒሳብ ባሙያዎች የሚታለሉ ኃላፊዎች እንዳሉ መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡መደረግ የሚገባውን በተመለከተ በዶ/ር አሸብር ለተነሳው ጥያቄ ዋና ኦዲተሩ የሰጡት ምላሽ በዋና ኦዲተርና በአፈ ጉባዔው መካከል በተደረገ ስምምነት በ2006 ዓ.ም. የኦዲት ሪፖርት ላይ የሚገኙ የኦዲት ግኝቶች እስካሁን በነበረው ግዝፈት የሚቀጥሉ ወይም የማይሻሻሉ ከሆነ፣ ሕጋዊ ቅጣት በመሥሪያ ቤቶቹ ኃላፊዎች ላይ ለመውሰድ ስምምነት መኖሩን አስረድተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የፓርላማው ቋሚ ከኮሚቴዎች የሚከታተሏቸውን አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች በይበልጥ መጠየቅ እንደሚገባቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ሚያዝያ 16 ቀን 2006 ዓ.ም. የ2006 ዓ.ም. የዘጠኝ ወራት ሪፖርት ለማቅረብ በፓርላማው የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በዚህ ጉዳይ ላይ በስፋት ጥያቄ ይቀርብላቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Thursday, April 24, 2014

ሰበር ዜና- ፖሊስ ቀስቃሾቹን እያሰረ ነው ፖሊስ የእውቅናው ደብዳቤ አልደረሰኝም በሚል በተለያዩ የአዲስ አበባ ክፍሎች ቅስቀሳ ላይ የተሰማሩትን የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች እያሰረ ነው፡፡



ፖሊስ ቀስቃሾቹን እያሰረ ነው ፖሊስ የእውቅናው ደብዳቤ አልደረሰኝም በሚል በተለያዩ የአዲስ አበባ ክፍሎች ቅስቀሳ ላይ የተሰማሩትን የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች እያሰረ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በየካ፣ ካሳንቺስና አቧሬ ሲቀሰቅሱ የነበሩ ወጣቶች በፖሊስ ተይዘው ታስረዋል፡፡ ቀስቃሾቹ ሰልፉ እውቅና እንደተሰጠው የሚያመለክተውን ወረቀት ለፖሊስ ቢያሳዩም ፖሊሶች የእውቅናው ደብዳቡ አልደረሰንም በሚል አስረዋቸዋል፡፡ ቀስቃሾቹ የያዙት የእውቅና ደብዳቤ ግልባጭ ለፖሊስ የተጻፈበት በመሆኑ ሰልፉ እውቅና አግኝቶ እያለ ሆን ተብሎ ለማደናቀፍ እንደሆነ ምክትር ሊቀመንበሩ አቶ ስለሽ ፈይሳ ገልፀዋል፡፡
በላም በረት፣ ቦሌ ድልድይ፣ ኮተቤ፣ መገናኛ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የነበሩ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ቅስቀሳቸውን በተሳካ መልኩ አጠናቀዋል፡፡ በሌሎች አካባቢዎች የተሰማሩት አባላት ቅስቀሳውን አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ በሌላ በኩል በየካ፣ ካሳንቺስና አቧሬን ጨምሮ በሌሎች የከተማይቱ ክፍሎች ፖሊስ ከ20 በላይ አባላትን ማሰሩ ታውቋል፡፡
ሰበር ዜና ፖሊስ ቅስቀሳው ላይ ያልነበሩ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችንም እያሰረ ነው፡፡ የታሰሩትን አባላትና ደጋፊዎች ሁኔታ ለማጣራት ወደ የካ ፖሊስ ጣቢያ ያቀኑ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላትን ፖሊስ አስሯቸዋል፡፡
በዛሬው ቀን ካሳንቺስ ስድስተኛ ፖሊስ ጣቢያ የታሰሩት 
1. ብሌን መስፍን
2. አስናቀ በቀለ
3. መስፍን
4. ተስፋዬ አሻግሬ
5. እዮብ ማሞ
6. ኩራባቸው
7. ተዋቸው ዳምጤ
የካ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው የሚገኙት የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች
1. ፍቅረ ማሪያም አስማማው
2. እያስፔድ ተስፋዬ
3. ጋሻው መርሻ
4. ተስፋዬ መርኔ
5. ሀብታሜ ደመቀ
6. ዘሪሁን ተስፋዬ
7. ጌታነህ ባልቻ
8. ንግስት ወንዲፍራው
9. ሜሪን አለማየሁ ናቸው
የካ አካባቢ ታስረው የሚገኙ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ምግብ እንዳይገባላቸው ተከልክለዋል፡፡ በሌላ በኩል አህመድ መሃመድ፣ሀይለማሪያም፣ ሱራፌልና አምሃ የተባሉ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት መገናኛ አካባቢ ተይዘው ወደ የካ ፖሊስ ጣቢያ ተዘዋውረዋል፡፡ በአጠቃላይ የካ ፖሊስ ጣቢያ የሚገኙት 14 መሆናቸው ታውቋል፡፡ በሁሉም ፖሊስ ጣቢያዎች የሚገኙት አመራሮችና አባላት በአሁኑ ወቅት ቃል እየሰጡ ሲሆን ሊያድሩ እንደሚችሉም ተነግሯቸዋል፡፡
በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ቢሮ ተደውሎ የሰላማዊ ሰልፉን አስተባባሪዎች ጧት ሁለት ሰዓት ላይ ‹‹ኑ እና እንነጋገር!›› የሚል ጥሪ አድርጓል፡፡ ከሰልፉ አስተባባሪዎች መካከል አቶ ጌታነህ ባልቻ ታስሮ ይገኛል፡፡

ከሰማያዊ ፓርቲ የሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ለንግዱ ማህበረሰብ የተላለፈ ጥሪ!

በንግዱ ዓለም ለተሰማራችሁት ኢትዮጵያውያን በሙሉ፤

በአሁኑ ወቅት ስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ሁሉንም የኢኮኖሚ መስክ ጠቅልሎ በመያዙ በአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚገባችሁን አስተዋጽኦ እያደረጋችሁ እንዳልሆነ እንረዳለን፡፡ ለይስሙላ ብቻ ነጻ ገበያን ‹‹ፈቅጃለሁ!›› የሚለው ገዥው ፓርቲ ኢኮኖሚውን በራሱ ድርጅቶች ተቆጣጥሮ ለስልጣን መቆያ መሳሪያ አድርጎታል፡፡ የመንግስት ድርጅት የሚባሉትም ቢሆኑ ኢኮኖሚው ጠቅልለው ለተመሳሳይ አላማ መሳሪያ በመሆን ላይ ናቸው፡፡ ይህን ተከትሎም አገራችን ነጻ ገበያና የግል ባለሃብቶች የተዳከሙባት ግንባር ቀደም አገር ሆናለች፡፡A call from Semayawi party April 2014
ይህ በአንድ ኃይል የተጠቀለለ የኢኮኖሚ ስርዓት እናንተ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት በነጻነት እንዳትሰሩ ከማድረጉም ባሻገር ህዝባችን በኑሮ ውድነት እንዲታመስ አንድ ምክንያት ሆኗል፡፡ በተለይ በቅርብ አመታት ከስርዓቱ ጋር አብሮ መሄድ ያልቻለውን የንግዱን ማህበረሰብ ለስርዓቱ እጁን እንዲሰጥ ለማድረግ እንዲመች ከሚሰራው ስራ ጋር የማይመጣጠን ግብር በመጫን ላይ መሆኑን ለመረዳት ችለናል፡፡ ሱቅ በደረቴ የሚሰሩ፤ እንጀራ ጋግረው የሚሸጡ እናቶች፤ የጀበና ቡናና ሌሎቹንም አነስተኛ ስራዎች የሚሰሩ ወጣት ኢትዮጵያውያን ሳይቀሩ የማይችሉት ግብር ተጭኖባቸዋል፡፡ የንግድ ፈቃድ እድሳት፤ የመስሪያ ቦታና ሌሎችም ነጋዴው በኢትዮጵያዊነቱና ለህዝብ በሚሰጠው ጥቅም ሊያገኛቸው የሚገባቸው መብቶች በሙስና ለፓርቲ ባለው ቅርበትና በሌሎች በዚህ ስርዓት በተሳሳቱ አሰራሮች የንግዱን ማህበረሰብ አስረው ይዘውታል፡፡
ነጋዴውን የሚፈራው ህወሓት/ኢህአዴግ የራሱን ነጋዴዎች ደጋፊ ማህበር አቋቁሟል፡፡ ይህም ነጋዴውን በነጻነት ከመስራት ይልቅ የኢሕአዲግ ተለጣፊ እንዲሆን ካለው ፍላጎት መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ በአንጻሩ ሌሎች የንግዱ ማህበረሰብ አካላት የራሳቸውን ነጻ የነጋዴ ማህበር ሲያቋቁሙ አይታዩም፡፡ የመስሪያ ቦታ፤ ግብር እና ሌሎችም ነጋዴው የሚጣልበት ግዴታና የሚገባው መብት ላይ ያለውን ኢፍትሃዊነት ለማስተካከል ጥረት የሚያደርግ የንግዱ ማህበረሰብ አካል አይታይም፡፡
ህወሓት/ኢህአዴግ በሁሉም የኢኮኖሚ መስኮች ሊሳካለት ባለመቻሉ እንዲሁም ነጻ ገበያ ተግባራዊ እንዲሆን አለመፍቀዱ የአገራችን ኢኮኖሚ ከመቸውም ጊዜ በተለየ ሁኔታ ተባብሷል፡፡ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያውያን በሰፊው የሚያመርቷቸው ምርቶችም ጭምር ለህዝብ የሚደፈሩ አልሆኑም፡፡ የእነዚህ ምርቶች እጥረት ሲከሰት ጥያቄውን ከእሱ ትከሻ ለማውረድ የሚከሰው የንግዱን ማህበረሰብ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ‹‹ዘይት የደበቀ፣ ስኳር ያልሸጠ፣…›› እየተባለ በሰበብ አስባቡ የስርዓቱ ግፍ ገፈት ቀማሾች ሆናችኋል፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ ድሃ ከሚባሉት አገራት ቀዳሚውን ተርታ መያዟን ለንግዱ ማህበረሰብ ማስረዳት ለቀባሪው አረዱት ይሆናል፡፡ የንግዱ ማህበረሰብ ይህን መሰረታዊ ችግር ከስር ከመሰረቱ ለመፍታት በሚደረገው ትግል የራሱን አስተዋጽኦ እያደረገ ባለመሆኑ አገሪቱን ከገባችበት አረንቋ ለማውጣት የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት መጠቆም ተገቢ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ይህን ለማድረግም መጀመሪያ የራሱን ነጻነት በማስከበር፣ በመደራጀት የንግዱን ማህበረሰብና ኢትዮጵያውያን አቅርቦቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያገኙበትን አጋጣሚ መፍጠር አስፈላጊ ነው፡፡ በተለይ በተለይ የራሱን የፖሊሲ ችግር ተለጣፊ ባልሆኑት የንግዱ ማህበረሰብ አካላት ላይ ለማላከክ የማይታክተውን የገዥውን ፓርቲ ተግባር በማጋለጥ እና ከህዝብ ጎን በመቆም ግዴታችሁን መወጣት ይገባችኋል እንላለን፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ ሚያዚያ 19/2006 ዓ.ም ጃን ሜዳ ‹‹የተነጠቁ መብቶቻችንን እናስመልሳለን!›› በሚል ሰላማዊ ሰልፍ ጠርቷል፡፡ መብታችሁን የተነጠቃችሁት የንግዱ ማህበረሰብ አካላትም የራሳችሁንና የቀሪ ኢትዮጵያውያንን መብት ለማስመለስ በሰልፉ ቀዳሚ ተሳታፊ እንድትሆኑ ፓርቲያችን ጥሪውን አቅርቦላችኋል፡፡
ኑ ራሳችንን ነጻ በማውጣት የአገራችንን እጣ ፈንታ እንወስን!
http://ecadforum.com/Amharic/archives/11933/

Monday, April 14, 2014

ስለፍትህ ሲባል ስርዓቱ ይፍረስ! ክፍል 2 (ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ)

በዚህ ርዕስ ሥር ባለፈው ሳምንት በይደር ካቆየሁት ተከታይ ጽሑፍ በፊት አንድ እርምት የሚያሻው ጉዳይን በአዲስ መስመር ላስቀድም፡፡
ሬዲዮ ፋና እና “አምደኞቹ”
በ1988 ዓ.ም በኤፈርት ባለቤትነት ስርጭቱን አሀዱ ያለው “ሬዲዮ ፋና”፣ ከምስረታው አንስቶ ዛሬም ድረስ ልክ እንደ በረሃው ዘመን ሁሉ የሥርዓቱ ቀኝ እጅና የርካሽ ፕሮፓጋንዳው ማስተላለፊያ ቱቦ ሆኖ መዝለቁ ለወዳጅም ለጠላትም የማያከራክር ገሀድ የወጣ ሐቅ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተወሰኑ የግል ሚዲያዎች ላይ የርግማን ዘመቻ የታወጀ ይመስል ለተከታታይ ሳምንታት “ስመ-ጥር” ረጋሚዎችን ጣቢያው ድረስ ጋብዞ ማብጠልጠልና ማውገዙን ቀንደኛ ሥራው አድርጎ ይዞታል፡፡ በርግጥ ይህ ዘመቻ ከወራት በፊት በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የፕሬስ ድርጅት በኩል በ“ጥናት” ስም የወጣው ውንጀላ ቅጥያ ሲሆን፣ በቅርቡ ኢቲቪ ሰርቶ እንዳጠናቀቀው የሚነገርለት ዶክመንተሪ ፊልም ደግሞ “ሳልሳዊ” ዘመቻ ሆኖ ለጥቆ የሚቀርብ መሆኑን የመረጃ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡Journalist Temasegan Dasaleg
ሰሞነኛውን የፋና ዘመቻ ከተለመደው አቀራረብ የተለየ የሚያደርገው ከህወሓት ከበሮ መቺነት መሻገር የተሳነው ዛሚ ሬዲዮ ጣቢያን ከወከለው አቶ ዘሪሁን ተሾመ በተጨማሪ፣ የኢዴፓው አቶ ሞሼ ሰሙ እና የ‹‹ፎርቹ››ኑ ጋዜጠኛ ታምራት ወልደጊዮርጊስ በውጋ-ንቀል ስልት የርግማኑ ቡራኬ ሰጪ ሆነው መቅረባቸው ነው፡፡ ‹‹አዲስ አማኝ ከጳጳስ በላይ ልሁን ይላል›› እንዲሉ ሩቅ አላሚው የሕዳሴው ግድብ የሕዝብ ተሳትፎ አስተባባሪ ም/ቤት ምክትል ዳይሬክተር የሆነው ዛዲግ አብረሃም ሆነ ሚኒስትር ዴኤታው ሽመልስ ከማል የረከሰውን የአፈና መንፈስ ‹‹ለማቀደስ›› በቁርጠኝነት መሰለፋቸውን ሳንዘነጋ ማለት ነው፡፡ በርግጥ እነዚህ ሰዎች በቀጥታ ከስርዓቱ ህብስት ተቋዳሽ በመሆናቸው በዚህ ደረጃ ‹‹ማሸብሸባቸው›› ብዙም አያስገርምም፤ አስገራሚው ነገር ታምራት ወልደጊዮርጊስ ‹‹እንቁ›› እና ‹‹ፋክት›› መጽሔቶችን በአንድ ሰው የሚዘጋጁ አስመስሎ ከማቅረብም አልፎ፣ ማሕበረ ቅዱሳን የገጠመውን የመበተን አደጋን በተመለከተ የወጣውን ዘገባ እስከማውገዝ የደረሰበት ጽንፍ ነው፡፡
በወቅቱ ዛዲግ አብረሃ ሚዲያዎቹ እንዲደመሰሱ ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ፣ ታምራትም የማሕበረ ቅዱሳን አባላት ተቋማቸውን ከመንግስታዊ አፈና መከላከል እንዳለባቸው የምትመክረውን የ‹‹ፋክት›› ዘገባ ቃል በቃል ጠቅሶ ሲያበቃ ‹‹ቋቅ እያለኝም ቢሆን ከዛዲግ አብረሃ ጋር የምስማማበት ጉዳይ ይህ ነው›› በማለት ከፕሬስ አፈናው ጎን መቆሙን አስረግጦ ተናግሯል፡፡ በአናቱም መጽሔቶቹ ‹‹አብዛኛው ህዝብ የሚፈልገውን መርጠው የሚዘግቡ ናቸው›› ያለበት አውድ ነቀፋ ይሁን ምስጋና ግልፅ ባይሆንም፣ ቢያንስ አምባገነኑን በረከት ስምኦን እና ጋሻ-ጃግሬዎቹን ከማስደሰት፤ ብዙሃኑን ግፉአን ማገልገል የተሻለ ብቻ ሳይሆን የተቀደሰ ተግባር ስለመሆኑ በረከትም በልበ-ሙሉነት እሰጥ-እገባ ሙግት የማይሞክርበት ነጭ እውነት እንደሆነ ታምራት ቢያስተውለው የተሻለ ይመስለኛል፡፡ ግና፣ ሐቁ ይህ ቢሆንም ወንድም ታምራት ራሱ ብቻ ሙያውን አክብሮ የሚሰራ ጋዜጠኛ፤ ሌላውን ደግሞ ኃላፊነት የማይሰማው ከማድረጉም በዘለለ፣ እነዚህን ሚዲያዎች ከአርበኝነት ጋር አዳብሎ ለማውገዝ መሞከሩ የተኮረኮርኩ ያህል ሳልወድ በግድ ያሳቀኝ ጉዳይ ሆኖብኛል፡፡ ምክንያቱም በእኔ እምነት በኢትዮጵያችን ላለፉት ሁለት ዓስርታት ሥልጣኑን የተቆጣጠረው ለሕግ የማይገዛ እና በሙስና የተጨማለቀ ሥርዓት ከመሆኑ አኳያ በጋዜጠኝነትም ሆነ በየትኛውም ሙያ ለሚንፀባረቅ አርበኝነት የተሻለው ብያኔ፣ ሀገርን ከፍርሰት መታደግ ማለት ነውና፡፡
ደግሞም በዚህች ሀገር ዝግመታዊ-ሞት ፊት ላይ ቆሞ የኮሪደር ሐሜቶችን ከመዘገብ በእጅጉ ለቆና ረቆ በመሻገር የውደቀታችን ምክንያት የሆነውን አገዛዝ በሕዝባዊ እምቢተኝነት ማስወገድ ቅድሚያ የሚሰጠው ነው፡፡ የሆነው ሆኖ ብዙ ጊዜ በእንዲህ አይነት ውይይቶች ላይ ሚዛናዊ ለመሆን ይሞክር የነበረው ታምራት (ለዚያኛውም አቋሙ በግሌ አመስግኘው አውቃለሁ)፣ ማሕበረ ቅዱሳንን በተመለከተ የወጡ ዘገባዎችን ባወገዘበት አዛው ሬዲዮ ጣቢያ ስቱዲዮ ውስጥ ተቀምጦ፣ ሽመልስ ከማል አንድ እንኳ የታሰረም የተሰደደም ጋዜጠኛ እንደሌለ ጠቅሶ አይኑን በጨው አጥቦ ሲከራከር ትንፍሽ አለማለቱ የቀራኒዮ መንገድ እና የንግድ ስራ ፍፁም የማይተዋወቁ ሆድና ጀርባ መሆናቸውን የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡
በነገራችን ላይ በዚህ ውይይት የአደባባይ ምሁሩ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ እና የኢትዮ-ምህዳሩ ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ መሳተፋቸው ከሞላ ጎደል ከዘመቻው ጀርባ ያለውን ኢህአዴጋዊ ሴራ አጋልጦታል ብዬ አስባለሁና ባርኔጣዬን ከፍ አድርጌ አክብሮቴን ልገልፅላቸው እወዳለሁ፡፡ በተለይ ጉምቱ የፍልስፍና መምህር ዶ/ር ዳኛቸው፣ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብቶችን ብቻ ሳይሆን የሥርዓቱን ሃሳብ አልባነት ለመሞገት ለሚያደርገው አበርክቶ በድጋሚ አመሰግነዋለሁ፡፡…ከዚህ ሁሉ ሰበር ሐተታ በኋላ ወደ ክፍል ሁለቱ ዋናው አጀንዳችን ዘልቀን፣ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ለፍትሕ መበላሸት የዳኝነት ሥርዓቱ ብቻ ሳይሆን ፖሊስ እና ዐቃቤ ሕግም የአንበሳውን ድርሻ ስለመውሰዳቸው ለማመልከት እሞክራለሁ፡፡
ፖሊስ ሲባል…
…የተወሰኑ የፌደራል ፖሊስ አባላት ዝሆን አድነው እንዲያመጡ በአለቃቸው ይታዘዛሉ፡፡ ከሰዓታት በኋላም ፖሊሶቹ ግዳያቸውን አምጥተው ለአለቃቸው ያስረክባሉ፡፡ ይሁንና አለቅየው ግዳያቸውን ባየ ጊዜ ባለማመን ዓይኖቹ ፈጥጠው ሊወድቁ ደረሱ፤ ለምን ቢሉ፣እሱ ያዘዛቸው ዝሆን፣ እነርሱ ያመጡት ግን ሁለት ጥርሱ የወለቀ፣ አንድ ቀንዱ የተሰበረ፣ አንድ አይኑ የጠፋ፣ ምላሱ የተቆረጠ… ብቻ ምን አለፋችሁ በድብደባ ብዛት ሊሞት የተቃረበ ፍየል ነበርና፡፡ እናም በቁጣ፡-
‹‹ዝሆን አይደል ወይ አምጡ ያልኳችሁ?›› ሲል ያፈጥባቸዋል፤
‹‹ጌታዬ፣ ዝሆን ነኝ ብሎ እኮ አምኗል!›› በማለት ቆፍጣና ፖሊሶቹም በሕብረት መለሱለት፡፡
…ይህችን ቀልድ ለዚህ ንዑስ-ርዕስ መግቢያ ያደረኩት፣ በነባሩ ባሕል እንዲህ ያሉ ጉዳዮች በቀልድ፣ በግጥም፣ በምሳሌዊ አባባል… መገለፃቸው የተለመደ ከመሆኑ አኳያ ስለሀገራችን የፖሊስ አባላት ስንነጋገር ከቀልዷ ጀርባ መራራ እውነት ማድፈጡን አምነን እንድንቀበል ገፊ-ምክንያቶች በመኖራቸው ነው፡፡
እንደሚታወሰው በየትም ሀገር የተፈፀመ ወንጀል ከዐቃቤ ሕግም ሆነ ከፍርድ ቤት በፊት በፖሊስ የምርመራ ሂደት ውስጥ ማለፉ የግድ ነው፡፡ የዘርፉ ምሁራን ‹‹የፖሊስ ምርመራ ሳይንስ ነው›› እንዲሉ ሙያው ክህሎት የሚጠይቅ መሆኑ አይካድም፡፡ ይሁንና ተጨባጩ እውነታ የሚነግረን የ83ቱን የመንግስት ለውጥ ተከትሎ በዘርፉ እንዲሰማሩ የተደረጉት አብዛኞቹ መርማሪዎች ድርጅቱን ለቡሕተ-ሥልጣን ያበቁ ታጋዮች መሆናቸውን ነው፡፡ በርግጥም በረባውም ባልረባውም ወንጀል ተጠርጥሮ እጃቸው የገባውን ሁሉ አፈር-ድሜ በማስጋጥ የ‹‹ሚመረምሩበት›› መንገድ ኩነቱን ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ ይህ ሁናቴም ይመስለኛል የፖሊስን ሙያ ከሳይንሳዊ ጥበብ ወደ አሳረ-ፍዳ ማሳያ አውርዶ የተጠላ ያደረገው፡፡ ለዚህም ኩነና በርካታ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ የሩቁን ትተን የቅርቡን እንኳ ብንመለከት የህዝበ-ሙስሊሙ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ችሎት ላይ ቀርበው በማዕከላዊ ምርመራ እስር ቤት መርማሪ ፖሊሶቹ ሰብዓዊ መብቶቻቸው ተገርስሶ ሲያበቃ ምን ያህል አካላዊና መንፈሳዊ ስቅየት እንደደረሰባቸው ከተናገሩት መሀል የሚከተሉትን በዋናነት እናገኛለን፡-
‹መርማሪ ፖሊሶቹ እንቅልፍ ከልክለው የተዳከመ አካልን ልብስ አስወልቆ እርቃን በማስቀረት መግረፍ፣ የዘር ፍሬ ብልት ላይ በውሃ የተሞላ ጠርሙስ ማንጠልጠል፣ በኤሌክትሪክ ገመድ የውስጥ እግርን መግረፍ፣ ጢምን በአሰቃቂ ሁኔታ መንጨት፣ እጅና እግርን ሰብዓዊነት በጎደለው መልኩ ለረጅም ሰዓታት ማሰር፣ ጭንቅላትን በቆሸሸ ውሃ ውስጥ መንከር፣ ከ24 ሰዓታት በላይ ቀጥ ብሎ እንዲቆሙ ማስገደድ፣ በኤሌክትሪክ ኃይል ሾክ ማደረግ እና የመሳሰሉት፡፡› በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማትም በተደጋጋሚ ጊዜ በተለይም ከደርግ ስርዓት ጀምሮ ዋነኛ ማሰቃያ በሆነው ማዕከላዊ የምርመራ ጣቢያ የሚፈፀመውን ተግባር በሪፖርት መልክ ማውጣታቸው ይታወሳል፡፡ ከወራት በፊት ሂዩማን ራይትስ ዎች ይህንን የስቃይ ጣቢያ አስመልክቶ ‹‹They want a confession: Torture and Ill-treatment in Ethiopia’s Makelawi Police Station›› በሚል ርዕስ ባሰራጨው ሪፖርት በጣቢያው የሚፈፀመውን ግፍ ከመግለፁም በተጨማሪ፣ ታሳሪዎች እንዴት ባለ ሁኔታ ‹‹የእምነት ቃል››እንደሚሰጡ አመላክቷል፡፡ ለማሳሌም አንድ ስሙ ያልተጠቀሰ፤ ነገር ግን በጣቢያው ታስሮ የነበረ ሰው ገጠመኝን ከሪፖርቱ እንደሚከተለው ልጥቀሰው፡-

‹‹ወደ ጣቢያው የገባሁ ቀን ኢ-ሜይል አድራሻዬን ከነምስጢር ቁልፉ እንድሰጣቸው ጠየቁኝ፤ ሰጠኋቸው፡፡ በውስጡም ምንም አይነት የፖለቲካ አንድምታ ያለው መልዕክት አልነበረም፡፡ ይሁንና ከሶስት ቀን በኋላ በዛው አድራሻዬ ‹ከኦነግ የተላከ መልዕክት ተግኝቷል› ብለው ጠየቁኝ፡፡ ሆኖም ነገሩን እንደማላውቅ እያወቁ ‹ለእኔ የተላከ መልዕክት ነው› ብለህ ፈርም ሲሉ አዘዙኝ፡፡ እኔም ከታሰርኩ በኋላ የተገኘ በመሆኑ አልፈርምም አልኩ፡፡ በዚህም የተነሳ ከፍተኛ ድብደባ ፈጽመውብኛል፡፡››
በርግጥም የሀገሪቱን የወንጀል ምርመራ ስራን ተነቃፊና ተወጋዥ ያደረገው በእውቀት ማነስ፣ በስቅየት (በቶርቸር) እና በሙስና የተተበተበ መሆኑ ብቻ አይደለም፡፡ በአደረጃጀቱም ነው፤ ለምሳሌ ከፌዴራልና ክልል ፖሊስ በተጨማሪ ግምሩክ የራሱ እስር ቤት፣ የራሱ መርማሪና ዐቃቢ-ሕግያን አሉት፡፡ ፀረ-ሙስናም እንዲሁ የጠረጠረውን ሁሉ አስሮ ይመረምራል፤ ይከስሳልም፡፡ አንዳንድ ምንጮቼ እንዳቀበሉኝ መረጃ ከሆነ ደግሞ በሽብር ጉዳይ የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን (ቡድኖችን) ራሱን ችሎ አስሮ የሚመረምር እና የሚከስ ተቋም በቅርቡ በአዋጅ ሊቋቋም ዝግጅቱ ተጠናቅቋል፡፡ እንግዲህ እነዚህ ሁሉ መዋቅራዊ ትስስር በሌለው ሁኔታ በፖሊስ ስራ የመሰማራታቸው ምስጢር፣ አንድም ሳይንስ እንጂ አሳር ዕውቀት ባለመጠየቁ፣ ሁለትም ንፁሀንን ከወንጀለኛ ጋር ደባልቆ ለመውቀጥ ስለሚመች፣ ሶስትም ስርዓቱ ተቀናቃኞቹን ለመደፍጠጥ በ‹‹ሕጋዊ አሠራር›› ሽፋን ተጨማሪ ጡንቻ እንዲኖረው ማስቻሉን በማስላት ይመስለኛል፡፡ በዚህ አይነት ምርመራ የተገኙ መረጃዎችም ፍርድ ቤት ቀርበው እንደሕጋዊ ማስረጃ እየተቆጠሩ እስከ ዕድሜ ልክ የእስር ቅጣት ሲያስበይኑ ደጋግመን ተመልክተናል፡፡
ይህም ሰፊው ሕዝብ በፍርሃት እየተርበደበደ ሰጥ-ለጥ ብሎ እንዲገዛ፤ አሊያም እንደ ጥንቸሊቷ አገር ጥሎ እንዲጠፋ ለማድረግ ያለው ጉልበት በግልፅ ተተግብሮ የታየ የሥርዓቱ የዕለት ተዕለት ምግባር ነውና ከዚህ በላይ ትንታኔ አያሻውም፡፡ ከዚህ ይልቅ የጥንቸሏ አፈ-ታሪክ ተብሎ የሚነገረው ነባራዊ እውነታውን በሚገባ ያንፀባርቃልና እንደወረደ ልጥቀሰው፡-…ከለታት አንድ ቀን አንዲት ጥንቸል ከመጣባት የመዓት ናዳ ማምለጥ የምትችለው ቀዬዋን ጥላ ስትሰደድ እንደሆነ ብቻ በማመኗ ልቧ እስኪፈነዳ ድረስ ጋራ-ሸንተረሩን እያቆራረጠች ስትሮጥ ድንገት ከሀገሪቱ ድንበር አጠገብ ከሚኖር አንድ ግድንግድ ጦጣ ጋር ፊት-ለፊት ተፋጠጠች፣ በድካም ዝላም ቁና ቁና እየተነፈሰች ‹‹ይህ ጦጣ ፖሊስ ይሆን እንዴ?›› ብላ እየተጠራጠረች ማምለጫ ዘዴ ስታውጠነጥን፣አያ ጦጣ፡- ‹‹ወይዘሪት ጥንቸል፣ ለመሆኑ ምን የከበደ ጉዳይ ቢገጥምሽ ነው እንዲህ ልብሽ እስኪፈርስ ድረስ የምትሮጪው?›› ሲል ይጠይቃታል፤‹‹የዝሆን ዘር በሙሉ ከያለበት ተለቅሞ በቁጥጥር ስር እንዲውል አስቸኳይ ትዕዛዝ መውጣቱን እስካሁን አልሰሙም እንዴ?›› ብላ በጥርጣሬ ትክ ብላ እያስተዋለችው ጥያቄውን በጥያቄ ስትመልስለት፣
አያ ጦጣ፣ እጅግ በጣም ከመደነቁም በላይ ግራ ግብት እያለው ‹‹ታዲያ አንቺ ምን አገባሽ፤ ዝሆን አይደለሽ?›› ሲል መልሶ ይጠይቃታል፤ ‹‹ወይ አያ ጦጣ! ዝሆን ባልሆንስ?! አለመሆኔ ተጣርቶ እስክለቀቅ ድረስ ለምን ብዬ ታስሬ ልገረፍ? ደግሞስ በዱላ ብዛት ዝሆን ነኝ ብዬ ያመንኩ እንደሆነ መጨረሻዬ ምን ሊሆን እንደሚችል አስበውታል? ይልቅ እርስዎም አይሞኙ! በጊዜ አብረውኝ ከመዓቱ ዘወር ብለው ቢቆዩ ይሻሎታል፤ ኑ እንሂድ›› ብላ በፍርሃት የተዋጠችው ምስኪኗ ጥንቸል ሩጫዋን ቀጠለች፡፡ …በእኛይቱ የመከራ ምድርም፣ እኛና ኢህአዴግ በዚህ ደረጃ ፍፁም የማንተማመን፣ በጎሪጥ የምንተያይ ሆነን ከቀረን እንደ ዘበት ሃያ ምናምን አመታት ተቆጥረዋል፡፡
ዐቃቢ ሕግ ሲባል….
በዚህ አውድ ሌላው ተጠቃሽ ተቋም፣ ፖሊስ በ‹‹የትም ፍጪው…›› መንገድ ያመጣለትን ‹‹መረጃ›› ሳያላምጥ በመዋጥ ለክስ የሚያበቃው ዐቃቤ ሕግ ሲሆን፣ ለአጠቃላዩ የፍትሕ መዛባትና መጨማለቅም በዕኩል ደረጃ ተጠያቂ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
ለአደባባይ ያልበቁ አያሌ የዐቃቢ-ሕግያን ሸፍጦችን ትተን በድህረ ምርጫ 97 የተከሰተውን አለመግባባት ተከትሎ ለእስር ከተዳረጉት የቅንጅት ለአንድነትና ለፍትህ ፓርቲ አመራሮች ጋር የተያያዘውን እንመልከት፡፡ እንደሚታወሰው መጀመሪያ የቀረበባቸው ክስ ‹‹የዘር ማጥፋት›› የሚል የነበረ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያን በተመለከተ ለረዥም ዓመታት ጥናት ያደረገው አሜሪካዊ ፕ/ር ዶናልድ ሌቨን፣ አቶ መለስን ‹‹ዘር ማጥፋት እኮ ቀልድ አይደለም›› በማለት አጥብቆ ከወቀሰው በኋላ ክሱ ‹‹ሕገ-መንግስቱን በኃይል የመናድ እና ዘር የማጥፋት ሙከራ›› ወደሚል መቀየሩን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ይናገራሉ፡፡
የሆነው ሆኖ ጉዳዩ ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት ዐቃቢ-ሕግያኑ በተከሳሾቹ ላይ በ‹‹ማስረጃ››ነት ካቀረቡት ሰነዶች መካከል የአባላዘር በሽታ የህክምና ምርመራ ወረቀትን ጨምሮ፣ ሀሰተኛ (ፎርጅድ) ደብዳቤዎች እና ከክሱ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌላቸው የቪዲዮ ፊልሞች እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ‹‹የቃሊቲው መንግስት›› በሚለው መጽሐፉ፣ በጥቅምት 25/1998 ከ‹‹አዲስ አበባ ፖሊ ከፍተኛ ክሊኒክ›› ቢኒያም (የአባቱም ስም ተጠቅሷል) ለተባለ ሰው የአባላዘር ምርመራ አድርጎ የተሰጠው የሕክምና ምስክር ወረቀት ‹‹ሕገ-መንግስቱን በኃይል ለመናድ ሞክረዋል›› በተባሉት የቅንጅት መሪዎች ላይ በ‹‹ማስረጃ››ነት መቅረቡን ከመጥቀሱም በላይ ሰነዱን በገጽ 444 ላይ እንዳለ በማተም ለታሪክ ምስክርነት አብቅቶታል፡፡ መቼም ይህ ሁናቴ አቶ መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያ ጦር ሶማሊያን የወረረው የአሜሪካንን ተልዕኮ ለማስፈፀም ነው? ተብሎ ለቀረበበት ወቀሳ አከል ጥያቄ፣ አሜሪካ የምትሰጠው ዕርዳታ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን መከላከል ላይ ያተኮረ እንደሆነ ከገለፀ በኋላ ‹‹ሶማሊያ ውስጥ ደግሞ በኮንዶም አንዋጋም!›› ብሎ እንደመለሰው አይነት ቧልት አቅልለን እንዳናልፈው የሚያግደን ጉዳዩ ‹‹አንድ ንፁህ በሀሰት ከሚፈረድበት፣ ሺ ወንጀለኞች በነፃ ቢለቀቁ ይመረጣል›› ከሚባልለት ፍትሕ ጋር የሚያያዝ በመሆኑ ነው፡፡
በጥቅሉ ላለፉት ሃያ ሁለት ዓመታት ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ ለእስር የተዳረጉ ንፁሀንም ሆነ በሙስና የተወነጀሉት ላይ እየቀረበ ያለው ክስና ማስረጃዎችን ሥራዬ ብሎ ለመረመረ ሰው፣ የፍትሕ መዛባቱን ደረጃ ፍንትው አድርገው ያሳዩታል ብዬ አስባለሁ፡፡ ለምሳሌም ከወራት በፊት ‹‹በገቢዎችና ግምሩክ ባለሥልጣን የአ/አ ኤርፖርት ቅ/ጽ/ቤት የመንገደኞች ጓዝ የሥራ ሂደት መሪ›› ባለሥልጣን ላይ የተመሰረተውን ክስ ብናየው እንዲህ የሚል ሆኖ እናገኘዋለን፡-
‹‹ከአሜሪካና ከአውሮፓ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ መንገደኞች ዕቃዎቻቸውን አስፈትሸው ቀረጥና ታክስ ሊከፈልባቸው የሚገቡት ላይ መክፈል እንዳለባቸው ኮንትሮባንድም ከሆነ እንደሚወረሱ እያወቀ ማንነታቸውና ብዛታቸው ያልተለዩ መንገደኞች ዕቃቸው እንዳይፈተሽ ማድረግ፡፡››
መቼም ይህ አይነቱ ክስ በምድራችን የመጀመሪያው ሳይሆን አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ማንነታቸውና ብዛታቸው፣ ቀኑና ወሩ ተለይቶ ባልታወቀበት ጊዜ ከመንገደኞች ጋር በመመሳጠር የተሰራ ወንጀል አለ ብሎ ክስ መመስረት ከጥንቆላ በምንም ሊለይ አይችልምና ነው፡፡ ኧረ ለመሆኑስ! የሰዎቹ ቁጥርና ያስገቡት የዕቃ ዓይነት ካልታወቀ ባለሥልጣኑ ‹‹ፈፀመ›› በተባለው ሙስና ሀገሪቱ ከቀረጥ ማግኘት የነበረባትና ያሳጣት ገቢ ምን ያህል ነው? አንድ ብር? አንድ ሺህ? አንድ ሚሊዮን ወይስ አንድ ቢሊዮን? ይሁንና የተከሳሽ ጠበቆች ክሱ በዚህ መልኩ መቅረቡን በፍርድ ቤት በመቃወማቸው ዐቃቢ ህግ አሻሽሎ እንዲያቀርብ ይታዘዛል፡፡ ተሻሽሎ የቀረበው ደግሞ ባጭሩ እንዲህ ይጠቀሳል፡-
‹‹ቀኑና ወሩ ተለይቶ ባልታወቀበት በ2002 ዓ.ም ዜግነታቸው አሜሪካዊ የሆነ ሁለት ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ሁለት ሻንጣ የመኪና መለዋወጫ ከተያዘባቸው በኋላ አስለቅቋል፡፡ ግንቦት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የሰንሻይን ኮንስትራክሽን ባለቤት አቶ ሳሙኤል ታፈሰ ከዱባይ ሀገር ያስገቡት የመኪና መለዋወጫ ዕቃ እንዲያልፍ ሲያስደርግ በሌላ ባልደረባው ተይዟል፤ ከሐምሌ ወር 2002 ዓ.ም እስከ ነሐሴ ወር 2003 ዓ.ም ከጠዋቱ አንድ ሰዓት እስከ አራት ሰዓት ባለው ጊዜ ከተለያዩ ሀገራት ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ መንገደኞች ሠልፍ ይዘው እያለ ከዚህ መለስ ያሉት መንገደኞች ሻንጣቸውን ሳያስፈትሹ፣ ቀረጥና ታክስ ሳይከፍሉ እንዲያልፉ ማድረግ፡፡››
እነሆም እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ሀገሪቱ እንዲህ ባሉ የሕግ ባለሙያዎች ስር ወድቃለችና ‹እግዚኦ በሉ›፡፡ እግዚኦታው ግን የሁለቱ እንስቶች ስም እና ያሳለፉት ዕቃ ተመን ባለመታወቁ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም በጽሁፍ በቀረበ ክስ ላይ ከሠልፈኞቹ መካከል ‹‹ከዚህ መለስ ያሉት መንገደኞች…›› ተብሎ ድፍን ያለ ነገር ‹‹መረጃ›› ሆኖ መቅረቡ ነው፡፡ ግና፣ ይህ ምን የሚሉት መረጃ ነው? ያውም ለፍርድ ቤት! እናም ጥያቄያችን እንዲህ እያለ ይቀጥላል፡- የትኛው ሠልፍ ጋ ያሉ መንገደኞች ናቸው በሕገ-ወጥ መንገድ ያለፉት? የቀኙ? የመሀለኛው? የግራው? የሠልፉስ ርዝመት ምን ያህል ነው? የሠልፈኞቹስ ብዛት? አምስት? ሀምሳ ወይስ አምስት መቶ? በርግጥ ክሱ ለአንዱም ጥያቄያችን ምንም አይነት ምላሽ አይሰጥም፡፡ ጉዳዩን ይበልጥ የሚያወሳስበው ደግሞ ይህ ‹ሾላ በድፍን› የሆነ ወንጀል የተፈፀመው ከሐምሌ ወር 2002 ዓ.ም እስከ ነሐሴ ወር 2003 ዓ.ም ድረስ በየቀኑ መሆኑ ነው፡፡ መቼም እነዚህ ሁሉ ጉዶች እውነት ከሆኑ በዚህች ሀገር፣ ማፍያ እንጂ መንግስት አለ ብሎ የሚመሰክር ደፋር ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡
በጥቅሉ የፖሊስም ሆነ የዐቃቢ-ሕግያኑና የዳኞቹ እንዲህ ሙያውን እና ተቋሙን የማራከስ አካሄድ ከአንድ ገፊ-ምክንያት የዘለለ ሌላ መነሾ የምናገኝለት አይመስለኝም፡፡ ይኸውም ሥልጣኑን ለማራዘም ምንም ነገር ከማድረግ የማይመለሰው ኢህአዴግ፣ በዋናነት ዋስትና የሚሆኑትን ፖሊስ፣ ዐቃቢ-ሕግ እና ፍርድ ቤቶችን በታጋዮች እና በካድሬዎች በመሙላት፣ በተለየ የፖለቲካ አቋም ከፊቱ የሚቆሙትን እየጨፈለቀ ለማለፍ አስልቶ የቀመረው በመሆኑ ነው፡፡
ኦርዌላዊ ስርዓት
የዚህን ስርዓት ቅጥ ያጣ አምባገነንነት ማብራራት አድካሚ እየሆነ ነው፡፡ የሚፈርሰው ማህበራዊ ዕሴት፣ የሚናደው ሀገራዊ ማንነት፣ እንደ አምባሻ የሚቆራረሰው መሬት፣ አልፎ ተርፎም እየጠፋ ያለው ትውልድ እና መሰል ጉዳዮችን ጠቃቅሶ፣ የነገይቷ ድህረ-ኢህአዴግ ኢትዮጵያ በገዢው ስብስብ ክፉ መዳፍ ሳቢያ ህልውናዋ ከገደሉ ጠርዝ ላይ ስለመቆሙ ማተት መደጋገም ነውና እንለፈው፡፡ ይህም ሆኖ ግን አገዛዙ በፍትሕ ስርዓቱ በኩል የሚያካሂዳቸው ዘግናኝ ድርጊቶች የመዓቱን ጊዜ ቅርብ የሚያደርጉ መሆናቸውን ማስታወስ (የሚሰማ ባይኖርም) የዜግነት ግዴታ ይመስለኛል፡፡ የአሜሪካ መንግስት ስቴት ዲፓርትመንትን ጨምሮ፣ ቁጥራቸው የበዛ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ተቋማት በተደጋጋሚ እንደዘገቡት፣ የዚህች አገር ምስኪን ልጆች በማይታወቁ ድብቅ እስር ቤቶች ጭምር መከራ እየወረደባቸው ነው (እኔ ይህንን ጽሑፍ በማዘጋጅበት፣ እናንተም አሁን በምታነቡበት ሰዓትም ቢሆን ለይተን በማናውቃቸው በርካታ የስቃይ እስር ቤቶች፣ በእልፍ አእላፍ ወገኖቻችን ላይ ግፍ እየተፈፀመ መሆኑን መካድ አይቻልም)፡፡
እነዚህ ማሰቃያ ቦታዎች ከምስራቅ እስከ ምዕራብ፣ ከደቡብ እስከ ሰሜን ባሉት የሀገሪቱ አካባቢዎች ተሰበጣጥረው የተዘጋጁ ናቸው፡፡ በነዚህ ካምፖችም የሚታጎሩት ዜጐች በዋነኝነት ከገዢው ግንባር የተለየ (የሚቃረን) ፖለቲካዊ አመለካከት ያላቸው ስለመሆኑ የተቋማቱ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡ በተለይም ብረት አንስተው የሚታገሉ ኃይሎች የተነሱባቸው ክልል ተወላጆችን ማሰቃያ ካምፖቹን የሚያደልቡ ‹የተመረጡ› መከረኞች ሆነዋል፡፡ ኢህአዴግ እንጥፍጣፊ ለሕገ-መንግስቱ አክብሮት ቢኖረው፣ የዜጎቹ ወንጀሎች የቱንም ያህል ቢከፉም እንኳ፣ በግልጽ የፍርድ ሂደት ተገቢ የሆነ ተመጣጣኝ ቅጣት ማግኘት በተገባቸው ነበር፡፡
የዚህ አይነቱን የፍትህ ምኩራቡ አስፀያፊ እርክስናን፣ በግላጭ የሚያሳየን ሌላኛው ጭብጥ በኦጋዴናውያኑ ላይ እየወረደ ላለው ግፍ ተጠያቂ ተቋምም ሆነ ባለሥልጣን እስካሁን ድረስ አለመኖሩ ነው፡፡ የስዊድናውያኑን ሁለት ጋዜጠኞች መታሰርና በይቅርታ መፈታት ተከትሎ፤ በክልሉ ያለው ፍርድ ቤት ስለማያውቀው ዝርፊያ፣ እስርና ግድያ በምስልና በድምፅ የተደገፉ ማስረጃዎች ከጥቂት ወራት ወዲህ ተሰምተዋል፡፡ የአካባቢው የቀድሞ ባለስልጣን ወደስዊድን በተሰደደ ማግስት ያቀረባቸውን እነዚህን ማስረጃዎች ኢህአዴግ እንደለመደው የኦብነግ ከንቱ ውግዘት አድርጎ ማለፍ አይቻለውም፡፡ በዚህ ሰው ማስረጃም ሆነ ክልሉን ባጠኑ ምሁራንና ተቋማት ዘገባዎች መሰረት የጠቀስኳቸው ዘግናኝ ክስተቶች ማህበረሰቡን እየናጡት ነው፡፡
በተለይ ልዩ ሚሊሺያ የሚባለው ሕገ-ወጥ ሀይል፣ በሱማሌ ክልል ጎዳና ላይ ያሻውን እያነቀ እንዲያስር፣ ልጃገረዶችን እንዲደፍር፤ ገፋ ካለም በጥይት አረር እንዲረሽን የተተወበት አግባብ የሚመሰክርልን የፍትሕ ስርዓቱ ድምጥማጡ ስለመጥፋቱ ብቻ ነው፡፡ በዚህ መልኩ በሌሎቹም የሀገራችን ክፍሎች ካለዘውግ፣ ሐይማኖት እና ዕድሜ ልዩነት፤ ካለፍርድ ቤት እውቅና እየተፈፀመ ያለው ግፍ፣ የፍትህ ተቋሙ የዜጎችን ህልውና ለመጨፍለቅ ከገዢዎች ጋር በጥብቅ የተጋመደ ስለመሆኑ ያስረግጡልናል፡፡ እንግዲህ ፍትሕና ርትዕ የሰማይ ላይ ሩቅ ተስፋዎች እንዲሆኑብን የፈቀደውን ስርዓት እስከ መቼ መታገስ ይቻለናል? ስለርትዕ በኢትዮጵያ ምድር ላይ መስፈን ሲባልስ፤ የኢህአዴግን ቅፅር በህዝባዊ ሰላማዊ አብዮት ብንንደው፣ መስዋዕትነታችን ሀገርን ከመዓት ለማዳን ሲባል በፈቃደኝነት የሚከፈል ትውልዳዊ ግዴታ አይደለምን?! (በቀጣዩ ከአራጣ ማበደር ወንጀል እስከ መንግስታዊ ሙስና ላሉ ጉዳዮች እና ለፍትሕ ሥርዓቱ ሞቶ መቀበር ማሰሪያ አበጅቼ አጀንዳውን ለጊዜው እደመድመዋለሁ)
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ
አዲስ አበባ

Sunday, April 13, 2014

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ:- ”…ይህን የውሃ ንብረቷን በቁጥር እየጨመረ ለሚሄደው ሕዝቧና በማደግ ላይ ላለው ኢኮኖሚ ጥቅም እንዲውል ማድረግ የኢትዮጵያ ተቀዳሚና የተቀደሰ ግዴታዋ ነው።…”

Image

ክፍል አንድ
“ለምንወደው ለዛሬው ሕዝባችንም ሆነ፤ ከዘመን ወደ ዘመን ለሚከተለው ትውልድም ጭምር፤ የዓባይን የውሃ ሃብት ለሕይወቱ ደህንነትና ለፍላጎቱ ማርኪያ እንዲውል ማድረግ፤ ኢትዮጵያ ከፍ ያለ ግምት የምትሰጠውና በቅድሚያ የሚያሳስባት ጉዳይ ነው።
አምላካችን ያበረከተላትን ይህን ሃብቷን ለሕዝባቸው ህይወትና ደህንነት በማዋል እንዲጠቀሙበት ከጎረቤት ወዳጅ አገሮች ጋር በለጋስነት በጋራ ለመካፈል ዝግጁ ብንሆንም፤ ይህን የውሃ ንብረቷን በቁጥር እየጨመረ ለሚሄደው ሕዝቧና በማደግ ላይ ላለው ኢኮኖሚ ጥቅም እንዲውል ማድረግ የኢትዮጵያ ተቀዳሚና የተቀደሰ ግዴታዋ ነው።”
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፤ ጥቅምት 1957 ዓም
“ወንዞችን በጋራ ፈሰስ የሚጋሩ አገሮች ሁሉ ውሃውን አግባብ፤ ፍትሃዊ፤ ለሁሉም ጠቃሚ በሆነ መንገድ የመጠቀም መብትና ግዴታ አለባቸው። ይህን ሲያደርጉ በተቻለ መጠን ለጋራ ጥቅም በመመካከርና አንዱ ሌላውን ሳይጎዳ፤ ውሃውንና አካባቢውን ዘላቂነት ባለው መንገድ በመንከባከብ ይሆናል።”
Convention on the Law of the Non-navigational Uses of International Watercourses, UN General Assembly resolution 43/52 of December 1994.
አባይን የመጠቀም ጥያቄ አጼ ኃይለ ሥላሴ ከላይ ከተናገሩት በበለጠ ደረጃ ዛሬ ወሳኝ ሆኗል። ባሁኑ ወቅት በዓለም አከራካሪ፤ አሳሳቢና ጦርነትን ፈጣሪ ከሆኑ አንኳር ጉዳዮች አንዱ ውሃንና ወንዞችን የመጠቀም መብት ነው። ከፍተኛ ሽሚያና ሴራ አለ። ጉዳዩን ያጠኑ ግለሰቦችና ተቋሞች እንዲህ ይላሉ። “የዛሬ አስራ ስድስት ዓመት (2030) የዓለም ሕዝብ ብዛት እየጨመረ፤ ፍላጎት እያደገ፤ ከተሜነትና ልማት እየተስፋፋ ስለሚሄድ፤ አራት ቢሊዮን ሕዝብ የውሓ እጥረት ያጋጥመዋል። ከዚህ ውስጥ ብዙ መቶ ሚሊዮን የሚገመተው በአፍሪካ ቀንድ፤ በሰሜን አፍሪካ፤ በሳሄል አገሮች ይገኛል።” ከሳሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ሕዝብ ዛሬ አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ሲገመት፤ በተባበሩት መንግሥታት ስሌት፤ በ2050 ይህ ቁጥር ወደ ሁለት ነጥብ አራት ቢሊዮን ከፍ ይላል። የውሃ ተፋሰስ ተፎካካሪ ወደ ሆኑት ግብጽና ኢትዮጵያ ብናተኩር የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ዛሬ ካለው እጥፍ ይሆንና ቢያንስ መቶ ሰማንያ አምስት ሚሊዮን ይደርሳል። ቀድሞ የተባበሩት መንግሥታት ከገመተው ዝቅ ብሏል ማለት ነው። በአንፃሩ፤ የግብፅ ሕዝብ ብዛት መቶ ሃያ አምስት ሚሊዮን ይሆናል። ኢትዮጵያ በሕዝብ ብዛት ግብፅን በስድሳ ሚሊዮን ሕዝብ ትበልጣለች ማለት ነው። ሆኖም፤ ከግብፅ ጋር ለመወዳደር፤ የኢትዮጵያን ብሄራዊ አንድነት፤ የመላዊ ሕዝቧን ኢትዮጵያውይነት መቀበል ወሳኝ ነው። በተጨማሪ ሁሉም ኢትዮጵውያን የሚሳተፉበትና ክፍጹም ድህነት የሚላቀቁበትን ዘላቂና ፍትሃዊ ኢኮኖሚ መመስረት ያስፈልጋ። ማንኛውም አገር በአፈና፤ በጎሰኛንትና በስደት በተበከለ አገዛዝ ጠንካራ ሕብረተሰብና ጥንካራ አገር ለመመስረት አይችልም። ኢትዮጵያ ታሪክ ያላት፤ መነሻና መድረሻ ያላት፤ ታላቅ ለመሆን የምትችል፤ የብዙ ብሄር/ብሄረሰብ ደሴት መሆኗን ተቀብለን ከልዩነቶች በላይ የሚገልጻት ዋናው እሴት ኢትዮጵያ አንድ አገር መሆኗን መቀበል፤ ዜግነት ኢትዮጵያዊ እንጅ ጎሳዊ አለመሆኑን በማንኛውም ግንኙነት ማስተጋባት የወቅቱ ጥያቄዎች ናቸው እላለሁ። ይኼን የተቀደሰ መርህ እንደዋዛ ካየነው፤ ኢትዮጵያን ለሌሎች (ጥቂት ተጠቃሚዎችና ለፈረንጆች) እንደምናስተላልፋት በአይናችን እያየን ነው። ዛሬ ኢትዮጵያውያን በጎሳ ስለተከፋፈሉ፤ መብታቸውና ነጻነታቸው ስለታፈነ በሃገራቸው የተፈጥሮ ሃብት፤ በቤታቸው፤ በመሬታቸው፤ ብህይዎታቸ፤ በሃብታቸው፤ ለማዘዝ አይችሉም። ለመጀመሪያ ጊዜ ፈረንጆች ከኢትዮጵያዊን የበለጠ ተሰሚነትና መብት አላቸው። አስደናቂውና የሚያኮራው የመሰረታዊ ለውጥ ምልክት ወጣቱ ትውልድ “መብት ይጠየቃል፤ አይለመንም፤ ፍርሃት አልወለደንም፤ በህሊናየ አታዝም” እያለ በደሴ፤ በሃህር ዳር፤ በጎንደር፤ በአዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች የሚያሰማው ድምፅ ነው። ሌሎቻችን እጆቻችን አጣጥፈን የምንመለከት ጊዜ ያለፈ ይመስለኛል። [ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ]

አባይን ለመንከባከብ የጎሰኛነት አገዛዝ በዲሞክራሳዊ አገዛዝ መተካት አለበት (ዶ/ር አክሎግ ቢራራ)

አንድ ባርያ ነጻ የሚወጣው መቼ ነው? ሲፈቅድ ነው? ወይስ ሲፈቀድለት?

አንድ ባርያ ነጻ የሚወጣው መቼ ነው? ሲፈቅድ ነው? ወይስ ሲፈቀድለት?

መስፍን ወልደ ማርያም
መጋቢት 2006
በአለፈው ሳምንት (ፋክት ቁጥር 36) ወይዘሮ መስከረም የተለያዩ መጻሕፍትን በመጥቀስ በሴቶች ላይ ያለውን መጥፎ ጫና በደንብ ያስመሰከረች ይመስለኛል፤ ግን እኮ በሴቶች ላይ ያለው ጫና የቆየ፣ ክፉና ጎጂ መሆኑን ማንም ያውቀዋል፤ ቁም-ነገሩ ያለው ከዚያ የባህል ጭነት በራስ ጥረት ወጥቶ፣ ነቀፌታንም ሆነ እርማትን ለመቀበል ሳይፈሩና ሳያፍሩ እንደመስከረም በአደባባይ ሀሳብን በመግለጽ በአገርና በወገን ጉዳይ መሳተፍና ሌሎችም እንዲሳተፉ የተቻለን ሁሉ ማድረጉ ላይ ነው፤ ለዚህ ነው ይህንን መልስ የምጽፈው፤ ወይዘሮ መስከረም በአጋጠሟትና በምታያቸው እንቅፋቶች ላይ ማተኮርዋ እንደርስዋ መንፈሳዊ ወኔው የሌላቸውን ያስፈራራቸዋል እንጂ አያበረታታቸውም፤ የማንንም አፍአዊ ጫና ተቋቁመው በራሳቸው የውስጥ ኃይል እንዲመሩ እናድርግ።
አንድ መጽሐፍን በመጥቀስ ወይዘሮ መስከረም የሚከተለውን ጽፋለች፡–
ፈጣሪ የሠራውን  ውጫዊ  ገጽታን ማሽሞንሞን በቂ እንደሆነ ሲነገራት የኖረች ሴት፣ በምን ተነሳሺነት አእምሮዋን የሚመግብ  እውቀት ልትሻ ትችላለች? … በልጅነት እውቀትን  ወደመሻት ያልተገፋ ማንነት በጉብዝና ወራት አላዋቂ በመሆን ቢወቀስ ትርጉም አይኖረውም፤ …››
ወይዘሮ መስከረም ሔዋን ሲነገራት የማትሰማ የመጀመሪያዋ ሰው (ልብ በሉ ሴት አላልሁም፤) መሆንዋን እንዴት እስከዛሬ ሳታውቅ ቀረች? ባለመጽሐፉም ይሁን መስከረም የሔዋንን ታሪክ ሳያነሡ መቅረታቸው መሠረታዊ ስሕተት ነው፤ በተጠቀሱት ሁለት ዓረፍተ ነገሮች ውስጥ አንድም እውነትን የሚመስል ነገር የለም፤ መስከረም ‹‹የሔዋን ዘር›› ከማለት በፊት የሔዋንን ሥራ ቆም ብላ ብታስታውስ የጠቀሰችውን መጽሐፍ እኔ እንደምነቅፈው ትነቅፈው ነበር፤ የሔዋን ታሪክ የሚነግረን የሚከተለውን ነው፡፡ ‹‹ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደሆነ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ፣ ለጥበብም  መልካም እንደሆነ አየች፤ ከፍሬውም ወሰደችና በላች፤ ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው፤ እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ፤ የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ፤›› ዘፍ. 3
የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ ማለት ‹‹እንደእግዚአብሔር መልካምንና ክፉን የሚያውቁ›› ሆኑ ማለት ነው፤ አሁንም ሔዋን መስከረምና ባለመጽሐፉ እንዳቀለሏት አለመሆንዋን መረዳት ይቻል ነበር፤ እንዲያውም ከዚህ በፊት እንደጻፍሁት ሔዋን የመጀመሪያዋ አብዮተኛና የነጻነት እናት ነች ለማለት ይቻላል! በአንጻሩ አዳም የፍርሃት አባት ነው፤ ‹‹ራቁቴን ስለሆንሁ ፈራሁ፤›› ያለው እሱ ነው! ስለዚህ ወይዘሮ መስከረም ‹‹የሔዋን ዘር›› የምትለውን በድላለችና ይቅርታ መጠየቅ ሳያስፈልጋት አይቀርም!
ሔዋን የተጠቀመችው ውጫዊ ገጽታን የሚያሽሞነሙን ሳይሆን የውስጥን የመንፈስ ኃይል ቆፍሮ በማውጣት ነበር፤ በዚህ የውስጥ ኃይል ለሚጠቀም ከውጭ ግፊት አይጠብቅም።
‹‹እውቀትን ወደመሻት ያልተገፋ ማንነት›› አይወቀስም፤ ትላለች ወይዘሮ መስከረም፤ እየተገፉ የሚገኘው ባርነት ነው፤ እውቀት የሚገኘው በነጻነት ነው፤ መገፋት ከእውቀት ያርቃል እንጂ ወደእውቀት አያስቀርብም፤ የመስከረም ዋናው መልእክት ሰላቢውን እንጂ ሰለባውን አትውቀስ የሚል ነው፣ ወይም የኔ ሀሳብ አህያውን ፈርቶ ዳውላውን ዓይነት ሆኖባታል፤ ለመሆኑ ሰለባ የሚሆን ከሌለ ሰላቢ ይኖራል ወይ? ሰለባ ከመሆን በፊት ሰለባ ላለመሆን መጣር አንዱ የኑሮ ዓላማ አይሆንም ወይ? ከዚህ በፊት ስለጨቋኝና ተጨቋኝ ደጋግሜ ጽፌ ነበር፤ ጭቆና የጨቋኙ ባሕርይ የሚሆነውን ያህል የተጨቋኙም ባሕርይ ይሆናል፤ ለጨቋኙ ጭቆና የሚጠቅመውን ያህል ለተጨቋኙም ጭቆና ይጠቅመዋል፤ ለጨቋኙ ጭቆና የኑሮው መሠረት የሆነውን ያህል ለሚርመሰመሱት የጨቋኝ ሎሌዎች ጭቆና የኑሮ መሠረታቸው ነው፤ እንዲህ እያለ ወርዶ ወርዶ የጭቆና ጠቃሚነት ለሎሌው ሎሌ፣ ለሎሌው ሎሌ ሎሌ … በኢትዮጵያ ምናልባትም የመጨረሻዋ የጭቆና ሰለባ ሚስት ትሆናለች፤ ወይም ልጆች ይሆናሉ! ጨቋኝና ተጨቋኝ የባሕርይ ቁርኝት አላቸው፤ አንዱ ያላንዱ አይኖርም፤ ወይዘሮ መስከረም ይህ እውነት ያልሆነበት ሁኔታ ወይም አጋጣሚ የምታውቀው ካለ ብታጋራን ደስ ይለኛል፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ሙታናቸውንም እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው፤›› የሚለው ኢየሱስ ክርስቶስ የሞቱትንና በቁማቸው የሞቱትን ሲያመሳስላቸው ነው! ለእኔ የሚታየኝ እንዲህ ነው።
መስከረም ብዙ ታላላቅ ሴቶችን ጠቅሳለች፤ በእስዋ ግምት ሁሉም በአባታቸው ወይም በባላቸው እየተገፉ ወደትልቅነት መድረኩ የወጡ ናቸው፤ አዙራ ብታየው የጠቀሰቻቸውን ሴቶች ገፉ የምትላቸው ወንዶች መጀመሪያውኑ በሴቶቹ ተገፍተው እንደነበረስ ሊታሰብ አይገባም? ምናልባት ከጠቀሰቻቸው ሴቶች ይልቅ መስከረም የሄለን ኬለርን ታሪክ ብታስታውስ ኖሮ መገፋትን አታነሣም ነበር፤ ሄለን ኬለር በሕጻንነትዋ ዓይኖችዋም ጆሮዎችዋም ሥራቸውን አቆሙ፤ የሄለን ኬለር የመንፈስ ጥንካሬ ከውስጥዋ አዲስና የተሻሉ ዓይኖችንና ጆሮዎችን እንድታበቅልና እንድትማር፣ ከታወቀ ዩኒቨርሲቲም የመጀመሪያዋ ሴት ምሩቅ ለመሆን እንድትበቃ አድርጓታል፤ ይህች አስደናቂ ሴት ከመቶ ሠላሳ ዓመታት ግድም በፊት ማኅበረሰቡ በሴቶች ላይ የነበረውን አጥር ሰብራ፣ ዓይኖችዋ ባለማየታቸውና ጆሮዎችዋ ባለመስማታቸው የገጠማትን እክል አሸንፋ ራስዋን ከወንዶች በላይ ለማድረግ በቅታለች።
መገፋትን የሚፈልግ ሁሉ፣ ካልገፉት የማይነቃነቅ ሁሉ፣ ሬትን ሲግቱት ይጣፍጣል እያለ የተቀበለ ሁሉ፣ ዶሮ ማታ፣ ዶሮ ማታ፣ እያሉ አታልለው እንኳን ዶሮ የለም ሹሮ ሲሉት የማይናደድ ሁሉ፣ ምኞቱ ልደግ ልመንደግ እያለ ሲነዘንዘው በአፈና ጭጭ የሚል ሁሉ ለወቀሳ ብቻ አይደለም ለውርደትም ክፍት ነው፤ ስለዚህም ተወቅሶ ከውርደት ከዳነ ወቀሳው ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል ማለት ነው፤ ዞሮ ዞሮ የሰው ልጆች ሁሉ — ሴት፣ ወንድ፣ ወጣት ሽማግሌ-አሮጊት፣ ባለሥልጣን ተራ፣ ገበሬ ነጋዴ፣ ወታደር ፖሊስ፣ አስተማሪ አስተዳዳሪ፣ ዳኛ ጠበቃ፣ ሀኪም መሀንዲስ፣ … — የፈለገውን ቢሆን ላለበት ሁኔታ ኃላፊነቱ የራሱና የግሉ ነው፤ ራሱን የሚገነባው ወይም ራሱን የሚንደው ራሱ ነው፤ ሰበብ እየፈለጉ ከዚህ ኃላፊነት መውጣት ቀላል ቢመስልም ተመልሶ እምቦጭ ነው፤ ዳገቱን ለመውጣት የሚመረውን እውነት መቀበል ያሻል።
በመጨረሻም በማናቸውም መንገድ፣ በማናቸውም ጊዜ፣ በየትኛውም ቦታ ወደቁልቁለት የሚገፉትን ወይም የሚነዱትን ‹‹እምቢ!›› ብሎ ድምጹን ያላሰማ ገደል ገብቶ ሲንፈራፈር ከራሱ በቀር የሚወቅሰው የለም፤ አቅመ-ቢስነት ከውጭ አይመጣም።
Ze-Habesha 

Wednesday, April 9, 2014

ዲና ሙፍቲ ይመችዎት – “በነጻው ፕሬስ” ስም

ቀጭኑ ዘ-ቄራ

dina_mufti


ለምሳሌ አንድ አናጢና ግንበኛ የነበረ ሰው ጊዜ ረድቶት ወይም ተምሮ ወይም እድገት አግኝቶ ወይም …. በቃ በሆነ ነገር የጦር ጄኔራል ቢሆንና ተመልሶ ግንበኛ ቢሆን ምን ተብሎ ሊሰየም ነው? ግራ ያጋባል። ግን ደግሞ ላያጋባም ይችላል። የዛሬዎቹ ጄኔራሎች ኢንቨስተር ስለሆኑ ነዋ!! ለምሳሌ አንድ አምባሳደር ተብሎ የ”ተመደበ” ሰው፣ በግምገማ በሉት በገገማ “በቃህ” ቢባልና ቀድሞ ወደነበረው ሙያ ወደ ነርስነቱ ቢመለስ ምን ተብሎ ሊጠራ ነው? “አምባሳደር፣ ነርስ፣ እገሌ …”?

ቀጭኑ ዘ-ቄራ ነኝ። በውል በማይገባችሁ ምክንያት ተሰውሬ ነበር። ዛሬ እግር ጣለኝና “ላሸብር” መጣሁ። ሰላምታዬ መሆኑ ነው። መለስ ድንጋዩ ይቅለላቸው፣ አርማታው ስፖንጅ ይሁንላቸውና ብዙ አይነት የሰላምታ ቋንቋና ስታይል “አውርሰውን” አልፈዋል። ታላቁና አርቆ አስተዋዩ መሪያችን!! ህወሃቶች በዚህም ይቀኑ ይሆናል እኮ። መለስዬን ማን የነሱ ብቻ አደረጋቸው? እስኪ አርፈው ይተኙ፣ ይሙቱበት… እኔ ወደ ጉዳዬ ላምራ። “ግን መቃብራቸው ልዩ ጥበቃ የማይደረግለት ለምንድነው?” ሳልል ማለፍ አልፈልግም። ዋ!! ድንገት ቢነሱ!! ዋ ብያለሁ …
ግን አሁን አምባሳደር የነበረ ሰው ጡረታ ወጥቶ ደላላ ቢሆን “አምባሳደር፣ ደላላው፣ እገሌ” እያልን ልንጠራ ነው? የአገራችን ሚዲያዎች ነጻ መውጣት ያቃታቸው ከስም ስያሜ ጀምሮ ነው። ካላይ ያነሳኋቸው የኢህአዴግ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ “አቶ” ይቅርታ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ስም ነው ሌላ ጉዳይ ውስጥ ቀርቅሮ ያስለፈለፈኝ። እሳቸው አሁን የተመደቡበት መደብ “አምባሳደር” በሚል ርዕስ ከሆነ ግድ የለኝም። ግን ለጌቶቻቸው ቀላጤ ሆነው በህዝብ ግንኙነትና አንደበትነት ተመድበው ከሆነ ለጊዜው “አቶ” በቂ ነው። የነጻው ፕሬስ ሰዎች ወይም የበርጫ ቤት ባልደረባዬ ሽመልስ ከማል እርማት ይስጡበት።
አንድ በርጫ የሚወድ ጋዜጠኛ፣ አምባሳደር ዲና ሙፍቲን “ይከይፉኛል” በማለት አድንቆቱን ይቸራቸዋል። ዜና ሲጠፋ ሚስኮል ማድርግ ብቻ ነው። ምን ልታዘዝ በማለት የተመደቡበትን መደብ ሳይለቁ መግለጫ ይሰጣሉ። መብራት ሃይል ሰንደቁን አባሮ የመደባቸው ካድሬ መግለጫ መስጠት የጀመሩ ሰሞን ባህር ዳር እየደወሉ “ዛሬ ማታ ዜና ተመልከቱ፣ እኔ እታያለሁ” ይሉ ነበር። የመጀመሪያ ቀን ለዋንየው ሰውዬ ደውለውለት “ማን ጋር እንደደወልክ አውቀሃል” አላቸው። እሳቸውም ስማቸውን በመጥራት “እኔ እኮ ከፌዴራል መንግስት ነው የምደውለው” እንዳሉት እጎናቸው ያለ ሰው አጫውቶኛል። “ማን ይሙት” ካላችሁ፣ አንድ የምምልበትና የምገዘትበት ስም ነበረኝ “ተሰዋብኝ”። ስምም ይሰዋል። ዘንድሮ!! እኔን!! ለነገሩ የዘንድሮ መሐላ “ሰለሜ ሰለሜ” ሆኗል።
አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ለመለስ ሲያለቅሱ የሚያሳውን ፊልም እስኪ ዝም በሉና እዩት። እየተዝረበረቡ ሲነፈርቁ ጅል ነው የሚመስሉት። ለነገሩ ጅል መስለው ቁብ አሉበት። ከሳቸው ጋር አገራቸው ኮንፍራንስ የተካፈለ ሰው ሲናገር እንደሰማሁት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር እያሉ ከአጃቢዎቻቸው ጋር መጡ። ኮንፍራንሱ ላይ እድል ተሰጣቸውና ተናገሩ። “እኔ የኢየሱስን ስም መጥራት የማይገባኝ … ” በማለት አነቡ። ተንበርክከው ነፈረቁ። ሁለት ኣመት ሳይሞላ እስክስታ ጀመሩ። ሰለሜ ሰለሜ እያሉ እሬብ ለሬብ ተያይዘው ዘለሉ።
አራዳው መለስ ነብሳቸውን ገለባ ያድርገውና፣ ቀላል ለማለት ነው ገለባ ያልኩት “የኢትዮጵያ ሚሌኒየም” ሲከበር አላሙዲን ባስገነቡት የኮንቴነር ቤት ውስጥ ነው። ለመሆኑ እሱ ቦታ የማን እንደነበር ስማቸው በኖህ የሚጀምር አንድ ሃብታምና አዋቂ ሰው አፈላልጋችሁ ድረሱበት። ከሂልተን እስከ ሸራተን በተደረገ ግብዣ የተሰረቀ ፕሮጀክት ነው። በትክክልም ላሸብር እንደመጣሁ የገባኝ አሁን ነው። ኮንቴነርም ቢሆን ይሁን፣ ፕሮጀክቱ ድራማ ቢኖረውም ማን እንደሳቸው። በብድርም ቢሰራ ይሁን ከማለት ውጪ ምን ይባላል? አላሙዲ ግን ይገርማሉ እኮ። በሄክታር 0.20 ሳንቲም ግብር መክፈል አቅቷቸው ከሆለታ አበባ እርሻቸው እንዲነሱ የገበሬ ማህበር ደብዳቤ ጽፎላቸዋል ነበር። ብዙ ነገር አለ። ጥልዬ ምንድን ነበር ያለው “ሆድ ይፍጀው” ግን ለምን ሆድ ይፍጀው እኛን ራሳችንን ፍጅ-ት ያድርገን።
እናም አምባሳደር ዲና ሙፍቲ “ሙድ” አላቸው። ሚዲያውን ለባላንስ/ማመጣጠኛ ረድተውታል። አንድ ወዳጄ ሲተርባቸው ሳይደወልላቸው ከዋለ “ምነው ወዳጆቼ ጠፉ ብለው ይጨነቃሉ። ለመረጃ ነው፣ የታሰረ ጋዜጠኛ ወይም የተዘጋ ፕሬስ አለ?” ብለው የወዳጆቻቸውን ደህንነት ይጠይቃሉ። ግን እኮ ዝም ከማለት መናገር ይሻላል። ለተመደቡበት ቦታ ብቃት አላቸው። ኢህአዴግም በረከትም “ይመችህ” ያሏቸው ይመስላል። በተለይ ለሰነፍ ጋዜጠኞች መተዳደሪያ ሆነዋል። በነገራችን ላይ “ለመረጃ” በማለት የታሰሩ ጋዜጠኞችና የተዘጋ ፕሬስ እንዳለ ሲጠይቁ መልሱ “ምን ነጻ ፕሬስ አለና” የሚል ነው አሉ።
እዚህ ላይ ተመቸኝ። አዎ ነጻ ፕሬስ ወዴት ግድም ነው የሚገኘው? የት ነው ነጻ ሚዲያ ያለው። ከኢህአዴግን እየበላ የሚያመሰግን አለያም ሲመች እየተቸ ሲነቃነቅ ጥብቅና የሚቆም ወገንተኛ፣ ይህ አንዱ ነው። ሌላው ጭልጥ ብሎ መቃወም ነው። “ይህ ጥሩ ነው ግን” ብሎ የሚጀምር እንኳን የለም። ከጅምሩ ራሱ ኢህአዴግ በረከትን ልጓም የሌለው በትር ሰጥቶ ሊማርና ሊገራ የሚችለውን ጅምር አከሸፉት። ተወደደም ተጠላም ግን የተመጣጠነ ሚዲያ ግድ ነው። አለያ መጀመር እንጂ መጨረስ ይከብዳል።
ሃይለማርያም ሰለሜ ሰለሜ መጨፈር የሚችሉ አይመስለኝም ነበር። በነፈረቁበት ቤት እየተፍለቀለቁ ተምነሸነሹ – ደስ ይላል። ቤተ ክርስቲያናቸውና የሚያመልኩት መንፈስ ምን እንደሚላቸው ባለውቅም ሲጨፍሩ ደስ ብሎኛል። ቴድሮስ አድሃኖም እንደውም የቱሪዝምና ባህል ሚኒስትር ሁነው ኪነቱን ቢያነቃንቁ እመርጣለሁ። በነጻነት ፉት እያሉ እንዲሰሩ!! ሃይለ ማርያም ሲጨፍሩ በደስታ ስሜት ሆኜ መለስን ነፍስ ዘራሁባቸው። ህዝብ ፊት ቀርበው ዘፈን ምረጡ ሲባል “ሱዳንኛ” መርጠው ነው ከውዳቸው/ይቅርታ ውዳቸው የሌሎችም ውድ ነበሩ/ አብረው መስታዋት ቤት ውስጥ ሆነው በእጥርጥር የደነሱት!! የት? ሚሌኒየም አዳራሽ። አስቡት ኮንቴነር ቤት ውስጥ፣ በጋርዶች በተከበበ፣ በከባድ መሳሪያ በታጠረ፣ ጥይት በማይበሳው መስታዋት ውስጥ ሆኖ መዝናናት … ለትዝታ ያህል ነው። ታዲያ እሳቸው ሲሞቱ ያርማጮ ገበሬ ደረት መታ፣ ጸጉር ነጨ፣ የመንዲ እናት ደረቷን ደቃች። አዲስ አበባ በየቀበሌው ድንኳን ተጥሎ የቀበሌ የጸጥታ ሃላፊና ሊቀመንበርን “ነብስ ይማር፣ እግዜር ያጽናችሁ” እያለ ህዝብ ሲሰናበት … ጉድ እኮ ነው።
ቀጭኑ ዘ-ቄራ ኢህአዴግ “እንዲቀየር” የሚፈልገው እንዲህ ያሉ መለኪያ አልባ በሽታዎች ገሀድ ሲወጡ በዛው በጠንባራ ሚዲያ ለመመልከት በመጎምጅት ነው። እና መለስ በሱዳን ዘፈን ጨፈሩ!! ለምን? መሄድ የምትፈልጉ ሂዱና ጠይቋቸው። ቀጭኑ ሞትን ይፈራዋል። በድንገት ተስፈንጥሮ መሔድን አይወድም። አሁን የአራራ ሰዓት ነው!! ልሂድበት። እናንተም ተቀንጠሱ!! አምባሳደር ሙፍቲ ይመችዎት!!
ማሳሰቢያ፡- ከላይ ስለ አምባሳደርነት በምሳሌ ያነሳሁት የሙያ መጠሪያ ከአምባሳደር ዲናም ሙፍቲም ሆነ ከማውቃቸው አምባሳደሮች ጋር አንዳችም ግንኙነት የለውም። አምባሳደርነት የስራና የቦታው ሹመት እንጂ እንደ ሙያ ስም ለዘላለም ከሞት በኋላም የሚያገለግል አይደለም ለማለት ብቻ ነው!!

በቴሌኮም ላይ የሚደረግ ክትትል መብቶችን ያቀጭጫል


የኢትዮጵያ መንግስት በሃገር ውስጥ እና ከሃር ውጭ የሚገኙ ተቃዋሚዎች እና ጋዜጠኞች ላይ በስፋት የሚያካሂደውን የቴሌኮም ክትትል ለማጠናከር ከውጭ ሃገራት የሚገኝ ቴክኖሎጂ እንደሚጠቀም ሂዩማን ራይትስ ዎች ዛሬ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ገለጸ፡፡
“ ‘የምንሰራውን ነገር ሁሉ ያውቃሉ’፡በቴሌኮም እና ኢንተርኔት የሚደረግ ክትትል
በኢትዮጵያ” የተሰኘው ባለ 100 ገጹ ሪፖርት የኢትዮጵያ መንግስት በሃገር ውስጥ እና ከሃገር ውጭ በሚኖሩ የፖለቲካ ተቃዋሚዎች ናቸው ተብለው በሚታሰቡ ሰዎች ላይ የሚያደርገውን ክትትል ለማስፈጸም ከተለያዩ ሃገራት በማግኘት ጥቅም ላይ ያዋላቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ መንግስት የሚያካሂደው ይህ ክትትል ሃሳብን የመግለጽ፣ የመደራጀት እና መረጃ የማግኘት ነጻነቶችን የሚጥስ ነው፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም በተሰኘው እና ሙሉ ባለቤትነቱ በመንግስት በተያዘው ብቸኛ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጭ አማካኝነት መንግስት የሞባይል እና የኢንተርኔት አገልግሎትን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩ ክትትል የማድረግ ስልጣኑን ባልተገባ መልኩ እንዲጠቀም ምቹ ሆኖለታል፡፡
በሂዩማን ራይትስ ዎች የቢዝነስ እና ሰብዓዊ መብቶች ዳይሬክተር አርቪድ ጋንሰን “የኢትዮጵያ መንግስት የቴሌኮም አገልግሎትን በመቆጣጠርየተቃውሞ ድምጾችን ለማፈን እየተጠቀመበት ነው” ብለዋል፡፡ አርቪድ ጋንሰን እንዳሉት “የኢትዮጵያን ህገወጥ የክትትል ተግባር ለማቀላጠፍ ምርቶችን እና አገልግሎቶችን እያቀረቡ የሚገኙ የውጭ ሃገራት ድርጅቶች የመብት ጥሰት ወንጀል ተባባሪ የመሆን እድላቸውን እያሰፉት ነው::”
ሪፖርቱ እ.ኤ.አ ከኖቬምበር 2012 እስከ ጃንዋሪ 2014 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ እና ሌሎች 10 ሃገራት የሚገኙ የጥቃቱ ሰለባዎችን እንዲሁም የቀድሞ የደህንነት ሠራተኞችን ባካተቱ ከ100 በላይ ቃለ-መጠይቆች ላይ የተመሰረተ ነው ፡፡ የቴሌኮም አገልግሎት ስርዓቱን መንግስት ሙሉ በሙሉ ስለሚቆጣጠረው የኢትዮጵያ የደህነነት ባለስልጣናትም ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የስልክ ተጠቃሚዎችን የተቀረጸ የስልክ መልዕክት ልውውጥ ያለምንም ገደብ ያገኛሉ፡፡ አንድም ሕጋዊ ሥርዓት ሳይከተሉ ወይም ያለምንም የበላይ አካል ተቆጣጣሪነት በመደበኛነት እና በቀላሉ የስልክ ልውውጦችን ይቀርጻሉ።
ከታገዱ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ተወንጅለው በዘፈቀደ የሚታሰሩ ሰዎች ላይ ህገወጥ ምርመራ በሚደረግበት ወቅት ከቤተሰብ አባላት እና ከጓደኞቻቸው ጋር ያደረጓቸውን እና በተለይም ደግሞ የውጭ ሀገራት ቁጥር ያላቸውን የተቀረጹ የስልክ ውይቶችን ያስደምጧቸዋል፡፡ በሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ወቅት የሞባይል ኔትወርኮች የሚዘጉ ሲሆን የተቃውሞ ሰልፍ ተሳታፊዎች የሚገኙባቸው አካባቢዎችም ከሞባይል ስልኮቻቸው በሚገኙ መረጃዎች አማካኝነት ተለይተው ይታወቃሉ፡፡
አንድ የቀድሞ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ለሂዩማን ራይትስ ዎች ሲናገር “አንደ ቀን አሰሩኝ እና ሁሉንም ነገር አሳዩኝ፡፡ ሁሉንም የስልክ ልውውጦቼን ዝርዝር ካሳዩኝ በኋላ ከወንድሜ ጋር ያደረኩትን የስልክ ንግግር አሰሙኝ፤ ያሰሩኝ በስልክ ስለፖለቲካ ስላወራን ብቻ ነው፤ ለመጀመሪያ ጊዜ የያዝኩት የራሴ ስልክ ነበርና ከዚያ በኋላ በነጻነት ማውራት የምችል መስሎኝ ነበር፡፡”ብሏል
መንግስት በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ማንኛውንም አይነት ነጻ እና ጠንከር ያለ ትንተና የሚያቀርቡ ድረ-ገጾችን በማገድ መረጃ የማግኘት ነጻነትን ገድቧል፡፡ ሂዩማን ራይትስ ዎች እና በኢንተርኔት ደህነንት እና መብቶች ላይ ምርምር የሚያደርገው የቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ ሲትዝን ላብ የጥናት ማዕከል ኢትዮጵያ ውስጥ በ2013 ዓ.ም ያደረጉት ሙከራ ኢትዮጵያ የተቃዋሚ ቡድኖችን፣ የመገናኛ ብዙኃንን እና የብሎገሮችን ድረ-ገጾች እንደምታግድ አረጋግጧል፡፡ ነፃ መገናኛ ብዙሃን እምብዛም በሌሉበት እንደ ኢትዮጵያ ባለ ሀገር ከድረ ገጾች የሚገኙ መረጃዎችን ማግኘት መቻል እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት በሞባይል ተጠቃሚዎች ላይ የሚያደርገው ክትትል ብዙ ጊዜ የኦሮሞ ብሔር አባል የሆኑ ሰዎችን ዒላማ ያደርጋል። በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች ለኦሮሞ ሕዝብ ሰፋ ያለ የራስ ገዝ አስተዳደር ለማጎናጸፍ የሚንቀሳቀሰው የኦሮሞ ነጻነት ግንባርን ከመሳሰሉ የታገዱ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ስለማድረጋቸው ወይም የእነዚህ ቡድኖች አባላትን በተመለከተ መረጃ እንዲሰጡ በማስገደድ የእምነት ቃል ለመቀበል የተጠለፉ የስልክ ልውውጦች ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ በሃገሪቱ አወዛጋቢ የጸረ-ሽብር ህግ መሰረት በፍርድ ቤት ትእዛዝ መሰረት ስለመፈጸማቸው ምንም አይነት ማሳያ በሌለበት ሁኔታ የተጠለፉ የኢሜይል እና የስልክ ልውውጦች ለፍርድ ቤት በማስረጃነት ይቀርባሉ፡፡
ከኢትዮ ቴሌኮም ዳታቤዝ ውጭ በሆኑ የስልክ ቁጥሮች ከኢትዮጵያ ውጭ ስልክ የተደወለላቸው ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ ተደርጎባቸዋል። በዚህም ምክንያት በርካታ ኢትዮጵያዊያን በተለይም በገጠራማው የሃገሪቱ ክፍል የሚኖሩ ሰዎች ወደውጭ ስልክ ለመደወል ወይም ከውጭ ሃገራት የሚደወሉ ስልኮችን ለመመለስ ይፈራሉ፤ ይህ ደግሞ በርካታ ዜጎቿ በውጭ ሃገራት ስራ ላይ ለሚገኙባት ሃገር ከፍተኛ ችግር ነው፡፡
በኢትዮጵያ ያለውን የቴሌኮም አገልግሎት ለመቆጣጠር የሚውለው አብዛኛው ቴክኖሎጂ የሚቀርበው ዜድ ቲ ኢ ከተባለው የቻይናው ትልቅ የቴሌኮም ኩባንያ ሲሆን ኩባንያው እ.ኤ.አ ከ 2000 ዓ.ም ጀምሮ በሃገሪቱ ውስጥ የሚገኝ እና በተለይ ደግሞ እ.ኤ.አ ከ2006 ዓ.ም እስከ 2009 ዓ.ም ብቸኛ የቴሌኮም እቃዎች አቅራቢ ሆኖ የቆየ ነው፡፡ ዜድ ቲ ኢ በአፍሪካ እና ብሎም በዓለም ደረጃ የቴሌኮም ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ነው፤ በማደግ ላይ በሚገኘው የኢትዮጵያ ቴሌኮም ኔትዎርክ እድገትም ቁልፍ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡ ህገወጥ ከሆነ የሞባይል ክትትል ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመከላከል እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ስለመሆን አለመሆኑ ከሂዩማን ራይትስ ዎች ለቀረበለት ጥያቄ ዜድ ቲ ኢ ምላሽ አልሰጠም፡፡
በርካታ የአውሮፓ ኩባንያዎችም በተለይ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ዒላማ ለማድረግ የኢትዮጵያ መንግስት የሚጠቀምበትን ላቅ ያለ የስለላ ቴክኖሎጂ አቅርበዋል፡፡ በዩናይትድ ኪንግደም እና ጀርመን መቀመጫውን ካደረገው ጋማ ኢንተርናሽናል ኩባንያ ፊንፊሸር የተሰኘውን ቴክኖሎጂ እንዲሁም በጣሊያን መሰረቱን ካደረገው ሃኪንግ ቲም ኩባንያ ሪሞት ኮንትሮል ሲስተም የሚባለውን ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያ አግኝታለች። እነዚህ ቴክኖሎጂዎች የደህንነት እና የስለላ ተቋማት የተጠቃሚዎችን ኮምፒውተሮችን ዒላማ በማድረግ በፈለጉት ጊዜ የኮምፒውተር ፋይሎችንና መረጃዎችን ለማግኘት እንዲሁም የዒላማውን እንቅስቃሴዎች ለመከታተል ያስችሏቸዋል። እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ኮምፒውተሮችን በመክፈት፣ የማለፊያ ቃል (ፓሰዎርድ) በማስገባት እንዲሁም የኮምፒውተር ካሜራዎችን (ዌብ ካም) እና ማይክሮፎኖችን በመክፈት ኮምፒውተሩን ወደ ማዳመጫ መሳሪያነት መቀየር ያስችላሉ፡፡ በዩናይትድ ኪንግደም፣ በሰሜን አሜሪካ፣ በኖርዌይ እና በስዊትዘርላንድ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በእነዚህ የኮምፒውተር ሶፍትዌሮች አማካኝነት ዒላማ ከተደረጉ ሰዎች መካከል ይገኙበታል፤ በሰሜን አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ መንግስት ከፈጸማቸው ሕገወጥ የመረጃ ጠለፋዎች ጋር የተያያዙ ክሶች ለፍርድ ቤቶች ቀርበዋል። ዒላማ ከተደረጉ የኢትዮጵያውያን ኮምፒውተሮች የተወሰዱ የስካይፕ ንግግሮች የመንግስት ደጋፊ በሆነ ድረ ገጽ ላይ እንዲወጣ ተደርጓል።
የሰብዓዊ መብቶች ይዞታቸው ደካማ የሆነ መንግስታት የቴክኖሎጂ ምርቶቹን እንዳያገኙ ወይም እንዳይጠቀሙ የሚያግድ ትርጉም ያለው አሰራር ይኖረው እንደሆነ ሂውማን ራይትስ ዎች ለጋማ ጥያቄ ቢያቀርብም ኩባንያው ምላሽ አልሰጠም፡፡ ሃኪንግ ቲም በአንጻሩ ምርቶቹ ያለአግባብ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ የተወሰነ ቅድመ ጥንቃቄ የሚያደርግ ቢሆንም እነዚህ ቅድመ ጥንቃቄዎች ለኢትዮጵያ መንግስት በተሸጡት ምርቶቹ ላይ ስለመተግበራቸው ሊያረጋግጥ አልቻለም፡፡
“ኢትዮጵያ በውጭ የሚገኙ የተቃዋሚ አባላትን ለማጥቃት የምትጠቀማቸው የውጭ ሃገራት ቴክኖሎጂዎች ቁጥጥር የሌለበት የዓለምዓቀፍ ንግድ ከፍተኛ አደጋ እየፈጠረ ስለመሆኑ የሚያሳይ አደገኛ ምሳሌ ነው” ያሉት ጋንሰን “የእነዚህ መሳሪያዎች እና ቴክኖሎጂዎች አምራቾች መሳሪያዎቹ ያለአግባብ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ የሚያስችሉ አስቸኳይ እርምጃዎችን መውሰድ እንዲሁም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ዒላማ ለማድረግ ስራ ላይ ስለዋለው ቴክኖሎጂ ምርመራ ማድረግ እና በኢትዮጵያ የሚያካሂዱት ስራ የሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚያደርስውን ተፅዕኖ መፈተሽ አለባቸው፡፡” ብለዋል።
እንዲህ አይነት በጣም አደገኛ የስለላ ሶፍትዌሮች በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ምንም ዓይነት ቁጥጥር አይደረግባቸውም እንዲሁም በሃገራት ደረጃ ያለው ቁጥጥርም በቂ አይደለም አልያም የውጭ ሽያጫቸው ላይ ገደብ አይጣልም በማለት ሂዩማን ራይትስ ዎች ይገልጻል፡፡ በ2013 ዓ.ም. በመብት ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ ቡድኖች ጉዳዩን አስመልክቶ ለኢኮኖሚ ትብብር እና ልማት ድርጅት (ኦኢሲዲ) አቤቱታ ያቀረቡ ሲሆን አቤቱታው እንዲህ አይነት ቴክኖሎጂ በባህሬን የሚገኙ የመብት ተሟጋቾችን ለመከታተል ጥቅም ላይ ውሏል፤ ሲትዝን ላብ መሳሪያዎቹና ቴክኖሎጂው ከ25 በላይ ሃገራት ጥቅም ላይ እንደሚውሉ የሚያሳይ ማስረጃ አግኝቷል የሚል ነው፡፡
በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ጥበቃ የሚደረግላቸው የግላዊ ጉዳይ፣ ሃሳብን የመግለጽ፣ መረጃ የማግኘት እና የመደራጀት መብቶች በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ውስጥም ተካተዋል፡፡ ነግር ግን የኢትዮጵያ መንግስት የሚያካሂደውን ህገወጥ ክትትል ለመከላከል የሚያስችል የህግ አውጭ እና የህግ ተርጓሚ አካላት የሚከተሉት አሰራር የለም ወይም ብዙም ዋጋ አይሰጠውም። አደጋውን የበለጠ የከፋ የሚያደርገው ደግሞ በኢትዮጵያ እስር ቤቶች በሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች ላይ በስፋት የሚፈጸመው ማሰቃየት እና ያልተገባ አያያዝ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ክትትል የማድረጊያ ቴክኖሎጂዎችን የምትጠቀምበት መጠን ውሱን የሚሆነው በአቅም ምክንያት ወይም በቁልፍ የሚኒስቴር መስሪያቤቶች ላይ ሙሉ እምነት ለማሳደር ካለመቻል ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ሂዩማን ራይትስ ዎች ገልጿል፡፡ ሆኖም ይህ አቅም ይበልጥ እያደገ በመጣ ቁጥር በሞባይል እና ኢሜይል ላይ የሚካሄደው ህገ ወጥ ክትትል የበለጠ ሊሰፋ ይችላል።
በርካታ ኢትዮጵያዊያን መንግስት ፍጹም የሆነ ክትትል የማድረግ አቅም እንዳለው ስለሚያስቡ ራሳቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ሳንሱር የሚያደርጉ ሲሆን ይህም ኢትዮጵያዊያን በቴሌኮም ኔትዎርኮች ላይ በተለያዩ ርዕሶች ዙሪያ በሚያካሂዱት ውይይት ሃሳባቸውን በግልጽ ከመሰንዘር እንዲቆጠቡ በማድረግ መንግስት በተጨባጭ ማድረግ ከሚችለው በላይ ቁጥጥሩ የከፋ ተጽእኖ እንዲኖረው አድርጓል። የሞባይል አገልግሎት ሽፋን እና የኢንተርኔት አገልግሎት እጅግ ውስን በሆነበት በተለይ በገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል ራስን ሳንሱር ማድረግ የተለመደ ሆኗል፡፡ ዋናው የመንግስት የመቆጣጠሪያ መንገድ በጣም ሰፊ የሆነው የመረጃ አቀባዮች መረቡ እና እስከታች የማህበረሰብ ስርዓት ድረስ የተዘረጋው የክትትል መንገዱ ነው፡፡ ይህም አብዛኞቹ በገጠር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የሞባይል ስልኮችን እና ሌሎች የቴሊኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂዎችን እንደ ተጨማሪ የመቆጣጠሪያ መሳሪያ አድርገው እንዲያዩ እንዳደረጋቸው ሂዩማን ራይትስ ዎች ለመረዳት ችሏል፡፡
ጋንሰን እንዳሉት “የኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎት እያደገ በሄደ ቁጥር አስፈላጊው የህግ ጥበቃ እንዲተገበር እና የደህንነት ሰራተኞች በሰዎች ግላዊ ግንኙነቶች ላይ ያልተገደበ ክትትል እንዳያደርጉ ያለው አስፈላጊነትም ይጨምራል፡፡” “የሞባይል እና የኢንተርኔት ቴክኖሎጂዎች ወደ ሃገር ውስጥ ሲገቡ ዴሞክራሲን ለመደገፍና የሃሳቦች እና አስተያየቶች ስርጭትን እንዲሁም ሃሳብን የመግለጽ ነጻነትን የበለጠ በሚያመቻች መልኩ እንጂ የህዝብን መብት ለማፈን ጥቅም ላይ መዋል የለባቸውም፡፡”

Sunday, April 6, 2014

10015653_835736346442828_702939082745029919_n
የሚሊዮኖች ድምፅ ለመሬት ባለቤትነት” በሚል መሪቃል በደሴ የተደረገው የተቃውሞ ሰልፍ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል፡፡ በስፍራው የሚገኙት የአንድነት ፓርቲ ከፍተና አመራሮችና የዞን አመራሮች በሰልፉ ለተሳተፈው የደሴ ህዝብ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ‪የደሴ ነዋሪዎችም “እድሜ ለአንድነት አስተነፈሰን” በማለት ደስታቸውን ገልጸዋል።

የሚሊዮኖች ድምጽ ለመሬት ባለቤትነት በሚል መሪ ቃል አንድነት ፓርቲ የጀመረውን ዘመቻ በማስመልከት የመጀመሪያውን ሰላማዊ ሰልፍ በደሴ ከተማ በተሳካ ሁኔታ ማድረጉ ታውቋል።

ከቅስቀሳ ጀምሮ በደህንነቶች እና በፖሊስ ሃይሎች ወከባ እና መንግስታዊ ውንብድና የተደረገበት የደሴው ሰልፍ ህዝቡ ከፓርቲው ጎን በመቆም ለመብቱ እና ለነጻነት ያለውን ቀናኢነት በማሳየት ትልቅ ትብብር አድርግዋል። በደሴ ከተማ በዛሬው እለት የተደረገው ሰልፍ ከጠዋት ጀምሮ ህዝቡ ፍርሃቱን በመስበር ወደ አደባባይ ወጥቶ ብሶቱን ያሰማ ሲሆን ፖሊሶች መንገድ በመዝጋት ሽብር ለመፍጠር ቢሞክሩም ህዝቡ እያሳበረ በሰልፉ ላይ በመገኘት ተቃውሞውን አሰምቷል።
ከ60 ሺህ በላይ የከተማው ነዋሪዎች የተሳተፉበት ይህ ሰላማዊ ሰልፍ በተለያዩ መፈክሮች ደምቆ ነበር።ህዝቡ አንግቦት ክንበሩት መፈክሮች ውስጥ ፦
-መሬት ከካድሬው ወደ ህዝቡ ይመለስ – አንድነት ኃይል ነው
- የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ – መሬት ለህዝብ ይመለስ
- ጭቆና በቃን – ድል የህዝብ ነው – በግፍ የታሰሩ ይፈቱ ……… የሚሉ ይገኙበታል።

የደሴው ሰላማዊ ሰልፍ በተሳካ ሁኔታ እየተካሄደ በነበረበት ወቅት የአዲስ አበባ ፖሊሶች እና ደህንነቶች ቀበና ሼል አከባቢ የሚገኘውን የአንድነት ዋና ጽ/ቤት በመክበብ ወከባ ሲፈጽሙ ተስተውሏል።

በደሴው ሰላማው ሰላፍ ላይ የአንድነት ከፍተኛ አመራሮች የሆኑት ተቀዳሚ ም/ፕሬዝዳንቱ አቶ ተክሌ በቀለ እንዲሁም የውጪ ጉዳይ ሃላፊው ዘለቅ ረዲ የደሴ የአንድነት ሰብሳቢ ንግግር ማድረጋቸው ታውቋል። የሚሊዮኖች ድምፅ ለመሬት ባለቤትነት” በሚል መሪቃል በደሴ የተደረገው የተቃውሞ ሰልፍ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል፡፡ በስፍራው የሚገኙት የአንድነት ፓርቲ ከፍተና አመራሮችና የዞን አመራሮች በሰልፉ ለተሳተፈው የደሴ ህዝብ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
10152391_835736339776162_7351371086334858666_n
10153092_836259806390482_8153608612627631063_n
10155032_616009748483963_362900362438077475_n
10155823_835669356449527_3760871470725215523_n
10167954_836259836390479_6240097630066552294_n
10169237_836259799723816_864490525410169866_n
10173673_836259819723814_4324534385503670790_n
10174878_702665629792189_7683975017900055174_n
10174887_702670359791716_622918347144100597_n
10174963_835669536449509_993779596150300973_n
10178024_616009418483996_7236771988187809640_n
10246832_835736313109498_4232990120556389759_n (1)

የሪያዱ ሚስጥራዊ ቦንድ ሽያጭ ከሸፈ!

ሐሙስ ጅዳ ላይ ያልቀናው ቦንድ ሽያጭ ትናንት ሪያድ ከተማም ከሽፏል።
የሁለቱም ከተሞች እቅድ መክሸፍ ምክንያት የሕወሐት ሰዎች ጉልበት የመጠቀም ስሕተት መሆኑ ያመሳስለዋል።ጅዳ ኮሚዩኒቲ አዳራሽ አቶ ከድር የሚባል የሕወሐት ሰው አንዲትን ስብሰባ የምትሳተፍ እህት በጥፊ መትቶ ሞባይሏን ለመንጠቅ ባደረገው ትንቅንቅ ስብሰባው ወደ
ሁከት ተቀይሮ መበተኑ ይታወሳል።ሪያድ ስለሆነው ደግሞ እንከታተል ።
የትናንቱ የሪያድ ስብሰባ ለኤምባሲው ሩቅ ያልሆኑ ከየብሄሩ ሐያ ሰዎች በድምሩ አንድ መቶ ሃምሳ ሰዎች ብቻ በሚስጥር የተጠሩበት ነበር።መረጃው ለህዝብ ይፋ ከተደረገ በኋላ በርካታ ሰው ወደኮሚዩኒቲው አዳራሽ በማምራት ለመግባት ይጠይቃል።ከመግቢያ በር “የጥሪ ካርድ አምጡ” ይባላል ።”የለንም” ይላል ህዝብ።”ከየትኛው ብሔር ናችሁ?”ብለው በረኞች ሲጠይቁ “ኢትዮጵያውያን ነን።ጉዳዩ እንደዜጋ ይመለከተናል።”ይላሉ።
በዚህ ምልልስ መሐል አንድ ሰው ሞባይል ሲቀርፅ የሕወሐት አባል የሆነ ግለሰብ ይመታውና ሞባይሉን ሊነጥቀው ይሞክራል ።በር ላይ የተሰበሰበው ኢትዮጵያዊ የዚህ ሕወሐት እብሪት አበሳጭቶት ግብግብ ሲጀመር ከአዳራሹ ውስጥ የነበሩ ሌሎች ህወሀቶች መቀመጫ ወንበር በማንሳት የአዳራሹ መስተዋት በመሰባበር ህዝቡን ለመደብደብ ወደውጭ ይወጣሉ።
የኮሚዩኒቲው ፀጥታ አስከባሪ የሳዑዲ ፖሊሶች በመሐል ገብተው ነገሮች በቁጥጥር ስር ዋለ።የችግሩን መከሰት የሰሙት አምባሳደር መሐመድ ሐሰን መጀመርያ ላይ ፀብ ያጫረውን ሰው አምጡልኝ።የኤምባሲው ሰራተኛ ቢሆን እንኳ በህግ ይከሰሳል።”አሉ።ሰውየውን ህወሀቶች አስቀድመው ቢያሸሹትም በሕዝብ ጥቆማ ያሸሸው ሰው ይያዛል።አምባሳደሩ ሰውየው ህወሐት መሆኑን ሲያውቁ አፈገፈጉ።”በቃ ጉዳዩን ጸውስጥ እንጨርሰዋለን።አሁን ወደጉዳያችን እንግባ።”ብለው በግርግሩ ያለጥሪ ከገቡት ሰዎች ጭምር ስብሰባው ተጀመረ።
ገና እንደተጀመረ አንድ ሰው ብድግ ብሎ “ሀገራችን ውስጥ በሃይማኖታችን ምክንያት ቁምስቅል የምታሳዩን አንሶ በሰው ሐገር እንዴት ትደበድቡናላችሁ?”ብሎ እምባ እየተናነቀው ተናገረ!
ከበር ላይ የህወሓት እብሪተኞች የፈፀሙት የንቀት ድርጊት ከዚህ ሰው ንግግር ታክሎ የመንግሥት ደጋፊ የሚባሉ ሰዎችን ሳይቀር አስከፍቶ እያንዳንዱ ሰው ከወንበሩ ብድግ አዳራሹን ለቆ ወጣ!
ኢትዮጵያ የግል መኝታ ቤታቸው የምትመስላቸውና በሌላው ዜጋ የሐገር ባለቤትነት የማያምኑ ጭፍን የህወሓት ግልፍተኞች የሪያድና ጅዳን የህዳሴ ግድብ የልማት ውይይት(የቦንድ ሽያጭ) በዚህ መልኩ አኮላሽተውታል!!

የኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሞት በካሌ ፈረንሳይ

ባሳለፈነው የካቲት ና በያዝነው የመጋቢት ወር ኢትዮጵያውያንና የሌሎች አገራት ስደተኞች በካሌ በተለያዩ አደጋዎችና ባልታወቁ ምክንያቶች ህይወታቸውን አጥተዋል ፡፡
ፈረንሣይን በስተሰሜን ከእንግሊዝ የምታዋሰነው የካሌ ደሴት ስደተኞች ወደ ታላቅ ብሪታንያ ለመግባት እንደ መሸጋገሪያ የሚጠቀሙባት የወደብ ከተማ ናት፡፡ በዚህች ወደብ በኩል ሰደተኞች በምግብ፣ በአልባሳት ና በቁሳቁስ መጫኛካሚዮኖች ተደበቀው ያለ ሕጋዊ የጉዞ ሰነድ ወደ እንግሊዝ ለመሻገር ይሞክራሉ። ከጊዜ ወደ ግዜ የሁለቱ አገራት ደንበር ጠባቂ ፖሊሶች ጥብቅ ክትትላቸውን ቢያጠነክሩም አሁንም በርካታ ሰደተኞች በአደገኛ ጉዞ ድንበር ለማቀረጥ ሲሞክሩ ሕይወታቸውን የሚያጡበት አጋጣሚ በርካታ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ባሳለፈነው የካቲት ና በያዝነው የመጋቢት ወር ኢትዮጵያውያንና የሌሎች አገራት ስደተኞች በካሌ በተለያዩ አደጋዎችና ባልታወቁ ምክንያቶች ህይወታቸውን አጥተዋል ፡፡ ከዚህ ቀደም ወደ እንግሊዝ በሚያሻግረው መሿለኪያ አቅራቢያ ይገኝ የነበረው የሳንጋት የሰደተኞች መቀቢያ ጣቢያ እ.ጎ.አ በ2002 ከተዘጋ በኋላ በአካባቢው ቃሚ የስደተኞች መቀበያ ጣቢያ አለመኖር የሰደተኞችን ሕይወት አስቸጋሪ እንዳደረገው ዶቼቬለ ያነጋገራቸው ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ገልፀዋል ።ዝርዝሩን ሃይማኖት ጥሩነህ ከፓሪስ ልካልናለች
ሃይማኖት ጥሩነህ
ሂሩት መለሰ

Saturday, April 5, 2014

ትንሽ ምላጭ አገር ትላጭ! መጠላለፍ ወደየትኛው ገደል እየመራን ነው? (ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም)

የአዲስ አበባን መኪናዎች በተለይም በጫት የሚሽከረከሩት ታክሲዎችን በማንኛውም መስቀልኛ መንገድ ላይ ለአምስት ደቂቃ ቆሞ የተመለከተ ሰው በቀላሉ እንደሚረዳው ‹እኔ ካላለፍሁ ማንም አያልፍም!› በሚል መመሪያ መኪናዎቹ ተቆላልፈው እንዲቆሙ ማድረግ ነው፤ እንደሚመስለኝ የአባቶቻችንን ዕዳ እየከፈልን ነው፤ ዱሮ በደጉ ዘመን ሁለት ኢትዮጵያውያን መስቀልኛ መንገድ ላይ ሲገናኙ አንተ-እለፍ አንተ-እለፍ እየተባባሉ የሰማዕታቱንና የቅዱሳኑን ስም እየጠሩ ይገባበዙ ነበር! ይህ ባህል በጠንካራ የሥልጣኔ ላጲስ ተደምስሶ ጠፍቶ በምትኩ እኔ ካላለፍሁ ማንም አያልፍም መንገዱን ሁሉ መቆላለፍ አዲስ የመጠላለፍ ባህል እየተተከለ ነው፤ የመጠላለፍ ባህል የሚታየው በባቡር መንገዶች ላይ ብቻ አይደለም፤ በብዙ ነገር መጠላለፍ ባህል እየሆነ ነው! የዚህ ዝንባሌ መጨረሻው አሸናፊ የሌለበት ሙሉ ጥፋት ነው።
Prof. Mesfin Woldemariam
Prof. Mesfin Woldemariam
በመንገዶች ላይ ጥቂት በጫት የሚነዱ መኪናዎች በመቶ የሚቆጠሩ መኪናዎች እንዳይንቀሳቀሱ ለማድረግ ይችላሉ፤ ሲያደርጉም በየቀኑ እየታየ ነው፤ በማኅበረሰባዊና በፖሊቲካ ግንኙነትም አንድ ሰው የሚዘራው መርዝ የጊዜው ሁኔታ በሚፈቅድለት ፍጥነት የማኅበረሰቡን አባላት ያዳርሳል፤ እንቆቅልሹ እንደሚለው ትንሽ ምላጭ አገር ትላጭ! ማለት መርዝ፣ እሳት፣ ተላላፊ በሽታ በሕዝቡ ላይ ማሰራጨት ከአምስትና ከአሥር ዓመታት በኋላ ውጤቱ ምን እንደሚሆን መገመት አያቅትም።
ድብብቆሽ አይጠቅምም፤ሁለት ነገሮችን በግልጽ ማውጣት አለብን፤አንደኛ በአሜሪካና በአውሮፓ መሽጎ ፍርሃቱንና ሽቁጥቁጥነቱን ለመሸሸግ መርዙን በኢትዮጵያውያን ላይ የሚረጨው ለምንድን ነው? አገዛዙ ይህንን የሚያደርግበት ምክንያት ግልጽ ነው፤ ከፋፍሎ የመግዛት ዘዴ ነው፤ ከአገዛዙ ጋር በሚደረግ ትግል ከታች ሆነው ከሥልጣን ውጭ የሆኑ ዜጎች በሥልጣን ላይ ከተቀመጡት ጋር እየተቆራቆዙና እየተጋጩ ናቸው፤ ይህንን እኔ የላይና-የታች ግጭት (vertical conflict) የምለው ነው፤ ከወያኔ/ኢሕአዴግ ጋር የሚደረገው ትግል ይህ ነው፤ ይህንን ለማክሸፍ ወያኔ/ኢሕአዴግ ትግሉን ከላይና-ታች አውጥቶ ወደጎን-ለጎን ግጭት (horizontal conflict) ሊለውጠው ይፈልጋል፤ ከወያኔ/ኢሕአዴግም ውጭ በጎሠኛነትና በሃይማኖት አክራሪነት የደነዘዙ ሰዎችም ትግሉን ጎን-ለጎን ሊያደርጉት እየሞከሩ ናቸው።
የፖሊቲካ ትግልን የሚመሩ ሰዎች በጎሠኛነትና በሃይማኖት አክራሪነት ስሜት እየተሳቡ ትግሉን የላይና-የታችነቱን ጠብቀው በተደራቢነት የጎን-ለጎን ትግሉን ይጨምሩበታል፤ ይህ ሲሆን ሀሳብ፣ ጉልበትና ሀብት ይከፋፈላል፤ ይበታተናል፤ ወደዓላማ ለመድረስም ያስቸግራል፤ ወያኔ ወደመጨረሻው ላይ ኢሕአዴግ ብሎ የሰየመውን ቀፎ አስቲፈጥር ድረስ በስሙ ውስጥ ኢትዮጵያን የሚያነሣ ነገር አልነበረውም፤ ወያኔን ለድል ያበቃው የማታለያ ስሙ እንደሆነ በበኩሌ አልጠራጠርም፤ ከሃያ ሁለት ዓመታት የጎሣ ሥርዓት በኋላ ኢትዮጵያ ቆስላለች እንጂ አልሞተችም፤ የአሐዝ ማስረጃ ለማቅረብ ባልችልም በብዙ ጎሣዎች መሀከል ጋብቻ እንደዱሮው እየቀጠለ ነው፤ ይህንን የቆየ የዝምድና ሰንሰለት ለመበጠስ የሚጥሩም አሉ።
ኒው ዮርክ ተቀምጦ ትኩስ ውሻ (ሆት ዶግ!) እየበላ ለእስላም ኦሮሞዎች የመገዳደያ መመሪያ የሚሰጥ ሰው የመንፈስ ጤንነቱን እጠራጠራለሁ፤ ይህንን የኒው ዮርክ ቀረርቶ ተከትሎ ሌላ የመጠላለፍ አዋጅ ሰማን፤ ቴዎድሮስ ካሣሁን ለአጼ ምኒልክ ስለዘፈነ ከበዴሌ ቢራ ፋብሪካ ጋር ለማስታወቂያ የገባው ውል ሥራ ላይ ከዋለ የበዴሌን ቢራ አንጠጣም ተባለና ማስታወቂያው ተሰረዘ ይመስለኛል፤ ማን እንዳሸነፈ ወደፊት ጊዜ ይነግረናል፤ አሁን ደግሞ ሌላ ማዘዣ ሰማሁ፤ ‹‹የስ›› በሚለው ውሀ ጠርሙስ ላይ እንስራ የተሸከመችው ኮረዳ መስቀል አድርጋ ነበር፤ ልጅቱ ከነመስቀልዋ የምትታይበትን ውሀ እስላሞች አንገዛም ስላሉ ነጋዴዎቹ መስቀሉን አወለቁባት! ይህንን ማዘዣ ላወጣው አክራሪ እስላም ወረባቦ ቅዳሜ ገበያ ሄዶ እንዲጎበኝ አሳስበዋለሁ፤ ዛሬ ተለውጦ እንደሆነ አላውቅም እንጂ እኔ ብዙ ጊዜ ተመላልሼ እንዳየሁት የወረባቦ ኮረዶች ሁሉ ትልልቅ መስቀል በአንገታቸው ላይ ይታይ ነበር፤ መስቀል የእምነት መግለጫ ይሆናል፤ አያጠራጥርም፤ ግን መስቀል ጌጥም ይሆናል! መስቀል የናዚ ምልክትም ሆኖ ነበር! ለማናቸውም የዚህ ዓይነቱን መጠላለፊያ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚገምዱ ሰዎች ዓላማቸው ማንንም ለመጥቀም ሳይሆን ፍቅርንና ሰላምን ለማደፍረስ ነው፤ የኢየሱስ ክርስቶስ መሠረታዊ ትምህርት ክፉን በክፉ አትመልሱ ነውና ለተበጠሰው መስቀል አጸፋውን ለመመለስ ማሰብ አይገባም።
ከኒው ዮርክ የተሰማው ቀረርቶም ሆነ የመስቀል ማስወለቁ ጉዳይ የተከሰተበትን ጊዜ ልብ ልንለው ይገባል፤ እስላሞች ስለነጻነት የሚያደርጉት ንቅናቄ በጣም እየጋለ በመሄድ ላይ እያለ ክርስቲያኖችም የዜግነት ግዳጃቸው አድርገውት ድጋፋቸውን በሚሰጡበት ጊዜ ነበር፤ ይህ መሆኑ ጥርጣሬን ይጋብዛል፤ የገጠመውን የእስላሞችና የክርስቲያኖች ሰልፍ በማደፍረስ ወይም በመክፈል የሚጠቀም ማን ነው? የሚጎዳውስ ማን ነው? ሁሉም የትግል አጋፋሪዎች ለዚህ ጉዳይ የሚያስፈልገውን ክብደት ቢሰጡት ትግሉ በጎን-ለጎን እንዳይሄድና እንዳይዳከም ይረዳል፤ ከዚያም በላይ አክራሪነት የሚባለውና የሚያስከትለውም ሽብርተኛነት የሚመጣው እንዲህ እያለ ነው፤ እግዚአብሔር ከዚያ ያውጣን!
http://ecadforum.com/Amharic/archives/11666/

Wednesday, April 2, 2014

የማሕበረ ቅዱሳን የመጨረሻዎቹ ቀናት (ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ )

“ማሕበረ-ወያኔ”
በኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም የሚመራው መንግስት ከናቅፋ እስከ ጉና ተራራ ያሉ ምሽጎቻቸውን ከሰማይ በጦር አይሮፕላን፣ ከምድር እሳት በሚያዘንቡ ቢ.ኤሞችና መድፎች ሳያቋርጥ ቢደበድብም፤ በሀገሪቱ ሰሜናዊ አካባቢ ከቀን ወደ ቀን ግዛታቸውን እያሰፉ የተጠናከሩት ‹‹ወንበዴዎች›› ራስ ምታት ሆነውበታል፡፡ የኤርትራ ‹‹ነጻ አውጪ›› ቤዝ-አምባው በተወሰነ መልኩም ቢሆን ለጥቃት የመጋለጥ እድሉ አናሳ በሆነው የሳህል በረሃ በመሆኑ አብዛኛው የአመራር አባል መሸሸጊያው አድርጎታል፡፡Temesgen Desalegn "Fact" Ethiopian Amharic newspaper editor
በተመሳሳይ መልኩ በትግራይ አካባቢ የሚንቀሳቀሱት የወያኔ መሪዎች ምሽጋቸው እንደ ሳህል ምቹ ባለመሆኑ፤ በርካታ ክፉ ቀናትን ያሳለፉት በተራራማ አካባቢዎች በሚገኙ የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ገዳማት ውስጥ ተደብቀው እንደሆነና ከቦታ ቦታ መዘዋወር ሲፈልጉም የመነኮሳቱን አልባሳት ይጠቀሙ እንደነበረ በትግሉ ዙሪያ የተዘጋጁ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ በተለይም ታጋይ መለስ ዜናዊ፣ አባይ ፀሀዬ፣ ግደይ ዘርአፅዮን፣ ስዩም መስፍን፣ ስብሐት ነጋን…. የመሳሰሉ የአመራር አባላት የገዳማቱ ቤተኛ ነበሩ፡፡ ከዚሁ ጋ ተያይዞ የሚነገርም አንድ ታሪክ አለ፤ የመንግስት ፀጥታ ሰራተኞች ሁለት የ‹‹ወንበዴ›› መሪዎች በትግራይ በሚገኝ አንድ ገዳም ውስጥ ከመነኮሳቱ ጋር ተመሳስለው መሸሸጋቸው መረጃ ይደርሳቸውና በጥቂት ሰዓታት ውስጥ እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ ወታደሮችን በመላክ ዙሪያ ከበባ ያደርጋሉ፡፡
ይሁንና መደበቂያ በመስጠት የረዷቸው መነኮሳት ሁለቱን ታጋዮች ‹‹ወይባ›› በመባል የሚታወቀውን ረጅሙን ቀሚሳቸውን አልብሰው እና ቆብ አስደፍተው ከአካባቢው በማሸሽ ይታደጉዋቸዋል፡፡ የታሪኩ ባለቤት መለስ ዜናዊ እና አባይ ፀሀዬ ነበሩ፡፡ በርግጥ እነዚህ የ‹‹ወንበዴ›› መሪዎች ‹በእንዲህ አይነቱ ከመርፌ አይን እጅግ በጠበበ ዕድል ህይወታችን ከሞት መንጋጋ ተርፎ ኮለኔል መንግሥቱን በጓሮ በር ወደ ዜምባብዌ ሸኝተን በትረ-መንግሥቱን ለመጨበጥና ለሃያ ምናምን ዓመታት ኢትዮጵያን ታህል ታላቅ ሀገር አንቀጥቅጠን ለመግዛት እንበቃለን› የሚል ጠንካራ እምነትና የእርግጠኝነት ስሜት በወቅቱ ነበራቸው ብሎ ማሰብ ለእነርሱም ቢሆን እጅግ አዳጋች ይመስለኛል፤ የሆነው ግን ይህ ነበር፡፡
‹‹ማሕበረ-ቅዱሳን››
መለስ ዜናዊና ጓዶቹ በለስ ቀንቷቸው ባልጠበቁት ፍጥነት የመንግሥት ‹‹ጠንካራ ይዞታ›› የሚባሉ ከተሞችን ሳይቀር እየተቆጣጠሩ ወደ አዲስ አበባ የሚያደርጉትን ግስጋሴ ሲያፋጥኑ፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ደግሞ በመንግሥቱ ኃይለማርያም ሰብሳቢበት፣ በደህንነት ሠራተኞች እና የኢሠፓ ካድሬዎች ገፋፊነት ትምህርታቸውን አቋርጠው ለወታደራዊ ስልጠና ደቡብ ኢትዮጵያ ወደሚገኘው ብላቴና የጦር ማሰልጠኛ ከተቱ፤ ዩኒቨርሲቲውም ተዘጋ፡፡
…ከመላው ዘማቾቹ አስራ ሁለት የሚሆኑ ተማሪዎች ተሰባስበው ሲያበቁ፣ በየቀኑ ካምፓቸው አቅራቢያ ወደሚገኘው ‹ሚካኤል ቤተ-ክርስቲያን› በመሄድ፣ ከመዓቱ ይታደጋቸው ዘንድ ፈጣሪያቸውን በፀሎት መማፀን የህይወታቸው አካል አደረጉት፤ ከቀናት በኋላም በአንዱ ዕለት አንድም ለመታሰቢያና ለበረከት፣ ሁለትም ስብስቡ ሳይበተን ወደፊት እንዲቀጥል በሚል ዕሳቤ ‹ማህበረ ሚካኤል› ብለው የሰየሙትን የፅዋ ማህበር መሠረቱ፡፡ …ይሁንና ከመካከላቸው አንዳቸውም እንኳ በ1977 ዓ.ም በ‹ፓዊ መተከል› ዞን የተደረገውን ‹የመልሶ ማቋቋም› ፕሮግራም እንዲያመቻቹ በዘመቱ ተማሪዎች ከተመሠረተውና ከተለያዩ የፅዋ ማህበራት ጋር በመዋሀድ የዛሬውን ‹ማህበረ-ቅዱሳን› እንደሚፈጥሩ መገመት የሚችሉበት የነብይነት ፀጋ አልነበራቸውም፤ የሆነው ግን እንዲያ ነበር፡፡
ኃይማኖትን ጠቅልሎ የመያዝ ዕቅድ
በትጥቅ ትግሉ ወቅት የህወሓት አመራር ገዳማትን ለመሸሸጊያነት ብቻ ሳይሆን ለእርካብ መወጣጫነትም ጭምር ተጠቅሞባቸዋል፡፡ ከድርጅቱ መስራቾች አንዱ የነበረው አረጋዊ በርሄ ለዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ ‹‹A Political History of the Tigray People’s Liberation Front (1975-1991): Revolt, Ideology and Mobilisation in Ethiopi›› በሚል ርዕስ ጽፎት፤ ኋላም ወደ መጽሐፍ በቀየረው የጥናት ጽሁፉ ላይ፣ ‹‹የቤተ-ክርስቲያኗን ሥልጣን (በትግራይ የነበረውን) ለማድቀቅ ሲባል በስብሀት ነጋ የሚመራ የስለላ ቡድን ተቋቋመ፡፡ ይህ ቡድንም ደብረ-ዳሞን ጨምሮ በትግራይ ውስጥ ባሉ ገዳማት አባላቱን መነኮሳት በማስመሰል፣ የገዳማቱን እንቅስቃሴ በህወሓት ፍላጎት ስር የማስገዛት ስራ ሰርቷል›› ሲል በገፅ 317 ላይ ገልጿል፡፡ ድርጅቱ ሙሉ በሙሉ ሐይማኖትን ጠቅልሎ ለመያዝ የተነሳበትን ገፊ-ምክንያትም እንዲህ በማለት አብራርቶታል፡-
‹‹ቤተ-ክርስቲያኗ ተከታዮቿን፣ ለነበረው የኢትዮጵያ መንግስት እንዲገዙ ከማስተማር በዘለለ የብሔራዊ ንቃት (ማንነት) ማስተማሪያም ነበረች፡፡ …ለህወሓት እንቅስቃሴ እንቅፋት እንደነበረች ግልፅ ነው፡፡ ስለዚህም ቤተ-ክርስቲያኒቱን በህወሓት ዓላማ ስር ለማሳደር ፍላጎት ነበር፤ በዚህ የተነሳም የእርሷን ተፅእኖ ለማግለል ጥልቅ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡›› (ገፅ 315-316)
ዶ/ር አረጋዊ ‹‹ጥልቅ እርምጃዎች›› ብሎ ከጠቀሳቸው መካከል አንደኛው ‹‹ለአጥቢያ ቀሳውስቱ ኮንፍረንስ በማዘጋጀት፣ በትግራይ ውስጥ ያሉትን ቤተ-ክርስቲያናት ለብቻ ነጥሎ ህወሓት በሚያራምደው የትግራይ ብሔርተኝነት ስር ማካተት›› እንደነበረ በዚሁ መጽሐፍ ጠቅሷል፡፡ ይሁንና አስገምጋሚ መብረቅ የወረደብን ያህል የምንደነግጠው፣ ዶ/ሩ ከዚሁ ጋ አያይዞ ‹‹የተጨቆነው የትግራይ ብሔርተኝነት የተነሳሳውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያንን ተፅእኖ ለመገዳደር ነው›› በማለት መመስከሩን ስናነብ ነው፡፡ የአረጋዊ መረጃ የሰሚ-ሰሚ ወይም በቢሆን ሃሳብ የተቀኘ አይደለም፤ ይልቁንም ራሱም በመሪነትና ሃሳብ በማዋጣት ከተሳተፈበት ከድርጅቱ የፖለቲካ ፕሮግራም የተቀዳ እንጂ፡፡
የሆነው ሆኖ ህወሓት ከ1970-72 ዓ.ም ድረስ ባሰለጠናቸው ካድሬ ‹‹ካህናት›› አማካኝነት ‹‹ነፃ በወጡ›› መሬቶች ላይ ራሱን የቻለ የቤተ-ክህነት አስተዳደር (ከሲኖዶሱ የተገነጠለ) መመስረቱ ይታወሳል፡፡ ድርጅቱ ለእነዚህ ቤተ-ክርስቲያናት መተዳደሪያ ደንብ ከመቅረፅ አልፎ ዓላማውንም እንደ አስርቱ ትዕዛዛት በፍፁም ልባቸው የተቀበሉ ‹‹መንፈሳዊ ክንፍ›› አድርጓቸው እንደነበረ፣ አረጋዊ በርሄ ተንትኖ አስረድቷል፡፡ እንዲህ አይነቱ ሰርጎ ገብነት በእስልምናም ላይ መተግበሩ አይዘነጋም፡፡ በተለይም የእምነቱ ተከታዮች በሚበዙበት አካባቢዎች ወላጆቻቸው ሙስሊም የሆኑ ታጋዮችን እየመረጠ እና ከክርስቲያን ቤተሰብ የወጡ ካድሬዎችንም ሀሰተኛ የሙስሊም ስም እየሰጠ ‹የትግሉ ዓላማ እስልምናን ማስፋፋት› እንደሆነ በመግለፅ የፕሮፓጋንዳ ስራ ይሰራ ነበር፡፡ በዚህ ስልቱ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የአንዳንድ ዓረብ ሀገራትን ቀልብ ማግኘት ችሏል፡፡ ይህ ደግሞ ከዓረቦች በገፍ ዕርዳታ ያጎረፈለት ሲሆን፣ ወደ መሀል ሀገር የሚያደርገውን ጉዞም አፋጥኖለታል፡፡
ከመንግስት ለውጥ በኋላም ሁለቱን ሐይማኖቶች የተቆጣጠረው በታጋይ ‹‹ካህናት›› እና ‹‹ሼሆች›› ለመሆኑ በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡ ዛሬም በኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት የበላይ በሆነው ጠቅላይ ቤተ-ክህነት ውስጥ ከሚገኙት አስራ ስምንት መምሪያዎች፣ አስራ ስድስቱ በህወሓት ሰዎች የመያዛቸው ኩነት ስልቱ በተሳካ ሁኔታ መተግበሩን ያስረግጣል፡፡ በተለይ ዋነኛው ሰው አቡነ ማቲያስ ሲኖዶሱን ብቻ በሚመለከት ጉዳይ ላይ ጭምር ውሳኔ ከመተላለፉ በፊት ‹‹የመንግስት ባለሥልጣናትን ላማክር›› ሲሉ በተደጋጋሚ መደመጣቸው እና አንዳንድ ጳጳሳት ተቃውሞ በሰነዘሩባቸው ቁጥር በአፃፋው ‹‹መንግስት ያግዘኛል ብዬ ነው እዚህ መንበር ላይ የተቀመጥኩት፤ ባያግዘኝ ሥልጣኑን አልቀበልም ነበር›› በማለት በግላጭ ሲመልሱ መስተዋላቸው ለስርዓቱ ጣልቃ-ገብነት እንደማሳያ ሊቆጠር ይችላል፡፡ ከዚህ ቀደም ለሶስት ወር የቋሚ ሲኖዶሱ አባል ሆነው የሰሩ አንድ ጳጳስም ‹‹ሁልጊዜም ቋሚ ሲኖዶሱ ሲሰበሰብ እርሳቸው (ፓትርያርኩ) ‹መንግስት እንዲህ አለ›፣ ‹መንግስት ሳይፈቅድ›… የሚል ንግግር ይጠቀማሉ›› በማለት ለፋክት አስተያየት ሰጥተዋል (በነገራችን ላይ
ፓትርያርኩ የመዘንጋት፣ ለውሳኔ የመቸገር፣ እንቅልፍ የማብዛትና መሰል ችግሮች ስራቸውን እያስተጓጎሉባቸው እንደሆነ ይነገራል፤ ራሳቸውም ‹‹ሲጨንቀኝ እተኛለሁ፤ ስተኛ ደግሞ እረሰዋለሁ›› በማለት ችግሩን አምነው ተቀብለዋል)
በእስልምና እምነት ውስጥም የመንግስት ጣልቃ-ገብነት ከቀድሞውም መጅሊስ የባሰ እንደሆነ በርካታ መዕምናን የሚያውቁት እውነታ ነው፡፡ ይህ መጅሊስ የሚዘወረው እንደተለመደው በምክትል ፕሬዚዳንቶች ሲሆን፤ ይች አይነቷ ጨዋታ ደግሞ ህወሓት ጥርሱን የነቀለበት ስለመሆኑ ነጋሪ አያሻም፡፡ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ሼህ ከድር ለ17 ዓመታት የትግራይ ክልል መጅሊስና የሸሪአ ፍ/ቤቱን ደርበው በመያዝ መእምናኑን ቀጥቅጠው ሲገዙ ከመቆየታቸውም በላይ ታጋይ እንደነበሩ በኩራት ለመናገር የሚደፍሩ እንደሆነ የቅርብ ሰዎቻቸው ይመሰክራሉ፡፡ በአናቱም ከታማኝ የመረጃ ምንጭ ባይረጋገጥም የመጅሊሱ ፕሬዚዳንት ሼህ ኪያር መሀመድ ከእኚሁ ‹‹ታጋይ›› ምክትላቸው ጋር በአንዳንድ ጉዳዮች መስማማት ባለመቻላቸው እና ‹‹መንግስት የሚያዘውን ሁሉ ለመስራት ለምን እንገደዳለን?›› የሚል ተቃውሞ እስከማሰማት በመድረሳቸው በቅርቡ ከኃላፊነታቸው ሊነሱ እንደሚችሉ ተወርቷል፡፡
ኢህአዴግ እና ‹‹መንፈሳዊ›› ገበያው
ግንባሩ የእምነት ተቋማትን በአብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ ጠርንፎ መያዝን እንደ ዋነኛ ዓላማ አድርጎ የመንቀሳቀሱ መግፍኤን ከሶስት ጉዳዮች አንፃር በአዲስ መስመር ለመተንተን እሞክራለሁ፡- የመጀመሪያው ቤተ-ክህነት በነገስታቶቹ ዘመን የነበራትን ፖለቲካዊ ተሰሚነት (ምንም እንኳን ራሱ ኢህአዴግም በአፋዊነት ከማውገዝ ቸል ባይልም) ለቅቡልነት መጠቀሚያ የማድረግ ፍላጎቱ ነው፡፡ በገቢር እንደታየውም በኃይል በተቆጣጠራቸውም ሆነ ካድሬዎቹ ሊደርሱባቸው በማይችሉ የገጠር ቀበሌዎች ተቀባይነት ለማግኘት ማህበራዊ አክብሮት ባላቸው ሼሆች፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት… ሲቀሰቅስ ተደጋጋሚ ጊዜ ተስተውሏል፡፡ እንዲሁም የእስልምና እምነት በታሪክ ያሳለፈውን አገዛዛዊ ጭቆናንም ሆነ የደርጉን ሁሉንም ሐይማኖት ማግለልን በማጎን ለፕሮፓጋንዳ ተጠቅሞበታል (በወቅቱ የድርጅቱ አመራር አባል የነበረው አቶ ገብሩ አስራት፣ እንደ ሼሆች በመልበስና በመጠምጠም ከፍተኛ አስተዋፆ ማበርከቱን ብዙሀኑ ታጋዮች አይዘነጉትም) በዚህ ዘመንም በቤተ-እምነቶች ካድሬ-ጳጳሳትንና ካድሬ- ሼሆችን አሰርጎ የማስገባቱ ምስጢር ይኸው ነው፡፡
በሁለተኛነት እንደምክንያት ሊጠቀስ የሚችለው የታገለለትን ዘውግ ተኮር ፖለቲካ ያለአንዳች ተግዳሮት ማሳለጥን ታሳቢ ማድረጉ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም የሁሉም ሐይማኖቶች ‹‹የሰው ልጅ በሙሉ የአንድ አምላክ ፍጡሮች ናቸው›› በሚል አስተምህሮ የሚመሩ ከመሆናቸው አኳያ፣ በዘውግ ከፋፍሎ ማስተዳደርን ቀላል አያደርገውምና ነው፡፡ ስለዚህም መፍትሔው አክራሪ ብሔርተኛ ‹‹መንፈሳውያን›› በየእምነት ተቋማቱ እንዲፈለፈሉ እና ከፍተኛውን የሥልጣን እርከን መቆጣጠር እንዲችሉ በማብቃት ላይ የተመሰረተ ብቻ መሆኑን የህወሓት መሪዎች ያውቃሉ፡፡ ይህ ‹‹እውቀታቸው››ም ይመስለኛል ሀገራዊ ስሜት የሌላቸው፣ በችሎታ ማነስ እና በስነ-ምግባር ጉድለት የሚታወቁ፤ እንዲሁም በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ቅቡል ያልሆኑ ሰዎች ቦታውን እንዲይዙ እስከማድረግ ያደረሳቸው፡፡ የራሳቸው የስለላ መዋቅርም በጥቅምት 2 ቀን 1995 ዓ.ም ‹‹ለዋናው መ/ቤት፣ አዲስ አበባ፤ ከ-ል.ዮ፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስን ጉዳይ ይመለከታል›› በሚል ርዕስ ለደህንነቱ ዋና መስሪያ ቤት በላከው ጥናታዊ ዘገባ ላይ እውነታውን እንዲህ ሲል ገልፆታል፡- ‹‹…ለፓትርያርኩ ወዳጅነት አላቸው የሚባሉ ሊቃነ ጳጳሳት ከሦስትና አራት ብዙም ያልበለጡ ናቸው፡፡ ፓትርያርኩ ምንም ዓይነት ተቀባይነትና ከበሬታ ያጡ በመሆናቸው ህልውናቸውን የአንዳንድ መሪዎችን ስም በመጥራትና እንደማስፈራሪያ በመጠቀም ላይ የተንጠላጠለ ሆኗል››፡፡ ከዚህ ሪፖርት በኋላም እንኳ ለማስተካከል አለመሞከሩ መከራከሪያውን አምነን እንድንቀበል ያስገድደናል፡፡
አገዛዙ መንፈሳዊ ተቋማትን ጠቅልሎ ለመያዝ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ በሶስተኛነት ሊጠቀስ የሚችለው ምክንያት፣ ምንም እንኳ ‹‹ተሳክቷል›› ሊባል ባይቻልም፤ በስነ-ምግባር መታነፅ፣ በሀገር አንድነት ማመን፣ ለሕዝብ ጥቅም መቆም፣ የትኛውንም ህገ-ወጥነት ‹ለምን› ብሎ መጠየቅና መሰል መንፈሳዊ አስተምህሮዎችን መርሁ አድርጎ የሚነሳ ትውልድ እንዳይፈጠር መከላከልን ታሳቢ በማድረግ እየሰራ ያለውን ሴራ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም የስርዓቱ ሰዎች በዚህ መልኩ የሚቀረፅ ትውልድን ዛሬ ባነበሩት አይነት የጭቆና ቀንበር ለተራዘሙ ዓመታት መግዛት ከባድ እንደሆነ ለመረዳት አይሳናቸውምና ነው፡፡ ከዚሁ ጋር አንስተን ማለፍ ያለብን ጭብጥ፤ መቃብር ከሚቆፈርለት የኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ጋር የሚያያዝ ነው፤ የሐይማኖቱና የማዕከላዊ መንግስቱ የቅድመ-አብዮቱ ጋብቻ (በምንም አይነት መከራከሪያ ትክክለኛነቱን ልንሟገትለት ባንችልም)፣ ቤተ-ክርስቲያኗ ለኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነቱ የታሪክ ብያኔ ከፍተኛ አስተዋፆ ማድረጓን አያስክደንም፡፡ ይህም ‹የሐይማኖቱን ተቋም የብሔርተኝነቱ ወካይ ሆኖ እንዲታሰብ ይገፋዋል› ብሎ ለሚያምነው ህወሓት፣ ሐይማኖቱ ተቋማዊ ነፃነት እንዳይኖረው የሚቻለውን ሁሉ ሲያደርግ፤ ሐይማኖቱን በማዳከም የብሔርተኝነት መንፈሱንም ማላላት ይቻላል ከሚል መነሾ ነው ብሎ መደምደም ተምኔታዊ አያስብልም፡፡
ገደል አፋፍ የቆመው ማሕበረ ቅዱሳን…
ስርዓቱ የሐይማኖት ተቋማትንና መንፈሳዊ መሪዎቹን ለመቆጣጠር ገፊ-ምክንያቶች ሆነውታል ብዬ ከላይ ለማብራራት የሞከርኳቸውን ሶስት ምክንያቶች ሙሉ ለሙሉ መተግበርን አስቸጋሪ ያደረገበት፣ ቀጥታ በምዕምናኑ የተመሰረቱ ማሕበራት መሆናቸውን መገመት ይቻላል፡፡ ለማስረጃም ያህል ከኦርቶዶክስ ክርስትና-ማሕበረ ቅዱሳን፤ ከእስልምና ያለፉትን ሁለት ዓመታት የእምነቱ ተከታዮች ወካይ ሆኖ የተመረጠው ኮሚቴ አባላት መንግስትንም ሆነ መጅሊሱን በመገዳደር ያደረጉትን አበርክቶ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይሁንና የሙስሊሙን ተወካዮች በገፍ ሰብስቦ እስር ቤት ካጎረ በኋላ፣ ከሲኖዶሱም ሆነ መሰል ማሕበራት ጠንካራ እንደሆነ የሚነገርለትን ማሕበረ ቅዱሳንን ዋነኛ ኢላማው አድርጎ ለመደፍጠጥ የቆረጠ ይመስላል፡፡ የማሕበሩ አባላት በዓለማዊ እውቀት የተራቀቁ፣ በሀገር አንድነት በፍፁም የማይደራደሩ፣ በጥቅመኝነት የማይደለሉ… የመሆናቸው ጉዳይ አገዛዙ ከኃይል አማራጭ የቀለለ መፍትሔ የለም ብሎ እንዲያምን አድርጎታል ብዬ እገምታለሁ፡፡
በርግጥ በአቶ መለስ ዜናዊ ይዘጋጅ እንደነበረ ከህልፈቱ በኋላ በተነገረለት የኢህአዴግ የንድፈ ሃሳብ መጽሔት ‹‹አዲስ ራዕይ›› ከተወሰኑ ዓመታት በፊት አብዛኛውን ጊዜ ‹‹የከሰሩ ፖለቲከኞች ‹ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት፣ አንድ ሐይማኖት አንድ ሀገር› እና ‹ሙስሊሙ ማሕበረሰብ ቀደም ሲል ሲደርስበት የነበረውን በደል በማራገብና በመቀስቀስ፤ ከዚህም አልፎ ተገቢነት የሌላቸው አዳዲስ ጥያቄዎችን በማቅረብ ለማነሳሳትና ለማተረማመስ ሲሰሩ ማየት የተለመደ ሆኗል›› በማለት ከሚያቀርበው የሾላ-በድፍን ፍረጃ ዘልሎ ብዙም መንፈሳዊ ማሕበራትን በስም ጠቅሶ ሲያወግዝ አይሰማም ነበር፡፡ ዛሬ ዛሬ ግን ማንኛውንም ሐይማኖታዊ የመብት ጥያቄን ‹‹ወሃቢያም ይሁን ማሕበረ ቅዱሳን…›› በማለት ማውገዙ የተለመደ ሆኗል፡፡ ከውግዘትም ተሻግሮ ጥያቄያቸውን በሕጋዊ መንገድ ወደ አደባባይ ያወጡትን የሙስሊሙን ተወካዮች ሰብስቦ አስሯል፤ በተለያየ ጊዜ የተደረጉ ሰላማዊ ተቃውሞዎችንም በማስታከክ በበርካታ የእምነቱ ተከታዮች ላይ ግድያና ስቀየትን ጨምሮ ብዙ ግፍ በመፈፀም ጉዳዩን በጠብ-መንጃ ብቻ የሚፈታ አድርጎ ካወሳሰበው ሰነባብቷል፡፡
‹‹ቀጣዩ የኢህአዴግ ኢላማ ማሕበረ ቅዱሳን ይሆን?›› በሚል ርዕስ ከስድስት ወር በፊት በዚሁ መጽሔት ላይ ለማተት እንደሞከርኩት ሁሉ፤ ከላይ በተዘረዘሩ የፖለቲካ አጀንዳዎች እና በሚቀጥለው ዓመት የሚካሄደውን አገር አቀፍ ምርጫ በለመደው የማጭበርበር መንገድ አሸንፎ ያለኮሽታ የሥልጣን እድሜውን ለማራዘም ዓለማዊም ሆነ መንፈሳዊ ነፃ ተቋማት እንዳይኖሩ በይፋ ኢ-ሕገ መንግስታዊ ድርጊቶችን እየፈፀመ ያለው የእነ አባይ-በረከት መንግስት፣ በአሁኑ ወቅት ሙሉ ትኩረቱን ማሕበረ ቅዱሳን ላይ ማድረጉን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህንን አፈና ለማሳካትም ፓትርያርኩ አቡነ ማትያስ በፍፁም ልባቸው ከመተባበር ለአፍታም እንደማያመነቱ በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያህልም አንዱን በአዲስ መስመር ላቅርብ፡-
ከወራት በፊት የአዲስ አበባ ሀገረ-ስብከት አስተዳደርን ወደ ዘመናዊነት ለማሻገር ሲኖዶሱ ጥናት ተደርጎ እንዲቀርብለት ውሳኔ አሳልፎ ነበር፡፡ እናም ጥናቱ ተጠናቆ ይፋ መደረጉን ተከትሎ ከአንዳንድ የደብር አስተዳዳሪዎች ብርቱ ተቃውሞ ስለገጠመው፣ በሀገረ-ስብከቱ ሥራ-አስኪያጅ አቡነ እስጢፋኖስ አማካኝነት በጠቅላይ ቤተ-ክህነት አዳራሽ ከሁሉም አድባራትና ገዳማት የተወጣጡ 2700 ሰዎች የሚሳተፉበትና አስራ አራት ቀን የሚፈጅ የውይይት ፕሮግራም ይዘጋጃል፡፡ ይሁንና ውይይቱ በተጀመረ በሁለተኛው ቀን ጠዋት ፓትርያርኩ፣ ከአቡነ እስጢፋኖስ ጋር በስልክ ከሞላ ጎደል እንደሚከተለው መወዛገባቸውን ሰምቻለሁ፡-
‹‹ጥናቱን የሚሰሩት ባለሙያዎች ናቸው ብለውኝ አልነበረም ወይ?››
‹‹አዎ! ታዲያስ ባለሙያዎች ናቸው የሰሩት፡፡››
‹‹አይደለም! የማሕበረ ቅዱሳን አባላት ናቸው፤ እርስዎ አታለውኛል!››
‹‹የጥናት ኮሚቴው አባላት በቤተ-ክርስቲያን ልጅነታቸውና በየአጥቢያው ባላቸው ተሳትፎ ተጠርተው የመጡ ሙያቸውን ‹አስራት› ያደረጉ ናቸው፡፡››
‹‹በፍፁም! ጥናቱ የማሕበረ ቅዱሳን ነው!››
‹‹ቅዱስ አባታችን ቢሆንስ? ከጠቀመን ችግሩ ምንድን ነው?››
‹‹በቃ! ውይይቱ ከመንግስት ይቋረጥ ተብሏል፡፡››
‹‹ለምን ይቋረጣል?››
‹‹የጥናቱ ተቃዋሚዎች ረብሻ ያስነሳሉና የፀጥታ ስጋት አለ፡፡››
‹‹ለምንድን ነው ረብሻ የሚያስነሱት? ከፈለጉ መጥተው መሳተፍ ይችላሉ፤ እኛ እየተወያየን አይደለም እንዴ! ተቃውሞ ያለው መጥቶ ሃሳቡን ይግለፅ እንጂ ማቋረጥ እንዴት መፍትሄ ይሆናል? ደግሞስ ሲኖዶሱ አይደለም ወይ ‹ሰነዱ ወደታች ወርዶ ይተችበት› ብሎ የወሰነው?››
‹‹የለም! ይቁም ተብሏል፤ ይቁም!››
‹‹እንግዲያውስ የከለከለው አካል ራሱ መጥቶ ይንገረን፡፡››
…የስልክ ምልልሱ ከተጠናቀቀ ከሰዓታት በኋላ አንድ ባለሥልጣን አቡነ እስጢፋኖስ ቢሮ ድረስ መጥቶ ትእዛዙን ያስተላለፈው እርሱ እንደሆነ ገልፆ ውይይቱ እንዲቋረጥ አሳሰባቸው፤ እርሳቸውም ‹‹እናቋርጣለን፤ ነገር ግን እናንተ ‹የፀጥታ ስጋት አለ› ብላችሁ በደብዳቤ ኃላፊነቱን ውሰዱ፡፡ እኛም ለካህናቱም ሆነ ለመዕምናኑ ሁኔታውን ዘርዝረን እንገልፃለን›› የሚል ምላሽ ሰጥተው ይሸኙታል፡፡ ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ ለጊዜው ግልፅ ባልሆነ አንድ ምክንያት መንግስት ‹‹ይቋረጥ›› የሚለውን ማስፈራሪያ ሊያነሳ የቻለው፡፡ ኩነቱ ግን ፓትርያርኩ ማሕበሩን በጥርጣሬ ማየታቸውንና አገዛዙ ለሚወስድበት ማንኛውም አይነት እርምጃ ተባባሪ መሆናቸውን የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡
ሌላው መንግስትና ፓትርያርኩ፣ ማሕበረ ቅዱሳንን ለማፍረስ በሰምና ወርቅነት እየሰሩ መሆናቸውን የሚያመላክተው የዛሬ ሳምንት በጠቅላይ ቤተ-ክህነት የማሕበሩ ተቃዋሚዎች ያደረጉትን ውይይትና የአቋም መግለጫ ስናስተውል ነው፡፡ ለመጽሔቱ ዝግጅት ክፍል የደረሰው በድምፅ የተቀረፀ የውይይቱ ሙሉ ክፍል እንደሚያስረዳው፣ ተሰብሳቢዎቹ ማሕበሩን በተመለከተ ባወጡት የአቋም መግለጫ የሚከተሉትን ነጥቦች ዘርዝረዋል፡- ‹‹የዋነኛ አመራሮቹ የባንክ አካውንት ይመርመር፣ የማሕበሩ ሒሳብ መንግስት በሚመድበው የውጪ ኦዲተር ይመርመር፣ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረቶቹ (ከቀረጥ ነፃ ያስገባቸው ቀላልና ከባድ መኪናዎቹ ሳይቀሩ) ወደ ቤተ-ክህነት ይግቡ፣ የንግድ ተቋማቱ (ትምህርት ቤት፣ ሬስቶራንቶቹን፣ ንዋየ ቅድሳት ማምረቻና ማከፋፈያውን) ያስረክብ፣ ከምዕምናን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚቀበለው አስራት እየፈረጠመበት ስለሆነ እንዳይቀበል ይከልከል፣ የግቢ ጉባኤ (በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት) እርሱ በሚቀርፀው እንዳይወሰዱ መስራት፣ ተጠሪነቱ ከዋና ሥራ-አስኪያጁ ተነስቶ፣ በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ ስር አንዱ ንዑስ ክፍል ይሁን…›› የሚሉና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡
ከዚህ ሴራ ጀርባ ፓትርያርኩና መንግስት በትብብር መቆማቸውን የሚያሳየው በተቀረፀው ድምፅ ላይ፣ የውይይቱ መሪ አዳራሹን መጠቀም የቻሉት በአቡኑ መልካም ፍቃድ እንደሆነና እርሳቸው በዛሬው ውይይት ያልተገኙት የሕዳሴው ግድብ ምክር ቤት አባል በመሆናቸው ግዮን ሆቴል ስብሰባ ስላለባቸው መሆኑን ከመግለፅም በዘለለ፤ ‹‹ቅዱስ አባታችን በዚህ የተቃውሞ ምክንያት ከሥራ የሚባረር የለም አይዟችሁ አትፍሩ ብለውናል›› በማለት ሲናገሩ መደመጣቸው ነው፡፡ በተጨማሪም ‹‹ከዚህ ግቢ አቅም ኖሮት የሚያስወጣን የለም፤ ካስወጡን ግን መንግስታችን ስለሚተባበረን (ቸር ስለሆነ) ከእርሱ ሌላ መሬት ተቀብለን የራሳችንን ቤተ-ክርስቲያን እናቋቁማለን›› እና ‹‹የኦርቶዶክስ እምነት አገልጋዮች የሚል ማሕበር እንመሰርታለን›› እስከማለት መድረሳቸው ከአገዛዙ ጋር ያላቸውን የጠበቀ ቁርኝት ያመላክታል፡፡ በነገራችን ላይ በስብሰባው እንዲሳተፉ ከተጠሩት ከመቶ ስልሳ ዘጠኙ አድባራትና ገዳማት፣ እንዲሁም ከ10 ሺህ በላይ ሠራተኞቻቸው መካከል የተገኙት የስምንት አድባራት አስተዳዳሪዎችና 150 ሠራተኞች ብቻ እንደነበሩ ከመረጃ ምንጮቼ አረጋግጫለሁ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በተለይም በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ምኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ተክለማሪያም አዝማችነት ማሕበሩ ላይ የደቦ ዘመቻ ከተከፈተ ሰነባብቷል፡፡ በተከታታይ በ‹‹ጥናት›› ስም የሚወጡ ወረቀቶች ማሕበሩን ከአክራሪነትም አሻግረው ‹‹የግንቦት ሰባት መንፈሳዊ ክንፍ›› ሲሉ ይወነጅሉታል፡፡ በጥቅሉ የእነዚህ ‹‹ጥናት›› ተብዬዎች መደምደሚያ ‹‹ማሕበሩ የትምክተኞች ምሽግ ነው፣ አክራሪነት አለበት፣ አመራሩና የሕትመት ውጤቶቹ የፖለቲካ አዝማሚያ ይታይባቸዋል፣ በቤተ-ክርስቲያን አስተዳደር ጣልቃ ይገባል፣ ሕዝቡ በመንግስት ላይ አመኔታ እንዳይኖረው ይሰራል፣ በውጭ ፅንፈኛ የፖለቲካ ኃይሎች ይዘወራል›› የሚሉ ናቸው፡፡ የማሕበሩ የአመራር አባላት እንዲህ አይነቱን ውንጀላ በተመለከተ በተለያየ ጊዜ ከአቶ በረከት ስምኦን እስከ ዶ/ር ሽፈራው ተክለማሪያም፤ ከአዲስ አበባ የፀጥታ ኃላፊዎች እስከ ጠቅላይ ሚንስትሩ የደህንነት አማካሪ ፀጋዬ በርሄ ድረስ ያሉ ባለሥልጣናትን በቢሮአቸው ተገኝተው ውንጀላው ማስረጃ የማይቀርበበት የሀሰት እንደሆነ ቢያስረዱም መፍትሄ እንዳላገኙ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ በግልባጩ በመንግስት ተቋማት ያሉ የፋክት መረጃ አቀባዮች፣ በግንቦት ወር ከሚካሄደው የሲኖዶሱ መደበኛ ጉባኤ በፊት፣ ከሃያ የሚበልጡ የማህበሩ አመራርን ከሽብርተኝነት ጋር በማያያዝ ለመክሰስ እና ማሕበሩንም እንደተለመደው በዶክመንተሪ ፊልም ለመወንጀል ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ከሶስት ሳምንት በፊት በአቡነ ገብርኤል ሰብሳቢነት የሚመራው የሐይማኖቶች ምክር ቤት ስብሰባውን ካጠናቀቀ በኋላ ዶ/ር ሽፈራው አቡኑን ቃል-በቃል የጠየቃቸው ጥያቄም ይህንን መረጃ የሚያጠናክር ነው፡-
‹‹በማሕበረ ቅዱሳን አመራር ውስጥ ከሃያ በላይ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት አሉ››
‹‹ለዚህ ምንድን ነው ማስረጃህ? አቅርበውና እስቲ እንየው?››
‹‹ሀገር ውስጥ ካሉ ፅንፈኛ ጋዜጠኞች በተጨማሪ በስደት የሚገኙና በሽብር ተግባር የተሰማሩ ጋዜጠኞች በአመራርነት አሉበት (የሁለት ሰዎችን ስም ጠቅሷል)››
‹‹እኛ እስከምናውቀው ማሕበሩ ከእንዲህ አይነት ተግባር የራቀ ነው፤ እናንተ ማስረጃ አለን ካላችሁ ደግሞ አቅርቡልንና እንየው፤ ከዚህ ውጪ ይህንን አይነት ክስ አንቀበልም፡፡››
በአናቱም ከወራት በፊት የስርዓቱ የንድፈ ሃሳብ መጽሔት የማሕበሩን ስም ሳይጠቅስ በደፈናው የወነጀለበትን እና ‹‹ለምን?›› ብለው የሚጠይቁ ጳጳሳትን በሚከተለው አገላለፅ ማሸማቀቁን ስናስታውስ የማሕበሩ ዕጣ-ፈንታ በመጨረሻዎቹ ቀናት ላይ መቆሙን ያስረግጥልናል፡፡
‹‹በኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ ትርምስና ብጥብጥ ለመፍጠር፤ በኦርቶዶክሶችና ሌሎች ሐይማኖቶች መካከል ግጭት ለመቀስቀስ የሚሞክሩት የደርግና የተለያዩ ትምክህተኛ ኃይሎች ቅሪቶች ናቸው፡፡ እነዚህ የትምክህት ኃይሎችና አንዳንድ የእምነቱ አባቶች በጋራ ሐይማኖትን በፖለቲካ ዓላማ ዙሪያ መጠቀሚያ አድርገው እየሰሩ ለመሆናቸው ከ97 ምርጫ በኋላ እንዳንድ በአሜሪካ የሚገኙ ጳጳሳት ቅንጅት በጠራው ሰልፍ ላይ የሐይማኖት አባትነት ካባቸውን እንደለበሱ ከመሰለፍ አልፈው አስተባባሪ ሆነው መታየታቸው በቂ ማረጋገጫ ነው፡፡›› (አዲስ ራዕይ ሐምሌ-ነሐሴ 2005)
የሆነው ሆኖ ከፍረጃውና ከእስራቱ በተጨማሪ ማሕበሩን ለማዳከም በዋናነት በአገዛዙ የተነደፉት እቅዶች ማሕበሩ መሰረቱን የጣለበት የግቢ ጉባኤን ከመከልከልና ንብረቶቹን ከመውረስ ጋር የሚያያዙ ናቸው (ከላይ የተጠቀሰው የአቋም መግለጫም ለማሕበሩ የደም-ስር የሆኑትን እነዚህን ሁለት ጉዳዮች ትኩረት እንደሰጣቸው ልብ ይሏል)
ስቅለትን-ለተቃውሞ
ኢህአዴግ ወደ ስልጣነ-መንበሩ ከመጣ ሦስተኛ ዓመት ላይ ‹‹የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ግቦችና ቀጣይ እርምጃዎች›› በሚል ርዕስ ለካድሬዎቹ በበተነው ድርሳን (በሟቹ አቶ መለስ ዜናዊ የተዘጋጀ ነው ተብሎ ይገመታል)፤ ይህን አሁን የተነጋገርንበትን ሐይማኖታዊ ተቋማትን በሚያቅዳቸው የስልጣን ማራዘሚያ አማራጮች ስለመጠቀም ካወሳ በኋላ ተቋማቱን ለስርዓቱ ፖሊሲዎች እንዲታመኑ ማድረጉ ዋነኛ እንደሆነ ያሰምርበታል፡፡ ይህ የማይቻል ከሆነ ደግሞ፣ እስከ ከፍተኞቹ መንፈሳዊያን መምህራን ድረስ ዘልቆ በመግባት ሐይማኖቶቹን መምራት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ግብ መሆን እንዳለበት ያው ሰነድ በግልፅ ቋንቋ ይናገራል፡፡ እንግዲህ ከመጅሊሱ እስከ ማሕበረ ቅዱሳን ያየነው መንግስታዊ አፈና የዚህን ሃያ ዓመት የሞላው የተፃፈ ሀሳብ መተግበርን ነው፡፡
ግና፣ ከዚህ ቀደም በተፃፈ ነውረኛ ሀሳብ ትግበራ ፊት ከሁለት አስርት በላይ ህልውናውን ለማቆየት የተጋው ማሕበረ ቅዱሳን፣ ከላይ በሚገባ በጠቀስኳቸው አሳማኝ መረጃዎች እና ተጨባጭ ሁነቶች በተከታታይ መከሰት መጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደደረሰ ተመልክተናል፡፡ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ደግሞ፤ መነሳት የሚኖርበት መሰረታዊ ጥያቄ፣ እንዴት ይህን ማሕበር ወደ ቀጣዩ ትውልድ ማሻገር ይቻላል? የሚለው ሲሆን፤ ምላሾቹም ሁለት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው የማሕበሩ አመራሮችና አባላት እስከዚህች ቀን እያደረጉ ያለው የውስጥ ለውስጥ የእርምት እንቅስቃሴን ይመለከታል፡፡ በሐይማኖቱ ተቋማት በኩል ለዓመታት ሲሞከር የቆየው ይኸኛው አማራጭ፣ እንደ አስተዋልነው ማሕበሩን ሞት አፋፍ ላይ ከመድረስ ሊታደገው አልቻለም፡፡ ስለዚህም፣ ወደ ሁለተኛውና ዋነኛ የመፍትሔ አማራጭ መሻገር ግድ የሚል ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ርዕሰ-ጉዳይ ላይ ስፅፍ ለማስረዳት እንደሞከርኩት፤ የማሕበሩ አመራሮች፣
አባላት እና ደጋፊዎች ወደ አደባባይ በመውጣት፤ ማሕበራቸውን ብቻ ሳይሆን ህልውናቸውንና ህያውነታቸውን የመሰረቱበትን ሐይማኖት ለማውደም የሚተጋውን ስርዓት በሰላማዊ አመፅ መናድ ብቸኛው የዚህ አስቸጋሪ ጊዜ መሻገሪያ መንገድ ነው፡፡ በዋናነት የተማሩ ከተሜ ወጣቶችን፣ በአለማዊም ሆነ በትምህርተ-ሐይማኖቱ የማይታሙ ዜጎችን የያዘው ይህ ማሕበር፤ ከህዝበ ሙስሊሙ ‹‹ድምፃችን ይሰማ›› የአደባባይ ተቃውሞ ስኬቶችና ሂደቶች በመማር፤ ፊቱ በተገተረው ኢህአዴግ ላይ በሕጋዊና ሰላማዊ እምቢተኝነት ከማመጽ የተሻለ አማራጭ እንደማይኖረው የሚረዳ ይመስለኛል፡፡
‹‹ችግሮች ሁሉ የየራሳቸው በጎ ገፆች አሏቸው›› እንዲሉ፤ ማሕበሩ የደረሰበት ይህ ፈታኝ ጊዜን ተከትለው የሚመጡ ሁለት ወቅቶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው፣ በቀጣዩ ወር የሚካሄደው የስቅለት በዓል ነው፡፡ የሐይማኖቱ ተከታዮች በሙሉ በየቤተ-ክርስቲያናቱ የሚውሉበት ይህ በዓል፣ አገዛዙ እጁን ከማህበሩ ላይ እንዲያነሳ ለመጠየቅ የተመቸ ቀን ስለመሆኑ ማስታወስ አባላቱን አሳንሶ መገመት እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ሁለተኛውና በእጅጉ የተሻለ ነው ብዬ የማስበው ጊዜ ደግሞ ቀጣዩ የ2007 ምርጫን ነው፡፡ ለየትኞቹም የህገ-መንግስቱ ሀሳቦች አልያም የሞራል ዕሴቶች የማይገዛው ኢህአዴግ፣ በሐይማኖቱ ላይም ሆነ በማሕበሩ ላይ የዘረጋውን የረከሰ እጅ እንዲያነሳ ያለው ብቸኛ አማራጭ ሕዝባዊ አመፅ መሆኑ ላይ እስከተማመንን ድረስ፣ ከዓመታዊ የንግስ በዓላት ጀምሮ ያሉ መድረኮችን በዕቅድ ለመጠቀም የዝግጅቱ ጊዜ ዛሬ ነው፡፡ ይህ አይነቱ የተቃውሞ እንቅስቃሴም፣ ካነሳነው ርዕሰ-ጉዳይ አኳያ የማሕበሩን መኖር የሚሹ ሁሉ ቀጣዩን የምርጫ ወቅት ለማስገደጃነት የመጠቀም ተሞክሮዎቻቸውን ተፈላጊው ብቃት ላይ እንደሚያደርሰው አምናለሁ፡፡ ጥቂት ሊባሉ የማይችሉ አባላቱ፣ የምርጫውን ተጨባጭ ዕድል መንግስታዊ ተቋማት በማሽመድመድ ጭምር እንዴት ስርዓቱን ወደመቃብሩ ማሻገር እንደሚያውቁ ስንገነዘብ፤ ቀሪው ጉዳይ ‹‹ሐይማኖታችሁን ተከላከሉ›› ብለው ላስተማሩት ቅዱሳን መጻሕፍትና ለሰማያዊው መንግስት የመታመን ብቻ እንደሚሆን እንረዳለን፡፡